96833 Pension law/ effect of extension of pension period

አንድ የመንግስት ሠራተኛ የጡረታ ዕድሜው ከደረሠ በኋላ አሠሪው መ/ቤት ፈቃድና ከየትኛውም አካል ተቃውሞ  ሣይቀርብ የጡረታ ጊዜው ከተራዘመ ለተራዘመበት ጊዜ የሠራበት ለጡረታ ሊያዝ የሚገባው ሥለመሆኑ፣

አዋጅ ቁጥር 714/2003፣ አዋጅ ቁጥር 515/99 አንቀጽ 85፣89

 

የሰ//.96833 ህዳር 08 ቀን 2007 ዓም

 

ዳኞች፡- አልማዉ ወሌ ዓሊ መሀመድ

ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

 

አመልካች፡- የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጄንሲ - ቀረቡ /ነ-ፈጅ/ ተጠሪ፡- አቶ አስፋዉ ደነቀ - የቀረበ የለም፡፡

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ርድ

 

ይህ ጉዳይ በማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የተጀመረው ተጠሪ አቶ አስፋዉ ደነቀ የተራዘመዉ አገልግሎት ለጡረታ ተግባር እንዲያዝላቸዉ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ነዉ፡፡ ተጠሪ የሚጠይቁት ተጠቃሹ መስሪያ ቤት በወቅቱ በነበረበት የሰዉ እጥረት የጡረታ ጊዜዬን ለ5 ዓመታት እንዲራዘም በጻፈዉ ደብዳቤ ለማ/ዋ/ቅ/ጽ/ቤት ሲጻፍ ለእኔም ግልባጩ ደርሶኝ በተከፈተዉ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት የውሃ ጽ/ቤት ተጠባባቂ ኃላፊነት ተመድቤ በ6 ወረዳዎች ሰራሁ፣በድጋሜ የጡረታ ግዜ ለ5 ዓመታት እንዲራዘም ለክልሉ ሲቪል ሰርቪስ  ተጽፎ የስምምነቱ ደብዳቤ ለመ/ቤቱ ሲደርስ ግልባጩ ለክልሉ ማ/ዋ/ኤ/ጽ/ቤት ደርሷል፣ የዉሃ ሀብት ቢሮ ባዘጋጀዉ አዲስ መዋቅር የተደረገዉ ስምምነት 2 ዓመት ሲቀረኝ እርምጃ ወስዷል፣ስለዚህ ከየካቲት 1995 እስከ ጥር 30 ቀን 2003 ዓ/ም ድረስ የተራዘመዉ የ8 ዓመታት አገልግሎቴ እንዲያዝልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ አመልካችም በሰጠዉ መልስም፡- አቶ አስናቀ ደነቀ የትዉልድ ዘመናቸዉ ጥር 13 ቀን 1940 ዓ.ም ሲሆን በጡረታ መገለል የሚገባቸዉ ከየካቲት 01 ቀን 1995 ዓም ጀምሮ ነዉ፣አሰሪዉ መ/ቤቱ መረጃ እንዲልክ በ2/9/95 ዓ.ም ቢጠየቅም የአገልግሎት ማራዘሚያ ጥያቄ ለሱማሌ ክልል መላኩ ስልጣኑ እንዳልሆነ በማሳወቅ የባለመብቱ መረጃ ተሟልቶ እንዲላክ በድጋሚ በ15/11/95 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የተጠየቀና የመጀመሪያ አምስት አመታት የጡረታ ጊዜ ማራዘሚያ ጥያቄ በሚመለከተዉ አካል ባልቀረበበት ሁኔታ በተጨማሪ ከ1/8/2000 እስከ 30/05/2005 ዓም እንዲራዘም የተደረገዉ የጡረታ መዉጫ ጊዜያቸዉ ካለፈና የጡረታ አዋጅ ቁ.345/95 አንቀጽ 11(ሀ) መሠረት  የጡረታ መዉጫ ጊዜያቸዉ ካለፈ አገልግሎታቸዉ እንዲራዘም የተፈቀደበት መረጃ ያልቀረበ በመሆኑ ከእድሜ ጣሪያ በላይ ላገለገሉበት የመዋጮ ተመላሽ ከሚከፈላቸዉ/ከሚጠይቁት በስተቀር የተራዘመዉ አገልግሎት ሊያዝላቸዉ አይገባም በማለት ተከራክሯል፡፡

ጉዳዩን ያየዉ ማህበራዊ ዋስትና ጉባኤም ከሱማሌ ክልል መንግስት የዉሃ ማዕድንና ኢነርጂ ሀብት ልማት ቢሮ በ12/10/1995 ዓም ለማህበራዊ ዋስትና ባለስልጣን ጅጅጋ ቅ/ጽ/ቤት በጻፈዉ ደብዳቤ የተጠሪ የአገልግሎት ጊዜ  እንዲራዘም ጥያቄ ያቀረበ መሆኑ ከቀረበዉ መረጃ  ለመረዳት


ተችሏል፣በተጨማሪም በ18/7/1995 ዓ.ም በቁጥር ሠአር ከሰ/2145/95 ከክልሉ የዉሃ ማዕድንና ኢነርጂ ሀብት ልማት ቢሮ የድሬዳዋ ጽ/ቤትን በመደበኛ ስራ ለማስጀመር የጽ/ቤቱ ጊዜያዊ ኃላፊ በመሆን የተሾሙ መሆኑን ከቀረበዉ ማስረጃ ለማረጋገጥ ተችሏል፣የሽንሌ ዞንም ከፍተኛ ድርቅ ተከስቶበት ስለነበር ችግሩን ለመቅረፍ ሲሰሩ እንደነበር እና ከፍተኛ ባለሙያ መሆናቸዉን ገልጾ በክልሉ የዉሃ ሀብት ኃላፊ ሆነዉ በሹመት ወደ ድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት ተዛዉረዉ በኃላፊነት ሲሰሩ እንደነበር ለጉባዔዉ ገልጸዋል የሚሉ ምክንያቶችን ይዞ በሹመት የቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን እንዲሰሩ የተመደቡ በመሆናቸዉ ከእድሜ ጣሪያ በላይ የፈጸሙት አገልግሎት ሊያዝላቸዉ እንደሚገባ በጉባኤዉ ታምኖበታል በማለት የኤጀንሲውን ዉሳኔ ሽሮ ተጠሪ ከዕድሜ ጣሪያ በላይ የፈጸሙት አገልግሎት ለጡረታ ተግባር እንዲያዝላቸዉ ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ ኤጀንሲዉ ይግባኝ በማለቱ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚዉ ችሎትም ቅሬታዉን በአዋጅ ቁ.515/99 አንቀጽ 76 መሰረት ባለመቀበል ዘግቶታል፡፡

የአመልካች የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ዉሳኔ ለማስቀየር  ነዉ፡፡ አመልካች ባቀረበዉ የሰበር አቤቱታም ቅሬታዉን ሲገልጽ፡- ተጠሪ በክልሉ የዉሃ ሀብት ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ሥር ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን ሲሰሩ የቆዩት በስራ ሀላፊነት እንጂ በሹመት አይደለም፣ ሃላፊ ተብለዉ መስራታቸዉ ሹመት ሊባል አይችልም፣ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ የፌደራል መንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁ. 515/99 ድንጋጌን በመጥቀሰ የተጠሪ አገልግሎት ከተቋረጠ 5 ዓመታት በኋላ እንዲራዘም መፍቀዱ ህግን የተከተለ አይደለም፣ የጡረታ አዋጅ ቁ.710/2003 አንቀጽ 17(4)(ሀ) መሠረት ማንኛዉም የመንግስት ሰራተኛ በህጉ መሰረት አገልግሎቱ ካልተራዘመ የጡረታዉ መዉጫ እድሜዉ ከደረሰበት ከሚቀጥለዉ ወር አንስቶ የሚሰጠዉ አገልግሎት ለጡረታ ተግባርአይያዝም እያልንኤጀንሲዉና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚዉ ችሎት የተጠሪ አገልግሎት እንዲራዘምና እንዲያዝላቸዉ  መወሰኑ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊሻር ይገባዋል በማለት ተከራክሯል፡፡ በዚህም መሰረት ችሎቱም ተጠሪ ከጡረታ መዉጫ በኋላ የአገልግሎት ዘመኑ ለተጨማሪ 5 ዓመታት ተራዝሟል መባሉን ከአዋጅ ቁ.515/99 አንቀጽ 89 ድንጋጌና ከዚሁ አዋጅ አንቀጽ 85/1 ድንጋጌ አንጻር ለማጣራት የግራ ቀኙ የመልስና መልስ መልስ በጽሑፍ ተቀባብለዉ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች አንጻር ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አኳያ እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡

አመልካች የሚለዉ የአዋጅ ቁ.515/99 ተጠቅሶ ተጠሪ አገልግሎት ከተቋረጠ ከ 5 ዓመታት በኋላ እንዲራዘም መፈቀዱ ህግን የተከተለ አይደለም ፣በህጉ መሠረት ማንኛዉም የመንግስት ሰራተኛ አገልግሎት ካልተራዘመ በስተቀር የጡረታ መዉጫ ዕድሜዉ ከደረሰበት ከሚቀጥለዉ ወር አንስቶ የሚሰጠዉ አገልግሎት ለጡረታ ተግባር  አይያዝም፣በመሆኑም ህጋዊነቱ ሳይረጋገጥ ተራዝሟል መባሉ ሊታረም ይገባዋል፡፡ ተጠሪ በበኩላቸው በወቅቱ በነበረዉ የዉሃ አጥረት የተነሳ እንዳገለግል ፈቅዶ ሲያሰራኝ ቆይቶ መራዘሙን አላዉቅም ማለቱ የራሱን የመረጃ አያያዝ ድክመት መኖሩን የሚያሳይ ነዉ፣ አመልካች ማገልገሌን ሳይቃወም ዉሳኔዉን መንቀፉ አግባብ ባለመሆኑ የስር ዉሳኔ ስህተት የለበትም በማለትተከራክሯል፡፡

በመሰረቱ የአዋጅ ቁ.515/99 አንቀጽ 89 እና አንቀጽ 85(1) ድንጋጌዎች ከተያዘዉ ክርክር አንጻር ስንመለከታቸው አንቀጽ 89(2) ሠ እና 85(1) በመርህ ደረጃ የጡረታ ጊዜ አገልግሎት ሊራዘም  የሚችለዉ  ለኤጀንሲዉ  ቀርቦ  በህጋዊ  መንገድ  መፈቀድ  እንዳለበት  ይህ ካልሆነ


ያለተጨማሪ ስነ-ስርዓት አገልግሎት የሚቋረጥ መሆኑን እና የአገልግሎት መራዘም ከ10 ዓመት የማይበልጥ መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡

እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት የህግ ድንጋጌዎች በመርህ ደረጃ ጡረታ መዉጫ ጊዜ ከደረሰ በኋላ አገልግሎት ዘመን ለማራዘም ሊከናወኑ የሚገባቸዉን ህጋዊ አካሄድን የሚያመላክቱ መሆናቸዉን መገንዘብ ተችሏል፡፡

በእጃችን ወዳለዉ ጉዳይ ስንመለስ ተጠሪ በክልሉ የዉሃ ማዕድንና ኢነርጂ ሀብት ልማት ቢሮ ሲያገለግሉ የነበሩና አስፈላጊ ባለሙያ በመሆናቸዉ ከጡረታ መዉጫ ጊዜያቸዉ በኋላ ተጨማሪ አገልግሎት እንዲሰጡ በመፈለጉ ምክንያት በ12/10/95 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ለማህበራዊ ዋስትና ባለስልጣን ማሳወቁን መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ተጠሪ ላለፉት 8 ዓመታት የውሃ አጥረት በገጠማቸዉ አካባቢዎች ተዘዋውረው ሲሰሩ እንደነበሩና ለስራቸዉም ክፍያ ሲያገኙ እንደነበሩ የምንገነዘበዉና በስር ፍርድ ቤትም ተረጋግጦ  እና በአመልካችም ያልተካደ ጉዳይ ነዉ፡፡ አከራካሪ የሆነዉ ጉዳይ ተጠሪ ይሁንታ ሳያገኙ የአዋጅ ቀ.714/2003"ን" መንፈስ ተከትሎ አስፈላጊውን ቅደመ ሁኔታ ሳያሟሉ (ጥያቄያቸዉ ተቀባይነት ሳያገኙ) በመስራታቸዉ ብቻ የተራዘመ አገልግሎት ለጡረታ አገልግሎት እንዲያዝላቸው መጠየቅ አይችሉም በማለት ነዉ፡፡ እንግዲህ ተጠሪ ለተጨማሪ ግዜ አገልግሎት  መስጠታቸዉ ባልተካደበት አስፈላጊዉን አስተዳደራዊ መጻጻፍ በማድረግ ጉዳዩን ወደ ህጋዊነት የማምጣት ኃላፊነት እና ግዴታ ያለበት አመልካች እንጂ ተጠሪ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ምክንያቱም አሰሪዉ አካል እያወቀና ተቃዉሞ ከየትኛዉም አካል ሳይገጥማቸዉ ተጠሪ ስራቸውን መስራታቸዉን ማረጋገጣቸዉ በቂ ነዉ፡፡

በአጠቃለይ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በስር በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠዉን በመቀበል ተጠሪ ከዕድሜ ጣሪያ በላይ ያገለገሉት ጊዜ ለጡረታ አገልግሎት እንዲያዝላቸዉ መወሰኑ በአግባቡ ነዉ ብለናል፡፡

በመጨረሻም ማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚዉ ጉባዔ እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት ዉሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነዉ ለማለት አልተቻለም፡፡ በመሆኑም ተከታዩ ተወስኗል፡፡

 ዉሳ ኔ

1. የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ በመ.ቁ.ጤ/ይ/1/1/43/2006 በቀን  29/02/2006 ዓ/ም እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.95017 በቀን 30/04/2006 ዓ.ም የሰጡት ዉሳኔ ጸንቷል፡

2. ተጠሪ ከዕድሜ ጣሪያ በላይ የፈጸሙት አገልግሎት ለጡረታ ተግባር እንዲያዝላቸዉ መባሉ ባግባቡ ነዉ ብለናል፡፡

3.  የግራቀኙ የወጪና ኪሳራቸዉን ይቻቻሉ፡፡

 

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡                የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡ ብ/ግ