105620 labor law dispute/ reduction of work force/ payments due

ከስራ በቅነሳ ምክንያት ለሚሰናበት ሠራተኛ የስራ ስንብት ክፍያ የሚከፈል ስለመሆኑ፡-

 

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 39(1)(ሐ)፣40(1)(3)፣28(2)(ሀ)(3)

የሰ.መ.ቁ. 105620

 

ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካቾች፡-1. አቶ ሀብቴ ብርሃኔ

 

2. አቶ በየነ ለሜቻ

 

3. አቶ ግርማ አንጉራ

 

4. አቶ ጌትነት ዘውዴ               ጠበቃ አቶ ሣሙኤል ሽፈራው - ቀረቡ

 

5. አቶ ጥላሁን ተክለመድህን

 

6. አቶ ተመስገን ግርማ

 

ተጠሪ፡- አቶ ሙሉነህ ቡና ላኪ ትራንስፖርትና ትሪንዚት አገልግሎት - ጠበቃ ፈጠነ ደረሰ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካቾች መዝገብ ቁጥር 140043 ሐምሌ 3 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልን በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ የሥራ ስንብት የሁለት ወር ደመወዝ ይከፈለን በማለት የቀረበ ጥያቄ የሚመለከት ነው፡፡ ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በሥር ፍርድ ቤት አመልካቾች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡

 

1. የክርክሩ መነሻ አመልካቾች ያቀረቡት ክስ ነው፡፡ ከሳሾች ተከሳሽ በሹፌርነት ተመድባችሁ የምታሽከረክሩት መኪና ተሸጧል በሚል ምክንያት የሁለት ወር ማስጠንቀቂያ ከሰጠን በኃላ የሥራ ውላችን አቋርጧል፡፡ ተከሳሽ የሥራ ውሉን በቅነሳ ምክንያት ማቋረጥ ሲገባው አላግባብ የሥራ መደብ ተሰርዟል በማለት ያቋረጠው በመሆኑ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ህግ መሠረት ሊከፍል የሚገባውን የሁለት ወር ደመወዝ የሥራ ስንብት ክፍያ ያልከፈለ በመሆኑ እንዲከፍል ውሣኔ ይስጥልን በማለት ክስ አቅርበዋል፡፡ ተጠሪ በሥር ፍርድ ቤት ተከሳሽ


ሆኖ ቀርቦ ከሳሾች የሚያሽከረክሯቸው መኪኖች በመሸጣቸው የሥራ መደቡ ተሰርዟል፡፡ ስለዚህ ተከሳሾች የስራ ስንብት ክፍያ የምንከፍልበት ምክንያት የለም በማለት ተከራክሯል፡፡

2. የሥር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኃላ ተከሳሽ ኪሣራ አልደረሰበትም፡፡ ኪሳራ የደረሰበት ራሱን የቻለ የህግ ሰውነት ያለው የቡና ላኪ ድርጅት ላይ ነው፡፡ ከሳሾች የሚያሽከረክሯቸው መኪኖች የተሸጡትም የቡና ላኪ ድርጅት ዕዳ መክፈያነት ነው፡፡ ተከሳሽ የሥራ ውሉን ከሳሾች የሚያሽከረክሯቸው መኪኖች በቡና ላኪ ድርጅት ላይ በደረሰው ኪሣራ ምክንያት በዕዳ መክፈያነት በመሸጣቸው የሥራ ውሉን ያቋረጠ በመሆኑ፣የሥራ ውሉ የተቋረጠው በቅነሳ እንጂ የሥራ መደብ በመሠረዙ ምክንያት አይደለም፡፡ ይህም በመሆኑ ከሳሽ በተከሳሾች የሁለት ወር ደመወዝና አገልግሎት ጊዜአቸውን አስልቶ የሥራ ስንብት ክፍያ የመክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡

3. አመልካች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ መልስ ሰጭዎች ያሽከረከሯቸውየነበሩት መኪናዎች መሸጣቸው ተረጋግጧል፡፡ መልስሰጭዎች ያሽከረክሯቸው የነበሩ መኪናዎች መሸጣቸው ከተረጋገጠ ይግባኝ ባይ ሌላ መኪና ገዝቶ እስኪተካ ድረስ የሹፌርነት የሥራ መደብ ተሰርዟል ለማለት ይቻላል፡፡ ይግባኝ ባይ መልስ ሰጭዎችን የሥራ መደብ በመሰረዙ ምክንያት ከሥራ ያሰናብታቸው በመሆኑ የሥራ ስንብት ክፍያ ሊከፍል አይገባም በማለት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ ሽሮታል፡፡

4. አመልካቾች መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ ካሉት ከመቶ በላይ ከሚሆኑ ሹፌሮች ዝቅተኛ አገልግሎትና የሥራ ልምድ በመምረጥ ቀንሶ ከሥራ አሰናብቶናል፡፡ ከዚህ አንፃር የተጠሪ አድራጎት ቅነሳ እንጂ የሥራ መደብ መሠረዝ ነው ሊባል አይገባውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሰሪው ሠራተኛውን ከሥራ ሲያሰናብት የአገልግሎት ክፍያ የመክፈል ሃላፊነት አለበት፡፡ በመሆኑም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የስራ ስንብት ክፍያ አይገባችሁም በማለት የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር እንዲታይልን በማለት አመልክተዋል፡፡ ተጠሪ ጥር 28 ቀን 2007 ዓ.ም በተፃፈ መልስ አመልካቾች የተሰናበቱት የሥራ መደቡ የተሠረዘ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይህንን በማገናዘብ የሥራ ስንብት ክፍያ ተጠሪ የመክፈል ኃላፊነት የለበትም በማለት የሰጠው ውሣኔ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክሯል፡፡ አመልካችዎች የካቲት 14 ቀን 2007 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡

5. ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ግራ ቀኙ ያቀረቡት ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ተጠሪ ለአመልካቾች የሥራ ስንብት ክፍያ ሊከፍል አይገባም በማለት የሰጠው ውሣኔ የሕግ መሠረት አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

6. አሠሪው ማስጠንቀቂያ በመስጠት የሥራ ውል ለማቋረጥ የሚችልባቸውን መሠረታዊ ምክንያቶች አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 28 በሁለት ከፍሎ አስቀምጧቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ከሠራተኛው ችሎታ ማጣት ወይም ሁኔታ የሚመለከቱ ምክንያቶችም ሲሆኑ በአዋጅ አንቀፅ 28 ንዑስ አንቀጽ 1 ከ’’ሀ’’ እስከ ‘’መ’’ በዝርዝር ደንግጓል፡፡ ሁለተኛው ከአሠሪው ድርጅታዊ አቋም ወይም የሥራ እንቅስቃሴ የሚመለከቱ ምክንያቶች የሥራ ውል ሲቋረጥ መሆኑ በአዋጅ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 2 ተመልክቷል፡፡ ተጠሪ አመልካቾች የሚያሽከረክሯቸው መኪኖች በዕዳ ምክንያት በመሸጣቸው የአመልካችዎች የሥራ መደብ በአዋጅ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 1 (መ) መሠረት ተሰርዟል በማለት የሚያቀርበው ክርክር ተጠሪ ከፈፀመው ተግባር አግባብነት ያለው ሆኖ አላገኘነውም፡፡


7. አመልካችዎች የሚያሽከረክሯቸው መኪኖች የተሸጡት በተጠሪ ድርጅታዊ አቋምና የሥራ እንቅስቃሴ ምክንያት በመሆኑና በተለይም ቡና የሚልከው የንግድ ድርጅት  ኪሣራ ስለደረሰበት መኪኖቹ ተሸጠው ዕዳ መክፈያነት የዋሉ መሆኑ በሥር ፍርድ ቤት ተረጋግጧል፡፡ አንድ ድርጅት ሠራተኞች የተሰማሩባቸው ሥራዎች በከፊልም ሆነ በሙሉ በቀጥታና በሌላ ቦታው የሚያስቆምና የሠራተኞች ቅነሳ የሚያስከትል ሁኔታ ሲያጋጥመው ማስጠንቀቂያ በመስጠት የሥራ ውሉን ሊያቋርጥ እንደሚችል በአዋጅ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 2(ሀ) ተደንግጓል፡፡ የተጠሪም አድራጎት በዚህ ድንጋጌ ሥር የሚሸፈን ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

8. ሰለ ሥራ ስንብት ክፍያ የሚደነግገው የአዋጅ ቁጥር 377/96 ምዕራፍ ሶስት በክፍል ሁለት የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ ሰራተኛ በዚህ አዋጅ በተመለከቱት ሁኔታዎች መሠረት ከሥራ ሲቀነስ የሥራ ስንብት ክፍያ የማግኘት መብት ያለው መሆኑ በአንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1(ሐ) በግልፅ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ በተጠሪ ድርጅታዊ አቋምና የሥራ እንቅስቃሴ ምክንያት ከሥራ የተቀነሱት አመልካቾች በአዋጁ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ  1 እና ንዑስ አንቀጽ 3 የተመለከቱትን የሥራ ስንብት ክፍያዎች የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑ ከድንጋጌዎቹ ይዘት መንፈስና ዓላማ የምንረዳው ጉዳይ ሆኖ እያለ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አመልካችዎች የሚያሽከረክሯቸው መኪናዎች በዕዳ ምክንያት መሸጥ ከተጠሪ ድርጅታዊ አቋምና የሥራ እንቅስቃሴ ነጥሎ በማየት ተጠሪ ለአመልካችዎች የሥራ ስንብት ክፍያ የመክፈል ግዴታ የለበትም በማለት የሰጠው ውሣኔ የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 2(ሀ) ና ንዑስ አንቀጽ 3 አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 (ሐ) እና የአዋጁን አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 1 እና ንዑስ አንቀጽ 3 ያላገናዘበና መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

1.  የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ተሽሯል፡፡

2. ተጠሪ ለአመልካችዎች የሥራ ስንብት ክፍያ የመክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት ወስነናል፡፡

3. ተጠሪ ለአመልካችዎች በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 1 ንዑስ አንቀጽ 2 እና ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት በማስላት የሥራ ስንብት ክፍያ ይክፈላቸው በማለት ወስነናል፡፡

4. በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡


 

የ/ማ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡