101079 property law/ rural land law/ Oromia region/ Execution of judgment

በገጠር የእርሻ መሬት ላይ በተሠጠ ፍርድ  የፍርድ መቃወሚያ ሲቀርብ ፍርድ ተፈፅሟል ሊባል የሚችለው የፍርድ ባለመብቱ በይዞታው ላይ ህጋዊ ማረጋገጫ ሲያገኝ ስለመሆኑ፣

የሰ/መ/ቁ 101079

 

ጥር 22 ቀን 2007 ዓ/ም

 

ዳኞች:- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- የይልማና ዴንሳ ወረዳ አከባቢ ጥበቃ መሬት አስተዳደርና  አጠቃቀም ፅ/ቤት ከክልል ፍትህ ቢሮ አይናዲስ አሰጋህኝ - ቀረቡ

ተጠሪ ፡- አቶ ውበት ገ/መድህን - የቀረበ የለም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ የገጠር የእርሻ መሬት የሚመለከት ሆኖ የተጀመረው በይልማና ዴንሳ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው፡፡ የአሁን ተጠሪ በአቶ ልንገርህ ውበት ላይ የእርሻ መሬት ይዞታዬን ያላግባብ ይዞብኛል በማለት ክስ መስርተው ፍርድ ቤቱን የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ አከራካሪውን መሬት አቶ ልንገርህ ውበት ለአሁኑ ተጠሪ እንዲያስረክቡ በማለት ውሳኔ ሰጥቶ የአሁኑ ተጠሪ በዚሁ ፍርድ መሰረት እንዲፈጸምላቸው የአፈጻጸም ማመልከቻ አቅርበዋል፡፡በዚህ ሂደት የአሁኑ አመልካች አከራካሪውን ይዞታ ይዘው የነበሩት አቶ ልንገርህ ውበት የመንግስት ሰራተኛ ስለሆኑና አመልካችም የይዞታ ባለመብት  ስላልሆኑ ይዞታውን ሊረከቡ የሚችሉበት የሕግ አግባብ የለም፣ ውሳኔው የህዝብንና የመንግስት ጥቅም የሚነካ በመሆኑ ሊነሳ ይገባል በማለት አቤቱታውን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 መሰረት ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም የአሁኑ ተጠሪ በአመልካች የፍርድ መቃወሚያ ላይ መልስ እንዲሰጡበት አድርጓል፡፡የአሁኑ ተጠሪ ለአመልካች የፍርድ መቃወሚያ አቤቱታ ላይ በሰጡት መልስም የአመልካች የፍርድ መቃወሚያ አቤቱታ አቀራረብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 ስር የተመለከተውን አግባብ ያልተከተለ መሆኑን፣አቶ ልንገርህ ውበት የተባሉት ግለሰብ መሬቱን ከተጠሪ በስጦታ ስለመቀበሉ ምንም ማስረጃ ባልቀረበበትና ራሱ የፍርድ ተቃዋሚ ወገን ባለሙያ መድቦ ይህንኑ ባረጋገጠበት ሁኔታ ፍርዱን መቃወሙ ያላግባብ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡ የወረዳው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የተጠሪን መከራከሪያ ነጥብ ውድቅ አድርጎና የቀድሞውን ውሳኔ በመሻር መሬቱ ለክፍሉ ቀበሌ የመሬት አስተዳደር ሊያስረክቡ ይገባል በማለት ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለምዕራብ ጎጃም አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ   በኋላ


ጉዳዩን መርምሮ የአመልካች የፍርድ መቃወሚያ የቀረበው ተጠሪ የመሬት ይዞታውን ከተረከቡ በኋላ በመሆኑ መቃወሚያው ዋናው ፍርድ ከተፈጸመ በኃላ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 መሰረት የሚቀርብበትና የሚስተናገድበት አግባብ የለም በማለት የወረዳውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ሽሮታል፡፡በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም፡፡የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎትም በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት የአመልካችን የሰበር አቤቱታ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበው ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ሲሆን የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም አመልካች የፍርድ መቃወሚያውን ፍርዱ ከመፈፀሙ በፊት ማቅረቡን፣ የአከራካሪው መሬት ይዞታ ስም በተጠሪ ሳይመዘገብ ርክክቡ ተፈፅሟል የሚባልበት አግባብ ያለመኖሩን ዘርዝሮ መቃወሚያው በሕግ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት የቀረበ ሁኖ እያለ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚና ሰበር ሰሚ ችሎቶች ውድቅ መደረጉ ያላግባብ ነው የሚል ነው፡፡አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርበውም  ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- በሚያከራክረው የገጠር መሬት ይዞታ ላይ አመልካች ያቀረበው የፍርድ መቃወሚያ ስርዓቱን ጠብቆ የቀረበ አይደለም ተብሎ ውድቅ መደረጉ በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል፡፡

 

ተጠሪ በልጃቸው ይዞታ ስር የነበረውን መሬት ልጃቸው ሕጋዊ መብት ሳይኖራቸው ይዘው እንደሚገኙ ገልፀው ባቀረቡት ክስ ከልጃቸው ጋር ተከራክረው መሬቱን እንዲለቀቅላቸው በተወሰነው መሰረት መሬቱን የተረከቡ መሆኑን የክርክሩ  ሂደት  ያሳያል፡፡አመልካች አሁን አጥብቆ የሚከራከረው የክርክሩ ምክንያት የሆነው የገጠር የእርሻ መሬት እንደመሆኑ መጠን አመልካች መሬቱን ተረክበዋል ሊባል የሚችለው የይዞታ ማረጋገጫ ሲያገኙ ነው በሚል ምክንያት ነው፡፡ተጠሪ በበኩላቸው ይህ አይነት አሰራር በተለያዩ የአስተዳደር አሰራሮች ሊዘገይ የሚችል በመሆኑ ተጠሪ መሬቱን አልተረከቡም ለማለት የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያት አይደለም በማለት ተከራክረዋል፡፡

 

በመሰረቱ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 358 መሠረት የተዘረጋው ሥርዓት አስቀድሞ በተሰጠው ውሣኔ መብቱ የሚነካበት ወገን ባለበት ውሣኔ እንዳልተሰጠበት ተቆጥሮ እንደገና ክርክር የሚጀምርበት ሥርዓት ነው፡፡ መሰረታዊ አላማም ቅን ልቦና ያላቸው ወገኖች በመሰረታዊ ሕግ የተጠበቀላቸው መብት ባለመከራከር ዋጋ እንዳያጣ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ድንጋጌው በክርክሩ ውስጥ ለመግባት የሚችልና ተካፋይ ባልሆነበት ክርክር የተሰጠው ፍርድ መብቱን የሚነካበት ማናቸውም ወገን አቤቱታውን ለማቅረብ መብት እንደአለው በመለኪያነት ያስቀመጠ ሲሆን ይኼው የድንጋጌ ይዘትም የተቃውሞ አቤቱታውን ለማቅረብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 39፣40 እና 41 አግባብ የክርክሩ ተካፋይ ሊሆን ይገባው የነበረውንና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 33 አግባብ ደግሞ በጉዳዩ መብትና ጥቅም ያለው ወገን መሆን እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ድንጋጌ የተቀመጠው የሕጉ ሐሳብ በተቃውሞ አቤቱታ አቀራረብ ስርዓት መብቱ ሊከበርለት የሚገባው ወገን ለጉዳዩ አግባብነት ካለው የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ክፍል አንፃር ክርክር ባስነሳው ንብረት ላይ ያለው የመሟገት መብት የተጠበቀ ነው ለማለት እንጂ በማንኛውም ጉዳይ ቢሆን በአንድ ጉዳይ አፈፃጸሙ  ማለቁ  የተረጋገጠበት  ወገን  አፈጻፀሙ  መብቱን  የሚነካበት  ሆኖ  ባገኘው  ጊዜ


ከአፈፃጸሙ መዝገብ መዘጋት በኃላ የፍርድ መቃወሚያ በማቅረብ የመሟገት መብት አለው በማለት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 358 ሰፊና የፍትሃ ብሔር ስነ ስርዓት ሕጉ አላማ ውጤት አልባ የሚያደርግ ትርጉም ለመስጠት ተፈልጎ አይደለም፡፡ይህ ዓይነት አተረጓጎም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግን መሠረታዊ ዓላማ የተከተለ ባለመሆኑ ተቀባይነት የሚያግኝበት አግባብ የለም፡፡አፈጻጸም የፍርድ ቤት ውሳኔ ትርጉም የሚያገኝበት ሂደት በመሆኑ አፈጻጸሙ በሕጉ አግባብ ከተጠናቀቀ በኋላ ይህንኑ ሂደት ወደ ኃላ መመለስ የአፈጻጸም ስርዓት የሚፈቅደው አይደለም፡፡በመሆኑም አንድ ፍርድ ከተፈፀመ በኃላ የፍርድ መቃወሚያ ማቅረብ የማይቻል መሆኑን ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 ድንጋጌ በቀላሉ መገንዘብ የምንችለው ጉዳይ ነው፡፡አከራካሪው ጉዳይ አንድ ፍርድ ተፈፀመ የሚባለው መቼ ነው? የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ይህ ጥያቄ እንደ ለክርክሩ  መነሻ እንደሆነው ንብረት ልዩ ባህርይ ታይቶ ሊመለስ የሚችል ነው፡፡ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ስንመለሰው የፍርድ ባለመብት ፍርዱ ተፈጽሞለታል የሚባለው ጥሬ ገንዘብ ከሆነ ገንዘቡ ሙሉ በሙሉ ሲመለስለት፣የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሆነ ደግሞ ንብረቶቹን  ተረክቦ በይዞታው ላይ ሲያደርግ መሆኑ ይታመናል፡፡

 

ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም ተጠሪ መሬቱን ከልጃቸው መረከባቸውን የበታች ፍርድ ቤቶች አረጋግጠዋል፡፡ይሁን እንጂ ተጠሪ በመሬቱ ላይ ያላቸው መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስትም ሆነ በክልሉ ህገ መንግስት እንዲሁም የገጠር የእርሻ መሬት አስተዳደርን አጠቃቀምን በተመለከተ በፌዴራሉ መንግስት በወጣው አዋጅ ቁጥር 456/1997 እንዲሁም ይህንኑ አዋጅ ተከትሎ በወጣው የክልሉ አዋጅ ቁጥር 133/1998 እና ደንብ ቁጥር 51/1999 አግባብ የይዞታ መብት ሲሆን ነው፡፡በመሆኑም መሬቱ ላይ ያላቸው የባለይዞታ መብት የሚረጋገጠው መሬቱን እንዲያስተዳደር በሕግ ስልጣን የተሰጠው አካል በሕጉ አግባብ ሲያስረክባቸውና በሕጉ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት የባለይዞታ መብት ማረጋገጫ ደብተር ሲያገኙ ነው፡፡ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው ተጠሪ መሬቱን ከልጃቸው ተረክበዋል ከመባሉ ውጪ ርክክቡ መሬቱን የሚያስተዳድረው የመንግስት አካል እውቅና ሰጥቶ የተፈፀመ መሆኑ አልተረጋገጠም፡፡ተጠሪ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲሰጣቸው በተገቢው ጊዜ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ጥያቄ አቅርበው በአስተዳዳራዊ አሰራር ችግር የዘገዬ ስለመሆኑም የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ስለሆነም ተጠሪ በሕጉ የተጠበቀላቸውን የባለይዞታነት መብት ተረክበዋል ሊባል የሚችለው ይዞታውን ከግለሰብ እንዲረከቡ በመደረጉ ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ ማረጋገጫ ሊሆን የሚችል ማስረጃ ሲያገኙ ነው፡፡የገጠር መሬትን በተመለከተ የሚነሱ ክርክሮችን መሰረት አድርጎ የሚቀርብ የፍርድ መቃወሚያ አቤቱታ አቀራረብ፤ ፍርድ ከተፈጸመ በኃላ የቀረበ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 ድንጋጌ መለኪያ ሕገ መንግስቱን መሰረት አድርገው ጉዳዩን ለመግዛት የወጡ ሕጎችን፣ደንቦችንና መመሪያዎችን በሚያሳካ መልኩ ካልተተረጎመና ተግባር ላይ ካልዋለ ግለሰቦች ተገቢ ያልሆነ ክርክር በማቅረብ አንዱ ላንዱ ይዞታውን አስረክቤአለሁ በማለቱ ብቻ የገጠር መሬትን የሚያስተዳድረው የመንግስት አካል የሕዝብና የመንግስት  ጥቅም ለማስከበር እንዳይችል የሚያደርግ ውጤትን የሚያስከትል በመሆኑ ተቀባይነት  ሊሰጠው የማይገባ ሁኖአግኝተናል፡፡ሲጠቃለልም አመልካች የፍርድ መቃወሚያውን ያቀረበው ፍርዱ ሙሉ በሙሉ ተፈጽሟል ሊባል በማይችልበት ሁኔታ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል፡፡በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡


 ው ሳ ኔ

 

1.  በምዕራብ ጎጃም አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 52990 የካቲት 07 ቀን

2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 35349 ግንቦት 16 ቀን 2005 ዓ/ም ፣የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/ 32961 መጋቢት 18 ቀን 2006 ዓ/ም በዋለው ችሎት በትዕዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት ሽረናል፡፡

2. በገጠር የእርሻ መሬት ላይ በተሰጠ ፍርድ የፍርድ መቃወሚያ  ሲቀርብ ፍርዱ ተፈጽሟል ሊባል የሚችለው የፍርድ ባለመብቱ በይዞታው ላይ ሕጋዊ ማረጋገጫ ሲያገኝ ነው ብለናል፡፡

3. አመልካች በሚያከራክረው መሬት ላይ የፍርድ መቃወሚያው ያቀረበው  ፍርዱ ከመፈጸሙ በፊት መሆኑን አውቆ በፍሬ ጉዳዩ ላይ የይልማና ዴንሳ ወረዳ ፍርድ ቤት ታህሳስ 11 ቀን 2004 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በሕግም ሆነ በፍሬ ነገሩ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን መርምሮ ዳኝነት እንዲሰጥበት ጉዳዩን ለምዕራብ ጎጃም አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 341(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል፡፡ይጻፍ፡፡

4.  በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

 

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::

 

 

መ/ተ