93234 criminal procedure/ amendment of charges/ interlocutory appeal

በወንጀል ክስ ክርክር የክስ ይሻሻል ጥያቄ ቀርቦ ጥያቄው ውድቅ ከተደረገ ጥያቄው ውድቅ የተደረገበት ትእዛዝ በድጋሚ ለክርክር ሊቀርብ የሚችልበት ዕድል የሌለ በመሆኑና ትእዛዙ የመጨረሻ እንጂ ጊዜያዊ አገልግሎት እንዳለው ተቆጥሮ በስረ ነገሩ ከሚሰጠው ፍርድ ጋር ተጠቃሎ ይግባኝ የሚባልበት ነው ሊባል የሚችል ስላለመሆኑና በተሠጠው ትእዛዝ ላይ በስረ ነገሩ ከሚሰጠው ፍርድ በፊት ይግባኝ ሊቀርብበት የሚችል ስለመሆኑ፡-

 

የወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 118፣184፣

የሰ/መ/ቁ. 93234

መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ሡልጣን አባተማም መኰንን ገ/ሕይወት ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

አመልካች፡- የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ - የቀረበ የለም፡፡

 

ተጠሪ፡- አቶ ኃይለኪሮስ ወልደብርሃን ካሕሳይ - የቀረበ የለም፡፡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ ር ድ

 

በዚህ መዝገብ አመልካች አቤቱታ ያቀረበው በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በማዕከላዊ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአሁኑ ተጠሪ ላይ አቅርቧቸው በነበሩት ሁለት የሙስና ወንጀል ክሶች ጉዳዩ የከሳሽን ምስክሮች ለመስማት በተቀጠረበት ዕለት ምስክሮቹ እንዲሰሙ ከመደረጉ በፊት ተከሳሹ ከተከሰሱባቸው ሁለት የሙስና ወንጀሎች መካከል በሁለተኛው ክስ የተመለከተውን ወንጀል ያደረጉት ከሌላ ሰው ጋር በመተባበር ስለመሆኑ በሂደት የተደረሰበት መሆኑን ገልጾ የወንጀሉ ተካፋይ ነው የተባለውን ሌላኛውን ግለሰብ በክሱ በማካተት ክሱን አሻሽሎ ለማቅረብ እንዲፈቀድለት ያቀረበውን ጥያቄ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአብላጫ ድምጽ ውድቅ በማድረግ የሰጠው ብይን እና በብይኑ ቅር በመሰኘት አመልካች ያቀረበውን ቅሬታ የክልሉ የበላይ ፍርድ ቤቶች ባለመቀበል የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡

 

የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክስ ማሻሻል ጥያቄውን በአብላጫ ድምጽ ሳይቀበል የቀረው በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ቁጥር 118 እና 119 ድንጋጌዎች መሰረት ክስ እንዲሻሻል ሊደረግ የሚችለው ክሱ ተከሳሹን የሚያሳስት ወይም ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት የሚያስቸግር በሆነ ጊዜ መሆኑን እና ተጨማሪ ተከሳሽን በክሱ የማካተት ጉዳይ ለክስ ማሻሻል ጥያቄ በምክንያትነት መቅረቡ ሕጋዊ መሰረት የሌለው መሆኑን በመግለጽ ሲሆን አነስተኛው ድምጽ በበኩሉ ክስ እንዲሻሻል የሚደረገው ተከሳሹን የሚያሳስት ወይም ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት የሚያስቸግር በሆነ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በቁጥር 118 ድንጋጌ አነጋገር መሰረት በክሱ መገለጽ ይገባው የነበረ ነገር ግን ሳይገለጽ የቀረ መሰረታዊ ነገር መኖሩ ሲረጋገጥ ጭምር መሆኑን እና በወንጀሉ ተሳታፊ ነበረ የተባለ ሰው በማናቸውም ምክንያት በክሱ ውስጥ በተከሳሽነት ሳይካተት መቅረቱም ለክሱ መሰረታዊ የሚባል ነገር መሆኑን በመግለጽ ክሱ እንዲሻሻል ሊደረግ ይገባው ነበር በማለት የልዩነት ሀሳቡን አስፍሯል፡፡


በዚህ ብይን ቅር በመሰኘት የማስረጃ ማሰማት ሂደቱን አቋርጦ አመልካች ባቀረበው ይግባኝ ሳቢያ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በስር ፍርድ ቤት የተያዘው ክርክር ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ በማድረግ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ይግባኝ ወደ ተባለበት ፍሬ ጉዳይ ሳይገባ በቅድሚያ ሊመረመር የሚገባው የይግባኝ አቀራረቡ ስነ ስርዓታዊ አግባብነት መሆኑን ገልጾ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ቁጥር 181(1) እና 184(መ) ድንጋጌዎች መሰረት ተከሳሹን ጥፋተኛ በማለት ወይም ነፃ በመልቀቅ ወይም ለጊዜው በመልቀቅ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በዋናው ጉዳይ በተሰጠው ውሳኔ ላይ ከሚቀርበው ይግባኝ ጋር በአንድነት ካልሆነ በቀር በዋናው ጉዳይ ላይ ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት በክስ ማሻሻል ክርክር ረገድ በሚሰጥ ብይን ወይም ትዕዛዝ ላይ ይግባኙን ነጥሎ ማቅረብ የሚቻልበት ስነ ስርዓታዊ አግባብ አለመኖሩን በምክንያትነት በመጥቀስ ይግባኙን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

 

አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበውም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ችሎት አቤቱታውን ዘግቶ በማሰናበቱ ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ አመልካች ክስ አቅርቦ ማስረጃ ከማሰማቱ በፊት ከተጠሪ ጋር አብሮ መከሰስ ያለበት ሌላ ግለሰብ መኖሩን ስለደረስኩበት ግለሰቡን ጨምሬ ክስ ላቅርብ በማለት ያቀረበውን ጥያቄ የስር ፍርድ ቤቶች ክስ ለማሻሻል የሚፈቀደው ክሱ ተከሳሹን የሚያሳስት ወይም ፍርድ ለመስጠት አስቸጋሪ ሲመስል ብቻ ነው በማለት ጥያቄውን ውድቅ የማድረጋቸውን አግባብነት ከወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ቁጥር 119 ድንጋጌ አንጻር ተጠሪው ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም ለክርክሩ ወደ ተያዘው የፍሬ ጉዳይ የክርክር ጭብጥ ከመገባቱ በፊት እልባት ማግኘት የሚገባው በዋናው ጉዳይ ላይ ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት በክስ ማሻሻል ክርክር ረገድ በሚሰጥ ብይን ወይም ትዕዛዝ ላይ ይግባኙን ነጥሎ ማቅረብ የሚቻልበት ስነ ስርዓታዊ አግባብ አለመኖሩን በምክንያትነት ጠቅሶ ይግባኙን ባለመቀበል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው እና በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ችሎት ተቀባይነት ያገኘው ውሳኔ ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ መሆኑን በመገንዘብ አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ከዚሁ ጭብጥ አንፃር መርምረናል፡፡

 

በዚህም መሰረት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት  ለውሳኔው መሰረት ካደረጋቸው የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ ሁለት ድንጋጌዎች መካከል ከላይ ለተጠቀሰው ጭብጥ ቀጥተኛ አግባብነት ያለው ቁጥር 184 ድንጋጌ ሲሆን ይህ ድንጋጌም ተከሳሹን ጥፋተኛ በማለት ወይም ነፃ በመልቀቅ ወይም ለጊዜው በመልቀቅ ውሳኔ ከተሰጠ በኃላ በዋናው ጉዳይ በተሰጠው ውሳኔ ላይ ከሚቀርበው ይግባኝ ጋር በአንድነት ካልሆነ በቀር በቁጥር 94 መሰረት ቀጠሮ መስጠትን ወይም አለመስጠትን ወይም በቁጥር 131 መሰረት የሚቀርብ መቃወሚያን ወይም በቁጥር 146 መሰረት ማስረጃን መቀበልን ወይም አለመቀበልን አስመልክቶ በሚሰጡ ትዕዛዞች ላይ ይግባኙን ነጥሎ ማቅረብን የሚከለክል ነው፡፡

 

እንደሚታየው ይህ ድንጋጌ ትዕዛዞቹ መሰረት የሚያደረጓቸውን ድንጋጌዎች ጭምር በመጥቀስ ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊት የትዕዛዝ ይግባኝ ክልከላ የተጣለባቸውን ጉዳዮች የሚዘረዝር ሲሆን ከዝርዝሩ ውስጥ የክስ ማሻሻል ጉዳይም ሆነ የክስ ማሻሻል ጉዳይ መሰረት የሚያደርጋቸውን ቁጥር 118 እና 119 ድንጋጌዎች አልተካተቱም፡፡ይህም ሕጉ የትዕዛዝ ይግባኝ ክልከላ በግልጽ ከጣለባቸው ውጪ በሆኑ የመጨረሻ ትዕዛዝ በተሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ (የክስ ማሻሻል   ጥያቄን


ውድቅ ከማድረግ ጉዳይ ጋር የተያያዙትን ጨምሮ) ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊትም ቢሆን ይግባኝ ማቅረብን አስመልክቶ የስነ ስርዓት ሕጉ ያስቀመጠው ክልከላ አለመኖሩን መገንዘብ የሚያስችል ነው፡፡በተያዘው ጉዳይ የክስ ማሻሻል ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ የተሰጠውን ትዕዛዝ በየትኛውም ደረጃ በሚገኝ ፍርድ ቤት ቢሆን ከአሁኑ ተጠሪ ቀጣይ የወንጀል ክርክር ሂደት ጋር የሚያስተሳስረው ነገር ባለመኖሩ እና ትዕዛዙ የተሰጠበት ጉዳይ በድጋሚ ለክርክር ሊቀርብ የሚችልበት ዕድል የሌለ በመሆኑ ትዕዛዙ የመጨረሻ እንጂ ጊዜያዊ አገልግሎት እንዳለው ተቆጥሮ በስረ ነገሩ ከሚሰጠው ፍርድ ጋር ተጠቃሎ ይግባኝ የሚባልበት ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡በመሆኑም ይግባኙ የቀረበው በስነ ስርዓት ሕጉ የተመለከተውን የይግባኝ አቀራረብ ስርዓት መሰረት አድርጎ ባለመሆኑ ሊስተናገድ አይገባውም በማለት በክልሉ የበላይ ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

ሲጠቃለል የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 184 ድንጋጌ የትዕዛዝ ይግባኝ ክልከላን የሚጥለው ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊት በሚሰጡ ሁሉም ትዕዛዞች ላይ እንደሆነ አድርጎ በመተርጎም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው እና በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ችሎት ተቀባይነት ያገኘው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 57074 በ06/06/2005 ዓ.ም. ተሰጥቶ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 58589 በ12/10/2005 ዓ.ም. በትዕዛዝ የጸናው ውሳኔ ተሽሯል፡፡

2. የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 184 ድንጋጌ የትዕዛዝ ይግባኝ ክልከላ በግልጽ ከጣለባቸው ውጪ በሆኑ የመጨረሻ ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ በተሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊትም ቢሆን ይግባኝ ማቅረብን አስመልክቶ የስነ ስርዓት ሕጉ ያስቀመጠው ግልጽ ክልከላ ባለመኖሩ በዚህ መዝገብ ለተያዘው ክርክር ምክንያት የሆነው የክስ ማሻሻል ጉዳይ ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊት ይግባኝ ሊቀርብበት የሚችል ነው በማለት ወስነናል፡፡

3. ይህንኑ በመገንዘብ የቀረበለትን የይግባኝ ክርክር መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እንዲላክ ወስነናል፡፡

4.  ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡