106286 civil procedure/ contract law/ contract of arbitration/ exhaustion of arbitration remedies

 

contract law

contract of arbitration

exhaustion of arbitration remedy

 

በአንድ መተዳደሪያ ደንብ በማህበር አባላትና በድርጅቱ  መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች በመጀመሪያ በእርቅ መፈታት  አለባቸው የሚል ድንጋጌ ሲኖር ይኸው ሥርዓት ሳይፈፀም ወደ ፍርድ ቤት ክስ ማቅረብ አግባብነትየሌለው ስለመሆኑ

 

ተዋዋይ ወገኖች በመካከላቸው የሚነሳ አለመግባባትን በተመለከተ ጉዳያቸው ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት በሽምግልና እንዲታይ ሊሰማሙ ሥለመቻላቸው፣

 

የፍ/ሕ/ቁ. 1731(1)፣1732፣1736፣1738

የሰ/መ/ቁ 106286

 

መጋቢት 29 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- ቦሮ ትራቪል የግንባታ ሥራዎች ኃ/የተ/የግ/ማህበር ነገረ ፈጅ ም/ስ አስኪያጅ ታከለ ንጉሴ ቀረቡ

ተጠሪ፡- አቶ ኤፍሬም ሽብሩ - ቀረቡ

 

መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ርድ

 

የሰበር አቤቱታ ሊቀርብ የቻለው የሥር ፍርድ ቤቶች ግራ ቀኙ እያከራከረ ያለው ጉዳይ በመጀመሪያ ወደ ፍርድ ቤት ከመሄዱ በፊት በሽምግልና ዳኞች መታየት ነበረበት የሚለውን የአመልካች ክርክር ነጥብ ውድቅ በማድረግ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዲታይ ብይን የመስጠታቸው አግባብነት አመልካች ከመተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 41(1) አንፃር መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ጭብጥ ለመመርመር ነው፡፡

 

ጉዳዩ የተጀመረው በቤንሻጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ በመሆን ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪ በአመልካች ድርጅት ያቀረቡት ክስ ከማህበሩ መሥራች አባልነት ያለአግባብ መሰረዛቸው እና የቼክ ፈራሚነታቸው ያለአግባብ እንደተነቀሉ የሚገልጽ ነው፡፡ የአሁኗ አመልካች ጉዳይ ከአሁኑ በፊት በፍርድ ያለቀ ነው፤ጉዳዩ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት በሽምግልና ዳኞች መታየት አለበት የሚል ክርክር አቅርበዋል፡፡ የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙ ክርክር ከመረመረ በኃላ ጉዳዩ በፍርድ ያለቀ ነው የሚል ክርክር ውድቅ ያደረገ ሲሆን፤ ጉዳዩ በመጀመሪያ ወደ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት በሽምግልና ዳኞች መታየት አለበት የሚለውን የአመልካች ክርክር በመቀበል በማህበራቸው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 41 መሰረት በሽምግልና ዳኞች መታየት እንዳለበት ብይን ሰጥቷል፡፡ ተጠሪ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት የይግባኝ አቤቱታው ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ግራቀኙ በማከራከር የግራ ቀኙ መተዳደሪያ ደንብ ሽምግልናን እንደ አንድ አማራጭ ማስቀመጡ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዲታይ መስማማታቸውን አያሳይም በማለት የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር ወስኗል፡፡ የአሁኑ አመልካች ይህንን ውሳኔ በመቃወም ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበው የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት አላገኙም፡፡ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም   በስር


ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተሰጠው ውሳኔ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት አይደለም በማለት መወሰኑ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

 

ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ ትዕዛዝ በመስጠቱ ግራቀኙ የጽሑፍ ክርክር ያደረጉ ሲሆን አመልካች በሰበር አቤቱታው የጠቀሳቸው አንኳር ነጥቦች፡- መተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 41 በአባላት መካከል የሚፈጠር አለመግባባት በእርቅ፣በሽምግልና እንዲታይ የተደነገገው በሥር ፍርድ ቤቶች መታለፉ አለአግባብ መሆኑን፤የግራቀኙ ስምምነት ደግሞ ሕግ መሆኑን ለመግለጽ ውሳኔ እንዲሻር መጠየቃቸውን የሚያሳይ ሲሆን የተጠሪ መልስ መሠረታዊ ይዘትም፡- በማህበሩ እና አባላት መካከል የሚነሳው ክርክር በሽምግልና እንደሚፈታ የተገለጸ ቢሆንም ብቸኛ አማራጭ አለመሆኑን፤ በክልሉ መንገዶች ባለሥልጣን የበኩሉን ጥረት ማድረጉን፤አዋጅ ቁጥር 147/91 ተፈፃሚነት እንደሌለው፤ ማህበሩም ሕልውና እንደሌለው ጉዳዩም በሽምግልና እንደማይፈታ በመግለጽ ለፍርድ ቤት ክስ ማቅረባቸው ተገቢ መሆኑን ተከራክሯል፡፡ አመልካች የመልስ መልስ ያቀረቡ ሲሆን የሰበር አቤቱታቸው የሚጠናከር ነው፡፡

 

ከሥር የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙ የጽሑፍ ክርክር፣ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ፤አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች እና ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡

 

ከሥር የክርክር ሂደት መረዳት እንደተቻለው አመልካች አጥብቆ የሚከራከረው የግራ ቀኙ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 41 ለክርክሩ መሰረት የሆነውን ጉዳይ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት በሽምግልና ዳኞች መታየት ነበረበት በሚል ነው፡፡ ተጠሪ በበኩሉ ጉዳዩ በቀጥታ ፍርድ ቤት እንዳይቀርብ የሚከለክል ስምምነት የሌለ መሆኑን ነው፡፡ የግራ ቀኙ መሰረታዊ የክርክር ነጥብ እልባት ለመስጠት የቦሮ ትራቭል የግንባታ ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መተዳደርያ ደንብ አግባብነት ያለው ድንጋጌ መሠረታዊ ይዘትና መንፈስ መመርመሩ ተገቢ ይሆናል፡፡ የአመልካች ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 41 በአባልነትና በማህበሩ መካከል የሚነሱ ክርክሮች የሚፈቱበትን አግባብ ደንግጓአል፡፡ በዚህ ድንጋጌ ንኡስ አንቀጽ 1 ሥር እንደተመለከተው አከራካሪ ጉዳዮች የሚነሱ ከሆነ የድርጅቱ ሥራ አመራር  ኮሚቴ በሚያመቻቸው በአስታራቂ ሽማግሌዎች በዕርቅ እንዲያልቅ እንደሚደረግ ተመልክቷል፡፡ ክርክሩ በዕርቅ ያላለቀ እንደሆነ ጉዳዩ በሽምግልና ዳኞች ይታያል፡፡ ጉዳዩ በሽምግልና ዳኞች የማይፈታ ከሆነ በአገሪቱ በህግአግባብ እንደሚታይ በዚህ ደንብ አንቀጽ 42.2 ሥር በግልጽ ተጠቅሷል፡፡

 

ከአመልካች የመተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 41 እና 42 ለመረዳት እንደተቻለው በአባልነትና በማህበሩ መካከል የሚነሱ ክርክሮች ለመፍታት ሦስት መንገዶች የሚከተል መሆኑን ነው፡፡ የመጀመሪያው እርቅ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሽምግልና ዳኞች አማካይነት ነው፡፡ ሦስተኛ እና የመጨረሻው አማራጭ በአገሪቱ በህግ አግባብ የሚል ሲሆን ይህ አማራጭ በቀጥታ ፍርድ ቤት የሚል ግልጽ መልስ የሚሰጥ ባይሆንም በሌሎች ሕጎች ጉዳዩ ለሌላ ተቋም ካልተሰጠ በስተቀር የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ከመሆኑ አኳያ ፍርድ ቤት የሚል ትርጉም ሊሰጠው የሚችል ስለመሆኑ ከአጠቃላይ የድንጋጌው መሠረታዊ ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ነው፡፡ ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመጣ ተጠሪ ጉዳዩን በቀጥታ ፍርድ ቤት ማቅረቡ ደንቡን የሚቃረን አለመሆኑን እየተከራከረ ነው፡፡ አመልካች በአንፃሩ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት በሽምግልና መታየት ነበረበት የሚል ክርክር በአፅንኦት አቅርበዋል፡፡ በመሰረቱ ተዋዋዮች ጉዳያቸው ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት በሽምግልና  ለማየት  ከስምምነት  ላይ ሊደርሱ ይችላሉ  የተዋዋይ    ወገኖች


ስምምነት በሕጉ አግባብ የተቋቋመ ከሆነ አስገዳጅ ስለመሆኑ በፍ/ህ/ቁ 1731(1) ተመልክቷል፡፡ በተዋዋይ ወገኖች የሚነሳው የውል አተረጓጎም ክርክርም የውሉ መሰረታዊ ይዘትና  ዓላማ መሰረት በማድረግ መታየት እንዳለበት በፍ/ህ/ቁ 1732፣ 1736 እና 1738 በግልጽ ተደንግጓል ፡፡ በአመልካች መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 41 በማሕበሩ አባላት እና ድርጀቱ ሊነሱ የሚችሉ ክርክሮች በመጀመሪ በዕርቅ መፈታት እንዳለባቸው የተደነገገ ሲሆን የዕርቅ ስምምነቱ ውጤት ካላመጣ ደግሞ የሽምግልና ዳኞች እንደሚሰየሙ ተመልክቷል ፡፡ እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ውጤት ካላስገኙ የመጨረሻው አማራጭ ጉዳዩ በአገሪቱ ሕግ የሚፈታ መሆኑ ተገልጻዋል፡፡

 

የአሁኑ ተጠሪ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ጉዳዩ በዕርቅ ለመጨረስ ጥረት ስለማድረጋቸው የቀረበ ክርክር የለም፡፡ በእርግጥ የቤንሻንጉል ጉምዝ መንገዶች ባለሥልጣን በፃፈው ደብዳቤ ጉዳዩ በሕግ አግባብ እንዲታይ መግለጽን ተጠሪ ቢከራከሩም የተጠሪ ክርክሩ በአመልካች መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 41 መሰረት በዕርቅ ለመጨረስ የተደረገ ጥረት ስለመኖሩ የሚያሳይ አይደለም ፡፡ ተጠሪ ሌላ ያነሱት ነጥብ ማህበሩ ሕጋዊ ሰውነቱን አጥቷል የሚል ቢሆንም አመልካች ወክለው እየተከራከሩ ያሉት ምክትል ስራ አስኪያጅ እና ባለአክሲዮን መሆናቸው የተካደ ጉዳይ አይደለም ፡፡ የማሀበሩ ሕልውና በሕግ አግባብ ስለመክሰሙም በሕግ የተደገፈ ክርክር አልቀረበም፡፡ተጠሪ የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ  41 የተዘረጋውን ሥርዓት በአግባቡ ሳይጠቀሙ እና አለመግባባቱን ለመፍታት ጥረት ሳያደርጉ ጉዳዩን  በቀጥታ ወደ ፍርድ ቤት መውሰዳቸው ከላይ የተመለከተው መተዳደሪያ ደንብ ያላገናዘበ ነው፡፡

 

የሥር ፍርድ ቤት ሽምግልናን እንደ አማራጭ የተወሰደ ነው በማለት በውሳኔው የገለጸ ቢሆንም የአመልካች መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 41 እንደተመለከትነው በድርጅቱ እና በማህበሩ የሚከሰት አለመግባባት የሚፈታበት ሥርዓት ቅደም ተከተል ማስቀመጡን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ተጠሪ በደንቡ የተዘረጋውን የክርክር አፈታት ሥርዓት ሳይከተል በቀጥታ በፍርድ ቤት ክስ ማቅረቡ የተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ያላገናዘበ ነው፡፡ በመሆኑም የግራቀኙ ክርክር በመጀመሪያ በእርቅ፣በሽምግልና ሳይታይ በቀጥታ በፍርድ ቤት መታየት ይችላል ተብሎ በሥር  ጠቅላይ ፍርድ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት መወሰኑ እና በሰበር ሳይታረም  መጽናቱ  መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ብለናል፡፡

 

በማጠቃለል የሥር ፍርድ ቤቶች ተጠሪ ጉዳዩን በዕርቅ እና በሽምግልና ሳይታይ በቀጥታ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል በማለት የሰጡት ብይን የአመልካች መተዳደርያ ደንብ አንቀጽ 41 እና 42 ያስቀመጣቸው የክርክር አፈታት ቅደም ተከተል ያላገናዘበ በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ ተከታዩን ወስነናል፡

 

 ው ሳኔ

 

1. የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍ/ይ/መ/ቁ 05440 በ 07-

11-2006 ዓ.ም የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍ/መ/ቁ 08575 በ 21-09-2006 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ በመሻር የሰጠው ፍርድ፤የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 05591 07/02/2007ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348(1) ተሽሯል፡፡ ይፃፍ፡፡

2. የአሶሳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍ/መ/ቁ 08575 በ 21/09/2006 የሰጠው ብይን ጸንቷል፡፡ ይፃፍ፡፡


3. አመልካች እና ተጠሪ እያከራከረ ያለው ጉዳይ በአመልካች መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 41 መሰረት በተዘረጋው ሥርዓት በዕርቅ፤ሽምግልና ሳይታይ በቀጥታ ፍርድ ቤት መቅረብ አይችልም በማለት ወስነናል፡፡

4. ግራ ቀኙ በዚህ ፍ/ቤት ያወጡትን ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ ብለናል፡፡

 

 ት ዕ ዛዝ

-   በዚህ ችሎት የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል፡፡

-   መዝገቡ ተዘጋ ወደ መ/ቤት ተመለሰ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት:፡