99679 arbitration/ recusal of arbitrator

በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የግልግል ተቋም ውስጥ አንድን ጉዳይ በግልግል እንዲያይ የተቀመጠ የግልግል ዳኛ ከተከራካሪ ወገኖች በአንዱ እንዲነሳ አቤቱታ በሚቀርብበት ጊዜ ይነሳ የተባለው ዳኛ ልነሳ አይገባም ብሎ ጥያቄውን ካነሳው ወገን ጋር ሊከራከር የማይገባው ሥለመሆኑና ልነሳ አይገባም እያለ በሚከራከርበት ሆኔታም ጉዳዩን ገለልተኛ ሆኖ ያየዋል ተብሎ ሥለማይገመት መነሳት ያለበት ሥለመሆኑ፣

 

አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 9 እና 10 የፍ/ህ/ቁ.3342/ 3340/2/

የግልግል ተቋሙ የተሻሻለ ደንብ አንቀጽ 13 እና 15

የሰ/መ/ቁ 99679

ታህሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- የኢትዮጵያ ኤርፓርቶች ድርጅት - ጠበቃ አቶ ሚካኤል ጉንታ ቀረቡ፡፡ ተጠሪ፡- አቶ በየነ ወልደገብርኤል - ጠበቃ ኃይሉ ብርሃኑ ጋር ቀረቡ፡፡

መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 96130 ጥር 6 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ መሠረታዊ የሕግ ሰህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልካች ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ የግልግል ጉባኤ ዳኛና ሰብሳቢ ሆኖ የተሰየመ ሰው ጉዳይን ከማየት ይነሳልኝ በሚል መንገድ በቀረበ ጥያቄ የተሰጠን ውሣኔ በመቃወም የቀረበ ነው፡፡

1. ጉዳዩ የተጀመረው ለአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትና የዘርፍ ማህበራት የግልግል ተቋም አመልካች ባቀረበው ጥያቄ ነው፡፡ በግልግል ተቋሙ መልስ ሰጭ የሆነው አመልካችና የይገባኛል ጥያቄ አቅራቢ የሆነው ጂኦሜትሪ ሉዊጅ ቫርኔሮ  አምፕራስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በመካከላቸው የተፈጠረው አለመግባባት በግልግል ዳኞች እንዲቀርብ በመስማማታቸው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትና የማህበራት ዘርፍ የግልግል ዳኝነት ተቋም የግልግል ዳኞች ጉባኤ ተቋቁሟል፡፡ የግልግል ዳኞች ጉባኤ ሰብሳቢ ተጠሪ እንዲሆን ሰይሞታል፡፡ የግልግል ዳኞች የተከራካሪዎችን ክርክር በማየት ሂደት ላይ እያሉ አመልካች ታህሳስ 04 ቀን 2006 ዓም በተፃፈ ማመልከቻ የግልግል ዳኞች ጉባኤ ሰብሳቢ የሆኑት ተጠሪ ጉዳዩን ከማየት እንዲነሱለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የግልግል ተቁሙ የግልግል ዳኞች ጉባኤው በአመልካች ጥያቄ ላይ አስተያየት እንዲያቀርብ በማድረግ፣ የግልግል ዳኞች በአመልካች ማመልከቻ ላይ ዝርዝር አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የግልግል ተቋሙ፣ የግልግል የዳኝነት ጉባኤው ሰብሳቢ የሆኑት የአሁኑ ተጠሪ ጉዳዩን ከማየት እንዲነሳለት አመልካች ያቀረበውን ጥያቄ ያልተቀበለው መሆኑን በመግለጽ ውሣኔ ሰጥቷል፡፡ አመልካች ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቧል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የአመልካችን ይግባኝ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 መሠረት ሰርዞታል፡፡

2. አመልካች ግንቦት 15 ቀን 2006 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ ግልግል ዳኝነትና ከሰብሳቢነት ሊነሳ ይገባል የሚልባቸውን ምክንያቶች በመዘርዘር የሰበር አቤቱታውን አቅርቧል፡፡ ከግልግል ዳኝነቱ እንዲነሳ የተጠየቀው ተጠሪ ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም


ከግልግል ዳኝነት አልነሳም የሚልበትን ዝርዝር ምክንያት በመግለፅ ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ መልስ አቅርቧል፡፡ አመልካች ሐምሌ 8 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡

3. የሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ሂደት ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም ተጠሪ ከዚህ በኋላ የግልግል ዳኛና ሰብሳሲ ሆኖ ለመቀጠል ይችላል ወይስ አይችልም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

4. ጉዳዩን እንደመረመርነው ከህዳር 16 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው የአዲስ አበባ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የግልግል ተቋም የተሻሻለ የግልግል ደንብ ስለዳኞች መነሳትና መተካት በአንቀፅ 15 የደነገገ መሆኑን ተረድተናል፡፡ በግልግል ደንቡ አንቀፅ 15 ንዑስ አንቀፅ በአንደኛው ተከራካሪ ወገን አቤቱታ ወይም ጥቆማ መሠረት የግልግል ዳኛ እንዲነሳ ጥያቄ ሲቀርብ፣ ተዋዋዮችና ወይም የይነሳልን ጥያቄ ያልቀረበባቸው የግልግል ችሎት ሌሎች አባላት የፅሑፍ አስተያየት ከተቀበለ በኋላ ተቋሙ ውሣኔ እንደሚሰጥ ይገልፃል፡፡

5. አከራካሪው ጉዳይ ተቋሙ ከግልግል ችሎቱ እንዲነሳ ጥያቄ የቀረበበት ዳኛ፣ ከግልግል ችሎቱ መነሳት የለበትም በማለት በሰጠው ውሣኔ ላይ የአዋጅ ቁጥር 25/1988  አንቀፅ 9 እና አንቀፅ 10 መሠረት የይግባኝና የሰበር አቤቱታ ሲቀርብበት ወይም በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 3342 መሠረት መቃወሚያ ሲቀርብበት የተቋሙን  ውሣኔ በመደገፍ ተከራካሪ ሆኖ መቅረብ ያለበት ማን ነው? ከጉዳዩ እንዲነሳ ጥያቄ የቀረበበት ዳኛ፣ ጉዳዩን ከማየት እንዳልነሳ የተሰጠው ውሣኔ ተገቢነት ያለው ነው በማለት ጉዳዩን ለግልግል ዳኝነት ካቀረበውና ጥያቄውን ካነሳው ተከራካሪ ወገን ጋር መልስ ሰጭ ወይም ተጠሪ ሆኖ ቀርቦ ዝርዝር ክርክር ካቀረበ በኋላ፣ በፍርድ ቤት ተከራካሪ ሆኖ በቀረበበት ጉዳይና በተከራካራነት ቀርቦ ሲሞግተው የነበረውን ተከራካሪ ወገን ለግልግል ዳኞች የሚያቀርበውን ክርክርና ማስረጃ በገለልተኝነት ስምቶ ሊወስን ይችላል ተብሎ በግልግል ዳኝነት እንዲሰየም ማድረግ የግልግል ዳኝነቱን ዓላማ የማያሳካ ነው ወይ?  የሚለው ነጥብ መታየት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

6. የአዲስ አበባ ንግድ ዘርፍ ማህበራት የግልግል ተቋም የግልግል ደንብ፣ ተቋሙ ጉዳዩን ከማየት እንዲነሳ ጥያቄ የቀረበበት የግልግል ዳኛ ጉዳዩን ከማየት አይነሳም በማለት በሰጠው ውሳኔ ላይ አንደኛው ተከራካሪ ወገን መቃወሚያ ፣ ይግባኝ ወይም የሰበር አቤቱታ በሚያቀርብበትና አቤቱታው ተቀባይነት አግኝቶ መልስ እንዲቀርብ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሚሰጥበት ጊዜ ፣ የግልግል ተቋሙ ዳኛው ጉዳዩን ከማየት የሚነሳበት በቂ ምክንያት የለም በማለት የሰጠው ውሳኔ በዝርዝር ለማስረዳት ክርክሩን በማን በኩልና እንዴት እንደሚያቀርብ በግልፅ ያስቀመጠው ስርዓት የለም፡፡ ሆኖም በመርህ ደረጃ የግልግል ተቋሙ ጉዳዩን በግልግል ዳኝነት (ሰብሳቢነት) ተሰይሞ ከማየት የሚከለክል በቂ ምክንያት የለም በማለት የሰጠውን ውሳኔ ለማስረዳት ከሚያቀርብ በስተቀር፣ጉዳዩን ከማየት እንዲነሳ ጥያቄ የቀረበበት የግልግል ዳኛ በተከራካሪነት ቢቀርብና፣የግልግል ዳኛውን ከዳኝነት የሚያስነሳው በቂ ምክንያት አለ ወይስ የለም በሚለው ጭብጥ ዙሪያ ተከራካሪ ሆኖ መሰለፍና ዝርዝር ክርክር የሚያቀርብበት ሁኔታ መኖር የለበትም፡፡

7. ከዚህ አንጻር ስናየው ተጠሪ በጉዳዩ ተከራካሪ ሆነው መጠራታቸው ስህተት ነወ፡፡ አመልካች ለግልግል ተቋሙ ተጠሪ ከግልግል ዳኛነትና ሰብሳቢነት እንዲነሳ ያቀርብኩት ምክንያት አላግባብ ውድቅ ተደርጎብኛል የሚል የሰበር አቤቱታ ሲደርሳቸው ተጠሪ


በጉዳዩ የተለየ ጥቅምና ፍላጎት የሌላቸው መሆኑንና ጉዳዩን በዳኝነት እንዳያይ ወይም ከግልግል ዳኝነት እንዲነሳ በህግ ስልጣን የተሰጣቸው አካላት ጉዳዩን አጣርተው የሚሰጡትን ውሳኔ በፀጋ እንደሚቀበሉ ከመግልጽ ማቆም ይገባዋል፡፡ ተጠሪም ጉዳዩን በግልግል ዳኝነት ተሰይሜ ማየት አለብኝ የሚል አቋም በመያዝ ሰፊና ዝርዝር ክርክር እንዳቀረቡ ለዚህ ሰበር ችሎት ካቀረቡት ክርክር ተርድተናል፡፡ ተጠሪ ከአመልካች ይዘት የቀረበውን ሙግት በመቃወም ፣ ተከራካሪ ሆነው ተሰልፈው ሰፊና ዝርዝር ክርክር ባቀረቡበት ሁኔታ የአመልካችንና በዚህ ክርክር ተሳታፊ ያልሆነውን “ቫርኔሮ” እየተባለ የሚጠራውን ድርጅት ጉዳይ ከዚህ በኋላ በግልግል ዳኝነት  ተሰይመው እንዲያዩ መፍቀዱ ከመሰረታዊነትም ሆነ ከዕይታ አንጻር ሲመዘን ፣ የግልግል ዳኝነት ነጻነትና ገለልተኝነት መርህ የሚያስከበር ነው ብሎ ለመደምደም የሚያስችል ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ይህ ሁኔታ በራሱ በሶስተኛ ወገን የተመረጠ ዳኛ ባለማዳላቱ ወይም በነጻነቱ ላይ ጥርጣሬ ለማስገባት የሚችል አንድ አንድ የአካባቢ ሁኔታ ምክንያት በሚኖርበት ጊዜ ዳኛው ከግልግል ዳኛነቱ ሊነሳ እንደሚችል በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 3340 ንዑስ አንቀጽ 2 የተደነገገውን የሚያሳይ ነው፡፡

8. ተጠሪ በጉዳዩ መልስ ሰጭ አድርጐ ሰይሞ በማቅረብ አመልካች በፈጸመውና ፍርድ ቤቱም ተጠሪን በተከራካሪነት በመጥራቱ ምክንያት በተፈጸመ ስህተት ፣ አመልካች ተጠሪ በአንድ አከራካሪ ጭብጥ ላይ በተከራካሪነት ተሰልፈው ሰፊ የሆነ ክርክር አቅርቧል፡፡ በሌላ አነጋገር በግልግል ዳኝነት አካሉ መልስ ሰጭ የሆነው አመልካችና የግልግል ዳኛ ሆኖ ጉዳዩን ከማየት የሚከለክለኝ ምክንያት  የለም  የሚል ክርክር ያቀረበው የግልግል ችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ የሆኑት ተጠሪ “ዳኛው ከግልግል ችሎቱ መነሳት አለበት ወይስ የለበትም” በሚለው ጭብጥ ላይ ሁለት ተቃራኒ አቋም በመያዝ ግራናቀኝ በተከራካሪነት ቆመው ተሟግተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ተጠሪ የግልግል ጉባኤው ዳኛና ሰብሳቢ ሆኖ እንዲቀጥል ቢደረግ የግልግል ዳኛ ሁሉንም ተከራካሪ ወገኖች ጋር የነበረው ያለውና የሚኖረው ግንኙነት በገለልተኝነትና በነፃነት መርህ ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል የሚለውን የግልግል ተቋሙ የተሻሻለ ደንብ አንቀፅ 13 ድንጋጌና ሌሎች ሕጎች የተደነገገውን መርህ የሚጥስ በመሆኑ ተጠሪ የግልግል ዳኛና ሰብሳቢ ሆኖ መቀጠል አይገባውም በማለት በተሻሻለው የግልግል ደንብ ከአንቀፅ 13 እና የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 3340 ንዑስ አንቀፅ 2 መሠረት በማድረግ ወስነናል፡፡

 ው ሣ ኔ

1. ተጠሪ በግልግል ዳኝነትና ሰብሳቢነት መቀጠል እንደሌለበት የተወሰነ መሆኑን አውቆ ተገቢውን እንዲፈፅም ለአዲስ አበባ ንግድ ዘርፍ ማህበራት  የግልግል ተቋም ውሣኔው ይተላለፍለት፡፡

2. ግራቀኙ በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡