94278 commercial law/ company dissolution/ period of limitation/ successive events

ክሱ የቀረበው በአንድ ተለይቶ በታወቀ ጊዜ ወይም ቀን የተፈጠረ ክስተትን መሠረት በማድረግ ሳይሆን በተለያየ ጊዜ  ተከስተዋል የተባሉ የተለያዩ ችግሮችን መሠረት አድርጐ ሲሆን የማህበር ይፍረስልኝ ጥያቄ ወይም ክስ በይርጋ ይታገዳል የሚባልበት ምክንያት

 

የሰ/መ/ቁ. 94278

 

ህዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- አቶ ሐሰን መሐመድ ቀረቡ

 

ተጠሪ፡- ማጂ አግሮ ፎረስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አሸናፊ ማሞ ቀረቡ

 

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል፡፡

 

 ፍ  ር ድ

 

በስር ፍርድ ቤት ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ አመልካች በዚህ መዝገብ አቤቱታ ያቀረቡት በተከሳሽነት ተሰይመው የነበሩት የማጂ አግሮ ፎረስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ በማህበሩ የመመስረቻ ፅሁፍና የመተዳደሪያ ደንብ የተሰጣቸውን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ ባለመቻላቸው ምክንያት የማህበሩ ሕልውና አደጋ ላይ የወደቀ መሆኑን በምክንያትነት በመጥቀስ በንግድ ሕግ ቁጥር 218 እና 542 መሰረት ማህበሩ እንዲፈርስ ይወሰንልኝ በማለት ያቀረቡት ክስ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1835 መሰረት በአስር አመት ይርጋ የሚታገድ ነው በማለት ክሱ የቀረበለት በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግስት የማጂ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው እና በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በትዕዛዝ የፀናው ብይን መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡

ከመዝገቡ ግልባጭ መገንዘብ እንደተቻለው ክሱ የቀረበለት የማጂ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከተከሳሽ የቀረበለትን የይርጋ መቃወሚያ በመቀበል የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር. 1835 ድንጋጌን ጠቅሶ ክሱ በአስር ዓመት ይርጋ የታገደ ነው በማለት ብይን የሰጠው የማህበሩ የመመሰረቻ ፅሁፍ ከተፈረመበት ከ19/06/1991 ዓ.ም ጀምሮ ማህበሩ እንዲፈርስ ክስ እስከቀረበበት 03/10/2005 ዓ.ም ድረስ ያለው ጊዜ ሲቆጠር አስር ዓመት አልፎታል በማለት ነው፡፡ የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ የስር ፍርድ ቤቶች ማህበሩ የተመሰረተበትን ጊዜ መነሻ አድርጐ በማስላት አመልካች መስራች ሆነው አቋቁመውት ሲንቀሳቀስ የነበረው ማህበር ሒሳብ በኦዲት ተመርምሮ ድርሻቸው እንዲታወቅ እና ማህበሩ እንዲፈርስ ያቀረቡት ክስ በይርጋ ይታገዳል በማለት የመወሰናቸውን አግባብነት ተጠሪው ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርቡ በመደረጉ ግራ ቀኙ የፅሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በክርክሩ እልባት ማግኘት የሚገባቸው ነጥቦች፡-


1. ክሱ በይርጋ የሚታገድ ነው በማለት በማጂ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ትዕዛዝ የፀናው ብይን ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው ወይስ አይደለም?

2. በከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበው ክስ ተገቢውን የክስ አቀራረብ ስርዓት ተከትሎ የቀረበ አይደለም በማለት ተጠሪ በሰበር መልሳቸው ያቀረቡት ክርክር ጉዳዩ አሁን ባለበት ደረጃ በዚህ ሰበር ችሎት ሊስተናገድ የሚችልበት አግባብ አለ ወይስ የለም? የሚሉ መሆናቸውን በመገንዘብ አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት መሆን አለመሆኑን ከእነዚሁ ጭብጦች አንፃር መርምረናል፡፡

በዚህ መሰረት የመጀመሪያው ነጥብ በተመለከተ አመልካች ለማጂ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡት ክስ መሰረታዊ ይዘት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ በማህበሩ የመመስረቻ ፁሁፍና የመተዳደሪያ ደንብ የተሰጣቸውን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ ባለመቻላቸው ምክንያት የማህበሩ ሕልውና በአደጋ ላይ የወደቀ በመሆኑ ሂሳብ ተጣርቶ ማህበሩ እንዲፈርስ ይወሰንልኝ የሚል መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ እና የግራ ቀኙ የክርክር ይዘት ያመለክታል፡፡ አመልካች የማህበሩ መስራች አባል መሆናቸው እና በ1995 ዓ.ም ከማህበሩ የስራ አስኪያጅነት ስልጣን ተነስተዋል ከመባሉ በቀር ክስ እስካቀረቡበት ጊዜ ድረስ የማህበሩ አባልነታቸው ያልተቋረጠ ስለመሆኑ በተጠሪው አልተካደም፡፡ የማጂ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክሱ በአስር ዓመት ይርጋ ይታገዳል ለማለት የቻለውም ጊዜውን የማህበሩ የመመስረቻ ፅሁፍ ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ በመቁጠር ስለመሆኑ የብይኑ ግልባጭ ያመለክታል፡፡ በመሰረቱ አንድ የንግድ ማህበር  በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲፈርስ የሚደረገው ጥያቄ ስለቀረበ ብቻ ሳይሆን ማህበሩን ለማፍረስ የሚያስችሉ ትክክለኛ ምክንያቶች ስለመኖራቸው በማስረጃ ተረጋግጦ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በንግድ ሕጉ ዕውቅና የተሰጣቸው የንግድ ማህበራት ከአባላቱ በአንዱ የይፍረስልኝ ጥያቄ ሊቀርብባቸው የሚችል ስለመሆኑ በንግድ ሕግ ቁጥር. 218(1) ስር ተደንግጐ የሚገኝ ሲሆን የተወሰነ ኃላፊነት ያለው የግል ማህበርን በተመለከተ በንግድ ሕግ ቁጥር 542(1) ስር የተመለከተው ድንጋጌም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ነው፡፡ እንደሚታወቀው የንግድ ማህበር ይፍረስልኝ ጥያቄ በውል ከተቋቋመ የማህበርተኝነት መብት የሚመነጭ እና በማህበሩ እንቅስቃሴ ሂደት የሚፈጠሩ የተለያዩ ችግሮችን መሰረት አደርጐ የማህበሩ ህልውና እስካለ ድረስ በማንኛውም ጊዜ ሊቀርብ የሚችል ነው ከሚባል በቀር በታወቀ የይርጋ ጊዜ የሚታገድ ስለመሆኑ የንግድ ሕጉ ድንጋጌዎች አያመለክቱም፡፡ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ለብይኑ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር. 1835 ድንጋጌን በምክንያትነት የጠቀሰው አለቦታው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በንግድ ሕጉ የተደነገገ የተለየ የይርጋ ዘመን በሌለ ጊዜ የዚህ ዓይነቱ ክስ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር. 1845 በተመለከተው ጠቅላላ የይርጋ ጊዜ ይታገዳል ሊባል ይችል የነበረውም የይፍረስልኝ ጥያቄው የቀረበው ተለይቶ በታወቀ ቀን የተፈጠረ ክስተትን ጠቅሶ ወይም መሰረት አደርጐ ቢሆን ኖሮ እና ክሱ የቀረበው ክስተቱ ከተፈጠረ አስር ዓመት ካለፈው በኋላ ቢሆን ኖሮ ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ አመልካች ክሱን ያቀረቡት በአንድ ተለይቶ በታወቀ ጊዜ ወይም ቀን የተፈጠረ ክስተትን መሰረት በማድረግ ሳይሆን ይልቁንም በማህበሩ እንቅስቃሴ ሂደት በተለያየ ጊዜ ተከስተዋል የተባሉ የተለያዩ ችግሮችን በምክንያትነት በመጥቀስ በመሆኑ ክስ የማቅረብ መብታቸው በይርጋ ይታገዳል የሚባልበት ሕጋዊ ምክንያት የለም፡፡ የማህበሩ የመመስረቻ ፅሁፍ የተፈረመበት ቀንም በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን በማህበሩ እንቅስቃሴ ሂደት በተለያየ ጊዜ  የተፈጠሩ የተለያዩ ችግሮችን መሰረት አድርጐ ለሚነሳ የማህበር ይፍረስልኝ ጥያቄ ለይርጋው አቆጣጠር የመነሻ ቀን ተደርጐ ሊወሰድ የሚችል አይደለም፡፡ በመሆኑም የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር. 1835 ድንጋጌን አለቦታው በመጥቀስ ክሱ በይርጋ የሚታገድ ነው በማለት በማጂ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት


ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በትዕዛዝ የፀናው ብይን ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡

ሁለተኛው ነጥብ በተመለከተ ተጠሪ በሰበር መልሳቸው ላይ በከፍተኛው ፍርድ ቤት  የቀረበው ክስ ተገቢውን የክስ አቀራረብ ስርዓት ተከትሎ የቀረበ ባለመሆኑ ሕጋዊ ተቀባይነት ሊሰጠው አይገባም በማለት የተከራከሩ ሲሆን አመልካች ክሱን ያቀረቡት በራሳቸው ስም ብቻ ነው ወይስ በሌሎች ሰዎች ስም ጭምር ነው? እንዲሁም ክሱን ያቀረቡት በማህበሩ ላይ ነው ወይም በማህበሩ ስራ አስኪያጅ ላይ ነው? በሚሉት ነጥቦች ላይ ግራ ቀኙ የአቋም ልዩነት ያላቸው መሆኑን በሰበር ደረጃ ከተለዋወጡት የፅሁፍ ክርክር መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩ በስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በብይን የተዘጋው በይርጋ ምክንያት በመሆኑ በሰበር ክርክራቸው ላይ ግራ ቀኙ የተለያዩባቸውን ጨምሮ ቀሪዎቹ የክርክሩ ነጥቦች በስር ፍርድ ቤት ተጣርተው ውሳኔ የሚያርፍባቸው ከሚሆን በቀር ጉዳዩ አሁን ባለበት ደረጃ በዚህ ሰበር ችሎት ሊስተናገዱ የሚችሉበት የህግ አግባብ አይኖርም፡፡

ሲጠቃለል ክሱ በይርጋ የሚታገድ ነው በማለት በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ብይን መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው  ሳ ኔ

1. በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግስት በማጂ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር

19372 በ20/12/2005 ዓ.ም ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 01174 በ15/01/2006 ዓ.ም በትዕዛዝ የፀናው ብይን በፍትሐብሔር ሥነ- ሥርዓት ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2. አመልካች ያቀረቡት የማህበር ይፍረስልኝ ክስ በይርጋ የሚታገድ  አይደለም በማለት ወስነናል፡፡

3. በግራ ቀኙ የቀረበውን ቀሪ ክርክር መርምሮ እና አጣርቶ ተገቢውን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩ በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር. 341(1) መሰረት ለማጂ አካባቢ ከፍተኛው ፍርድ ቤት እንዲመለስ ወስነናል፡፡

4. የውሳኔው ግልባጭ በዚህ ውሳኔ መሰረት ተገቢውን መፈፀም ያስችለው ዘንድ በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግስት ለማጂ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ እንዲያውቀው ደግሞ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይላክ፡፡

5.  የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

6.  ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

 

 

 

የማይበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት