105555 labor law dispute/ occupational accident

አንድን ሰው ሠራተኛ ነው ለማለት በቅጥር ላይ የተመሰረተ የሥራ ግንኙነት መኖር፣ሠራተኛው አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ያለበት መሆኑ፣ ሊሰጥ የሚገባውን አገልግሎትመቼ ሊያከናውን እንደሚገባና እንዴት ማከናወን እንደሚኖርበት አሰሪው የመቆጣጠር ስልጣን ያለው ስለመሆኑ መረጋገጥ ያለባቸው ስለመሆኑ፣

 

አንድን አደጋ በስራ ላይ የደረሰ ነው ለማለት ሠራተኛው ስራውን በማከናወን ላይ እያለ ወይም ከስራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ ከራሱ ውጪ በሆነ ምክንያት ወይም በአካሉ በማንኛውም ክፍል ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ ላይ በድንገት የደረሰበት ጉዳት ስለመሆኑ፣

 

አዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀፅ 2.4፣58.96፣97፣107፣110

 

የሰበር መ/ቁ 105555

 

መጋቢት 18 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ

 

ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- 1.መፍትሃ ሙሜ

 

2. ናቶሊ መሃመድ ነጂብ       የቀረበ የለም

 

3. ሐናን መሃመድ ነጂብ

 

ተጠሪ፡- አቶ ዑስማን ዓሊ - ጠበቃ ይማጅ ዮኒስ ቀረቡ

 

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅን መሠረት ያደረገ ሁኖ የጉዳት ካሣ ክፍያን የሚመለከት ነው፡፡ ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካቾች ባቀረቡት የክስ ማመልከቻ የ1ኛ አመልካች ህጋዊ ባለቤት የሌሎች አመልካቾች ወላጅ አባት የሆኑት ሟች መሃመድ ነጂብ በተጠሪ በሠራተኛነት ተቀጥረው በማገልግል ላይ እያሉ የተጠሪ ንብረት የሆነውንና የሻንሲ ቁጥር JAAKP- 34HbB7P5165፣የሞተር ቁጥሩ 4HG1-865627 የሆነና የሰሌዳ ቁጥር ያልወጣለትን አይሱዙ ተሸከርካሪ ከድሬዳዋ አዲስ አበባ ለማድረስ በማሽከርከር ላይ እንዳሉ ተጠሪ በእሩምታ ጥይት ተተኮሶባቸው ሕይወታቸው በማለፉየጉዳት ካሳ 903.000.00(ዘጠኝ መቶ ሰለሳ ሺህ) ብር እንዲከፈላቸው ይወሰንላቸው ዘንድ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በተጠሪ ላይ በመሠረቱት ክስ መነሻ ነው። የአሁኑ ተጠሪም በተከሣሽነት ቀርበው ከሟች ጋር የስራ ቅጥር ውል የሌላቸው መሆኑንና ሟቹ በራሳቸው ኃላፊነትና መሪነት ለተለያዩ ሰዎች የሙያ አገልግሎት የሚሰጡ እንጂየተጠሪ ተቀጣሪ ያለመሆናቸውን፣ግንኙነቱ የሙያ አገልግሎት በመሆኑ ሊገዛ የሚገባው በፍትሐ ብሔር ሕጉ ድንጋጌዎች ነው በማለት ክሱ ውድቅ እንዲሆንላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

 

የስር ፍ/ቤትም የግራ ቀኙን የቃል ክርክር እና ማስረጃዎችን ከሠማ በኋላ በተጠሪ በኩል በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት የቀረቡትን የክርክር ነጥቦች ውድቅ በማድረግ በሟችና በተጠሪ መካከል የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት የነበረ መሆኑ ተረጋግጧል የሚል ድምዳሜ ደርሶ የጉዳት ካሣውን መጠንን በተመለከተም የሟቹ የወር ደመወዝ ብር 12,000.00(አስራ ሁለት ሺህ) መሆኑን መገንዘቡን ጠቅሶ በዚሁ ወርሃዊ የደመወዝ መጠን በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 110(3) የሞት ጉዳት ካሳው ሲሳላ ብር 720,000.00 (ሰባት መቶ ሃያ ሺህ) እንደሚሆንና


የቀብር ማስፈጸሚያም የሁለት ወር ደመወዝ ብር 24,000.00 ሊያዝ እንደሚገባ ገልፆ በድምሩ ብር 744,000.00(ሰባት መቶ አርባ አራት ሺህ ብር) ካሳ ለአመልካቾች ሊከፈል እንደሚገባ፣ አከፋፈሉን በተመለከተም ከዚሁ ገንዘብ ውስጥ 50% የሟች ሚስት ለሆኑት ለአሁኗ 1ኛ አመልካች፣ ቀሪው 50% ደግሞ ለሟች ተወላጆች ለአሁኑ 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ሊከፈል ይገባል በማለት ወስኗል፡፡በጉዳት ካሳ መጠኑ ላይ 10% ደግሞ ለጠበቃ አበል እንዲከፈል ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሣኔ የአሁኑ ተጠሪ ባለመስማማት ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ በሟች እና በተጠሪ መካከል ያለው ግንኙነት የአሰሪና ሠራተኛ አይደለም፣ ሟች በራሳቸው ኃላፊነትና መሪነት ስራውን ሲሰሩ የነበሩ ናቸው በማለት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ሽሮታል፡፡ የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ የበታች ፍ/ቤቶችን ውሣኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

 

የአመልካቾች ጠበቃ መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም በፃፉት 4/አራት/ ገፅ የሠበር አቤቱታ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሣኔ መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶች ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ፡-ሟች ሹፌር ሁነው ለተጠሪ ሲሰሩ የነበሩ መሆኑ በተረጋገጠበት ሁኔታ በራሳቸው ኃላፊነትና መሪነት የሙያ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ናቸው ተብሎ ግንኙነቱ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ህግ አይገዛም ሲባል የተወሰነው ውሳኔ ስለሙያ አግባብነት ባላቸው ሕጎች የተቀመጠውን መስፈርት ያላገናዘበ በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ተጠሪ ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን የጽሑፍ እና የቃል ክርክር የሠበር አቤቱታው ከቀረበበት ውሣኔ እና አግባብነት ከላቸው የህግ ድንጋጌዎች ጋር አገናዝቦ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልጋቸው አበይት ጭብጦች፡-

 

1.   በተጠሪ እና በሟች መካከል የነበረው ግንኙነት በአዋጅ ቁጥር 377/96  ድንጋጌዎች አግባብ የሚገዛ ነው? ወይስ አይደለም?

2.  ከተባለስ የጉዳት ካሳ መጠኑ ምን ያህል ሊሆን ይገባል? የሚሉት ሁነው አግኝተናል፡፡

 የ መጀ መሪያ ውን ጭ ብጥ በተመ ለከተ፡ -

 

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ሟች ህይወታቸው ያለፈው በሹፌነታቸው የተጠሪ ንብረት የሆነውን መኪና ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ በማሽከርከር ላይ እንዳሉ በተከፈተባቸው እሩምታ ተኩስ መሆኑን፣ሟች አንድ ጊዜ መኪና ሲያደርስ ብር 800.00 (ስምንት መቶ) ብር ለመከፈል ተጠሪ መስማማታቸውን ተጠሪ ባቀረቡት ክርክርም ሆነ የአመልካቾች ምስክሮች መረጋገጡን የስር ፍርድ ቤት በውሳኔው ላይ በግልጽ ያሰፈረው ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡ በሟችና በተጠሪ መካከል እንደዚህ አይነት ስምምነት የተደረገው ከሚያዚያ ወር 2002 ዓ/ም ጀምሮ መሆኑንና የሞት አደጋው የደረሰው ደግሞ የካቲት 08 ቀን 2003 ዓ/ም ስለመሆኑ በአመልካቾች ማስረጃዎች የተነገረ መሆኑንም ከስር ከበታች ፍርድ ቤቶች የውሳኔ ይዘት ተመልክተናል፡፡

 

ይህንኑ ለመመለስም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አሰሪና ሰራተኛ ማን ነው የሚለውን ጉዳይ መመልከቱ የግድ ይላል፡፡ ይህ ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ የሚችለውም በአዋጁ የሚገዙት የትኞቹ አሰሪዎች እና ሰራተኞች ናቸው? የሚለው ጥያቄ መሰረት በማድረግ መሆኑ ይታመናል፡፡


በመሰረቱ አዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀፅ 2/3/ ስር ሰራተኛ ማለት በዚህ አዋጅ አንቀፅ 4 ስር በተመለከተው መሰረት ከአሰሪ ጋር በቅጥር ላይ የተመሰረተ የስራ ግንኙነት ያለው ግለሰብ ነው በማለት በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም ይህ ሰራተኛ ለአሰሪው በአሰሪው ቁጥጥር ስር ሁኖ አሰሪው በሚከፍለው ደሞዝ በራሱ የጉልበት ወይም የእውቀት አገልግሎት ለተወሰነ ጊዜ ወይም ስራ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ የሚሰጥ መሆኑን አዋጅ ያስገነዝባል፡፡ በሌላ በኩል አዋጁ በአንቀፅ 2/1/ ስር አሰሪ ማለት አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎችን በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 በተመለከተው መሰረት ቀጥሮ የሚያሰራ ግለሰብ ወይም ድርጅት ሊሆን እንደሚችል በመግለፅ ድርጅት የሆነውን አሰሪ በማየት አሰሪ ማን ነው? የሚለውን ጥያቄውን ለመፍታት የሚያስችል መሆኑ የሚያስረዳ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ጥያቄውን ስንመለከተውም አሰሪው  ግለሰብ ወይም ድርጅት ሲሆን የስራ ውሉ ግንኙነት በአዋጅ የሚገዛ መሆኑን፣ አሰሪው ከነዚህ ውጭ ከሆነ እንደሁኔታው የሌሎች ህጎች ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት የሚኖራቸው መሆኑን ሕጉ የሚያመለክት መሆኑን መረዳት የምንችለው ጉዳይ ይሆናል፡፡ በአዋጁ ስለሰራተኛ የተቀመጠው ትርጉም የሚያሳየው በአዋጁ አንቀጽ 4 በተመለከተው መሰረት ከአሰሪ ጋር በቅጥር ላይ የተመሰረተ የስራ ግንኙነት ያለው ግለሰብ መሆኑን አንቀጽ 2(3) በግልጽ ያሳያል፡፡ በዚህ ድንጋጌ ይዘት አንድን ሰው ሰራተኛ ነው ለማለት በቅጥር ላይ የተመሰረተ የስራ ግንኙነት መኖሩና በአዋጁ አንቀጽ 4 ድንጋጌ አግባብ መሰረት ሰራተኛው አገልግሎት ለመስጠት መስማማቱ፣ሰራተኛው አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ያለበት መሆኑንና ሰራተኛው ሊሰጥ የሚገባውን አገልግሎት አይነት፣ የት አገልግሎቱን መስጠት እንደአለበት፣አገልግሎቱን መቼ ሊያከናውነው እንደሚገባና እንዴት ማከናወን እንደሚኖርበት አሰሪው የመቆጣጣር ስልጣን ያለው መሆኑ መረጋገጥ ያለባቸው መሆኑን ነው፡፡ አሰሪው ሰራተኛውን በዚሁ በህጉ በተቀመጠው አግባብ ተቆጣጥሮ ስራውን የሚያሰራ መሆኑ መረጋገጡ አንድ ተዋዋይ ወገን ዋጋ እየተከፈለው የንግድ ስራ ወይም በራሱ የሙያ ኃላፊነት የሚሰራ ስራ ከሚያከናውን ወገን በትክክል ለመለየት የሚረዳ መሆኑም ተቀባይነት ያለው መለኪያ ነው፡፡በአዋጁ ለቅጥር ውሉ ከተሰጠው ትርጉም መካከል አንዱ የደመወዝ ጉዳይ ሲሆን ሰራተኛው ለአሰሪው በገባው ለአሰሪው ጥቅምና በአሰሪው ቁጥጥር ችሎታውንና ጊዜውን በመጠቀም ተገቢውን አገልግሎት ለአሰሪው ለመስጠት ግዴታ የሚገባው አሰሪው ለሰራተኛው ተገቢውን የድካም ዋጋ በደመወዝ መልክ የመክፈል ግዴታ ሲገባነው፡፡ ደመወዝ ደግሞ በጥሬ ገንዘብ ወይም በአይነት ሊሆን የሚችል ሁኖ የአከፋፈሉ ጊዜም አንደነገሩ ሁኔታ በየቀኑ፣በየሁለት ቀኑ፣ በየሁለት ሳምንቱ፣በየወሩ፣በተሰራው ሰራ መጠን……ወዘተ ሊሆን እንደሚችል ከአዋጁ አንቀጽ 4 እና 58 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡በመሆኑም በእነዚህ የአከፋፈል ጊዜያት ወይ ዘዴዎች ደመወዝ የመከፈሉ ሁኔታ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል በተመሰረተው የቅጥር ሁኔታ ላይ በሕጉ ረገድ ለውጥ የማያስከትል መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

 

ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም ሟች ተጠሪ ግለሰብ ከውጪ ከሚያስመጣቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ በማመላለስ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበርና ስራውን የሚሰራው ጊዜና ቦታ መኖሩን፣ይህም በተጠሪው መሪነት ወይም ቁጥጥር ሲከናወን የነበረ መሆኑን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡ተጠሪ ሟቹ ሲከፈላቸው የነበረው ደወመዝ በቁርጥ መሆኑን ጠቅሰው ከመከራከራቸው ውጪ ሟቹ የሚሰጡትን አገልግሎት በራሳቸው ቁጥጥር ስር ያልነበረ መሆኑን አላስረዱም፡፡ የደመወዝ አከፋፈል በቁርጥ መሆኑ ደግሞ የቅጥር ግንኙነት ከላይ በተመለከቱት የአዋጁ ድንጋጌ ስለ ሰራተኛ ማንነት የተቀመጠውን ትርጉም ላለመቀበል የሚያስችል አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር  ጉዳዩን  ስንመለከተው ሟች  በተጠሪ ቁጥጥር ስር  ሁነው የሹፍርና አገልግሎት


ሲሰጡ የነበረ መሆኑ በሚገባ የተረጋገጠ ሁኖ እያለ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሟች በራሱ የሙያ ኃላፊነት ሲሰሩ የነበሩ ናቸው በማለት ግንኙነቱ በአዋጅ  ቁጥር  377/96 የሚገዛ አይደለም በማለት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ መሻሩ በሕጉ ስለሰራተኛ ማንነት የተቀመጡ መለኪያዎችን በአግባቡ ባላገናዘበ መልኩ ሁኖ አግኝተናል፡፡ በመሆኑም ውሳኔው የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 2(1)(2)፣3(2(ረ))፣ 4 እና 58 ድንጋጌዎችን ይዘትና መንፈስ የጣሰ በመሆኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል፡፡

 

 ሁ ለተ ኛ ውን ነጥ ብ በተ መለከተ -ሟች የተጠሪ ሠራተኛ ናቸው ከተባለ በስራ ላይ እያሉ ሕይወታቸው ማለፉ ግራ ቀኙን ያላከራከረ ጉዳይ ነው፡፡ በስራ ምክንያት ለሚመጡ ጉዳቶች አሠሪው ሀላፊነት አለበት፡፡ ስለዚህ በስራ ምክንያት የሚመጣ ጉዳት ከሆነ አሠሪው ኃላፊነቱን እንዲወስድ የተደረገ ሲሆን በአዋጁም በስራ ላይ የሚደርስ ጉዳት ማለት በስራ ላይ የሚደርስ አደጋ ወይም በስራ ምክንያት የሚመጣ በሽታ መሆኑን በቁጥር 95(2) ደንግጓል በአዋጅ አንቀጽ 96(1) ”አሠራው ጥፋት ባይኖረውም…..” ተብሎ መመልከቱ የአሠሪው የኃላፊነት ዓይነት ጥፋት ሣይኖር ኃፊነት /Strict Liability or Liability in the absence of Fault/ መሆኑን የሚያሣይ ነው፡፡ አሠሪው ከዚህ ዓይነት ኃላፊነት የሚድነው ጉዳት የደረሠበት ሠራተኛ ሆነ ብሎ በራሡ ላይ ያደረሠው ጉዳት መሆኑን ማስረዳት ሲችል ስለመሆኑ አንቀጽ 98(2) ያስገነዝባል፡፡ሆነ ብሎ ያደረሠው ጉዳት የሚባሉት ሁኔታዎችም ሠራተኛው አስቀድሞ በግል የተሠጡትን የደህንነት መጠበቂያ መመሪያዎችን መጣስ ወይም የአደጋ መከላከያ ደንቦችን መተላለፍ ወይም አካሉን ወይም አእምሮውን በሚገባ ለመቆጣጠር በማይችልበት ሁኔታ በመጠጥ ወይም በአደንዛዥ እፅ ሠክሮ በሥራ ላይ መገኘት መሆናቸውን ህጉ በቁጥር 96(2(ሀ እና ለ)) ስር አመላክቷል፡፡

 

የአዋጁ አንቀጽ 97(1) ድንጋጌ ሲታይም አንድን አደጋ በስራ ላይ የደረሠ ነው ለማለት ሠራተኛው ስራውን በማከናወን ላይ እያለ ወይም ከስራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ ከራሡ ውጭ በሆነ ምክንያት ወይም ስራውን ለማከናወን ባደረገው ጥረት ምክንያት በአካሉ ወይም በአካሉ በማንኛውም ክፍል ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ ላይ በድንገት የደረሠበት ጉዳት ስለመሆኑ መርሁን ያስቀመጠ ሲሆን ይኽው ድንጋጌ ከፊደል (ሀ) እስከ ፊደል (መ) በተመለከቱት ንዑስ ድንጋጌዎች የተመለከቱት ምክንያቶች በስራ ላይ የደረሠ አደጋ ተብለው የሚጨመሩ ስለመሆኑ ያሣያል፡፡ ስለሆነም በመርሁ መሠረት ሠራተኛው የጉዳት ካሣ ለማግኘት ማሣየት የሚጠበቅበት አደጋው ስራውን በማከናወን ላይ እያለ የደረሠ መሆኑን፣ ወይም ደግሞ በራሡ ባልሆነ ምክንያት ግን ከሥራው ጋር ግንኙነት ባለው መልኩ የደረሠበት አደጋ መሆኑን ነው ፡፡ከላይ እንደተገለፀው ከስራ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ ህጉ አስቀምጧል፡፡ ለዚህ ጉዳይ ቀጥተኛ አግባብነት ያለው ድንጋጌ በአንቀጽ 97(1(ሐ)) ስር የተመለከተው ሲሆን በዚህ ድንጋጌ መሠረት አሠሪው በመደበው የመጓጓዝ አገልግሎት ሠራተኛው ሲጠቀም ጉዳት ከደረሠ አደጋው በስራ ላይ እንደደረሠ ተቆጥሮ ኃፊነቱን ከአሠሪው ሊወሰድ የሚገባ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ይኽው ድንጋጌ አሠሪው የመደበው የመጓጓዝ አገልግሎት አደጋው ከደረሠበት በአሰሪው ስር ባለው ሌላ ሠራተኛ ወይም 3ኛ ወገን ከሆነ አሰሪው ለተጐጂው ሠራተኛ የጉዳት ካሣ ኃፊነት የሌለበት ስለመሆኑ አያሣይም ይልቁንም ድንጋጌው በአዋጁ አንቀጽ 96(1) ስር ከተመለከተው የአሠሪ አላፊነት ዓይነት ጋር ተዳምሮ ሲታይ አሠሪው አላፊነት ያለበት መሆኑን የሚያጠናክር ነው በሌላ አገላለፅ በሠራተኛው ላይ ጉዳት ያደረሠው ሠራተኛው ወደ ስራ ሲሄድና ከስራ ወጥቶ ወደ ቤቱ ሲመለስ አሠሪው በመደበው የመጓጓዠ አገልግሎት ሲጠቀም አደጋ የደረሠበት መሆኑ ከተረጋገጠ 3ኛ ወገኖች ለአደጋው ያደረጉት አስተዋጽኦ ለአሰሪው    መከላከያ


ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ሟች የተጠሪን መኪና በወቅቱ ሲያሽከረክሩ የነበሩ መሆኑ መረጋገጡ ተጠሪን ነፃ ሊያደርገው የሚችልበት ህጋዊ ምክንያት ስለሌለ ተጠሪ ለጉዳቱ ኃላፊነት ያለባቸው ናቸው፡፡

 

ተጠሪ ለጉዳቱ ኃላፊ ናቸው ከተባለ የጉዳት ካሣ መጠኑ ምን ያህል ሊሆን ይገባል?፣ ካሳው መክፈል ያለበት ለየትኞቹ የተጐጂ ጥገኞች ነው? የሚለው ጥያቄም በህጉ አግባብ መታየት ያለበት ነው፡፡ ለዚህጥያቄ ምላሽ የሚሠጠው ድንጋጌም በአዋጅ ቁጥር 377/96  አንቀጽ 107(1(ሐ) ስር ተመልክቷል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ማንኛውም በስራ ላይ የሚመጣ ጉዳት የደረሠበት ሠራተኛ የሞተ እንደሆነ ለጥገኞች የጡረታ አበል ወይም ዳረጐት ወይም ካሣ የማግኘት መብት ያለው ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡የአዋጁ አንቀጽ 110 ድንጋጌ ሲታይም ለሟች ሠራተኛ ጥገኞች የሚከፍሉትን የክፍያ ዓይነቶችንና ጥገኛ የሚባሉትን ወገኖች በንዑስ ቁጥር አንድና ሁለት በግልፅ ዘርዝሯል፡፡ በዚህም መሠረት ማንኛውም ሠራተኛ ወይም ለማጅ ሠራተኛ በስራ ምክንያት በደረሠበት ጉዳት የተነሣ የሞተ እንደሆነ የጉዳት ካሣ ለጥገኞች፣ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወጪ እንደሚከፈልና ጥገኞች የሚባሉትም የሟች ህጋዊ ባል ወይም ሚስት፣ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ የሟች ልጆችና በሟች ሠራተኛ ድጋፍ ይረዱ የነበሩ የሟች ወላጆች ስለመሆናቸው ተመልክቷል፡፡

 

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም 1ኛ አመልካች የሟች ሚስት፣ ሌሎች ተጠሪዎች ደግሞ ተወላጅ ናቸው፡፡ በመሆኑም አመልካቾች በህጉ አግባብም የሟች ጥገኛ መሆናቸው ስለተረጋገጠ የጉዳት ካሣ የሚገባቸው ሆኖ ተገኝቷል፡፡

 

የጉዳት ካሳ መጠኑም በሰራተኛው በስራ ላይ እያለ የሞተ እንደሆነ የሰራተኛው የዓመት ደሞዝ በአምስት ተባዝቶ የሚከፈል እንደሆነ አንቀፅ 110(3) ተመልክቷል፡፡ይህንኑ ለመወሰን ደግሞ የሰራተኛው ደመወዝ መጠኑ በትክክል ሊታወቅ ይገባል፡፡በተያዘው ጉዳይ የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሟችን ደመወዝ መጠን በወር 12,000.00 ያደረገው በወር ውስጥ አስራ አምስት ቀናትን ለተጠሪ አገልግሎት ለመስጠት ይችላሉ በሚል መነሻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ በግልጽ የቀረበ ማስረጃ የለም፡፡በፍሬ ነገር ደረጃ በሚገባ የተረጋገጠው ሟች ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ለሚያደርሱት አንድ ተሸከርካሪ ብር 800.00(ስምንት መቶ ) የሚከፈላቸው መሆኑ ነው፡፡ይህ ደግሞ ሟች በወር አስራ አምስት ቀናት ሙሉ ስራውን ይሰራሉ ተብሎ ስላልተረጋገጠ የወርሃዊ ደመወዝ መጠን በብር 800.00 ሊታሰብ የሚገባው ሁኖ አልተገኘም፡፡በመሆኑም ይህ ችሎት የሟች ወርሃዊ ደመወዝ ከብር 3200.00 ሊበልጥ የሚችልበትን አግባብ አላገኘም፡፡ ይኼው የደመወዝ መጠን መሰረት ተደርጎ አመታዊ ደመወዝ ሲሰላ ደግሞ ብር 38,400.00(ሰላሳ ስምንት ሺህ አራት መቶ ብር) ሁኖ በአዋጁ አንቀጽ 110(3) መሰረት የአምስት ዓመቱ ሲሰላ ብር 192,000.00(አንድ መቶ ዘጠና ሁለት ሺህ ብር) የጉዳት ካሳ ሊሆን የሚገባው ሁኖ አግኝተናል፡፡

 

የቀብር ሥርዓት ማስፈፀሚያ ክፍያ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 110(1(ለ) መሠረት ሲሰላም የሁለት ወር ደመወዝ ብር 6,400.00(ስድስት ሺህ አራት መቶ ብር) መሆን ያለበት ሁኖ አግኝተናል፡፡

 

በአጠቃላይ 198,400.00 (አንድ መቶ ዘጠና ስምንት ሺህ አራት መቶ ብር) የሟች ጥገኛ ለሆኑት ለአሁኑ አመልካቾች በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 110(3) እና (4) ስር በተመለከተው


አግባብ የሚከፈል የጉዳት ካሣ መጠን ሁኖ አግኝተናል፡፡ ሲጠቃለልም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ፣ የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔ ደግሞ በከፊል መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለባቸው በመሆኑ ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሣ ኔ

 

1. በፌዴራሉ ከፍ/ፍ/ቤት በመ/ቁ 09770 ሐምሌ 23 ቀን 2006  ዓ/ም  ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 348(1) መሠረት ተሽሯል፡፡

2. በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ 38410 ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም እና መጋቢት 29 ቀን 2006 ዓ.ም የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

3. በሟች እና በተጠሪ መካከል የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ውል አለ፣ ሟቹ የሞቱት በስራ ላይ እያሉ በመሆኑ ለሟቹ ጥገኞች የሞት ጉዳት ካሳ የሟቹ የአምስት አመት ደመወዝና የሁለት ወር ደመወዝ ለቀብር ስነ ስርዓት ማስፈፀሚያ ተጠሪ የመክፈል ኃላፊነት አለባቸው ብለናል፡፡

4. ተጠሪ ለአመልካቾች የሚከፍሉት የካሳ መጠንም ብር 198,400.00(አንድ መቶ ዘጠናስምንት ሺህ አራት መቶ) ሁኖ አከፋፈሉም በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 110(3(ሀ) ((ለ)) በተመለከተው አግባብ 50% ለ1ኛ አመልካች (የሟች ሚስት) ቀሪው 50% ደግሞ ለሟች ልጆች (2ኛ እና 3ኛ አመልካቾች) ሊሆን ይገባል ብለናል፡፡ የጠበቃ አበል በዚህ ችሎት በተወሰነው የገንዘብ መጠን 10% ተጠሪ ለአመልካቾች ሊተኩ ይገባል ብለናል፡፡

5.   ሌሎች ወጪና ኪሳራዎች የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡