113973 family law/ immovable property/ rural land /

በገጠር መሬት ላይ የሚኖረው መብት የመጠቀም መብት ሲሆን ይህንን መብት ለ3ኛ ወገን /ለሌላ/ ሰው ለረጅም ጊዜ ሰጥቶ ተጠቃሚነቱ የተቋረጠበት ባለመብት መልሶ መጠየቅ የማይችል ስለመሆኑ፣ የኦሮሚያ ክልለ የገጠር መሬት አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/1997 አንቀፅ 9(5)

 

የሰ/መ/ቁ. 113973

ቀን 21/04/2008 ዓ/ም

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሱ ሲርጋጋ ፈይሳ ወርቁ

አመልካች፡- ወ/ሮ ጠጅቱ ኡርጋ - ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ገመዳ ሬባ - አልቀረቡም

መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የባልና ሚስት ንብረት ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የጀመረው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ሮቢ ወ/ፍ/ቤት ነው፡፡ አመልካች በዚህ ወረዳ ፍ/ቤት ባለቤታቸው በነበሩት አቶ አሰፋ ገመዳ ላይ ክስ የመሰረቱት ኤዴ ከተባለ አከባቢ የሚገኝ ሁለት የበሬ መዋያ  መሬት እና ሰምንተኛ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ግማሸ የበሬ መዋያ ይዞታ መሬታችንን እኩል እንደንካፈል ይወሰንልኝ የሚል ሲሆን ተከሳሽ በበኩላቸው የተጠቀሰው ይዞታ መሬት የጋራ ይዞታችን አይደለም ሊካፈል አይገባም ብለዋል፡፡ የአሁኑ ተጠሪ ወደ ክርክሩ ጣልቃ ገብተው ግራ ቀኙ የሚከረከሩበት መሬት የግል ይዞታዬ ነው በስሜ ተለከቶ የሚገኝ እና በስሜ የምግብርበት ነው ከሳሽና ተከሳሽ በዚህ መሬት ላይ አንዳችም መብት የላቸውም ብለው ተከራካረዋል፡፡

 

ከሳሽ (የአሁኑ አመልካች) በበኩላቸው ለክርክር ምክንያት የሆነውን መሬት በ1994 ዓ/ም ከተከሳሽ ጋር ስንጋባ የተከሳሽ አባት የሆኑት ጣልቃ ገብ ሰጥተውን በጋብቻ ውላችን ላይም ተጠቅሶ ከ1994 ዓ/ም ጀምሮ በይዞታችን ስር ሆኖ ስንጠቀምበት ቆይተናል፡፡ ሰሞንኛ ተብሎ ከሚታወቀው አካባቢ ባለን ይዞታ ላይ ቤት ያለን ሲሆን በመ/ቁ. 15710 እና 14792 በሆኑ መዝገቦች በዚህ ቤት ውስጥ ሆኜ ልጆችን እንደሳደግ ፍ/ቤት አዞልኛል የጣልቃ ገብ አቤቱታ ውድቅ ይደረግልኝ ብለው ተከራከረዋል፡፡


ፍ/ቤቱ የግራ ቀኙ ምስክሮችን ሰምቶ ክርክራቸው ከቀረበው ማስረጃ ጋር በማገናዘብ መርምሮ ለክርክር ምክንያት የሆነው መሬት በጋብቻ ውሉ ላይ የተመዘገበ እና ከሳሽና ተከሳሽ ይዘውት ሲጠቀሙበት የቆዩ በመሆኑ ጣልቃ ገብ የመሬቱ ይዞታ በስማቸው የሚገኝና ግብር በስማቸው የሚገብርብት ቢሆንም ከሳሽና ተከሳሽ ይዘው የሚጠቀሙበትን መሬት ጣልቃ ገብ መጠየቅ አይችሉም ለክርክር ምክንያት የሆነውን መሬት ከሳሽና ተከሳሽ እኩል ይካፈሉ በማለት ወስኗል፡፡

 

ጣልቃ ገብ (የአሁኑ ተጠሪ) በዚህ ውሳኔ ላይ ቅሬታቸውን ለምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍ/ፍ/ቤት አቅርበዋል፡፡ ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን አከራክሮ ለክርክር ምክንያት የሆነውን መሬት የስር ከሳሽና ተከሳሽ ሲጋቡ ይ/ባይ (የስር ጣልቃ ገብ) የሰጠው መሆኑን የስር ከሳሽ ምስክሮች ያስረዳ ቢሆንም መሬት የሚሰጠው በቃል ሳይሆን በጽሁፍ ማስረጃ ሆኖ ስልጣን ባለው አካል መመዝገብ እንዳለበት ከገጠር መሬት አዋጅና ከፍ/ብ/ህ/ቁ. 1723 መረዳት ይቻላል፡፡ መሬቱ የጣልቃ ገብ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ለይግባኝ መልስ ሰጭ ከባለቤታቸው ጋር በህጋዊ  መንገድ የተሰጠ ስለመሆኑ ሳይረጋገጥ የጋብቻ ውሉም ለወደፊቱ ከአባታችን ላይ የምናገኛው መሬት የሚል በመሆኑ እና ከዚያ ወዲህም የተደረገ ስጦታ የሌለ በመሆኑ ክርክር ያስነሳው መሬት የይግባኝ ባይ (የስር ጣልቃ ገብ) ይዞታ ነው በማለት የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ በመሻር ወስኗል፡፡

 

የአሁኑ አመልካች በዚህ ውሳኔ ላይ ቅሬታቸውን ለኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍ/ቤት በይግባኝ አቅርበው ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን አከራክሮ በሰጠው ውሳኔ ክርክር ያስነሳውን መሬት ይ/ባይ ከስር ተከሳሽ ጋር በሚጋቡበት ጊዜ በጋብቻ ውላቸው ላይ የተገለጸ እና ከዚያ ወዲህ ይ/ባይ ከባለቤታቸው ጋር እየተጠቀሙበት የቆዩ መሆኑ ተመስከሯል የቀበሌው አስተዳደር ለወረዳ ፍ/ቤት በጻፈው ሪፖርት ላይም መሬቱን ተጋቢዎቹ በጋራ ሲጠቀሙበት የቆዩ መሆኑን ገልጿል፡፡ የመሬት እና አካባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት ለወ/ፍ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ መሬቱ በመልስ ሰጭ (በስር ጣልቃ ገብ) ስም የተለካ መሆኑን ነገር ግን እየተጠቀሙበት ያሉት ተጋቢዎቹ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ መሬቱ በጋብቻ ውል ላይ የተጠቀሰ መሆኑን ግራ ቀኙ አልተካካዱም ከዚያ ወዲህም ተጋቢዎቹ ሲጠቀሙበት የቆዩ መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ መ/ሰጭ በስሙ በመመዝገቡ ብቻ እስካሁን ያልተጠቀሙበትን መሬት በስሜ ተለክቷል በማለት ያቀረቡት መከራከሪያ ተቀባይነት የለውም፡፡ ቤት የሰሩበትን መሬት ይ/ባይ ቀደም ሲል እንደኖርበት በፍ/ቤት ተውስኖልኛል ብለው ያቀረቡትን መከራካሪያ መ/ሰጭ አላስተባበሉም ክርክር ያስናሳውን መሬት ይ/ባይ ከባለቤታቸው ጋር ሊካፈሉ ይገባል በማለት የከፍ/ፍ/ቤቱን ውሳኔ በመሻር ወስኗል፡፡ የአሁኑ ተጠሪ በዚህ ውሳኔ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለማስረም ለኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ሰበር ችሎቱም የግራ ቀኙን ክርክር እና የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ በማገናዘብ መርምሮ ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን መሬት ተጠሪዋ ከባለቤቷ አባት (ከአመልካች) ያገኙትና ለ9 ዓመት ሲጠቀሙበት የቆዩ መሆኑ  በምስክሮች  ተረጋግጧል፡፡  ይሁን  እንጂ  የገጠር  መሬት  አጠቃቀም  ደንብ    እና


ፍ/ብ/ህ/ቁ.1723 መሰረት የገጠር መሬት ስጦታ በጽሁፍ መሆንና መመዝገበ አለበት ተጠሪ መሬቱን በጋብቻ ወቅት በስጦታ ያገኙ ስለመሆኑ አግባብነት ያለው ማስረጃ አቅርበው ያላረጋገጡ በመሆኑ ክርክር ያስነሳው መሬት የአመልካች (የስር ጣ/ገብ) ይዞታ ነው በማለት ወረዳ እና የጠቅላይ ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት ውሳኔን በመሻር ወስኗል፡፡

 

አመልካች በዚህ ውሳኔ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በመዘርዘር እንዲታረምላቸውን አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ አቤቱታው ተመርምሮ አመልካች አከራካሪውን 2 ጥማድ እርሻ መሬት ከ1994 ዓ/ም ጀምሮ ከስር ተከሳሽ ጋር እስከተፋቱበት ጊዜ 2003 ዓ/ም ድረስ በጋራ ሲጠቀሙ መቆየታቸው ተረጋግጦ እያለ መሬቱን ልትካፈል አይገባም ተብሎ ጥያቄዋ በክልሉ ሰበር ችሎት  ተቀባይነት የማጣቱን አግባብነት ለመመርመር ተጠሪ መልስ እንዲሰጡበት ተደርጓል፡፡ ግራ ቀኙ በጽሁፍ ክርክራቸውን አቅርበዋል፡፡

 

የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ጋር በማገናዘብ አቤቱታው እንዲመረመር ከተያዝው ጭብጥ አንጻር የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመ መሆን አለመሆኑን መርምረናል፡፡

 

እንደመረመርነውም ክርክር ያስነሳውን መሬት አመልካች የስር ተከሳሽ ከነበሩበት  ባለቤታቸው ጋር በ1994 ዓ/ም ሲጋቡ የባለቤታቸው አባት የሆኑት ተጠሪ ሰጥተዋቸው በጋብቻ ውላቸው ላይም ተጠቅሶ ጋብቻ ከመሰረቱበት ከ1994 ዓ/ም ጀምሮ ጋብቻው በፍቺ እስከፈረሰበት 2003 ዓ/ም ድረስ ተጋቢዎቹ በጋራ ሲጠቀሙበት የነበረ መሆኑ ፍሬ ነገርን ለማጣራት እና ማስረጃ ለመመዘን በህግ ስልጣን በተሰጣቸው የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ላይ ተረጋግጧል፡፡ ክርክር ያስነሳው መሬት ተመዝግቦ የሚገኘው እና ግብር የሚከፈልበት በተጠሪው ስም ቢሆንም ይህን መሬት ለአመልካቹ እና ለባለቤታቸው ሰጡ ከተባለበት ከ1994 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 2003 ዓ/ም ድረስ ተጠሪ ተጠቅመውበት የማያውቁ መሆኑና ሲጠቀሙበት የቆዩት አመልካች ከባለቤታቸው (የስር ተከሳሽ) ጋር መሆኑ በስር ፍ/ቤቶች ተረጋግጧል፡፡ ማንኛውም አርሶአደር በመሬት ይዞታው የመጠቀም መብቱን በዚያ መሬት ገቢ ለሚተዳደሩ ወይም ሌላ ገቢ ለሌላቸው የቤተሰብ አባላት ወይም መሬት ለሌላቸው ልጆቹ በስጦታ ማስተላለፍ እንደሚችል በኦሮሚያ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/1997 አንቀጽ 9(5) ላይ ተመልክቷል፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ በጽሁፍ የተደረጉ የስጦታ ውል ባይኖርም ለክርክር ምክንያት የሆነውን መሬት በተጠሪ ስም ተመዝግቦ ያለ መሆኑን ነገር ግን እየተጠቀሙበት ያሉት አመልካች  እና ባለቤታቸው መሆኑን ገልጻ ለሜታ ሮቢ ወ/ፍ/ቤት መልስ የሰጠ ሲሆን የቀበሌው አስተዳደርም ለስር ፍ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ ለክርክር ምክንያት በሆነው መሬት አመልካች ከባለቤታቸው ጋር ሲጠቀሙበት የቆዩ መሆኑን ገልጿል፡፡ ስር ፍ/ቤት ቀርበው የተሰሙ የአመልካች ምስክሮችም


መሬቱን ተጠሪ ሰጥተዋቸው አመልካችና ባለቤታቸው ሲጠቀሙበት የቆዩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ተጠሪ ለከርክር ምክንያት በሆነው መሬት ላይ የነበራቸውን የመጠቀም መብት ልጃቸው የሆነው የአመልካች ባለቤት ከአመልካች ጋር ጋብቻ ሲፈጽሙ በዚህ መሬት እንዲተዳደሩ በአባትነታቸው አስልፈው ሰጥተው ከ1994 ዓ/ም ጀምሮ አመልካች ከባለቤታቸው ጋር በፍቺ ውሳኔ እስከተለያዩበት 2003 ዓ/ም ድረስ ሲጠቀሙበት የቆዩ በመሆኑ በመሬቱ የነበራቸውን የተጠቃሚነት መብት ካስተላለፉ በኋላ መሬቱ ተመዝግቦ የሚገኘው እና ግብርም የሚከፈለው በተጠሪው ስም ብቻ በመሆኑ መሬቱ ለተጠሪ ሊመለስላቸው ይገባል ማለት የሚቻል አይደለም፡፡ ለክርክር ምክንያት የሆነውን መሬት እንደቤተሰብ በእኔ ስር ሆነው አመልካች ባለቤቷ ተጠቀሙ እንጂ በግላቸው ስር ሆኖ አንድም ቀን አልተጠቀሙበትም በማለት ተጠሪ ለዚህ ችሎት ባቀረቡት መልስ የተጠቀሱ ቢሆንም ይህን ስር ፍ/ቤት በነበረው ክርከራቸው አላስረዳም፡፡ በስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ላይ የተረጋገጠው መሬቱን ተጠሪ ለአመልካች ከሰጡ በኃላ ሲጠቀሙበት የቆዩት አመልካች እና ባለቤታቸው መሆናቸውን ነው፡፡ በገጠር መሬት ላይ የሚኖረው መብት የመጠቀም መብት ሲሆን ተጠሪ ይህን መብታቸውን ለአመልካችና ባለቤታቸው አሳልፈው ሰጥተው ለረጀም ጊዜ በዚህ መሬት ላይ ተጠቃሚነታቸው በተቋረጠበት ሁኔታ የምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍ/ፍ/ቤት እና የኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በጽሁፍ የተደረገ ስጦታ ውል አለመኖሩን ብቻ መሰረት በማድረግ በክርክሩ ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር ውጪ የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆነ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍ/ፍ/ቤት በመ/ቁ. 55478 በቀን 3/03/2006 ዓ/ም በዋለ ችሎት የሰጠው ውሳኔ እና የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ/ቁ.186326 በቀን 26/08/2007 ዓ/ም በዋለ ችሎት የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2. በኦሮሚያ  ክልል   ምዕራብ   ሸዋ  ዞን  ሜታ   ሮቤ   //ቤት  በመ/ቁ.15357   በቀን

10/01/2006 ዓ/ም በዋለ ችሎት የሰጠው ውሳኔ እና የኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 170790 በቀን 8/11/2006 ዓ/ም በዋለ ችሎት የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ቁ.348(1) መሰረት ጸንቷል፡፡

3. ለክርክሩ ምክንያት የሆነው መሬት የአመልካች እና ባለቤታቸው የነበሩተ የስር ተከሳሽ የጋራ ይዘት ነው ብለናል፡፡

 

4. ግራ ቀኙ በዚህ ችሎት ላደረጉት ክርክር ያወጡትን ወጪ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ዕልባት ያገኘ በመሆኑ ወደ መ/ቤት ይመለሰ፡፡ የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት