111778 contract/ suretyship/ validity of contract of surety

የዋስትና ውል በግልፅ መደረግና ዋሱ ለግዴታው ዋስ የሆነበት የገንዘብ ልክ በዋስትናው ውል መገለጽ ያለበት ስለመሆኑ ለዋስትናው መሠረት የሆነው ዋናው ጉዳይም ሕጋዊና ግራ ቀኙን የተስማሙበትና የሚታወቅ መሆን ያለበት ስለመሆኑ፡- ፍ/ሕ/ቁ 1928፣1922 አዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2/1/

 

 

የሰ/መ/ቁ. 111778

ጥር 16 ቀን 2008 ዓ.ም.


አመልካች፡- ወ/ሪት ገንዘብ ስጦታው ቀረቡ

ተጠሪ፡- የራያ ቆቦ ወረዳ ፍርድ ቤት የክ/ዐ/ህግ ዘላለም ተስፋዬ ቀረቡ፡፡

መዝገቡንመርምረንተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 ፍ ር ድ

ጉዳዩ ለመንግስት መስሪያ ቤት ለሚፈጸም ቅጥር የተገባውን የዋስትና ውልን መሠረት ያደረገ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰሜን ወሎ አስተዳደር ዞንራያ ቆቦ ወረዳ ፍርድ ቤትየአሁን ተጠሪ ባሁኑ አመልካችና በአቶ ዘመኑ ይላቅ (የሥር 1ኛ ተከሳሽ) ላይ በመሰረተው ክስ መነሻ ነው፡፡ ተጠሪ በመሰረተው ክስ አቶ ዘመኑ ይላቅ በራያ ቆቦ ወረዳ ፍርድ ቤት በግዥና በፋይናንስ የሥራ ሂደት ተቀጥሮ እየሰራ እያለ በተሰጠው ውክልና መሰረት ከልዩ ልዩ ገቢ ደረሰኝ 2617.00 ብርና ከሞዴል 85 ብር 10,070.00 አጠቃላይ ብር 12,687 (አስራ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሰማንያ ሰባት ብር) ያጎደለ ሲሆን አመልካች በሲቪል ሰርቪስ ሐምሌ 2002 ዓ/ም በወጣው መመሪያ መሰረት ለስር 1ኛ ተከሳሽ አቶ ዘመኑ ይላቅ ዋስትና ስለገቡ የጎደለውን ብር 12,687.00 ከወለድ ጋር በዋስትና ግዴታቸው መሰረት ይክፈሉ ሲል ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጡት መልስ የፍርድ ቤቱን የሥረ ነገር ስልጣን መሰረት አድርገው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን በፍሬ ነገር ደረጃ ደግሞ የስር 1ኛ ተከሳሽ የተቀጠሩት በግዥ ኦፊሰርነት ሁኖ አመልካች ዋስ የሆኑትም ለዚሁ የስራ መደብ መሆኑን፣ ለክሱ መሰረት የሆነው ገንዘብ ሊጎድል የቻለው የሥር 1ኛ ተከሳሽ በእለት ገንዘብ ተቀባይነት የስራ መደብ ተጠሪ መድቦ ሲያሰራውና አመልካችም ስምምነት ሳይሰጡበት መሆኑን ጠቅሰው ኃላፊነት የለብኝም በማለት ተከራክረዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤትም 1ኛ ተከሳሽ ተጠርተው ባለመቅረባቸው ጉዳዩ በሌሉበት እንዲታይ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ በአመልካችና በተጠሪ መካከል የተነሳውን ክርክር መርምሮ አመልካችን ለክሱ ኃላፊ ያደረጋቸው ሲሆን አመልካች እስከ ብር 60,000.00 የዋስትና ግዴታ የገቡ በመሆኑ ለክሱ መሰረት የሆነውን ገንዘብ በገቡት ዋስትና መሰረት ከህጋዊ ወለድ ጋር ለተጠሪ ሊከፍሉ ይገባል በማለት ወስኖአል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለሰሜን ወሎ አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ   ፍርድ


ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር በመመርመር አመልካች ለስር 1ኛ ተከሳሽ ዋስ የሆኑት ሰራተኛው በግዥ ኦፊሰርነት የሥራ መደብ ተቀጥረው ለሚከሰት ጉዳት መሆኑን፣ ለክሱ መሰረት የሆነው ጉድለት የተከሰተው ደግሞ ሰራተኛው በውክልና በእለት ገንዘብ ያዥነት ተመድበው  ሲሰሩና ተጠሪ ደግሞ ይህንኑ እንዲያውቁ ሳይደረግ መሆኑን፣ በክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ሐምሌ 2002 ዓ/ም የወጣው መመሪያም የሥራ መደብ ለውጥ ሲደረግ ዋሱ እንዲያውቅ መደረግ እንደአለበት የሚደነግግ መሆኑን በምክንያትነት ይዞ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ አመልካች ዋስትና የገቡበትን የስራ መደብና ለክሱ መስረት የሆነው ጉድለት የተከሰተው አመልካች በማያውቀት የስራ መደብ ላይ ሰራተኛው ተወክሎ ሲሰራ መሆኑን አግባብነት ያላቸውንየመመሪያ ድንጋጌዎችን ያላገናዘበ ነው በማለት ሽሮታል፡፡

በዚህ ውሳኔ የአሁኑ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቦ ተቀባይነት ያጣ ቢሆንም የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ግን ግራ ቀኙን አከራክሮ አንድን የመንግስት ሰራተኛ ከተቀጠረበት የስራ መደብ ውጪ በሌላ የስራ መደብ ወክሎ ማስራት በክልሉ የመንግስት ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 171/2002 የተፈቀደ መሆኑን፣ በክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ወጣ የተባለው መመሪያም ተፈፃሚነት ያለው የስራ መደቡ ሲቀየር እንጂ በውክልና ለሚሰራ ስራ አለመሆኑን በምክንያነት ይዞ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡትን ውሳኔ ሽሮ የወረዳው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በማጽናት አመልካችን ለጉድለቱ ኃላፊ አድርጎአል፡፡ የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች የሠበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አመልካችን ለጉድለቱ ኃላፊ ያደረገው አመልካች ከገቡት የዋስትና አድማስ ውጪና በክልሉ ሲቭል ሰርቪስ ቢሮ የወጣውን መመሪያ እንዲሁም የፍ/ብ/ህ/ቁጥር 1928 ድንጋጌን ሳያገናዘብ መሆኑን ዘርዝው ውሳኔው ሊስተካከል ይገባል በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታቸው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርቦም ግራ ቀኙ በፅሑፍ ተከራክረዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም አመልካች የገቡት የመንግስት ስራ ቅጥር ዋስትና ውል ተቀጣሪው በመንግስት መስሪያ ቤት ባለበት ጊዜ ከተቀጠረበት የስራ መደብ በተጨማሪ በውክልና እንዲሰራ ቢደረግና በዚሁ በውክልና ደርቦ እንዲሰራ በተደረገበት  የስራ መደብ ላይ ሁኖ ለሚያጠፋው ጥፋት ሁሉ ለዋናው የሥራ መደብ ዋስ በሆነው ሰው ላይ ኃላፊነትን የሚያስከትል ነው? ወይስ አይደለም?፣ የኃላፊነት መጠኑስ ምን ያህል ይሆናል? የሚሉትን ጭብጦች ምላሽ መስጠቱ ተገቢ ሁኖ አግኝቷል፡፡


የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አመልካችን ለክሱ ገንዘብ ኃላፊ ያደረገው አሰሪው የመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጣሪውን ሰራተኛ ከተቀጠረበት የስራ መደብ በተጨማሪ በውክልና በሌላ የሥራ መደብ ላይ መድቦ ማስራት በህግ የተፈቀደ ነው በሚል አቢይ ምክንያት ሲሆን የስራ መደብ ለውጥ ሳይደረግ በውክልና ይሰራ በነበረው የሥራ መደብ ሰራተኛው ተመድቦ ሲሰራ ለሰራተኛው ዋስ ለሆኑት   ለአመልካች     እንዲያውቁት    ማድረግን   የሚያስገድድ       ሕግ       የለም    በማለት  ነው፡፡ በመሆኑምአመልካች የዋስትና ግዴታቸውን የገቡት ሰራተኛው ለግዥ ኦፊሰርነት ስራ ሲቀጠሩ መሆኑና አሁን ክርክር ያስነሳው ደግሞ ይኼው ሰራተኛ በዚሁ አመልካች ግዴታ በገቡበት መስሪያ ቤት ውስጥ የስራ መደብ ለውጥ ሳይደረግ በውክልና ደርበው እንዲሰሩ በተደረገበት የእለት ገንዘብ ተቀባይ የሥራ መደብ ላይ በመስራት ላይ እያሉ በፈጸሙበት የእምነት ማጉደል ድርጊት የጎደለ ገንዘብ መሆኑ ግራ ቀኙን ያላከራከረና ሁሉም የበታች ፍርድ ቤቶችም የተቀበሉት የፍሬ ነገር ጉዳይ ነው፡፡ስለዚህ የሕግ ጥያቄው የሚሆነውና የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት የተቀጠረ ሰራተኛ በውክልና ሲሰራላጎደለውገንዘብ ሰራተኛው ሲቀጠር ዋስ የሆነ ሰው የዋስትና ግዴታ አለበት? ወይስ የለበትም? የሚለው ነው፡፡ በመሰረቱ     የዋስትና ግዴታ     በሕጉ ጥበቃ      የሚያገኘው በፍ//ቁጥር    1922        ድንጋጌ       ስር የተመለከተውን መስፈርት አሟልቶ ሲገኝ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት ዋስትና ግልፅ መሆን ያለበት ከመሆኑም በላይ ከተደረገው ውል ወሰን ለማለፍ የማይችል እና ለግዴታው ዋስ የሆነበት የገንዘቡ      ልክ        በዋስትናው   ውል  መገለፅ አለበት፡፡  ዋስትና   ይህን ፎርማሊቲ  ከማሟላቱም በተጨማሪ ለዋስትናው መሰረት የሆነው ዋናው ጉዳይም ሕጋዊና ግራ ቀኙ የተስማሙበትና የሚታወቅ መሆን አለበት፡፡

አመልካች አቶ ዘመኑ ይላቅ በግዥ ኦፊሰርነት የሥራ መደብ ሲቀጠሩ የዋስትና ውል ግዴታ መፈረማቸው እና የውሉ አይነት ዋስትና እንደመሆኑ መጠን በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1922 እንደተመለከተው የዋስትና ግዴታውን በግልፅ ጠቅሶ አመልካቿ እስከ ብር 60,000.00 ግዴታ መግባታቸውም የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ውሉ የዋስትና መጠኑን በግልፅ ከገለፀ አመልካች ሊገደዱ የሚገባው በዚሁ በውሉ በተገለፀው የገንዘብ መጠን ልክ ነው፡፡ አመልካች አቶ ዘመን ይላቅ የተቀጠሩት በመንግስት መስሪያ ቤት መሆኑን አውቀው እስከፈረሙ ድረስ ሰራተኛው በዚያው መስሪያ ቤት በተለያዩ ምክንያቶች ከተቀጠሩበት የስራ መደብ በተጨማሪ ሌላ የስራ መደብ ላይ ተወክለውየመንግስትን ስራ ሊሰሩ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩን እንደሚያውቁ የሚታወቅ ነው፡፡ ሰራተኛው የሰራበት የስራ መደብ ባህርይ ለዋስትና ግዴታ ወሳኝነት ያለው መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን አመልካች መጀመሪያ ግዴታ የገቡበትየግዥ ኦፊሰርነት የሥራ መደብም ከመስሪያ ቤቱ አጠቃላይ ገንዘብና ንብረት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ከእለት ገንዘብ ተቀባይነት የስራ መደብ የሥራ ባህርይ ያነሰ ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ በመሆኑም አመልካች ሰራተኛው ሲቀጥር የዋስትና ግዴታውን መግባታቸው ከተረጋገጠና ሰራተኛው በስራ መደቡ ላይ ተጨማሪ የሥራ    ኃላፊነት


ሲሰጣቸውም ተከታትለው ግዴታቻውን እንዲወርድ ሳያደርጉ ሰራተኛው በዚያው በተቀጠረበት መስሪያ ቤት ክፍት በሆነው የሥራ መደብ ላይ በሕጉ አግባብ በውክልና እንዲሰሩ ተደርጎ ስራውን ሲሰራ ለተከሰተው ጉድለት የዋስትና ግዴታ ያልገባሁበትና ሰራተኛው ስራውን በውክልና እንዲሰራ ሲደረግ እንዳውቅ ያልተደረገ የስራ መደብ በመሆኑ ኃላፊነት የለብኝም የሚሉት ክርክር የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1731(1) ፣1922 እና 1928 ድንጋጌዎችን ይዘትና መንፈስ ሰራተኛው ከተቀጠረበት የስራ ባህርይ ጋር ያልተገናዘበ በመሆኑ የሕግ መሰረት ያለው ሁኖ አልተገኘም፡፡

 

አመልካች ተጠሪ ሰራተኛውን ከተመደበበት የስራ መደብ ውጪ በውክልና ማሰራቱ የዋሱን ግዴታ የሚያባብስ/የሚያከብድ/ በመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1928(2) ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ተቀባይነት የለውም በማለት የሚከራከሩ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ይሁን እንጂ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1928(2) ስር የተመለከተው ድንጋጌ አይነተኛ አላማ ከዋስትና ውል መፈጸም በኋላ በባለገንዘቡና ባለእዳው መካከል የዋሱን ግዴታዎች የሚያባብሱ አዲስ ስምምነቶች እንዳይደረጉና ዋሱን ለተጨማሪ ጉዳት እንዳይዳርጉት ለመጠበቅ ስለመሆኑ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር 17077 በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ቤትን የሚያስገድድ የሕግ ትርጉም የሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከትምአመልካች ስራተኛውን ተጨማሪ የስራ መደብ ላይ በውክልና ማስራቱ በክልሉ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 171/2002 አንቀጽ 61(3) የተሰጠው ኃላፊነትና ተግባር በመሆኑ ይህ ድንጋጌ ለዚህ ጉዳይ ተፈፃሚነት አለው ለማለት የሚቻል ሁኖ አልተገኘም፡፡

 

አመልካች ለጉዳዩ አግባብነት አለው የሚሉት የክልሉ የመንግስት ሰራተኞች ዋስትና አፈፃጸም መመሪያም የስራ መደብ ለውጥ ሲደረግ ዋስ ይህንኑ እንዲያውቅ የሚደረግበትን አግባብ የሚመለከት እንጂ በውክልና ሰራተኛው ከተቀጠረበት ስራ ሌላ የሥራ መደብ ደርቦ እንዲሰራ ሲደረግ አሰሪው መስሪያ ቤት ይህንኑ ለዋስ እንዲያሳውቅ ግዴታ የሚጥል ድንጋጌን ያልያዘ በመሆኑ በዚህ ረገድ የቀረበው የአመልካች ክርክርም ከመመሪያው ድንጋጌዎችና ከክልሉ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 171/2002 አንቀጽ 61(3) ድንጋጌ መሰረታዊ አላማ አንፃር ተቀባይነት ሊሰጠው የሚገባ ሁኖ አልተገኘም፡፡ በአጠቃላይ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት  ነው ለማለት ስላልተቻለ ተከታዩን ወስነናል፡፡


 

              

1. በራያ ቆቦ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 01017692 ጥር 26 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 03-08884 የካቲት 25 ቀን 2007 ዓ/ም የጸናው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348/1/ መሠረት ጸንቷል፡፡

2. አመልካች በገቡት የዋስትና ግዴታ ውል መሠረት ለተጠሪ ኃላፊ ነው ተብለው ለክርክሩ ምክንያት እንዲከፍሉ መወሰኑ ባግባቡ ነው ብለናል፡፡

3.  በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

 ት ዕ      ዛ ዝ

በዚህ ችሎት መጋቢት 25 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም ተሰጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል፡፡ ለሚመለከታቸው አካላት ይፃፍ፡፡ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቶአል፤ ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

 

ወ/ከ