Draft Hate Speech Proclamation

Amharic

English

የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅአጭር ማብራርያ
1. መግቢያ
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት ዕውቅና ከተሰጣቸው መብቶች አንዱ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ነው፡፡ ይህ መብት በሕገ-መንግስቱ ብቻ ሣይሆን ሕገ-መንግስቱን ለመተርጐም እንደ አጋዥ ተደርገው በሚቆጠሩና የሃገራችን የሕግ ስርዓት አካል በሆኑት አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶችም የተካተተ ነው፡፡ ሕገ-መንግስቱንና እነዚህን አለም አቀፍ ስምምነቶች ስንመለከት፣ እንዲሁም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን በማክበር ረገድ ጥሩ ሥም ያላቸውን ሃገራት ልምድም ስንመለከት ይህ መብት ፍፁም የሆነ መብት ሣይሆን፣ ገደብ ሊጣልበት የሚችል መብት መሆኑን እንረዳለን፡፡ በመብቱ ላይ የሚጣለውን ገደብ ዓላማ፣የገደቡን አስፈላጊነትና ተመጣጣኝነትን በጥንቃቄ መርምሮና አመዛዝኖ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ በሕግ ገደብ ማስቀመጥ በዲሞክራሲያዊ ሃገራት ተቀባይነት ያለውና የተለመደ አሰራር ነው፡፡ በሃገራችን ኢትዮጵያ ያለው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን የማጠናከር እንቅስቃሴም ከዚህ ልምድና አሰራር ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ በተለይም አሁን ካለው ፓለቲካዊ ነፃነት ጋር እየተበራከተ የመጣው የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ ንግግር ሥርጭት መፍትሔ ካልተበጀለት ለሃገራዊ ሠላምና ደህንነት እንዲሁም ለለውጥ እንቅስቃሴው ዘላቂነት ትልቅ አደጋ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር ተስፋፍቶ በጠረገው መንገድ እ.ኤ.አ በ1994 በሩዋንዳ፣ እንዲሁም በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በጀርመንና በመላው አውሮፖ የደረሰው የከፋ እልቂት ተጠቃሽና ትምህርት ሊወሰድባቸው የሚገቡ ክስተቶች ናቸው፡፡ ይህን መሰል ጥፋት እንዳይደርስ የጥላቻ ንግግርን መከልከልና በወንጀልነት መደንገግ አስፈላጊ ነው፡፡ የአለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ወይም ICCPR አንቀጽ 19(3) ሃሣብን በነፃነት የመግለፅ መብት ከኃላፊነት ጋር እንደሚመጣና አስፈላጊ የሆኑ ገደቦች፣ በተለይም የሌሎችን መብት፣ ብሔራዊ ደህንነትና ሠላምን ለመጠበቅ ሲባል በሕግ ሊደነገጉ  እንደሚችሉ በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ የዚሁ ስምምነት አንቀጽ 20 ከዚህም በማለፍ በሃገራት ላይ በብሄር፣ በዘር ወይም በሃይማኖት ላይ በመመስረት ጥላቻን፣ ጥቃትና መድልኦን የሚያራግቡ ንግግሮችን በሕግ እንዲከለከሉ ግዴታ ይጥላል፡፡ከላይ ከተጠቀሱት እውነታዎች በመነሳት የጥላቻ ንግግርን በግልፅና በቀጥታ የሚከለክል ሕግ አስፈላጊነት ግልፅ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ ሆን ተብሎ የሚደረግ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ነው፡፡ በተለይም የማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋትንና ከዚህ ጋር የተገናኙ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን በመጠቀም ሃሰተኛ የሆኑና ሆን ተብሎ የተዛቡ መረጃዎችን ማሠራጨት በተለያዩ ሃገራት የፖለቲካ ቀውስ ከማስከተል አልፎ ለግጭትና ጉዳት መንስኤ ሆኗል፡፡ ይህ ችግር ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እድገት ጋር እየተስፋፋ የመጣና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ጠንቅ መሆኑን በመገንዘብ የተለያዩ ሃገራት ችግሩን ለመቅረፍ ሕጐችን በማውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ሃገራት መካከል ፈረንሣይ፣ጀርመንና ኬንያ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዓለማችን ትልቋ ዲሞክራሲ በሆነችው ህንድም የሃሰት መረጃ ስርጭት ያስከተለውን ጦስ ለመከላከል የሕግ ማሻሻያ ለማድረግ ሂደቱ የተጀመረ ሲሆን፣ የችግሩ አስከፊነት በተለያዩ ጊዜያት የኢንተርኔት አገልግሎት እስከመዝጋት ድረስ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ አስገዳጅ ሆኗል፡፡ በሃገራችን ኢትዮጵያም በቅርቡ በሃሰተኛ መረጃ ስርጭት የተነሣ የተቀሰቀሱ ግጭቶችንና ጥቃቶች የሰው ህይወት እንዲጠፋና ሌላም ጉዳት እንዲደርስ መንስዔ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም ይህንን ጉዳይ በቀጥታና በበቂ ሁኔታ ሊሸፍን የሚችል ሕግ አለመኖሩ የፈጠረው ክፍተት ችግሩ እንዲባባስና ከፍተኛ ሃገራዊ ጉዳት እንዲደርስ እድል ሊፈጥር ይችላል፡፡
ስለዚህ ይህን ክፍተት የሚሞላና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ፈፅሞ አግባብነት በሌለውና ከመብቱ መነሻና ዓላማ በተቃረነ መንገድ በመጠቀም በሃገርና በሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መከላከል ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ልብ ሊባል የሚገባው የጥላቻ ንግግርንና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት ሕግ የሚወጣው መሠረታዊ የሆኑ የዜጐችን መብቶች፣ የሃገርና የህዝብ ደህንነትን፣ ሠላምን ለመጠበቅ፣ዲሞክራሲንና ነፃነትን ከጥላቻና ከሃሰት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ መነሻ ሃሣብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ የሚጣል ገደብ፣ ተመጣጣኝና በጥንቃቄ ተግባራዊ የሚደረግ እስከሆነ ድረስ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተቀባይነት ያለው ነው፡፡
2. ረቂቅ አዋጁ በሚዘጋጅበት ጊዜ የነበረው ሂደት
ረቂቁን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከላክነው በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቢት ቤት በሰጠው አቅጣጫ መሰረት በረቂቁ ላይ የሚመለከታቸው አካላት እንዲሳተፉ ጥሪ በማድረግ በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲገኙ በማድረግ ውይይት  ተደርጓል፡፡ ከዚህ በፊት በላክነው ረቂቅ  አዋጅ ላይም የተለያዩ የወይይት መደረኮችን በማዘጋጀት፣ እንዲሁም ረቂቁን በጠቅላይ አቃቤ ህግ ይፋዊ የማህበራዊ ገጽ በመልቀቀና በጹሁፍ አሰተያየት የሚሰበሰብበትን መንገድ በማመቻቸ፣ ረቂቁን ለማሻሻል የሚረዳ ግብዐት ለማሰባሰብ ተችሎዋል። ይተዘጋጁት የውይይይት መደርኮች ያተኮሩት በዘርፉ ላይ ምርምር ያደረጉ ምሁራን፣ ከጋዜጠኞች፣ ከሲቪል ማበረሰብና ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ነው። ገጽ ለገጽ ከተካሄዱ የውይይት መደረኮች በተጨማሪ በጽሁፍም የተሰጡ አስተያየቶች ነበሩ። በነዚህ መንገዶች የተገኙ አስተያየቶች የተለያዩ ሲሆኑ በቅድሚያ አሰተያየትቶቹ ያተኮሩት በህጉ አስፈላጊነት ላይ ነበር። አንዳንዶች ይህን አይነት ህግ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፣ መንግስት የሚተቹትን ለማሸማቀቅ ሊጠቀመው ይችላል በማለት የተከራከሩ ሲሆን ባንጻሩ ህጉ ያስፈልጋል፣ ከዚህም ቀደም ብሎ መውጣት ነበረበት ብለው አስተያየት የሰጡም አሉ። በተለይም እንዲህ ያለ ህግ ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ መብት ጋር ባለው ግንኙነት ዙርያ ሰፊ ክርክርና ውይይት  ተካሄዶዋል። በማስከተልም በረቂቁ ይዘት ላይ በተለይም  የተከለከሉ ተግባራት ብያኔ፣ የቅጣት መጠንን በተመለከተ፣ እንዲሁም የተከለከሉ አይነት ንግግሮችን ለማሰራጨት በማሰብ መያዝን አስመልክቶ በተደጋጋሚ የተሰጡ አስተያየቶች የተስተናገዱ ሲሆን እነዚህንም አስተያየቶች እንደያግባብነታቸው በማካተት፣ ረቂቂን ለማሻሻል ጥረት ተደርጓል።
3. የረቂቅ አዋጁ ዝርዝር ይዘት
አጠቃላይ
ስለ ጠቅላላ ድንጋጌዎች የሚያትተዉ የአዋጁ ክፍል አንድ ሶስት አንቀጾችን የያዘ ሲሆን አንቀጽ አንድ የአዋጁን አጭር ርእስ ወይም ስያሜዉን የሚያስረዳ ነዉ፡፡  አንቀጽ ሁለት ደግሞ በአዋጁ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉና ለዚህ አዋጅ አጠቃቀም ትርጉም ያስፈልጋቸዋል የተባሉ ቃላቶችን እና ሀረጎችን ትርጓሜ ያስቀምጣል፡፡ በአንቀጽ ሶስት ላይ የተገለጸዉ የአዋጁ ዓላማ ሲሆን አዋጁን ማዉጣት ያስፈለገዉ በሶስት አላማዎች እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ እነዚህም አንደኛ ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ሲጠቀሙ ግጭት ወይም ሁከትን የሚቀሰቅስ ወይም ብሄርን፤ ሀይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ በግለሰብ ወይም በተለየ ቡድን ላይ ጥላቻ ወይም መድልዎ የሚያስፋፋ ንግግር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ማድረግ፤ ሁለተኛ  መቻቻልን፣ የዜጎች ውይይትና ምክክርን፣ መከባበርና መግባባትን ማበረታታትና ዲሞክራሲያዊ ስርዐትን ማጎልበት በሶስተኛነት የጥላቻ ንግግርን፣ የሃሰተኛ መረጃና ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች የውሸትና አሳሳች መረጃዎችን ስርጭትና መበራከትን ለመቆጣጠርና ለመግታት መሆናቸው ተገልጾዋል። በአጭሩ፣ እነዚህን አላማዎች ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችሉ እና አሁን እየታዩ ያሉ የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የሚያስከትሉትን አደጋዎች በሚፈለገዉ ደረጃ ለመዋጋት የሚያስችሉ ነባር ህጎች ባለመኖራቸዉ ይህንን አዋጅ ማዉጣት አስፈልጓል፡፡
የተከለከሉ ተግባራት
በአዋጁ ክፍል ሁለት የተከለከሉ ተግባራት በሚለዉ ርእስ ስር የጥላቻ ንግግር መከልከል ፤ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት መከልከል እንዲሁም በልዩ ሁኔታ የሚታዩ ድርጊቶች ተዘርዝረዉ ተቀምጠዋል፡፡ በአንቀጽ 4  የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚድያ በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪድዮ ማሰራጨት የተከለከለ  መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በአንቀጽ 2(2) መሰረት የጥላቻ ንግግር ማለት በአንድ  ሰዉ ወይም የተወሰነ ቡድን ላይ ያነጣጠረ፣ ብሄርን፤ ሀይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያበረታታ ንግግር ነው።በአንቀጽ 5  የሃሰት መረጃን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚድያ በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪድዮ ማሰራጨት  የተከለከለ መሆኑን  ይደነግጋል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሰረት አንድ መረጃ ሀሰተኛ መሆኑ ብቻ በወንጀል የሚያስጠይቀው መቼ እንደሆነ ለመረዳት በአንቀጽ 2(3) የተቀመጠውን የሃሰተኛ መረጃ ትርጉም በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በአንቀጽ 2(3) መሰረት“ሃስተኛ መረጃ” ውሸት የሆነና የመረጃውን ውሸት መሆኑን በሚያውቅ፣ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን ሃሰተኝነት ሊያውቅ ይገባ ነበር የሚያስብል በቂ ምክንያት እያለ የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው።
የአዋጁ አንቀጽ 6 የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት የተከለከለ ከመሆኑ ጋር  በተያያዘ በልዩ ሁኔታ የሚታዩ ነጥቦችን የሚዘረዝር ሲሆን በንኡስ አንቀፅ 1 ስር አንድ ንግግር እንደ ጥላቻ ንግግር ወይም እንደ ሃሰት መረጃ ተወስዶ ማሰራጨት የማይከለከለው  መረጃው የትምህርታዊ ወይም ሳይንሳዊ ምርምር አካል ፤የዜና ዘገባ፤ ትንታኔ ወይም የፖለቲካ ትችት አካል ፤ የኪነጥበበ ፣ ትወና ወይም መሰል የስነጥበበ ውጤት፣ ወይም የሃይማኖታ አስተምህሮት አካል እንደሆነ ተገልጾዋል፡፡  ስለሆነም ከእነዚህ ከተገለጹት  መንገዶች ለአንደኛዉ አላማ የሚደረግ ንግግር እንደ የጥላቻ ንግግር ወይም እንደ ሃስተኛ መረጃ ተወስዶ የሚከለከልና የሚያስቀጣ አይሆንም፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 2 ስር የተደነገገዉ ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨትን በተመለከተ በልዩ ሁኔታ የሚታይ ሀሳብን ነዉ፡፡ ይኸዉም  አንድ ንግግር እንደ ሃሰተኛ መረጃ  ተወስዶ የማይከለከለው ንግግሩን ያሰራጨው ወይም ያደረገው ሰው የመረጃውን እውነተኛነት ለማረጋገጥ በሱ ሁኔታ ካለ ሰው የሚጠበቀውን ምክንያታዊ ጥረት ያደረገ እንደሆነ ወይም ወይም ንግግሩ የጥሬ ሃቅ ዘገባ ወይም ዜና ከመሆን ይልቅ ወደ ፖለቲካ አስተያየትና ትችትነት ያጋደለ መሆኑ ተገልጾዋል።  ይህን አይነት ልዩ ሁኒታዎች መደንገግ የሚያስፈልገው ህጉ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ ሊኖረው የሚችለውን አሉታዊ ተጽንዖ ለመቀነስ ነው።
/ የወንጀል ተጠያቂነት፣ የተቋማትና የአገልግሎት ሰጪዎች ሀላፊነት
የአዋጁ ክፍል ሶስት የሚያስቀምጠዉ በአንቀጽ 4 እና 5 ላይ የተደነገጉት የጥላቻ ንግግር እና የሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ወንጀሎች የሚያስቀጡትን ቅጣት፤ የተቋማት እና የአገልግሎት ሰጪዎች ሀላፊነት፤ ስለ ተሻሩ ህጎች እና አዋጁ የሚጸናበት ግዜን ይደነግጋል፡፡
በአዋጁ አንቀጽ 7 ስር የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ወንጀሎች የሚያስቀጡትን ቅጣቶች ይደነግጋል፡፡ የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ በንኡስ ቁጥር 1 ላይ የተቀመጠዉ በአዋጁ አንቀጽ 4 የተመለከቱትን ወንጀሎች መፈጸም እስከ ሶስት አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከመቶ ሺህ ብር ያልበለጠ መቀጮ እደሚያስቀጣ፤  በዚህ አዋጅ አንቀፅ 4 የተከለከሉት ተግባራት በመፈጸማቸው የተነሳ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ወይም የተሞከረ ከሆነ በአንቀጹ የተከለከሉትን ተግባራት የፈጸመ ሰው እንደነገሩ ሁኔታ እስከ አምስት አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ
ይደነግጋል፡፡ በሌላ በኩል የሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨትን በተመለከተ ማንም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 የተመለከትውን የተከለከለ ተግባር የፈጸመ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ እስከ አንድ አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከሀምሳ ሺህ ብር ያልበለጠ መቀጮ እንደሚቀጣ፤ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 የተመለከተውን የተከለከለ ተግባር የፈጸመው ሰው ድርጊቱን የፈጸመው ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚድያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ ሶስት አመት በሚደርስ በቀላል እስራት ወይም ከብር100,000 ያልበለጠ መቀጮ እንደሚቀጣ፤ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 የተከለከለው ተግባር በመፈጸሙ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ወይም የተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት የተከሰተ እንደሆነ የአንቀጽ 5 ድርጊትን የፈጸመ ሰው እንደነገሩ ሁኔታ እስከ አምስት አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ፍርድ ቤት በዚህ አዋጅ የወንጀል ተጠያቂ የሆነ ሰውን ለማረም የተሻለ ነው ብሎ ሲያምንና የተከለከለው ተግባር በመፈጸሙ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት ያልተፈጸመ ወይም ያልተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት ያልተከሰተ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ በእስራት ምትክ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራን በአማራጭ ቅጣትነት ሊወስን እንደሚችል ይደነግጋል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ በአንቀጹ የተቀመጡትን ቅጣቶች በዚህ መጠን ማስቀመጥ ያስፈለገበት በተጠቀሱት ወንጀሎች የሚሳተፉ አካላትን ለማስተማር በቂ እና ተመጣጣኝ ናቸዉ የሚል እሳቤ በመያዝ ሲሆን ወንጀሉን ቅጣት በማግዘፍ ብቻ ከማስወገድ ይልቅ ትምህርት እና ስልጠና በመስጠት የሚቀንስ ብሎም የሚወገድበት አግባብ በሂደት መቀየስ አስፈላጊነትን ታሳቢ በማድረግ ነዉ፡፡ 
ተቋማት እና አገልገልግሎት ሰጪዎች ሀላፊነት
በአዋጁ አንቀጽ 8 ስር ተቋማት እና አገልግሎት ሰጪዎች የሚኖራቸዉን ሀላፊነት የሚደነግግ ሲሆን ማንኛዉም ማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት በአንቀጽ 4 እና በአንቀጽ 5 ስር የተከለከሉ ንግግሮች እንዳይተላለፉ ወይም እንዳይሰራጩ የመቆጣጠር እና የመግታት የተከለከሉ ንግግሮችን በተመለከተ ጥቆማ ሲደርሰዉ እና ጥቆማዉ አሳማኝ ሲሆን ንግግሩን በአፋጣኝ የማስወገድ ወይም ከስርጭት የማዉጣት ግዴታ እንዳለበት፤ ማንኛዉም የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት በንኡስ ቁጥር 1 እና 2 የተደነገገዉን ግዴታ ለመወጣት የሚያስችለዉ አሰራር እና ፖሊሲ ሊኖረዉ እንደሚገባ፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በአዋጁ የተደነገገውን ግዴታቸውን ባግባቡ እንዲወጡ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ እና የሃሰት መረጃ ስርጭትና ጉዳትን ለመከላከል የሚረዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብሮችን በማዘጋጀት ተግባራዊ እንደሚያደርግ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የሚረዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብሮችን በማዘጋጀት ተግባራዊ እንደሚያደርግ እና የተቋማትና የአገልግሎት ሰጪዎች ሀላፊነትን ዝርዝር የሚደነግግ ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊወጣ እንደሚችል ተደንግጓል። ከዚህም በተጨማሪ በአዋጁ የተደነገገውን ግዴታ አለመወጣት ሊያስከትል የሚችለው የፍትሃ ብሄር ተጠያቂነት እንደተጠበቀ ሆኖ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በአዋጁ የተቀመጠውን ግዴታቸውን ባግባቡ  መወጣታቸውን እየተከታተለ በአመት ሁለት ጊዜ ለህዝብ ይፋ የሚሆን ረፖርት እንደሚያዘጋጅ ተግልጾዋል። የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ላይ የተጣለው ግዴታ በቅጣትና በወንጀል ተጠያቂነት ላይ ያተኮረ ሳይሆን፣ እነዚህ ተቋማት ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንዲንቀሳቀሱ የሞራል ተጽኖ ለማሳረፍ እና ከዛም አልፎ  ለሚኖርባቸው የፍትሃ ብሄር ተጠያቂነት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የታሰበ ነው።
 
 
ሠ/ስለ ተሻሩ ህጎች እና አዋጁ የሚጸናበት ግዜ
በመጨረሻም አዋጁ በአንቀጽ 9 ላይ የወንጀል ህግ አንቀጽ 486 የተሻረ መሆኑን እንዲሁም በአንቀጽ 10 ላይ አዋጁ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተቀምጧል፡፡ የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 486 መሻር አስፈላጊ የሚደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። በቅድሚያ ይህ አንቀጽ መንግስትና ባለስጣኖችን ከሓሰት ወሬና ሃሜታዎች የሚጠብቅ አንቀጽ ነው። ይህን አይነት ጥበቃ ለባለሰልጣናት ማድረግ በተለይም በዲሞክራሲያዊ አውድ ተቀባይነት የለውም። በዲሞክራሲያዊ ስርዐት ባለስልጣናትና መንግስት ከሌሎች ዜጎች በተለየ ሁኔታ ክሓሰት ወሬና ከጥርጣሬ ወይም ከሃሜታ ጥበቃ አይደረግላቸውም። ባለስልጣናትና መንግስት ከተራ ዜጋ በተሻለ መልኩ የብዙሃን መገናኛ ዘዴዎችን የመጠቀምና የተወራባቸውን የማስተባበል እድልና አቅም አላችው ተብሎ ይገመታል። በተጨማሪም የመንግስት ሃላፊነትን የያዘ ሰው ክሃላፊነቱ ጋር ምክንያታዊ የሆኑም ሆነ ያልሆኑ፣ በሃቅ ላይ የተመሰረቱም ሆነ ከሃቅ የራቁ ትችቶች ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ እያወቀ ሃላፊነቱን ተረክቦዋል ተብሎ ይታሰባል። የተጋነኑና በእውነታ ላይ ያልተመሰረቱ ትችቶችን ማድረግ ወንጀል ሆኖ ቢያስጠይቅና ቢያስቀጣ የፖለቲካ ትችትና ክርክር ላይ እጅግ ከባድ ጥላ ስለሚያጠላ በዲሞክራሲያዊ አውድና ስርዐት ይህን አይነት ንግግሮች ወንጀል ሊደረጉ አይገባም። በተጨማሪም አንቀጽ 486 በበቂ ሁኔታ ዝርዝር ሆኖ የሃሰትት መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የሚያስችል ስላልሆነ በዚህ አዋጅ መተካቱ የተሻለ አማራጭ ነው።
 
4. ማጠቃለያ
ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሰዎች መሰረታዊ መብት ከሚባሉት ዉስጥ የሚጠቀስ ሲሆን ይህ መብት ምንም እንኳን መሰረታዊነቱ የሚጠያይቅ ባይሆንም በህግ ክልከላ ከሚቀመጥባቸዉ መብቶች ዉስጥም የሚመደብ ነዉ፡፡ ማለትም ሀሳብን በነፃነት በመግለፅ ሽፋን  የሚከሰቱ ጥላቻን፣ ማግለልን፣ ግጭት፤ ጥቃትን እና መሰል በግለሰቦች እና እንደ አጠቃላይ በመሀበረሰቡ መካካል ያለ መልካም ግንኙነትን የሚያሳሱ እና የሚጎዱ ንግግሮችን እና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን በህግ መከላከል  ያስፈልጋል፡፡ በተለይም በአሁን ወቅት በሀገራችን በህብረተሰቡ መካከል ያሉ መልካም እሴቶች በእነዚህ ጥላቻ ንግግሮች እና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየተሸረሸሩ እና ለሀገርም ስጋት የደቀኑ በመሆናቸዉ እንዲሁም እነዚህን ችግሮች አሁን ባሉት ህጎች መፍታት የማይቻል በመሆኑ የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን የሚቆጣጠር አዋጅ አርቅቀን ከዚህ ማብራርያ ጋር የላክን መሆኑን እንገልጻለን።