119734 labor dispute/ merger / conversion/ termination of contract of employment

የአንድ ድርጅት ከሌላ ጋር መቀላቀል ወይም  መከፋፈል  ወይም የባለቤትነት መብት ወደ ሌላ መተላለፍ የስራ ውልን የማቋረጥ ውጤት የማይኖረው ስለመሆኑ

አዋጅ ቁ. 377/1996 አንቀፅ 23(2)

የሰ/መ/ቁ. 119734

 

የካቲት 30 ቀን 2008 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ

 

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ተብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ አብረሃ መሰለ

አመልካች፡- ይርጋ ትሬዲንግ  ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የቀረበ የለም ተጠሪዎች፡-

1.  አቶ ብዙነህ መኮንን

2.  አቶ ሻምበል አሰፋ             ጠበቃ እስጢፋኖስ ተስፋ ቀረቡ

3.  አቶ ረድኤት መሐመድ

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የስራ ስንብት እርምጃን በመቃወም የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 “ን” መሰረት አድርጎ የተነሳ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም በኦሮሚያ ብ/ክ/መንግስት በአዳማ ልዩ ዞን በአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት ከሳሾች የነበሩት የአሁኖቹ ተጠሪዎች በአሁኑ አመልካች ላይ ባቀረቡት ክስ ነው፡፡ ከሳሾቹ በ16/10/2007 ዓ.ም. ያቀረቡት ክስ ይዘትም ባጭሩ፡- ከሳሾቹ በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ ከተለያየ ጊዜ ጀምሮ በተለያየ የስራ መደብ የተለያየ መጠን ያለው ደመወዝ እየተከፈላቸው በመስራት ላይ እያሉ የድርጅቱ ባለቤት ተከሳሽ ድርጅትን ሽጠው ተከሳሽ ድርጅት ለከሳሾቹ ሌላ ስራ ሳይሰጥ ወይም ተገቢ ክፍያዎችን ሳይከፍል አላግባብ ከስራ ያሰናበታቸው መሆኑን የሚገልጽ ሆኖ የስንብት እርምጃው ሕገወጥ ነው ተብሎ ሕገወጥ የስራ ስንብት እርምጃ የሚያስከትላቸው እና ተያያዥ ክፍያዎች በአዋጁ መሰረት  ተሰልቶ እንዲከፈላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው፡፡ተከሳሽ ድርጅት በበኩሉ በ02/11/2007 ዓ.ም. በሰጠው መልስ ከሳሾቹ ከስራ እንዲሰናበቱ የተደረገው ድርጅቱ በመሸጡ እና የሚመደቡበት ሌላ የስራ ቦታ ባለመገኘቱ መሆኑን ገልጾ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ተከራክሯል፡፡


ፍርድ ቤቱም ክሱን እና የግራ ቀኙን ምስክሮች ከሰማ በኃላ የግራ ቀኙን አጠቃላይ ክርክር እና ማስረጃ መርምሮ ከሳሾቹ ከስራ እንዲሰናበቱ የተደረገው ድርጅቱ በመሸጡ ምክንያት ቢሆንም ተከሳሽ ደርጅት ይህንኑ በመግለጽ ለከሳሾቹ አስቀደሞ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ከዛሬ ጀምሮ ስራ የለም በማለት ከሳሾቹን በቀጥታ ማሰናበቱ ሕገወጥ መሆኑን ገልጾ ተከሳሽ ድርጅት ለእያንዳንዱ ከሳሽ በውሳኔው ላይ ተለይቶ በተገለጸው መጠን ሕገ ወጥ የስራ ስንብት  እርምጃ የሚያስከትላቸው እና ተያያዥ ክፍያዎችን ከአስር በመቶ የጠበቃ አበል ጋር እንዲከፍል ውሳኔ ሰጥቶአል፡፡

 

አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ይዘቱ ከላይ የተመለከተውን የወረዳ ፍርድ ቤት ውሳኔ በትዕዛዝ በማጽናታቸው የሶስቱም ስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ አመልካች ድርጅት ተሽጦ ንብረትነቱ ለዘለቄታው ወደ ሌላ ሰው መተላፉ እና ተጠሪዎቹን ወደ ሌላ ስፍራ አዛውሮ ለማሰራት የሚችል መሆኑ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ተጠሪዎቹ የማስጠንቀቂያ እና የስንብት ክፍያ የሚያገኙ ከሚሆን በቀር ለተሸጠ ድርጅት ስንብቱ ሕገወጥ ነው ተብሎ የካሳ ክፍያ እንዲከፈላቸው የተሰጠውን ውሳኔ አግባብነት ተጠሪዎቹ ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ ጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለጉዳዩ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምረናል፡፡

 

በዚህም መሰረት አመልካቹ ከስር ጀምሮ የሚከራከረው ተጠሪዎቹ ይሰሩበት የነበረው ድርጅት የተሸጠ እና ለሶስተኛ ወገን የተላለፈ በመሆኑ ምክንያት የስራ መደባቸው የተሰረዘ በመሆኑ ተጠሪዎቹ የተሰናበቱት በሕግ አግባብ መሰረት ነው በማለት መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡በመሰረቱ ተከሳሽ ድርጅት “ይርጋ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል  ማህበር” በሚል የሚታወቅ ሲሆን የተሸጠውም ይኸው ማህበር በባለቤትነት ከሚያስተዳድራቸው ንብረቶች መካከል አንዱ የሆነው እና ተጠሪዎቹ ሲሰሩበት የነበረው በአዳማ ከተማ የሚገኝ መጋዘን ነው፡፡

 

በመሆኑም የተሸጠው ተከሳሽ ድርጅት በአጠቃላይ ወይም በሙሉ አይደለም፡፡በመሰረቱ የስራ ውል የሚቋረጠው በአሰሪው ወይም በሰራተኛው አነሳሽነት ወይም በሕግ በተደነገገው መሰረት ወይም በሕብረት ስምምነት ወይም በተዋዋይ ወገኖች በሚደረግ ስምምነት ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 23 (1) ስር የተደነገገ ሲሆን የአንድ ድርጅት ከሌላ ጋር መቀላቀል ወይም መከፋፈል ወይም የባለቤትነት መብት ወደ ሌላ መተላፍ የስራ ውልን የማቋረጥ ውጤት


የማይኖረው ስለመሆኑም በዚሁ አንቀጽ በንዑስ ቁጥር (2) ስር ተመልክቷል፡፡አመልካች የድርጅቱ አካል የሆነውን መጋዘን ለሶስተኛ ወገን በሽያጭ በሚያስተላልፍበት ጊዜ የሰራተኞቹ የቅጥር ውል ከገዥው አካል ጋር የሚቀጥልበትን አግባብ ማመቻቸት ወይም ለሰራተኞቹ በሕጉ የተመለከተውን ተገቢ ክፍያዎች ከፍሎ ማሰናበት ሲገባው ድርጅቱ የተሸጠ በመሆኑ ምክንያት የስራ መደባቸው ተሰርዞአል የሚል ምክንያት በመስጠት ተጠሪዎቹን ማሰናበቱ ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡የመጋዘኑን መሸጥም ከስራ መደብ ስረዛ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡ከመሰረቱ የመጋዘኑ በሽያጭ መተላለፍ የስራ ውሉን በማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ የሚያበቃ ምክንያት ባለመሆኑ የመጋዘኑ መሸጥ ሰራተኞቹን በማስጠንቀቂያ ለማሰናበት እንደሚያስችል አድርጎ አመልካች ያቀረበው ክርክርም ሆነ በዚህ ረገድ በሰበር አጣሪ ችሎት ለክርክሩ በጭብጥነት የተያዘው ነጥብ ከላይ የተጠቀሱትን የአዋጁን ድንጋጌዎች መሰረት ያደረጉ ናቸው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡አመልካቹ የወሰደው የስንብት እርምጃ የአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 23 (2) ድንጋጌን በቀጥታ የሚቃረን ከሆነ ደግሞ የስንብት እርምጃው ሕገ ወጥ የማይሆንብት ምክንያት አይኖርም፡፡

 

ሲጠቃለል በአመልካቹ የተወሰደውን የስራ ስንብት እርምጃ ሕገ ወጥነት በማረጋገጥ ሕገ ወጥ የስራ ስንብት የሚያስከትላቸውን ክፍያዎች አመልካች ለተጠሪዎቹ እንዲከፍል በስር ፍርድ ቤቶች በየደረጃው የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ ስሕተት ተፈጸመበት ነው ለማለት  የሚቻል ሆኖ ስላልተገኘ  የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. በአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 90108 በ27/01/2008 ዓ.ም. ተሰጥቶ በአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት እንደቅደም ተከተሉ በመዝገብ ቁጥር 21815 በ23/02/2008 ዓ.ም. እና በመዝገብ ቁጥር 231434 በ02/03/2008 ዓ.ም. በትዕዛዝ የጸናው ውሳኔ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348 (1) መሰረት ፀንቶአል፡፡

2.  እንዲያውቁት የውሳኔው ቅጂ ለስር ፍርድ ቤቶች ይላክ፡፡

3. በአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 91780 የተያዘው አፈጻጸም ታግዶ እንዲቆይ በዙህ መዝገብ በ09/03/2007 ዓ.ም. ተሰጥቶ የነበረው ትዕዛዝ ተነስቷል፡፡ይጻፍ፡፡

4.  የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

5.  ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡


 

 

መ/ተ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡