104465 Labor dispute Unlawful termination of contract of employment

Labor dispute

Unlawful termination of contract of employment

Proclamation no 377/96 art. 4/1/, 23, 26, 30, 31, 33, 39, 40/2/, 43/4/ሀ/,

35/1/, 38

የአንድ ድርጅት ሠራተኛ ለአሰሪው የስራ መልቀቂያ  አስገብቶ የስራ መልቀቂያው በአሰሪው ምክንያት በወቅቱ ሣይሠጠው ቆይቶ ሰራተኛው የስራ ግዴታውን እየተወጣና የስራ ግንኙነታቸው በተግባር ቀጥሎ ባለበት ሁኔታ ከረጅም ጊዜ በኋላ አሰሪው ሰራተኛው ቀደም ብሎ ያስገባውን የስራ መልቀቂያ መሰረት በማድረግ የስራ ውሉን ቢያቋርጥ የስራ ውሉ የተቋረጠው በህገወጥ መንገድ ነው ሊባል የሚችል ስለመሆኑ፣ 

 

አዋጁ ቁ.377/96 አንቀፅ 4/1/፣23፣26፣30፣31፣33፣39፣40/2/፣43/4/ሀ/፣ 35/1/ለ/፣38

 

የሰመ// 104465

መጋቢት 30 ቀን 2007 /

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

ሡልጣን አባተማም

ሙስጠፋ አህመድ

ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- /ሪት ሸዊት ኃይሉ - VC - ስላልሰራ ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

ተጠሪ፡- መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራዝ - /ፈጅ ደረጀ ከበደ - ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

   

አዋጅ ቁጥር 377/96 “መሰረት አድርጎ የቀረበ የአሠሪና ሠራተኛ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች ባሁኑ ተጠሪ ላይ በደጉዓ ተምቤን ወረዳ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም ባጭሩ፡- በተጠሪ ድርጅት ውስጥ በካሼር የስራ መደብ  ላይ በወር ብር 1744.00 እየከፈላቸው ከሰኔ 27 ቀን 2004 / ጀምሮ እስከ ሀምሌ 25 ቀን 2005 ድረስ ቀጥሮ ሲያሰራቸው እንደቆዩና ከህግ ውጪ የስራ ውሉ ያለማስጠንቀቂያ በአሰሪው ድርጅት የተቋረጠ መሆኑን ገልጸው የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈሏቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪ ለክሱ በሰጠው መልስም፡- የስራ ውሉ  የተቋረጠው አመልካች ታህሳስ 17 ቀን 2005 / ባቀረቡት መልቀቂያ መሰረት መሆኑን ጠቅሶ ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል በማለት ተከራክሯል፡፡ የስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ በመመርመር አመልካች ታህሳስ 17 ቀን 2005 / ባስገቡት የስራ ውል መነሻ ግንኙነቱ መቋረጡን ገልጾ ስንብቱ ሕጋዊ ነው በማለት ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ የአሁኗ ተጠሪ ለምስራቅ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው ተቀባይነት አላገኙም፡፡ ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታቸውን አቅርበውም ችሎቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ስንብቱ በአመልካች ጥያቄ መሰረት የተደረገ በመሆኑ ሕጋዊ ነው በማለት የበታች ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በድምጽ ብልጫ አጽንቷል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም አመልካች ታህሳስ 17 ቀን 2005 / ስራውን ለመልቀቅ ለተጠሪ ድርጅት መልቀቂያ አስገብተው ቆይ ተብለው ለሰባት ወራት ያህል ስራ እንዲሰሩ ከተደረገ በኋላ የስራ ውሉን ከሰባት ወራት በፊት በቀረበ ማመልከቻ መነሻ ተቋርጧል ተብሎ ስንብት መደረጉና ሁሉም ክፍያዎች ውድቅ መደረጋቸው ያላግባብ ነው የሚል ነው፡፡አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም ተጠሪ ከአመልካች ጋር የነበረውን የስራ ውል ያቋረጠው በአመልካች የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ነው ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ሊታይ የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል፡፡ ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው በአመልካችና በተጠሪ መካከል በ17/04/2005 ዓ/ም በተጻፈ ማመልከቻ የስራ መልቀቂያ እንዲሰጣቸው ለተጠሪ ጥያቄ አቅርበው ተጠሪም የአመልካችን ጥያቄ አቆይቶ አመልካች ለሰባት ወራት ምድብ ስራቸው ላይ እየተገኙ ስራውን እንዲሰሩና ግዴታቸውን እንዲወጡ ሲያደርግ ቆይቶ ከነሐሴ ወር 2005 ዓ/ም ጀምሮ የአመልካች የወር ደመወዝ ሳይያዝና ስማቸው ከአቴንዳንስ ተሰርዞ በአመልካች የስራ መደብ ላይ ሌላ ገንዘብ ያዥን በመመደብ አመልካች በ17/04/2005 ዓ/ም ያስገቡትን የስራ መልቀቂያ በመጥቀስ የስራ ውሉን ያቋረጠ መሆኑን ነው፡፡

በመሰረቱ የስራ ውል ሁለት ወገኖች አንዱ አሰሪ ሌላኛዉ ሠራተኛ ሆነው በአሠሪው ቁጥጥር እያደረገ ሠራተኛው ለሚሰራለት የጉልበት ወይም የዕወቅት ስራ ደሞዝ የሚከፍልበት የስራ ግንኙነት የሚፈጥር ስምምነት ስለመሆኑ ከአዋጅ ቁጥር 377/96 በአንቀጽ 4/1/ ስር ከተደነገገው ድንጋጌ ይዘት የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ የህጉ የትርጉም ይዘት መሰረት ከሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች አንዱ በሕጉ መሰረት አሠሪ ነው ተብሎ የሚወሰድ ሲሆን ይህ ወገን ለሚያገኘው አገልግሎት ተገቢውን ደሞዝ የሚከፍልና አገልግሎቱም በእርሱ ቁጥጥር የሚመራ መሆኑ፣ሠራተኛ ደግሞ በአሠሪው ቁጥጥር  መሠረት አገልግሎት  የሚሰጥ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ የስራ ውሉ መኖሩ ደግሞ በማናቸውም አይነት ሊረጋገጥ የሚችል ነው፡፡ በሕጉ አግባብ የተመሰረተ የስራ ውል ደግሞ የሚቋረጥባቸው መንገዶች ስለመኖራቸው ሕጉ ያስቀመጠው ጉዳይ ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 377/96 የስራ ውል ስለሚቋረጥበት ምክንያቶችና ሁኔታዎችን በአንቀጽ 23 ስር ተመልክተዋል፡፡ እነዚህም በሰራተኛው አነሳሽነት የሚደረግ፣ በሕግ በተደነገገው መሰረት፣በህብረት ስምምነት መሰረት እና በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት የሚደረግ የውል ማቋረጥ ሲሆኑ ዝርዝር ምክንያቶቻቸውና ሁኔታዎችንም ህጉ አስቀምጧል፡፡ በአሰሪው አነሳሽነት የሚደረግ የስራ ውል መቋረጥ እንደየሁኔታው በማስጠንቀቂያ ወይም ያለማሰጠንቀቂያ ሊደረግ የሚችል ሆኖ የምክንያቶቹ ዝርዝር እና አፈጻጸሙ በአዋጁ አንቀጽ 26 እስከ 30 ባሉት ድንጋጌዎች ስር በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ሌላው በህጉ በዝርዝር የተቀመጠው የስራ ውል ማቋረጥ ስርዓት በሰራተኛው አነሳሽነት የሚደረገው ሲሆን ይህም በአሰሪው አነሳሽነት ሊደረግ እንደሚችለው በማስጠንቀቂያ እና ያለማሰጠንቀቂያ ውሉን ሰራተኛው የሚያቋርጥበት መንገድ ስለመኖሩና ውሉን ለማቋረጥ የሚቻልባቸው ሁኔታዎቹና ምክንያቶቹን ዘርዝሮ የያዘ ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎችና ምክንያቶቹ በአዋጁ ከአንቀጽ 31 እስከ 33 ድንጋጌዎች ስር በግልጽ ተደንግገው ይገኛሉ፡፡  እንግዲህ ሕጉ የስራ ውሉ ሊቋረጥ የሚችልባቸውን መንገዶች በዝርዝር ከአስቀመጠ በግራ ቀኙ መካከል ክርክር ሲነሳም ውሉ የተቋረጠበትን መንገድ ሕጋዊ መሆን ያለመሆኑ ተለይቶ ዳኝነት መሰጠት ያለበት በሕጉ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ነው፡፡

በተያዘው ጉዳይ በአመልካችና በተጠሪ ከሰኔ 27 ቀን 2004 ዓ/ም ጀምሮ ህጋዊ የስራ ውል መኖሩ ግራ ቀኙን ያላከራከረ ሲሆን ግራ ቀኙን እያከራከረ ያለው ጉዳይ ይኼው ውል የተቋረጠው በማን አነሳሽነት ነው? የሚለው ነው፡፡ ተጠሪ አመልካች ታህሳስ 17 ቀን 2005 ዓ/ም ያስገቡትን የስራ መልቀቂያ መሰረት አድርጎ የስራ ውሉን ማቋረጡን ያልካደው ሲሆን አመልካችም ታህሳስ 17 ቀን 2005 ዓ/ም የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ሳይክዱ መልቀቂያው ሳይሰጣቸው ቆይቶ የስራ ግዴታቸውን እየተወጡ እስከ ሰኔ ወር 2005 ዓ/ም ድረስ ያለው ደመወዝም እየተከፈላቸው ስራቸውን ሲሰሩ የቆዩ መሆኑን ገልጸው የስራ መልቀቂያ ጥያቄአቸው በተጠሪ ምክንያት ተግባራዊ ያለመሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው የተጠሪ የስራ ስንብት የተከናወነው አመልካች የስራ መልቀቂያ ከአስገቡ ከሰባት ወራት በኋላ መሆኑንና መልቀቂያው ለሰባት ወራት የቆየው በአመልካች ፍላጎት ስላለመሆኑ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ አመልካች መልቀቂያውን ያነሱ ስላለመሆናቸው በተጠሪ በኩል የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ የአመልካች የስራ መደብ ላይ ተገቢው ሰራተኛ ባለመገኘቱ ሰራተኛ እስከሚገኝ ድረስ አመልካች በስራቸው ላይ እንዲቆዩ የተደረጉ ስለመሆኑና ስራተኛው ሲገኝ መልቀቂያው የሚሰጣቸው ሰለመሆኑ በተጠሪ በኩል የቀረበ ግልጽ ክርክርና ማስረጃ ያለመኖሩን ከክርክሩ ሂደት ተገንዝበናል፡፡ አመልካች የስራ መልቀቂያ ከአስገቡ በኋላ ለረዥም ወራት እንደ ሰራተኛነታቸው በሕጉ የተጣለባቸውን የስራ ግዴታ ሲወጡ መቆታቸውና ተጠሪም ለአመልካች ስራ እየሰጠና ደመወዝም እስከ ሰኔ ወር 2005 ዓ/ም ድረስ እየከፈለ መቆየቱ ሲታይ ግራ ቀኙ በነጻ ፍላጎታቸው የቀደመውን የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት እንዲቀጥል የተስማሙ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ አግባብ እንዲቀጥል የተደረገ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ደግሞ በተግባር ቀሪ በሆነው የስራ መልቀቂያ ጥያቄ በሕጉ የተቀመጠውን ስርዓት ሳይከተል ሊቋረጥ የሚችልበት አግባብ የለም፡፡ በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ከዚህ አንፃር መመልከት ሲገባቸው አመልካች ስራውን የለቀቁት በራሳቸው ተነሳሽነት ነው በሚል የሰጡት ውሳኔ የስራ ውል አመሰራረት፣ውሉ የሚቋረጥባቸውን ሁኔታዎችና ምክንያቶችን እንዲሁም በሕጉ የተቀመጡትን ስርዓቶችን ያላገናዘበ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የተሠጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡ 

1.    በደጉዓ ተምቤን ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 02582 ህዳር 23 ቀን 2006 / ተሰጥቶ በምስራቃዊ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥ 06144 ጥር 01 ቀን 2006 /ም፣በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 64078 ግንቦት 23 ቀን 2006 / በአብላጭ ደምጽ የጸናው ውሳኔ በፍ/////ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2.    ተጠሪ አመልካችን ያሰናበተው በራሱ ተነሳሽነት እና ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ነው ብለናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተጠሪ ለአመልካች በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 39 እና 40(2) መሰረት የስራ ስንብት ክፍያ፣ በአንቀጽ 43(4()) መሰረት የካሳ ክፍያ፣ በአንቀጽ 35(1()) መሰረት የማስንጠቀቂያ ጊዜ ክፍያ እና በአንቀጽ 38 መሰረት ክፍያ ለዘገዬበት ክፍያ የሁለት ወር ደመወዝ  እንዲከፍል ብለናል፡፡

3.    ሌሎች ክፍያዎች ማለትም ከስር ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት የተጠየቁት የትርፍ ሰዓት እና ህዝባዊ ባዕላት ክፍያዎች ግን በስር ፍርድ ቤት በማስረጃ ያልተጣሩ በመሆኑ የወረዳው ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን አከራክሮና በማስረጃ አጣርቶ ተገቢውን ሊወሰን ይገባል በማለት በፍ/////ቁጥር 343(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል፡፡ይፃፍ፡፡

4.    ብር 518.00 የዳኝነት ገንዘብ አመልካች ለተጠሪ ሊተኩ አይገባም ብለናል፡፡

5.    በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

ማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት ፡፡