94952 family law/ common property/ substantial improvement on private property

ከጋብቻ በፊት በአንደኛው ተጋቢ ስም የነበረን የግል ንብረት በጋብቻ ወቅት በንብረቱ ላይ መሰረታዊ መሻሻል ቢደረግበትና ይሄው መሻሻል የተደረገው የባለንብረቱ የግል ገንዘብ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ ህጉ ንብረቱ የጋራ ነው የሚል ግምት የሚወስድ ስለመሆኑ፣

አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀፅ 63(1)

የሰ/መ/ቁ. 94952

 

መስከረም 30 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ሡልጣን አባተማም መኰንን ገ/ሕይወት ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

አመልካች፡- ወ/ሮ ዙሪያሽ ተገኝ - የቀረበ የለም፡፡

 

ተጠሪ፡- ወ/ሮ የሺ ውድዬ - ረ/ኢንስፔክተር ይመር ዮሴፍ ቀረቡ፡፡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ በሞት የተለየው ተጋቢ የግል ንብረት ነው የተባለን ቤት ከሌላኛዋ ተጋቢ  ለማስለቀቅ ከቀረበ ክስ ጋር ተያይዞ የተነሳ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም ከሳሽ የነበሩት የአሁኗ ተጠሪ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተከሳሽ በነበሩት በአሁኗ አመልካች ላይ በ08/02/2003 ዓ.ም. አዘጋጅተው ባቀረቡት ክስ ነው፡፡

 

የክሱይዘትም ባጭሩ፡-ከሳሽ የሟች ልጃቸው አቶታደሰ የሱፍ እናት እና ወራሽ መሆናቸውን፣ሟች እና ተከሳሽ በ17/09/1997 ዓ.ም. በባህላዊ ስርዓት ጋብቻ ፈጽመው አብረው ይኖሩ የነበረ መሆኑን፣በን/ስ/ላፍቶ ክፍለ ከተማ በቀበሌ 09/14 የሚገኘው ቁጥሩ አዲስ የሆነው መኖሪያ ቤት ከጋብቻው በፊት የተፈራ የአቶ ታደሰ የሱፍ የግል ሀብት ስለመሆኑ ጋብቻውን በፈጸሙበት ጊዜ ባደረጉት የጋብቻ ውል ማረጋገጣቸውን፣ይሁን እንጂ ጋብቻው በልጃቸው ሞት ምክንያት መፍረሱን ተከትሎ ተከሳሽ ቤቱን እና በክሱ የተጠቀሱ የቤት ቁሳቁሶችን ለከሳሽ እንዲያስረክቡ ተጠይቀው ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን የሚገልጽ ሆኖ ተከሳሽ የዋጋ ግምቱ ብር 25,000 (ሃያ አምስት ሺህ) የሆነውን ቤት እና የብር 10,000 (አስር ሺህ) የዋጋ ግምት ያላቸውን የቤት ቁሳቁሶች ለከሳሽ እንዲያስረክቡ እና ለስምንት ወራት ከቤቱ ኪራይ የሰበሰቡትን ገንዘብ ብር 8,000 (ስምንት ሺህ) ለከሳሽ እንዲከፍሉ ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ሲሆን ተከሳሽ በበኩላቸው በ09/07/2003 ዓ.ም. በሰጡት መልስ ከጋብቻው በፊት ሟች የሰሩት አንድ ሳሎን እና አንድ መኝታ ያለው ሁለት ክፍል ቤት ሆኖ ከጋብቻቸው በኃላ ሶስት ተጨማሪ ክፍሎችን ከሟች ጋር የሰሩ በመሆኑ ቤቱ በሙሉ የሟች የግል ሀብት እንደሆነ ተደርጎ የቀረበው ክስ ተገቢነት የሌለው መሆኑን፣የቤት ቁሳቁሶቹ ግምት ከብር 1,000 የማይበልጥ መሆኑን እና ከቤቱ ኪራይ የተሰበሰበው የገንዘብ መጠንም ከቀለብ አልፎ ሊጠራቀም የማይችል መሆኑን በመግለጽ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ተከራክረዋል፡፡


ፍርድ ቤቱ ውርሱ ተጣርቶ ሪፖርት እንዲቀርብለት ጉዳዩን ለውርስ አጣሪ የመራው ሲሆን አጣሪው ውርሱን ማጣራቱን ገልጾ ነገር ግን ቤቱ ሰነድ አልባ ስለመሆኑ ግራ ቀኙ የተማመኑ በመሆኑ የውርስ ሀብት ነው ለማለት ያልተቻለ መሆኑን በመግለጽ ሪፖርት  አቅርቧል፡፡ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ቤቱ ሰነድ አልባ መሆኑ ክርክሩን አይቶ ውሳኔ ከመስጠት የማይከለክል  መሆኑን እና በመዝገቡ የሚሰጠው ውሳኔ ተፈጻሚነት የሚኖረው የቤቱን ሕጋዊነት በተመለከተ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ተመስርቶ መሆኑን ገልጾ ተጋቢዎቹ ከጋብቻቸው በኃላ የሰሩት ተጨማሪ ግንባታ መኖር አለመኖሩን ለማጣራት የግራ ቀኙን ምስክሮች ከሰማ በኋላ ቤቱ የአንደኛው ተጋቢ የግል ሀብት ስለመሆኑ ተከሳሽ                                        በፈረሙት  የጋብቻ ውል በማረጋገጣቸው ከቤቱ ድርሻ አላቸው ማለት ያልተቻለ መሆኑን፣ቤቱ በጋብቻ  ውሉ ላይ የተገለጸው "ቤት" ተብሎ እንጂ የተከሳሽ ምስክሮች እንደገለጹት "የሸራ ወይም የላስቲክ ቤት" ተብሎ አለመሆኑን፣ስለቤት ቁሳቁሶች በከሳሽ ምስክሮች የተገለጸ ነገር አለመኖሩን እና ከቤቱ ኪራይ ይሰበሰብ የነበረው የገንዘብ መጠንም ከቀለብ አልፎ ሊጠራቀም የሚችል አለመሆኑን በዝርዝር በመግለጽ ተከሳሽ ክስ ያስነሳውን ቤት ለከሳሽ ለቀው እንዲያስረክቡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ አመልካች አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኙን ዘግቶ በማሰናበቱ ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮ በጋብቻ ውሉ ላይ ቤቱ የአቶ ታደሰ የሱፍ የግል ንብረት ነው ተብሎ መጠቀሱን ብቻ መሰረት በማድረግ በጋብቻው ጊዜ በሁለቱ ተጋቢዎች በጋራ ከታደሰው ቤት እና በጋራ ከተሰሩት ተጨማሪ ክፍሎች ውስጥ አመልካች ድርሻ የላቸውም ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት ተጠሪዋ  ባሉበት                                        ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር  ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም ክርክሩ የታየበትን የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መዝገብ በማስቀረብ ጭምር ውሳኔው መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለጉዳዩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርምረናል፡፡

በዚህም መሰረት አመልካች አድራሻው በክሱ የተጠቀሰው ቤት ከጋብቻው በፊት የተፈራ የተጠሪ አውራሽ የግል ንብረት መሆኑን በማረጋገጥ ጋብቻው በተፈጸመበት ጊዜ የጋብቻ ውል የፈረሙ መሆኑ በአመልካች ያልተካደ እና የጋብቻ የውል ሰነዱን ጨምሮ በማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ የጋብቻ ውሉ በተፈረመበት ጊዜ የነበረው ከላስቲክ እና ከሸራ የተሰራ ዳስ ሆኖ እያለ ቤት እንደሆነ አድርገው ያስፈረሙኝ አላግባብ ነው በማለት አመልካች  በሰበር ማመልከቻቸው ያቀረቡት ክርክር ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡

በሌላ በኩል ግን በጋብቻው ወቅት ተጨማሪ ክፍሎች የተገነቡ ወይም የተሰሩ ስለመሆኑ በማስረጃ ተረጋግጦ እያለ ቤቱ ሙሉ በሙሉ የሟች የግል ሀብት እንደሆነ ተደርጎ ለተጠሪ እንድትለቅ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው በማለት አመልካች ያቀረቡት የአቤቱታ ነጥብ በክርክሩ ከተረጋገጡት ፍሬ ነገሮች አንጻር በአግባቡ ሊጤን እና ሊመረመር የሚገባው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡በዚህም መሰረት ጉዳዩን በመጀመሪያ  ደረጃ የሚያየው ፍርድ ቤት በፍትሐብሄር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 246፣247 እና 248 ድንጋጌዎች መሰረት ለጉዳዩ ትክክለኛ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችለውን ጭብጥ ይዞ ጉዳዩን በማስረጃ ካጣራ በኃላ ፍርድ በሚሰጥበት ጊዜ በክርክሩ የተያዘው ጭብጥ ምን እንደሆነ፣ጭብጡ እንዴት እንደተወሰነና በአንድ ወይም በሌላ አግባብ የተወሰነው በምን  ምክንያት  እንደሆነ በፍርድ ሀተታው ውስጥ መግለጽ እንዳለበት በቁጥር 182 (1) ስር በአስገዳጅነት ተደንግጎአል፡፡

በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ ክስ ያቀረቡት እና የተከራከሩት በጋብቻ ውሉ መሰረት ክርክር ያስነሳው ቤት የልጃቸው የግል ሀብት መሆኑን በመግለጽ ሲሆን አመልካች በበኩላቸው መልስ  የሰጡት እና የተከራከሩት ከተጠሪ  ልጅ ጋር  በጋብቻ  ውስጥ  በኖሩባቸው ከ1997  ዓ.ም.እስከ   2002


ዓ.ም.ድረስ ባሉት ጊዜያት ቀደም ሲል ከነበሩት ሁለት ክፍል ቤቶች በተጨማሪ ሶስት ክፍል ቤቶችን በጋራ መስራታቸውን በመግለጽ ነው፡፡ከዚህ የግራ ቀኙ የክርክር አቋም በመነሳት በማስረጃ ሊጣራ የሚገባው ተጋቢዎቹ ከጋብቻቸው በኃላ የሰሩት ተጨማሪ ግንባታ አለ ወይስ የለም? የሚል ነጥብ መሆኑን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ለክርክሩ የያዘው ጭብጥ ተገቢነት ያለው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡

በዚህ ጭብጥ ላይ የተሰሙት የግራ ቀኙ ምስክሮች ቃል ሲታይም በአሁኗ አመልካች በኩል የተሰሙት ሁለት ምስክሮች ሟች ከቀድሞ ሚስታቸው ጋር የሰሩትን አንድ ክፍል ቤት አመልካች እና የተጠሪ ልጅ በጋብቻቸው ጊዜ አፍርሰው ቤቱን እንደ አዲስ ሶስት ክፍል አድርገው መስራታቸውን በተመሳሳይ ሁኔታ የገለጹ መሆኑን እንዲሁም በአሁኗ ተጠሪ በኩል ከተሰሙት ሁለት ምስክሮች መካከል 2ኛው ምስክር ቤቱ ጎርፍ የሚገባበት በመሆኑ አጥሩ ሲፈርስ የተጠጋገነ ከመሆኑ ውጪ ከጋብቻው በኃላ የተሰራ ቤት አለመኖሩን በመግለጽ የመሰከሩ ቢሆንም የተጠሪ 1ኛ ምስክር ግን ሟች ከቀድሞ ባለቤታቸው ጋር የሰሩት ዋናውን ቤት መሆኑን እና ከአመልካች ጋር ጋብቻ ከፈጸሙ በኃላ ደግሞ ሁለት ክፍል ቤት እና ኩሽና በጋራ መስራታቸውን በመግለጽ መመስከራቸውን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡ፍርድ ቤቱም ከላይ በተጠቀሰው የፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 182 (1) አስገዳጅ ድንጋጌ መሰረት ውሳኔውን በሚሰጥበት ጊዜ ይህንን የግራ ቀኙን ምስክሮች የምስክርነት ቃል መዝኖ የአንደኛውን ወይም የሌላኛውን ወገን ምስክሮች የምስክርነት ቃል የተቀበለበትን ወይም ያልተቀበለበትን ምክንያት በውሳኔው ላይ ማስፈር የሚጠበቅበት ሆኖ እያለ ቤቱ የሟች የግል ሀብት ነው በማለት ለደረሰበት ድምዳሜ እና ለሰጠው ውሳኔ መሰረት ያደረገው የጋብቻ ውሉን ብቻ መሆኑን የውሳኔው ይዘት ያመለክታል፡፡ ይህም በአንድ በኩል ተጋቢዎቹ ከጋብቻቸው በኃላ የሰሩት ተጨማሪ ግንባታ አለ ወይስ የለም? በሚል ፍርድ ቤቱ በጭብጥነት የያዘው ነጥብ ከግራ ቀኙ የክርክር አቋም አንጻር ተገቢነት ያለው ቢሆንም በሌላ በኩል ግን ቤቱ በጋብቻ ውሉ መሰረት የሟች የግል ሀብት  ነው በማለት የደረሰበት ድማዳሜ እና የሰጠው ውሳኔ ከላይ የተጠቀሰውን ጭብጥ ለማጣራት በተሰሙት የግራ ቀኙ ምስክሮች ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር ውጪ መሆኑን መገንዘብ የሚያስችል ነው፡፡የዚህ ዓይነቱ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ደግሞ የፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 182 (1) አስገዳጅ ድንጋጌን እና በአንድ ክርክር በመዝገቡ ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር ውጪ የሚሰጥ ውሳኔ ተገቢነት የሌለው ስለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 36848 በ11/02/2001 ዓ.ም. እና በሌሎችም መዝገቦች የሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሚቃረን በመሆኑ ሕጋዊ ተቀባይነት ሊሰጠው የሚገባ አይደለም፡፡

በክርክሩ በማስረጃ የተረጋገጠው ፍሬ ነገር ከጋብቻው በፊት የአንደኛው ተጋቢ የግል ሀብት መሆኑ በጋብቻ ውሉ ከተረጋገጠው አንድ ክፍል ዋናው ቤት በተጨማሪ ተጋቢዎቹ በጋብቻቸው ጊዜ ሶስት ተጨማሪ ክፍሎችን መስራታቸው ከሆነ ደግሞ ይህ ሁኔታ በግራ ቀኙ መብትና ግዴታ ላይ የሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት መታየት ይኖርበታል፡፡በመሰረቱ ተጋቢዎች ከጋብቻቸው በፊት በየግል የነበሯቸው ንብረቶች የየግላቸው ሆነው እንደሚቀሩ እና ከጋብቻቸው በኃላ ያፈሯቸው ንብረቶች ግን የጋራቸው እንደሚሆኑ በአዋጅ ቁጥር 213/1992 በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በአንቀጽ 57 እና 62 ድንጋጌዎች ተመልክቷል፡፡በተያዘው ጉዳይ ከጋብቻው በፊት የነበረው እና በጋብቻ ውሉ የአንደኛው ተጋቢ የግል ንብረት ነው ተብሎ የነበረው አንድ ክፍል ዋናው ቤትም ቢሆን በጋብቻው ውስጥ ፈርሶ እንደ አዲስ መሰራቱ እና ኩሽናውን ጨምሮ ሶስት ተጨማሪ ክፍሎች በጋብቻው ውስጥ መሰራታቸው በማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ከጋብቻው በፊት የነበረው ቤት ፈርሶ እንደ አዲስ የተሰራ እና ሶስት ተጨማሪ ክፍሎች የተሰሩ መሆኑ ከተረጋገጠ ደግሞ እነዚህ ስራዎች የተከናወኑት በጋብቻው ውስጥ እስከሆነ እና እነዚህ ተጨማሪ   ስራዎች


የተከናወኑት በሟች የግል ገንዘብ ነው በሚል የቀረበ ክርክር እና ማስረጃ እስከሌለ ድረስ በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 63 (1) መሰረት ክርክር ያስነሳው ቤት የተጋቢዎቹ የጋራ ሀብት ስለመሆኑ የሕግ ግምት የሚወሰድበት ነው፡፡

ሲጠቃለል ከጋብቻው በኃላ ስለተከናወኑት ተጨማሪ ስራዎች በግራ ቀኙ ምስክሮች የተመሰከረውን ፍሬ ነገር በዝምታ አልፎ በጋብቻ ውሉ ላይ ብቻ በማተኮር ክርክር ያስነሳው ቤት ከጋብቻው በፊት የተፈራ የሟች የግል ንብረት ነው በማለት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተሰጥቶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጸናው ውሳኔ በማስረጃ ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር ውጪ የተሰጠ እና መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 ው ሳ ኔ

1. በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 58686 በ02/07/2005 ዓ.ም. ተሰጥቶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 135319 በ22/02/2006 ዓ.ም. በትዕዛዝ የጸናው ውሳኔ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 348  (1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

2. በተራ ቁጥር 1 ከተጠቀሰው ውሳኔ ውስጥ በን/ላ/ክፍለ ከተማ በቀበሌ 09/14 የሚገኘው ቁጥሩ አዲስ የሆነው መኖሪያ ቤት ከጋብቻው በፊት የተፈራ የአቶ ታደሰ የሱፍ የግል ንብረት በመሆኑ አመልካች ቤቱን ለቀው ለተጠሪ ሊያስረክቡ ይገባል በሚል የተሰጠው የውሳኔ ክፍል በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

3. ለክርክሩ ምክንያት የሆነው በን/ላ/ክፍለ ከተማ በቀበሌ 09/14 የሚገኘው ቁጥሩ አዲስ የሆነው መኖሪያ ቤት ሟች አቶ ታደሰ የሱፍ እና አመልካች በጋብቻው ጊዜ ያፈሩት የጋራ ሀብት ነው በማለት ወስነናል፡፡

4. ከላይ ከተጠቀሰው ቤት ውስጥ ግማሹ የአመልካች በጋብቻ ወቅት የተፈራ የጋራ ሀብት፣ቀሪው ግማሽ ደግሞ የተጠሪ የውርስ ሀብት በመሆኑ ግራ ቀኙ የሚቻል ከሆነ በዓይነት፣የማይቻል ከሆነ በስምምነት አንዳቸው ለሌላኛው የዋጋ ግምት ድርሻ ከፍሎ በማስቀረት፣በዚህ የማይስማሙ ከሆነም በሐራጅ እንዲሸጥ ተደርጎ የሽያጩን ገንዘብ እኩል እንዲካፈሉ በማድረግ ሊካፈሉት ይገባል በማለት ወስነናል፡፡

5. ከላይ በተራ ቁጥር 4 የተጠቀሰው የክፍፍል ውሳኔ አፈጻጸም  ጉዳዩ የሚመለከተው የአስተዳደር አካል የቤቱን ሕጋዊነት አስመልክቶ ሊያነሳ የሚችለውን ጥያቄ የሚያስቀር አይሆንም በማለት ወስነናል፡፡

6. በተራ ቁጥር 1 ከተጠቀሰው ውሳኔ ውስጥ የቤት ቁሳቁሶችን እና ከቤቱ ኪራይ  የተገኘውን ገቢ አስመልክቶ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 348 (1) መሰረት ፀንቷል፡፡

7. ጥያቄው ሲቀርብለት ከላይ በተራ ቁጥር 3፣4 እና 5 በተጠቀሰው ውሳኔ መሰረት እንዲያስፈጽም የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ይላክ፡፡

8.  ቁጥሩ 58686 የሆነው መዝገብ ተመላሽ ይደረግ፡፡

9.  የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

10. ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡                              ብ/ግ