117383 criminal procedure/ criminal law/ breach of trust/ bail

በወ/መ/ህ//አ/ቁ. 676(1) የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሰው የዋስትና መሰጠት (መፈቀድ) ጥያቄ የሚሰጠው በጉዳዩ ላይ በአግባቡ ተመርምሮ እንጂ ከወዲሁ ስላለመሆኑ አዲሱ የፀረ ሙስና ህግ አዋጅ ቁ. 881/2007 አንቀፅ 31

 

የሰ/መ/ቁ 117383

ቀን 6/03/2008 ዓ.ም

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ሙስጠፍ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸመሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሠለ

አመልካች፡- አቶ አዲስ ዋለልኝ በላይ ተጠሪ፡- የፌ/ሥ/ፀ/ሙ/ኮ/ዐ/ሕግ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዮ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ በወንጀል የዋስትና ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የጀመረው በፌ/ከፍ/ፍ/ቤት የአሁኑ አመልካች አብረዋቸው ከተከሰሱ ሌሎች ተከሳሽ ጋር በመሆን ተከሰንበት የነበረው የወ/ህ/ቁ. 676/1/ በአዲሱ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁ. 881/2007 የተሻረ በመሆኑ እና በዚህ አዋጅ አንቀጽ 31/1/ የተመለከተው ድንጋጌ ዋስትና መብት ስለማይከላከል የዋስትና መብት ይፈቀድልን ብለው ያመለከቱ ሲሆን ተጠሪ በበኩሉ በአዋጅ ቁ. 881/2007 አንቀጽ 37 የመሸጋገሪያ ድንጋጌ ስር ይህ አዋጅ በስራ ላይ ከመዋሉ በፊት የተያዘው የሙስና ወንጀሎች የሚታዮት በወንጀል ሕጉ ድንጋጌ መሠረት ይሆናል ስለሊልና የወ/ህ/አ/676/1/ የዋስትና መብት ስለማያሰጥ ዋስትና ሊፈቀድ አይገባም፡፡ የሚሰጥ ከሆነም የዐ/ሕግ ምስክሮች ከተሰሙ በኃላ ማስረጃ ተመዝኖ መሆን አለበት በማለት ተከራክረዋል፡፡ ፍ/ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር አግባብነት ካለው ህግ ጋር መርምሮ የወንጀል ህግ አንቀጽ 6 እና የህገ መንግስቱ አንቀጽ 22 መሠረት ቅጣት ሲወሰን ለተከሳሽ ጠቀሜታ ካለው ሕግ አኳያ ሊታይ ይገባል፡፡ የተከሰሱበት የወ/ህ/ቁ. 676/1/ በአዲሱ አዋጅ ቁ. 881/2007 አንቀጽ 31/1/ ስለሚወድቅ እና ቅጣቱ ከ10 ዓመት በታች በሆነ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ በመሆኑ በፌ/ሥ/ፀ/ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና ማስረጃ አዋጅ ቁ.434/97 መሠረት በብር 10,000 ዋስትና ከእስር ሊፈቱ ይገባል በማለት ብይን የሰጠ መሆኑን ከስር መዝገብ ለመረዳት ተችሏል፡፡


የአሁኑ ተጠሪ በዚህ ብይን ቅሬታውን ለማሳረም ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት በይግባኝ አቅርቦ ፍ/ቤት ግራ ቀኙ ካከራከረ በኃላ መልስ ሰጪዎች የተከሰሱበት የወ/ህ/ቁ. 676/1/ ከ 5 ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ቅጣት እና ከአንድ መቶ ሺህ ብር  በማይበልጥ  የገንዘብ መቀጫ የሚያስቀጣ ነው፡፡ ተከሳሽ (መ/ሰጪዎች) የተከሰሱበት የወ/ህ/ቁ. 676/1/ በአዲሱ አዋጅ ቁ. 881/2007 አንቀጽ 31 የተካተተ ቢሆንም፡፡ ቀደም ሲል በመ/ሰጪዎች ላይ የቀረበው የከባድ እምነት ማጉደል ወንጀል ክስ ባለበት የቀጠለ እንጂ እንደገና ተሻሽሎ በአዲስ መልክ የቀረበ አይደለም፡፡ መሸጋገሪያ ድንጓጌው ቀደም ሲል የተፈፀሙ ወንጀሎች ባሉበት ሁኔታ መታየታቸው እንደሚቀጥል የሚጠቁም ነው አዲሱ አዋጅ ቁጥር 881/2007 መውጣቱ አስቀድሞ የተከላከሉትን የዋስትና መብት በአዲስ መልክ ለማቅረብ የሚያስችላቸው አይደለም፡፡ መ/ሰጪዎች የተከሰሱበት የወ/ህ/ቁ. 676/1/ በአዲሱ አዋጅ ቁ. 881/2007 አንቀጽ 31/1/ ሥር የማሸፍን መሆን አለመሆኑ ማስረጃ ተሰምቶ ከሚረጋግጠው ፍሬ ነገር አንፃር ታይቶ የሚወሰን እንጂ ማስረጃ ተሰምቶ ባልተጠናቀቅበት ጉዳዩና የተረጋገጠውም ፍሬ ነገር ምን እንደሆነ ባልታወቀበት ሁኔታ እንደገና በቀረበ የዋስትና ጥያቄ መነሻ ከወዲሁ ወደ ፍሬ ነገር ምዘና በመግባት ከአስር ዓመት በታች በሚያስቀጣው በአዋጅ አንቀጽ 31/1/ ሥር የሚሸፍን ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ የህጉን ስርዓት የሚንድ ነው አደሱ አዋጅ መውጣቱ እና መ/ሰጩዎች የተከሰሱበት ወንጀል የአዲሱ አዋጅ አንቀጽ 31 መተካቱ እንደገና የዋስትና ጥያቄ ለማቅረብም ሆነ በዋስትና መልቀቅን ለመፍቀድ የሚያስችል ባለመሆኑ የፌ/ከ/ፍ/ቤት መልስ ሰጭዎች  በዋስትና  ይፈቱ በማለት የሰጠው ብይን ተሽሯል በማለት ወስኗል፡፡

 

የአሁኑ አመልካች በዚህ ውሳኔ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በመዘርዘር አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ የአመልካች አቤቱታ ለዚህ ሰበር ችሎት ያስቀርባል የተባለው በአመልካች ላይ ተጠሪ ጠቅሶ ያቀረበው የወ/ህ/አ/676/1/ በተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የስነ ስርዓት እና ማስረጃ ህግ አ. 434/97 አንቀጽ 4 መሠረት ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ በመሆኑ የዋስ መብት የተከላከለ ሲሆን የሙስና ወንጀሎችን አዋጅ ቁ. 881/2007 አንቀጽ 31/1/ ስር የወ/ህ/ቁ. 676/1/ የሚወድቅ በመሆኑ የዋስትና መብት አይከላከልም በማለት የፌ/ከፍ/ፍ/ቤት ለብር 10,000 ለሚበቃ ዋስትና የፈቀደውን በይግባኝ ደረጃ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት አመልካች ዋስትና የተከለከለበት ጉዳይ የወ/ህግ አንቀጽ 676/1/ በአዋጅ ቁ 881/2007 አንቀጽ 31/1/ ስር የሚወድቅ መሆን ያለመሆኑ ወደ ፊት ማስረጃ ተሰምቶ የሚረጋገጥ እንጂ ከወዲሁ መተበይ የማይቻል ስለሆነ የዋስትና ጥያቄ ተቀባይነት የለውም በማለት የፌ/ከፍ/ፍ/ቤትን ብይን የሻረበትን አግባብነት ለማጣራት ተብሎ ነው፡፡

 

ግራ ቀኙ በፅሑፍ ክርክራቸውን አድርገዋል፡፡


ይህ ሰበር ችሎት የአመልካችና የተጠሪን ክርክር ለሰበር አቤቱታው ምክንያት ከሆነው የስር ፍ/ቤት ውሳኔ እና አግባብነት አለው የህግ ድንጋጌ ጋር መርምረናል፡፡

 

እንደመረመርነውም አመልካች በስር ፍ/ቤት የተከሰሰበት ወንጀል የወ/ህግ አንቀጽ 27፣32/1/ሀ/ እና 676/1/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ከባድ የእምነት መጉደል ወንጀል የሙስና ወንጀል ተከሰዋል የሚል ነው፡፡ የወ/ህ/ቁ. 676/1/ ላይ የተመለከተው የቅጣት መጠን ከ5 ዓመት እስከ 25 ዓመት ሊደርስ በሚችል ፅኑ እስራት እና ከአንድ ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ ቅጣት እንደሚያስቀጣ የተመለከተ ሲሆን የሙስና ወንጀሎቹን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 31 እምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል ተክቷል፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 31 ሥር 4 ንዕስ አንቀጽ ያሉ ሲሆን ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የተመለከተው የቅጣት መጠን ከ3 ዓመት እስከ 7 ዓመት ሊደርስ በሚችል ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ የተመለከተ ሲሆን በንዑስ ቁጥር 2 የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት የጥፍተኛው የስልጣን ወይም የኃላፊነት ደረጃ ወይም በመንግስት በህዝብ ወይም በግለሰብ ጥቅም ላይ ያደረሰ ጉዳት ከፍተኛነት በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የተፈፀመውን ወንጀል ከባድ አድራጐት እንደሆነ ቅጣቱ ከ7 ዓመት እስከ 25 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራትና ከሀምሳ ሺህ እስከ መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንደሚያስቀጣ ተመልክቷል፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ አመልካች በፌ/ከፍ/ቤት የተከሰሰበት ወንጀል የሙስና ወጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 በአንቀጽ 31 የተደነገገ ሲሆን፡፡ በዚህ አንቀጽ ስር 4 ንዑስ አንቀጾች ተመልክተዋል በንዕስ ቁጥር 1 የተመለከተው የቅጣት መጠን ከ3 ዓመት እስከ 7 ዓመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ተመልክቷል በንዑስ ቁ. 2 የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት የጥፋተኛው የሥልጣን ወይም የኃላፊነት ደረጃ ወይም  በመንግስት፣ በሕዝባዊ ድርጅት በሕዝብ ወይም በግለሰብ ጥቅም ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የተፈፀመውን ወንጀል ከባድ አድራጐት እንደሆነና ቅጣቱ ከ7 ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና ከሃምሳ ሺህ እስከ መቶ ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ተመልክቷል፡፡

 

አመልካች የተከሰሱበት ወንጀል ክስ ማመልከቻ ላይ የተመለከተውን የወንጀል  ዝርዝር ከሚቀርበው የዐ/ሕግ /የተጠሪ/ ማስረጃ ጋር መዝኖ አመልካች የተከሰሱበት ወንጀል በአዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 31 ስር በየትኛም ንዑስ አንቀጽ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ክሱ እየታየ ባለበት ለፌ/ከፍ/ፍ/ቤት ብይን የሚሰጥበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በአመልካች ላይ በተመሰረተው ወንጀል ክስ በወንጀሉ ዝርዝር ከተመለከተው አንፃር የአመልካች በዋስትና የመለቀቅ ጥያቄ  በስር


ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ተቀባይነት ማጣቱ ወይም የፌ/ከፍ/ፍ/ቤት አመልካች በዋስትና ይፈቱ በማለት የሰጠውን ብይን የፌ/ጠ/ፍ/ቤት መሻሩ በአግባቡ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሐምሌ 24 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለ ችሎት በወ/ይ/መ/ቁ. 113580 የሰጠውን ውሳኔ አፅንተናል፡፡

 

መዝገቡ እልባት ያገኘ በመሆኑ መ/ቤት ይመለስ

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 

ወ/ከ