75560 Jurisdiction of court/ Jurisdiction of Addis Ababa City court/ marriage certificate

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍ/ቤቶች ጋብቻን በተመለከተ የባልነት ወይም የሚስትነት የምስክር ወረቀት ከመስጠት ባለፈ በማስረጃው ላይ ክርክር ከተነሳበት ወይም የጋብቻ መኖር አለመኖርን ለመወሠን የስረ ነገር ሥልጣን ያልተሠጣቸው ሥለመሆኑ፣

 

አዋጅ ቁጥር 408/1996 አንቀፅ 2

 

አዋጅ ቁጥር 361/1995 አንቀጽ 41/1/ /ሸ/

የሰ/መ/ቁ. 75560

ሐምሌ 26 ቀን 2004 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

አልማው ወሌ ዓሊ መሐመድ ነጋ ዱፊሳ

አዳነ  ንጉሴ

 

አመልካች፡- ወ/ሮ ኪሮስ ገ/ማሪያም - ጠበቃ ዮሴፍ  አእምሮ ቀረቡ ተጠሪ፡-አቶ ገብረ ስላሴ ሃይሌ- ወኪል ወርቅነሽ መንግስቱ ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

              

 

ጉዳዩ የባልነት ማስረጃን መሰረት ያደረገ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአሁኑ አመልካች ባቀረቡት የመቃወም አቤቱታ መነሻ ነው፡፡አመልካች የመቃወም አቤቱታ ሊያቀርቡ የቻሉት የአሁኑ ተጠሪ በስር ፍርድ ቤት የሟች ወ/ሮ ኪሮስ ውቤ ባል ነኝ በማለት በሐሰት የወሰዱት ማስረጃ ያላግባብ ነው በማለት የተወሰደው ማስረጃ እንዲሰረዝላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የስር ፍርድ ቤትም ግራ ቀኙን ከአከራከረና የምስክሮች ቃል ከሰማ በኋላ በተጠሪና በሟች ወ/ሮ ኪሮስ ውቤ መካከል ጋብቻ ስለመፈፀሙ በትዳር ሁኔታ ተረጋግጧል በሚል ምክንያት የአመልካችን አቤቱታ ባለመቀበል ቀድሞ ተጠሪ የሟች ወ/ሮ ኪሮስ ውቤ ናቸው በማለት የሰጠውን ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 360(2) መሰረት በማጽናት ወስኗል፡፡ከዚህም በኋላ አመልካች የይግባኝ ቅሬታቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት  አላገኙም፡፡ ጉዳዩን ለከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበውም ተቀባይነት አላገኙም፡፡የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡የአመልካች ሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የባልነት ጉዳይ አከራካሪ በሆነበት ሁኔታ ጉዳዩ በበታች ፍርድ ቤቶች የታየው ያለስልጣናቸው መሆኑንና የተጠሪ የባልነት ማስረጃ ከመጀመሪያውም የተሰጠው ተገቢ ያልሆነ አቤቱታ ቀርቦና በሕግ አግባብ መቅረብ ያለበት ማስረጃ ሳይቀርብ ነው የሚል ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮም ጉዳዩን የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች ለማየት ስልጣን ያላቸው መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪም ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ተገቢ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡አመልካች በበኩላቸው የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡እንደመረመረውም የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ


ቤቶች ጉዳዩን የማየት የስረ ነገር ዳኝነት ሥልጣን አላቸው? ወይስ የላቸውም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ሊመረመር የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥረ ነገር ሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 361/1995 እና 408/1996 ስር ተመልክቷል፡፡በዚህም መሰረት በአዋጅ ቁጥር 361/1995 እና አዋጅ ቁጥር

408/1996 ከተሰጧቸው ስልጣኖች መካከል የወራሽነት ምስክር ወረቀት መስጠት፣የባልና ሚስትነት፣የሞግዚትነት ማስረጃ መስጠት ይገኙበታል፡፡በዚህ ረገድ የተሻሻለውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 408/1996 አንቀጽ 2 በአዋጅ ቁጥር 361/1995 አንቀጽ 41(1)(ሸ) ስር የተመለከተው ድንጋጌ ሰርዞ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የወራሽነት፣የባልና ሚስትነት እና የሞግዚትነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚቀርብ አቤቱታ ላይ የዳኝነት ሥልጣን ያላቸው መሆኑ ተደንግጓል፡፡የድንጋጌው የእንግሊዝኛው ቅጂም "application for certification of succession,marriage and guardianship."በሚል የተቀመጠ ነው፡፡ከእነዚህ የድንጋጌዎች ይዘት መገንዘብ የሚቻለው የአዲስ አበባ ፍርድ ቤቶች ስለጋብቻ በሚሰጡት ማስረጃ ላይ በሚቀርብ ክርክር የሚኖራቸው የዳኝነት ሥልጣን አድማሱ እስከምን ድረስ መሄድ አለበት? የሚለው ጥያቄ የሚነሳ መሆኑን ነው፡፡በሌላ አገላለጽ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን የባልና ሚስትነት ማስረጃ ለመስጠት ነው ተብሎ የተቀመጠው የሕጉ አገላለፅ ፍርድ ቤቶቹ የባልነት ወይም የሚስትነት ማስረጃ ከሰጡ በኃላ በማስረጃው ተቃውሞ ቢቀርብ እና የተቃውሞው መሰረት የሚሆኑት ምክንያቶች የባልነት ወይም የሚስትነት ማስረጃው የተሰጠው በቤተሰብ ሕጉ ስለጋብቻ መኖር ያለመኖር ሊቀርቡ የሚገባቸው የማስረጃ አይነቶች ሳይቀርቡ ነው፣ጋብቻ ሳይኖር ነው፣የቀረበው አቤቱታ ከሕጉ ስርዓት ውጪ ነው፤ሕጉን በሚጻረር መልኩ ነው የሚል ከሆነ ማስረጃዎች በማስረጃነቱ ከመስጠት ባለፈ በተጠቀሱት ነጥቦች ክርክር እንዲካሄድ በማድረግ ዳኝነት ሊሰጡ ይችላሉ? ወይስ አይችሉም? የሚል ነው፡፡ይህንኑ ጥያቄ ለመመለስ የባልነት ወይም የሚስትነት ማስረጃ ምንነት፣ማስረጃው የሚሰጥበትን ሁኔታ፣የማስረጃውን ይዘት፣አቤቱታው የሚስተናገድበትን ሥርዓት መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡

የጋብቻ ምስክር ወረቀት ስለሚሰጥበት ሁኔታና ስለይዘቱ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግአዋጅ ቁጥር 213/1992 ይደነግጋል፡፡ ይሄው ህግ ለጋብቻ መኖር መቅረብ ያለባቸውን የማስረጃ አይነቶች ቅደም ተከተል እንዲሁም በማስረጃው ሊረጋገጡ ስለሚገባቸውሁኔታዎች አስፍሮ እናገኛለን፡፡ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ መገንዘብ የሚቻለው ፍርድ ቤቱ በሕጉ በተመለከተው አግባብ መረጋገጡን በቂ ነው ብሎ የገመተውን ያህል ማስረጃ ተቀብሎና መዝኖ ጋብቻ መኖር ያለመኖሩን የሚያረጋገጥ መሆኑን፣ጋብቻው አለ ወይም የለም ተብሎ ሊሰጥ የሚችለውም በሕግ የተቀመጠውን መመዘኛ በማሟላታቸው በመለየት ስለሆነ ይህንኑ የሚገልፅ ወይም የሚያሳይ ምክንያት በመስጠት ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን ነው፡፡በአንፃሩ የባልነት ወይም የሚስትነት ማስረጃ መስጠት ግን ከላይ የተመለከቱት ሕጋዊ ክርክሮች በሌሉበት ሁኔታ የሚሰጥ ማስረጃ እንጂ ጋብቻ ስለመኖሩ ያለመኖሩ ክርክር ተደርጎ የግራ ቀኙ ተከራካሪ ወገኖች ማስረጃ በሕጉ አይን ተመዝኖ የሚሰጥ አይደለም፡፡ፍርድ ቤቱ ጥያቄው ሲቀርብ የሚሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕጉ ስለውሳኔ የተቀመጠውን ትርጉም የሚያሟላ ነው ሊባል የሚችል ሳይሆን የባልነት ወይም የሚስትነት የምስክር ወረቀቱን ስለሕጋዊ ማስረጃነቱ የሚያረጋገጥበት ነው፡፡ ይህን አይነት ውሳኔ ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ሊከተለው የሚገባው ስነ ሥርዓት ሲታይም ተከራካሪ ወገን የሌለበት፣አቤቱታ አቅራቢው ብቻ በማስረጃ በተደገፈ አቤቱታ መሰረት ይገባኛል የሚለውን መብት ወይም ጥቅም ትክክለኛነቱን፣ሕጋዊነቱን እንዲረጋገጥለት የሚያቀርብ በመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 305 መሰረት የተፋጠነ ሥርዓት ነው ሊባል የሚገባው ነው፡፡   ስለሆነም


የባልነት ወይም የሚስትነት ማስረጃ ይሰጠኝ አቤቱታ ይዘቱና ፍርድ ቤቱ ሊከተለው  የሚገባው ስነ ሥርዓት ሲታይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የማስረጃ ይሰጠኝ ጥያቄውን ተገቢነቱን፣ ትክክለኛቱንና ሕጋዊነቱን ከማረጋገጥ ባለፈ ጋብቻ አለ ወይስ የለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘው በጉዳዩ ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎችን በመስማት፣ጉዳዩን በማጣራት እና ሌሎች ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ክርክር ሲኖር አቤቱታውን ተቀብሎ ለማስተናገድ የዳኝነት ሥረ ነገር ሥልጣን የሌላቸው መሆኑን ያስገነዝባል፡፡በጉዳዩ ላይ ሚስትነት ወይም ባልነት የለም የሚልና ተቃውሞውን ለማቅረብ መብትና ጥቅም ያለው ወገን ጋብቻው ያለመኖሩንና እና ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች ሕጋዊ ክርክሮችን መሰረት በማድረግ ተቃውሞ በማቅረብ ሕጋዊ መፍትሔ ሊያገኝ የሚገባው ጥያቄውን ወይም አቤቱታውን ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ለማቅረብ እንጂ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች በማቅረብ አይደለም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች በባልነት ወይም የሚስትነት ማስረጃ ወረቀት ላይ ውሳኔ ሰጥተዋል በሚል ምክንያት ብቻ ተቃውሞ ያለው ወገን የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358"ን" መሰረት በማድረግ የተቃውሞ አቤቱታ ሲያቀርብና ፍርድ ቤቶቹም አቤቱታውን ተቀብለው የባልነት ወይም የሚስትነት ማስረጃ ትክክለኛነቱንና ሕጋዊነቱን ከማረጋገጥ ባለፈ ተከራካሪ ወገኖችን በማከራከር ስለጋብቻ መኖር ያለመኖር ላይ ማስረጃ ሳይሆን በጋብቻ ውጤት ላይ የራሱ የሆነ ትርጉም ያለውንና ሊፈፀም የሚችል ውሳኔ ሲሰጡ በተግባር ይስተዋላል፡፡ይሁን እንጂ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 መሰረት የተቃውሞ አቤቱታ የሚቀርበው በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ በተሰጠው የውሳኔ ትርጉም(አንቀፅ 3 ይመልክቷል) መሰረት ሊፈፀም የሚችል ውሳኔ ከተሰጠ እና ውሳኔው የክርክሩ ተካፋይ ያልሆነ ወገን መብትና ጥቅም የሚነካ መሆኑ ሲረጋገጥና አቤቱታው ውሳኔው ከመፈፀሙ በፊት ከቀረበ ነው፡፡የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 አይነተኛ አላማ ማስረጃው ትክክለኛነቱና ሕጋዊነቱ ተረጋግጦ በማስረጃነቱ (Declaratory Judgement) በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ሳይሆን ከላይ እንደተገለፀው ሊፈፀም በሚችል ውሳኔ የክርክሩ ተካፋይ ያልሆነ ወገን መብትና ጥቅምን ማስከበር ነው፡፡በአጠቃላይ የባልነት ወይም የሚስትነት ማስረጃ አቤቱታ ስለሚሰጥበት ሁኔታና ስለይዘቱ እንዲሁም  በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁጥር 358 መሰረት ተቃውሞ የሚቀርብበት ሥርዓት በአንድነት ሲታዩ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ የማስረጃው ይሰጠኝ ጥያቄ /አቤቱታ/ ትክክለኛነቱንና ሕጋዊነቱን በማረጋገጥ ለማስረጃነት ውሳኔ ከመስጠት ባለፈ ማስረጃውን ትክክለኛነቱንና ሕጋዊነቱን የሚቃወም ወገን አቤቱታ ሲያቀርብ ለተቃውሞው መሰረት ሊሆኑ በሚችሉት ጋብቻ የለም፣ተገቢው ማስረጃ አልቀረበም፣የቀረቡት ማስረጃዎችም ሐሰተኛ ናቸው በሚሉት ነጥቦች ላይ ክርክር በመስማት ዳኝነት ለመስጠት በአዋጅ ቁጥር 361/1995"ም" ሆነ የዚሁ አዋጅ ማሻሻያ በሆነው አዋጅ ቁጥር 408/1996 መሰረት ሥልጣን ያልተሰጣቸው ሆኖ አግኝተናል፡፡

ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም ተጠሪ ለአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቤቱታ ሲያቀርቡ መሰረት ያደረጉት ከሟች ወ/ሮ ኪሮስ ጋር በጋብቻ ተሳስረው የነበሩ መሆኑን ጠቅሰው የባልነት ማስረጃ እንዲሰጣቸው ሲሆን ይህ ማስረጃ እንዲሰጣቸው ሲያመለክቱም አቤቱታቸውን በቃለ መሃላ ያስደገፉ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ለተጠሪ በተጠየቁት አግባብ ማስረጃ ከሰጠ በሁዋላ የአሁኗ አመልካች ተጠሪና ሟች ወ/ሮ ኪሮስ ውቤ ባልና ሚስት አይደሉም፣ጥያቄውና ማስረጃው የተሰጠበት አግባብ ሕጋዊ አይደለም የሚል ይዘት ያለው ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ይህ በግልፅ የሚያሳየው የአመልካች የተቃውሞ አቤቱታ ተጠሪ ያገኙት የባልነት ማስረጃ ከማስረጃነቱ ባለፈ ሌሎች የቤተሰብ ሕግ ክርክሮችን የሚያስነሳ መሆኑን ሲሆን ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የከተማው ፍርድ ቤትም የተሻሻለውን የፌዴራሉን የቤተሰብ ሕግ ሁሉ በመጥቀስ ውሳኔ መስጠቱን ከውሳኔው ተመልክተናል፡፡የአዲስ አበባ   ከተማ


ፍርድ ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 361/1995 እና 408/1996 መሰረት ካገኟቸው ሥልጣኖች መካከል ከመሰረታቸው የፌዴራል ጉዳዮች የሆኑት የሚገኙት ሲሆን እነዚህ ጉዳዮች ለእነዚህ ፍርድ ቤቶች ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ተቆርሰው ሲሰጡ በሕግ አውጪው የታሰበው በባሕርያቸው ውስብስብ ያልሆኑ ናቸው በሚል ነው፡፡የጋብቻ መኖር ያለመኖር ውስብስብ ያልሆነ ክርክር የማይቀርብበት ሳይሆን ክርክር ተደርጎበት ውስብስብ የሕግ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥበት ነው፡፡በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የጋብቻ መኖር ያለመኖርን ለመወሰን ሥረ ነገር ስልጣን ያልተሰጣቸው በመሆኑ ጉዳዩ በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች መስተናገዱ ያላግባብ ነው፡፡ተጠሪ ያገኙትን ማስረጃ አመልካች ሊቃወሙት የሚገባቸው ስልጣን ባለው የፌዴራል ፍርድ ቤት ነው፡፡ስለሆነም የአዲስ አበባ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአመልካች የቀረቡት ምክንያቶችን በመመልከት ጉዳዩን ለማስተናገድ ስልጣን የሌለው መሆኑን ገልፆ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 9 እና 231(1(ለ)) መሰረት መዝገቡን መዝጋት ሲገባው ጉዳዩን ማስተናገዱም ሆነ የበላይ ፍርድ ቤቶች ይህንኑ ሳያረጋግጡ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በትእዛዝ ማፅናታቸው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ሁኖ አግኝተናል፡፡በዚህም መሰረት ተከታዩን ወስነናል፡፡

 ው ሣ ኔ

1. በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 961/02 ጥቅምት 16 ቀን

2004 ዓ/ም ተሰጥቶ በከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 17036 ሕዳር 25 ቀን

2004 ዓ/ም፣በከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 17119ታህሳስ 13 ቀን 2004 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት በአብላጫ ድምፅ ተሽሯል፡፡

2. የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የባልነት ወይም የሚስትነት ማስረጃ በተመለከተ የቀረበው ጥያቄ ትክክለኛነቱንና ሕጋዊነቱን በማረጋገጥ በማስረጃነቱ ውሳኔ (Declaratory Judgement) ከመስጠት ውጪ ማስረጃው የተሰጠበትን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 መሰረት የተቃውሞ አቤቱታ መቀበልና ጋብቻ መኖር ያለመኖርን ሌሎች ተያያዥነት ያላቸውን ክርክሮችን ለማስተናገድ የሥረ ነገር ሥልጣን የላቸውም ብለናል፡፡

3. ተጠሪ አለኝ የሚሉትን ማስረጃ አመልካች በተጠሪና በሟች ወ/ሮ ኪሮስ ውቤ ጋር ጋብቻ የላቸውም የሚሉበትን ምክንያት መሰረት አድርገው ሊቃወሙ የሚችሉት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 መሰረት ሳይሆን በሌላ ክስ ሁኖ ስልጣን ባለው በፌዴራሉ ፍርድ ቤት ነው ብለናል፡፡

4.  በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

 

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት

 

 የሃ ሳብ ል ዩነ ት

 

እኔ ስሜ በሶስተኛው ተራ ቁጥር የተጠቀሰው ዳኛ አብላጫው ድምፅ በሰጠው የሕግ ትርጉምና ከደረሰበት መደምደሚያ የማልስማማ በመሆኑ በሀሳብ ተለይቻለሁ፡፡

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የወራሽነት፣ የባልና ሚስትነት የሞግዚትነትና የምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚቀርብ አቤቱታ አከራክረው የመወሰን የዳኝነት ሥልጣን ያላቸው


መሆኑ አዋጅ ቁጥር 361/1995 አንቀጽ 41/ሸ/ ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 408/1996 አንቀጽ 1 በግልፅ ተደንግጓል፡፡

 

የባልና ሚስትነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚቀርብ አቤቱታ፣ ባል ወይም ሚስት ነኝ በማለት አንድ ሰው የሚያቀርበውን ማመልከቻና መግለጫ ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ የባልና ሚስትነት ምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚቀርብ አቤቱታ ማናቸውም ያገባኛል የሚል ሰው ባል ወይም ሚስት አይደለም በማለት የሚያቀርበውን ተቃውሞና ክርክርን የሚጨምር እንደሆነ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ ህጉ አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 1 "የአቤቱታ ፅሁፍ ማለት ከሳሽ የሚጠይቀውን ሁሉ ዘርዝሮ የሚገልፅ ፅሁፍ፣ ተከሳሽ የሚሰጠው የመከላከያ ፅሁፍ፣ የተከሳሽ ከሳሽ የሚያቀርበው ፅሁፍ የይግባኝ ማቅረቢያ ፅሑፍ ወይም በሌላ አይነት ተፅፎ ለፍርድ ቤትና ክስ መነሻ ወይም ለዚሁ መልስ የሚመለከት ማናቸውም ፅሑፍ ነው በማለት የሰጠውን ሰፊ ትርጉም በማየት ለመረዳት ይቻላል፡፡

 

ከአዋጅ ቁጥር 408/1996 አንቀጽ 1 የባልና ሚስትነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚቀርብ አቤቱታ የመዳኘት ሥልጣን የአዲስ አበባ ፍርድ ቤቶች እንደሆነ ሲደነግግ፣ አንዲት ሴት የአንድ ሰው ሚስት መሆኔ ተጣርቶና በማስረጃ ተረጋግጦ ይወሰንልኝ በማለት የምትጠይቀውን የዳኝነት ጥያቄ ወይም አንድ ሰው የአንዲት ሴት ባል መሆኔ ተጣርቶና በማስረጃ ተረጋግጦ ውሳኔ ይሰጥልኝ በማለት በሚያቀርበው የዳኝነት ጥያቄ ላይ ባል ነው የተባለው ሰው ወይም ሚስት ናት የተባለችው ሰው በህይወት ያለች ከሆነ የመከላከያ መልሷንና ማስረጃዋን  እንድታቀርብ በማድረግ፣ ፍሬ ጉዳይ በማጣራት፣ ማስረጃ በመመርመርና በመመዘን በሁለቱ ተከራካሪዎች መካከል ህጋዊ ዕውቅና ያለው ጋብቻ መኖሩን ወይም አለመኖሩን የመወሰን ሙሉ ሥልጣን ያላቸው መሆኑን የሚያጠቃልል ነው፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪ የባልነት ወይም ሚስትነት የምስክር ወረቀት እንዲሰጥና አቤቱታ የቀረበው አንደኛው ወገን ላይ የመጥፋት ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ወይም አንደኛው ወገን ከሞተ በኋላ እንደሆነ፣ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 መሰረት በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው የመከራከር መብት ያላቸው ሰዎች የሚያቀርቡትን ክርክርና የመከላከያ ማስረጃ በተሟላ ሁኔታ በመስማት ተገቢውን ውሳኔ የመስጠት ሥልጣንን የሚያካትት ስለመሆኑ የአዋጅ ቁጥር 408/1996 አንቀጽ 1 ድንጋጌ ከፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 41 ድንጋጌ ጋር በማጣመር ለመገንዘብ ይቻላል፡፡

 

የአዲስ አበባ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ባል ወይም ሚስት መሆናቸውን የሚያረጋገጥ ማስረጃ ከመስጠታቸው በፊት፣ ተገቢውን የፍሬ ጉዳይ ማጣራት በማድረግ፣ አስፈላጊም በሆነ ጊዜ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 145/1/ እና በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 264 መሠረት ተጨማሪ የሰነድና የሰው ማስረጃ በማስቀረብ ፣ ውሣኔ የመስጠት ኃላፊነት ያለባቸው የከተማው ፍርድ ሰጭ ተቋማት መሆናቸውን በአዋጅ ቁጥር 361/1995 አንቀፅ 39 ተደንግጓል፡፡

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ባል መሆኑ ወይም ሚስት መሆኗ ተጣርቶና ተረጋግጦ ማስረጃ እንዲሰጣቸው የቀረቡ የዳኝነት ጥያቄዎችን ፣ ለጉዳዩ መልስ መስጠት ያለበት

- የትዳር አጋር /ካለ/ች/ መልስ እንዲሰጡና መከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ በማድረግ፣ በራሳቸው አነሳሽነት ተጨማሪ የሰውና የፅሑፍ ማስረጃ በማስቀረብ ወይም በጉዳዩ ጣልቃ ገብ ተከራካሪ


ወገን ሊሆን የሚችል ሰው ሲቀርብ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 መሠረት የጣልቃገቡን ክርክርና ማስረጃ በመስማት በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ጋብቻ መኖሩን ወይም በጋብቻ አለመኖሩን በማረጋገጥ የሰጡት ውሣኔ መብቴንና ጥቅሜን ይነካብኛል፤ በክርክሩ ተካፋይ መሆን ነበረብኝ የሚለው ሰው በክርክሩ ተካፋይ ያልሆነ ሰው ቀደም ብሎ የተሰጠውን ውሣኔ ለማሰረዝ የፍርድ መቃወሚያ የሚያቀርበው ቀደም ብሎ ጋብቻ መኖሩን ወይም አለመኖሩን አከራክሮና አጣርቶ ለወሰነው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤት እንደሆነ የአዋጅ ቁጥር 408/1996 አንቀፅ 1 ድንጋጌና የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 358 እና በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 359 ንዑስ አንቀፅ 1 “መቃወሚያው የሚቀርበው በአቤቱታ አቀራረብ መልክ ሆኖ ተገቢው ዳኝነት ተከፍሎበት፣ መቃወሚያ ያቀረበለትን ለወሰነው ፍርድ ቤት ነው” በማለት በግልፅ የደነገገውን ድንጋጌ ይዘት መንፈስና ዓላማ በማገናዘብ ለመረዳት ይቻላል፡፡

 

ስለሆነም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የባል ወይም ሚስት ስለመሆን የቀረበላቸውን አቤቱታ ተቀብለው አጣርተው በሰጡት ውሣኔ ላይ የሚቀርብን  የፍርድ መቃወሚያ አቤቱታ ተቀብሎ የማስተናገድ ሙሉ የዳኝነት ሥልጣን አላቸው፡፡ አብላጫው ድምፅ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ጋብቻ አለ ወይም የለም በሚለው ጭብጥ ላይ መከራከር ያለባቸውን ሰዎች ክርክር በመስማት አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ ውሣኔ እንደማይሰጡና ሥልጣን እንደሌላቸው በመቁጠር፣ የፍርድ መቃወሚያው መቅረብ ያለበት ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች መሆን አለበት በማለት የሰጠው ትርጉም የአዋጅ ቁጥር 408/96 አንቀፅ 1፣ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር አንቀጽ 80/1/፣ አንቀጽ 41 እና አንቀጽ 358፣ አንቀጽ 359/1/፣ ድንጋጌዎች ይዘትና ተግባራዊ ተፈፃሚነት መሠረት ያደረገ ነው የሚል እምነት የሌለኝ በመሆኑ፣ በጉዳዩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የፍርድ መቃወሚያውን በመቀበል የማከራከርና የመወሰን የዳኝነት ሥልጣን አላቸው፡፡ ስለሆነም ጉዳዩ ጭብጥ በተያዘበት በዳኝነት ሥልጣንን መሠረት በማድረግ ሳይሆን የአዲስ አበባ ፍርድ ቤቶች የተጠሪን የፍርድ መቃወሚያ በመቀበል የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ወይስ አይደለም? በሚለው ነጥብ ላይ ግራ ቀኙን በማከራከር ውሣኔ ሊሰጠው ይገባ ነበር በማለት በሀሳብ ተለይቻለሁ፡፡

 

 

የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡