101631 civil procedure/ execution of judgment

አንድ ፍርድ የማይፈፀምበት ምክንያት ያለመኖሩ ሲረጋገጥ ለአፈፃፀም ተስማሚ በሆነ መንገድ ፍርድ እንዲፈፀም ትእዛዝ መስጠት የሚቻል ስለመሆኑ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 392(1)

 

የሰ/መ/ቁ. 101618

 

ታህሳስ 19 ቀን 2008 ዓ.ም

 

ዳኞች ፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመስል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- የደቡብ ብ/ብ/ሕ/መ/ፀረ- ሙስና ኮሚሽን - ዐ/ህግ የቀረበ የለም ተጠሪ፡- መስከረም ፋንታዬ የቀረበ የለም

መዝገቡን መርምረን የሚከተውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ይህ የሰበር ጉዳይ መንግስታዊ ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀትና ወደ ሐሰት መለወጥ የሙስና ወንጀል ድርጊትን የሚመለከት ክርክር ነው፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ ሲታይ፡- የሥር ከሳሽ /የአሁን አመልካች / ለጌድኦ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ባቀረበው ክስ ተከሳሽ የወንጀል ሕግ ቁ. 379/1/ሀ በመተላለፍ ተከሳሽ በ26/03/2001 ዓ.ም የንግድ ሥራ ፈቃድ ቁጥር የተጠቀሰ የንግድና ኢንዲስትሪ ቢሮ የንግድ ምዝገባ ፈቃድ ክትትልና ድጋፍ አሰጣጥ የሥራ ሂደት በሚል የሚጀምር እና በሀሮ ወላቦ ክ/ከተማ ንግድ ምዝገባና ፍቃድ ክትትልና ድጋፍ አሰጣጥ የስራ ሂደት የተዘጋጀ በማስመሰል በስሙ የተዘጋጀ የቡና አቅራቢነት ሀሰተኛ ንግድ ፈቃድ በሀሰተኛ ክብ ማህተም፣ ሀሰተኛ ስምና ስልጣን ቲተሮች የተዘጋጀውን ሰነድ በመያዝ በቀን 18/08/2005 ዓ.ም 9፡30 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ ከሀሮ ወላቡ ክ/ከተማ ንግድ ኢንዱስትሪ ጽ/ቤት ወደ ጌድኦ ዞን ንግድ ማስፋፊያ ይዛወርልኝ በማለት ሲገለገል ሊያዝ ችሏል ፡፡ በመሆኑም ተከሳሹ የሕዝብ ጥቅም የሚሰራበት ሰነድ ላይ በሀሰት የተዘጋጀ ስለመሆኑ እያወቀ በመገልገሉ በፈጸመው መንግስታዊ ወይም ወታደራዊ ሰነዶችን አስመስሎ በማዘጋጀት ወይም ወደ ሀሰት መለወጥ የሙስና ወንጀል ተከሷል የሚል ነው፡፡


የሥር ተከሳሽ/ የአሁን ተጠሪ/ ፍ/ቤት ቀርቦ ይህ ክስ ተነቦለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ቢያቀርብም ፍ/ቤቱ ሳይቀበለው በመቅረቱ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ወንጀሉን አልፈጸምኩም በማለት ክዶ ተከራክሯል ፡፡

 

ከዚህ በኋላ ፍ/ቤቱ የዐ/ሕግ ምስክሮችን በመስማት ተከሳሽ እንዲከላከል ባዘዘው መሰረት ተከሳሽ ራሱ ቃሉን በመስጠት የመከላከያ ምስክር አንድ ሰው ያቀረበውን ሰምቷል ፡፡ በመቀጠልም ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ተከሳሽ የተከሰሰበት ሐሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀት የሚል ሲሆን ተከሳሹ የፈጸመው ድርጊት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 379/1ሀ/ ሥር የሚሸፈን አይሆንም ፣ ተከሳሽ የፈጸመው ድርጊት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 378 ሥር የሚሸፈን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የዐ/ሕግ ምስክሮችም በሰጡት የምስክርነት ቃል ይህ የሀሰት ሰነድ በተከሳሹ መዘጋጀቱን አናውቅም በማለት መስክሯል ፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት በሐሰት የተዘጋጀ ሰነድ እያወቀ የተገለገለበት በወ/ሕ/ቁ. 375 መሰረት ቅጣት ይጣልበታል፡፡ ነገር ግን የዐ/ሕግ ምስክሮች ተከሳሹ ይህ የሐሰት ሰነድ ይዞ ከመገኘት ውጭ በሰነዱ መገልገሉን አልመሰከሩም፡፡ የተከሳሽ የመከላከያ ምስክሮች ተከሳሽ የሐሰት ሰነዱን አለማዘጋጀቱንና አለመገልግሉን፣ ይህንንም የሀሰት ሰነድ አምጥቶ ለሚስቱ የተሰጠው ተከሳሽ ለትምህርት ወደ ጎንደር ዩኒቨርስቲ በሄደበት ወቅት ጉዳይ አስፈጻሚ እንደሆነ የመሰከሩ  ሲሆን እና በተባለ ጊዜ ተከሳሹ ዩኒቨርስቲ እንደነበር በዩኒቨርስቲ የተጻፈ ደብዳቤ ያመለክታል፡፡ ተከሳሹ በተጠቀሰው የሐሰት ሰነድ ምንም አይነት የቡና ንግድ ያላካሄደ መሆኑን የዲላ ዙሪያ ወረዳ ግብይትና ኃ/ሥራ ማህበር ጽ/ቤት መግለጹ እንዲሁም የሚፈለገው ምንም እዳ የሌለ መሆኑን ከገቢዎች ጽ/ቤት የተጻፉ ደብዳቤዎች ያስረዳሉ፡፡ ተከሳሹ በሀሰት ሰነድ አለመገልገሉ የግራ ቀኙ ማስረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ ተከሳሹ ይህ ሰነድ ይዞ መገኘቱ እንደወንጀል ሊቆጠር ስለማይገባ ተከሳሹ ከተከሰሰበት የወንጀል ክስ በነጻ እንዲለቀቅ ወስኗል ፡፡ የሥር ከሳሽ ይህን ውሳኔ በመቃወም ቅሬታውን ለደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት እና ለክልሉ ሰበር ሰሚ  ችሎት ያቀረበ ቢሆንም ፍ/ቤቶች ቅሬታውን ባለመቀበል ውድቅ በማድረግ የሥር ውሳኔ በማጽናት ወስኗል ፡፡ የአሁን የሠበር አቤቱታ የቀረበው ይህን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

 

አመልካች በ27/09/2006 ዓ.ም የተጻፈ አቤቱታ የሥር ፍ/ቤት ለወ/ሕ/ቁ. 379/1፣ሀ/ የሰጠው የሕግ ትርጉም አግባብነት የሌለው እና መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው፡፡ የዐ/ህግ ምስክሮች ተጠሪው በሐሰተኛ የንግድ ፈቃዱ እያወቀ መገልገሉን አስረድተዋል፡፡ ስለዚህ የሥር ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት በመሆኑ እንዲታረምልን ተጠሪ ላይ ተገቢው የጥፋተኝነት እና ቅጣት ውሳኔ እንዲወሰንበት በማለት አመልክተዋል፡፡

 

ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን በማየት ፣ ተጠሪ ሐሰተኛ የንግድ ፈቃድ ተጠቅሞ ማህደሩ ከአንዱ የመንግስት መ/ቤት ወደ ሌላ እንዲዛወርለት ጠይቆ ይህንኑ ሂደት በማስፈጸም ላይ  እያለ


የተደረሰበት ሆኖ ሳለ ድርጊቱ የወንጀል ሃላፊነትን አያስከትልም ተብሎ በነጻ የመሰናበቱ፣ አግባብነት ለመመርመር ያስቀርባል በማለት ተጠሪ መልስ እንዲሰጥ በታዘዘው መሰረት ታህሳስ 06 ቀን 2007 ዓ.ም የተጻፈ መልስ አቅርበዋል፡፡ የመልሱም ይዘት ተጠሪ ሀሰተኛ ሰነድ መሆኑን እያወቅሁ ማህደር ከአንዱ የመንግስት መ/ቤት ወደ ሌላ የመንግስት  መ/ቤት እንዲዛወር ያላደረግኩ ስለመሆኑ በማስረጃ አረጋግጠዋል፡፡ የሥር ፍ/ቤቶች ለወ/ሕ/ቁ. 379/1ሀ/ የሰጡት ትርጉም አግባብነት ያለው ነው፡፡ አመልካች ተጠሪ ሰነዱ ሀሰተኛ የንግድ ፈቃድ መሆኑን እያወቅኩ ስለመገልገሌ በማስረጃ ያላረጋገጠ ስለሆነ የቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ የሥር ፍ/ቤቶች አመልካች ያቀረበው ወንጀል ክስ በማስረጃ ባለመረጋገጡ ተጠሪን በነጻ በማሰናበት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የሌለው በመሆኑ ውሳኔው እንዲጸናልኝ በማለት ተከራክረዋል፡፡ አመልካች በ04/05/2007 ዓ.ም የተጻፈ የመልስ መልስ አቤቱታውን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ እንደተመለከተው ሲሆን፤ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው  የሕግ  ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እና መዝገቡ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘው ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለው   መርምሯል

፡፡ መዝገቡን እንደመረመርነው አመልካች ባቀረበው ክስ መሰረት የቀረቡት ምስክሮች በሰጡት የምስክርነት ቃል መንግስታዊ ወይም ወታደራዊ ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት ወይም ወደ ሀሰት መለወጥ ያረጋገጡት ነገር እንደሌለ የሥር ፍ/ቤት ውሳኔ ያመለክታል፡፡

 

እንዲያውም የዐ/ሕግ ምስክሮች እንደገለጹት ተጠሪን ከየት አመጥተህ ነው ብሎ ሲጠይቁት እሱ ለትምህርት በሄደ ጊዜ የተወከለ ሰው እንዳወጣለት እና ተጠሪው ሰነዱን ማዘጋጀቱን እና መገልገል አመለገልገሉን እንደማያውቁ መስክረዋል ፡፡ የሥር ፍ/ቤት አመልካች ያቀረበውን ክስ ከምስክሮች ቃል አንጻር ሲታይ ተጠሪ የፈጸመው ድርጊት የተባለውን ድርጊት እንደማይሸፍን በመግለጽ ወደ ወ/ሕ/ቁ. 378 መለወጡ በአግባቡ ነው እንጂ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ፈጽመዋል የሚያስብል ነገር የለም፡፡ የሥር ፍ/ቤቶች በፍሬ ነገር ደረጃ እንዳረጋገጡት ዐ/ሕግ ያቀረባቸው ማስረጃዎች ተጠሪው ይህን ሀሰተኛ የንግድ ፈቃድ አዘጋጅቶ እያወቀ የተገለገለበት እንደሆነ የሚያረጋግጡት አይደለም፡፡ በወ/ሕ/ቁ. 378 መሰረት የወንጀል ሃላፊነት ሊያስከትል የሚችለው በሀሰት የተዘጋጀ ወይም የተለወጠ ሰነድ እያወቀ የተገለገለበት እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ተጠሪ እና ያቀረበው መከላከያ ምስክር በሰጡት ቃል ተጠሪ ይህን ሀሰተኛ የንግድ ፈቃድ እንዳላዘጋጀ እና ሐሰተኛ መሆኑን አውቆ እንዳልተገለገለበት ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል በስር ፍ/ቤት የቀረበው የሠነድ ማስረጃ ተጠሪ በዚህ ሀሰተኛ የንግድ ፈቃፈድ በመገልገል ያካሄደው የቡና ንግድ እንደሌለ አረጋግጧል፡፡ ስለዚህ አመልካች የሥር ፍ/ቤቶች ተጠሪው ይህ ሀሰተኛ የንግድ ፈቃድ በማዘጋጀት እያወቀ የተገለገለበት መሆኑን በማስረጃ አላረጋገጠም በማለት ተጠሪ ከተከሰሰበት ወንጀል   በነጻ


እንዲሰናበት የሠጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጿሟል በማለት ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት የለውም፡፡ የሥር ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ስለሌለው የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የጌድኦ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ . 09459 በ30/05/2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እና የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 61255 በ26/06/2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እና የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 61563 በ14/08/2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የሌለው በመሆኑ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 195/2፣ለ፣2 መሰረት ጸንቷል፡፡

2. የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይድረስ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ/ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 


 

 

ወ/ከ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት