96364 law of succession/ will/ Manner of revoking will

አንድ ተናዛዥ ኑዛዜውን መሻር ሲፈልግ ሀሳቡን በማያሻማ አኳኋን በመግለጽ ከሻረ ኑዛዜዎች ዋጋ ያላቸው እንደሆኑ በሚያስፈልገው ፎርም አይነት ግልጽ አድርጐአልሻረውም ሊባል  የማይችል ስለመሆኑ፣

የፍ/ህ/ቁ. 898(1)፣ 899(1)

የሰ/መ/ቁ. 96364

 

ጥቅምት 10 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡-ተገኔ ጌታነህ

 

አልማው ወሌ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመስል

አመልካች፡- እልፍነሽ ወርቁ ጠበቃ አሳምነው ቀረቡ ተጠሪ፡- ኤልሳቤጥ አስራት ጠበቃ መስፍን ጌታቸው ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሠጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ይህ ጉዳይ የተጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሲሆን የአሁን አመልካች የመ/አመልካች፣ተጠሪ ደግሞ የመ/ተጠሪ ነበሩ የመ/አመልካች የነበሩት የአሁን  አመልካች ባቀረቡት የመቃወም አቤቱታ የመቃወም ተጠሪ ሟች ወ/ሮ አስረስ እሸቴ መስከረም 28/2000 ዓ.ም. ያደረጉትን ኑዛዜ ነሐሴ 23 ቀን 2003 ዓ.ም የሻሩት መሆኑን እያወቁ በተሻረው ኑዛዜ የወራሽነት ማስረጃ መውሰዳቸው ተገቢነት ስለሌለው ማስረጃው ይሻርልኝ በማለት ጠይቀዋል፤ተጠሪም በሰጡት መልስ ሟች መፃፍ እና መፈረም ይችላሉ መስከረም 28/2000 ዓ.ም ባደረጉት ኑዛዜም ላይ ስማቸውን ጽፈው የፈረሙ ሲሆን አመልካች የኑዛዜ መሻሪያ ብለው ያቀረቡት ሰነድ ላይ ግን የሟች ፊርማ ተብሎ የተቀመጠው የጣት ምልክት ሲሆን ከምልክቱ በላይ ግን የሟች ስም ተፅፏል፡፡ በመሆኑም መሻሪያ የተባለው ሰነድና መስከረም 28/2000 ዓ.ም. ያደረጉት ኑዛዜ ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡ ሟችም ለረዥም አመት ታመው ፓራላይዝ ሆነው የሚያደርጉትን አያውቁም ባጠቃላይ መሻሪያ ተብሎ የቀረበው ሰነድ የኑዛዜን ፎርማሊቲ የማያሟላና ህጉን ተከትሎ የተፈፀመ አይደለም፣ንብረቱንም ቢሆን ተጠሪ ወደ ስሜ አዙሬዋለሁ፣ ተቃወሞዋቸው ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

 

ጉዳዩን ያየው ፍ/ቤትም፡- ሟች መስከረም 28/2000 ዓ.ም ያደረጉትን ኑዛዜ በግልፅ የሻሩት መሆኑን ነሐሴ 23/2003 ዓ.ም. ባስመዘገቡት መሻሪያ ሰነድ ገልጸዋል፤ፎርሙን አስመልክቶ አመልካች ያቀረቡት መቃወሚያ ተቀባይነት የለውም፡፡ሟች ወ/ሮ አስረስ እሸቴ በፍ.ብ.ሕ.ቁ.898 ላይ በተቀመጠው መሰረት መስከረም 28/2000 ዓ.ም ያደረጉትን ኑዛዜ የሻሩት መሆኑን ስለገለፀ አመልካች በተሻረ የኑዛዜ ሰነድ የተሰጣቸው የወራሽነት ማስረጃ ተሰርዟል ሲል ወሰነ ፡፡የከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤትም የአመልካችን ይግባኝ ሳይቀበለው አፀንቶታል፡፡ በመጨረሻ ጉዳዩ የቀረበለት የአዲስ አበባ ከተማ ሰበር ሰሚ ችሎት የኑዛዜ መሻሪያ ሰነዱ ተናዛዥና በቦታው ለነበሩ ምስክሮች


የተነበበላቸው ስለመሆኑ የሚያመለክት ቃል በሰነዱ ላይ አይታይም፡፡የፍ.ብ.ሕ.ቁ. 881 እና 898(1) ላይ የተጠቀሰውን የመሻሪያ ሰነዱ አያሟላም ሲል የሥር ውሣኔዎችን ሽሮታል፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ የቀረበው ይህንን ውሳኔ ለማሳረም ነው፡፡

አመልካች በሰበር አቤቱታው ቅሬታውን ሳያቀርብ በፍ.ሕ.ቁ. 898 መሠረት የግልፅ ኑዛዜ በሚያደርገው አይነት ኑዛዜን መሻር ይቻላል፡፡ በቀጣይ የፍ/ሕ/ቁጥር 899 መሠረት ደግሞ ተናዘዡ ያለውን የኑዛዜ መሻር ሀሳብ በቂ አድርጎ በመግለፅ አይነት የኑዛዜው አነጋገር በመሰረዝ ኑዛዜውን በማጥፋት በመቅደዱ ኑዛዜውን መሻር እንደሚቻል ህጉ እያመላከተ ፎርማሊት አላሟላም ተብሎ መወሰኑ እና ተናዛዥ ኑዛዜውን በፈለገው ጊዜ የመሻር መብቱን ያጣበበ በመሆኑ የፍ.ህ.ቁ. 881 አልተሟላም ተብሎ መወሰኑ መሰረታዊ የህግ ሥህተት የተፈፀመበት ስለሆነ ሊታረም ይገባዋል በማለት አመልክተዋል፡፡

በዚህም መሰረት ይህ ችሎት ኑዛዜ ሲሻር ኑዛዜው በተሰጠበት አግባብ ብቻ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ከፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 898,899 እና 900 አኳያ ለመመርመር በጭብጥነት በመያዝ የግራ ቀኙን መልስና የመልስ መልስ በፅሑፍ እንዲቀባበሉ በማድረግ አከራክሯል፡፡

አመልካች ክርክራቸውን በማጠናከር የሟች የመሻሪያ ኑዛዜ ሰነድ በአግባቡ የተከናወነ እና የፍ.ህ.ቁ. 881 (ፎርማሊትን) ሊከተል የሚገባው አይደለም በመሆኑም የፍ.ሕ.ቁ. 898 መሰረት አድርጐ መሻሩበተረጋገጠበት የከተማው ሰበር ችሎት የሥር ውሳኔን መሻራቸው አግባብነት የለውም ሲሉ፡፡ ተጠሪ በበኩላቸው በተቃራኒው የሥር ውሳኔ መሻሩ በአግባቡ ነው ሲሉ ክርክራቸውን አጠናክረዋል፡፡

ባጠቃላይ የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተጠቀሰው ነው፡ በመሆኑም የግራ ቀኙን ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች አንፃር መርምረናል፡፡ በመሰረቱ የተያዘውን ጉዳይ ጠቅለል ባለመላኩ ስናየው እያከራከረ ያለው የህግ ጥያቄ ከተያዘው ጭብጥ አኳያ ሲጤን ተጠሪ ከሟች መስከረም 28/2000 ዓ.ም አገኘሁት የሚሉት ኑዛዜ በድጋሚ ሟች በህይወት እያሉ ነሐሴ 23/2003 ዓ.ም. በውል አዋዋይ ጽ/ቤት ያደረጉት የመሻርያ ሰነድ በቀጥታ የመጀመሪያውን ኑዛዜ ዋጋ አልባ ያደረገዋል ወይስ የኋለኛው የመሻሪያ ሰነድ ሊከተለው የሚገባው ልዩ ስርዓት አለው የሚለውን አከራካሪ ነጥብ ከተጠቀሱት የፍ/ሕግ ድንጋጌዎች አንፃር ተገናዝቦ ሊታይ የሚገባው ሆኗል፡፡በመሠረቱ ኑዛዜ የሟች ጥብቅ የሆነ የግል ጠባይ ያለው እና ራሱ የሚተገብረው ነው በመሆኑም የተናዛዡ ሀሳብና ፍላጐት በጥንቃቄ ልንከተለው የሚገባው ነው፡፡ ወደ ያዝነው ጉዳይ ስንመለስ የፍ.ህ.ቁ. 898(1)ተናዛዡ ኑዛዜዎቹ ዋጋ ያላቸው እንዲሆኑ በሚያስፈልገው ፎርም ዓይነት ግልፅ አድርጎ በማስታወቅ ኑዛዜውን የሻረ እንደሆነ በጠቅላላው አኳኃን የሚሻር ይሆናል ይላል፡፡በዚሁ ህግ አንቀፅ 899(1) ተናዛዥ የተናዘዘውን ለመሻር ወይም ለመለወጥ ያለውን ሀሳብ በቂ አድርጎ በመግለፅ ይህንንበኑዛዜው የተመለከተውን ቃል መሻር ይችላል በማለት ተደንግጔል፡፡

በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱትን ሁለቱንም ድንጋጌዎች ስናይ አንዱ ሌላኛውን በሚያጠናክር መልኩ የተቀመጠ እንጂ የሚቃረኑ አይደለም፡፡

ይህም ሲባል ሁለቱም አንቀፆች ተናዛዡ ያደረጋቸው ኑዛዜ መሻር ሲፈልግ ሀሳቡን በማያሻማ አኳኋን ግልፅ በሆነ መንገድ መሻር እንደሚችል የሚገልፅ ነው፡፡ ይህም የሚያመለክተው ሟች (ተናዛዡ) ከዚህ ውጭ ሊከተላቸው የሚገባው ሥርዓት መኖሩን አይደለም፡፡ ይልቁንም ተናዛዡ ኑዛዜውን ለመሻር ሊከተላቸው የሚገባውን አማራጮች የሚያመለክት (የሚገልፅ) ነው፡፡ እንግዲህ በያዝነው ጉዳይም ሟች ነሐሴ 23/2003 ዓ.ም.ባደረጉት የመሻሪያ ሰነድ ተጠሪ (ተሻሪዋ) ከዚህ ቀደም እንደተገበሩት የተሰጣቸውን ሀላፊነት ባለመወጣታቸው እና ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው


ምክንያት በትክክለኛ አእምሯቸውና በፍላጐታቸው የመጀመሪያውን የኑዛዜ ሰነድ በግልፅ ቃልና አነጋገር የሻሩት መሆኑን ነው፡፡ ይህም የተፈፀመው በውል አዋዋይ ጽ/ቤት መሆኑም ተመልክቷል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የግድ ሟች የመስከረም 28/01/2000 የፈፀሙትን ሥርዓት ሊከተሉ አይገባቸውም፡፡ ይህን ኑዛዜ ለመሻር በቂና ግልፅ ቃል መሻራቸውን መግለፃቸው የመጀመሪያውን ያስቀረዋል፡፡ የፍ/ህ/ቁ. 881ን አልተከተለም በማለት ብቻ የሟችን የግል ሀሳብና ፍላጎት መቃረን አይገባም፡፡

በመጨረሻም በሥር (ከተማው የሰበር ሰሚ ችሎት ሟች በመስከረም 28/01/2000 ዓ.ም.ያደረጉት ኑዛዜ በነሐሴ 23/2003 ዓ.ም. በተደረገው ሊሻር አይገባውም (ሊሽረው) አይችልም፤መባሉን ይህ ችሎት የሚቀበለው ሆኖ አልተገኘም፡፡

ስለዚህ የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት የከተማውን የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እና የይግባኝ ሰሚውን ውሣኔዎች መሻሩ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነው፡፡በመሆኑም የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 ው ሣ ኔ

1. የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ.ቁ. 927105 3/11/05  እና የከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት በመ.ቁ. 20673 በቀን 10/01/2006 ዓ.ም. የተሰጠው ውሳኔ ፀንቷል፡፡

2. የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ. 21133 በቀን 27/3/2006 የተሰጠው ውሳኔ ተሽሯል፡፡

3. ለተጠሪ በመስከረም 28/2003 ዓ.ም. የተሰጠው ኑዛዜ ነሐሴ 23/2003 ዓ.ም. በተደረገው የመሻሪያ ሰነድ ተሽሯል (ቀሪ) ሆኗል ብለናል፡፡

4.  ወጪና ኪሣራ የግራ ቀኙ ይቻቻሉ፡፡ መዝገቡ በውሣኔ ተዘግቷል፡፡ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

እ/ኢ