-የማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ ውልን በተመለከተ እዳው እንዲከፈል በተወሠነ ጊዜ ሳይከፈል የቀረ እንደሆነ ገንዘብ ጠያቂው የመያዣ መብት ያገኘበትን የማይንቀሳቀስ ንብረት ይወስዳል በሚል የተደረገ ውል ፈራሽ ስለመሆኑ፣
-የብድር ውልን በተመለከተ ተዋዋዬች ወለዱ በወር እንዲታሠብ የሚዋዋሉት ውል ፈራሽ ስለመሆኑና በህጉ መሠረት ወለድ ሊታሠብ የሚችለው በዓመት ሥለመሆኑ፣
የፍ/ህ/ቁ. 3060/1/፣ 1711 እና 2479/1/
የሰ/መ/ቁ.102711 ህዳር 10 ቀን 2007 ዓ.ም
ዳኞች፡- አልማው ወሌ
ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመስል
አመልካች፡- ፋንታዬ ፍሰሐ የቀረበ የለም ተጠሪ፡- አቶ ደጀኔ ማርዬ የቀረበ የለም
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
ጉዳዩ በግለሰቦች መካከል በተደረገ የብድር ገንዘብ ውልን መሰረት አድርጐ የቀረበውን የቤት ልረከብ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የጀመረው በሰሜን ወሎ አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በላስታ ወረዳ ፍርድ ቤት የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡ ተጠሪ ከአሁኑ አመልካች ጋር ጥር 15 ቀን 2000 ዓ.ም ባደረጉት የብድር ውል በወር አምስት በመቶ ወለድ ሂሳብ የሚታሰብ ሁኖ ብር 8000.00 (ስምንት ሺህ ብር) ለአሁኑ አመልካች እንደአበደሯቸው፣ የብድሩ መመለሻ ጊዜም ጥር 14 ቀን 2001 ዓ.ም መሆኑን፣ በዚህ ጊዜ አመልካች የብድር ገንዘቡን ካልመለሱ በላስታ ወረዳ ላሊበላ ከተማ 01 ቀበሌ ልዩ ስሙ ሸብጽ ከተባለው ቦታ የሚገኘውንና በ200 ካ/ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ የሰፈረውን ቆርቆሮ ቤትና ባህርዛፍ ተክል አመልካች ለተጠሪ ሊያስረክቧቸው መስማማታቸውን በውሉ በተመለከተው የጊዜ ገደብና ወለድ ስሌት መሰረት በድምሩ ብር 9600.00 (ዘጠኝ ሺህ ስድስት መቶ ብር) አመልካች ያለመመለሳቸውን ዘርዝረው አመልካች በውሉ መሰረት ንብረቱን እንዲያስረክቧቸው ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካች ፍርድ ቤት ቀርቦ በሰጡት መልስም ከተጠሪ ጋር ለክሱ መሰረት የሆነውን ውል ማድረጋቸውን በማመን ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ውሉን አምነዋል በማለትና የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 242 ድንጋጌን በዋቢነት ጠቅሶ አመልካች ለክሱ መሰረት የሆነውን ቆርቆሮ ቤትና ባህርዛፍ ተክል ለተጠሪ ሊያስረክቡ ይገባል በማለት የወሰነ ሲሆን በዚህ ውሳኔ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለሰሜን ወሎ አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት ያጡ ሲሆን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበውም በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት የለም ተብሎ መዝገቡ ተዘግቶባቸዋል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡
የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ከአመልካች ጋር በተደረገው ውል የገንዘብ ብድሩ የተደረገ መሆኑን ሳይክዱ የመያዣውን ንብረት በተመለከተ ግን የባህርዛፍ ተክል ብቻ መያዣ አድርገው የተስማሙ ሁኖ እያለ ተጠሪ የአመልካችን መሃይምነት በመጠቀም የአመልካች መኖሪያ ቤት ለመያዣነት እንደተሰጠ አድርገው በውሉ ላይ አስፍረው መገኘታቸውንና ለብር 9600.00 የብድር ገንዘብ ግምቱ ከብር 150.000.00 (አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ) በላይ የሆነውን መኖሪያ ቤታቸውን እንዲያስረክቡ መወሰኑ ጉዳዩ በአግባቡ ባልተጠራበትና ሕጉን መሰረት ሳያደርግ መሆኑን ዘርዝረው በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ እንዲታረምላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታቸው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጐላቸው ቀርበውም የአመልካች የሰበር አቤቱታ በሕጉ በተመለከተው የጊዜ ገደብ ያለመቅረቡን፣ አመልካች በስር ፍርድ ቤት ክሱን ሳይክዱ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት የንብረቱን ግምትና የመያዣውን አይነት መሰረት አድርገው ያቀረቡት ክርክር ሥነ- ሥርዓቱን መሰረት አድርጐ ያልቀረበ መሆኑን ዘርዝረው በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት የለበትም ተብሎ ሊጸና ይገባል በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አመልካችም የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተጠቀሰው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም በዚህ ችሎት እልባት ሊያገኙ የሚገባቸው ጭብጦች፡-
1. የአመልካች የሰበር አቤቱታ በሕጉ በተመለከተው የጊዜ ገደብ የቀረበ ነው ወይስ አይደለም?
2. አመልካች ለተጠሪ ቤቱንና የባህር ዛፍ ተክል ሊያስረክቡ ይገባል ተብሎ መወሰኑ ሕጋዊ ነው ወይስ አይደለም የሚሉት ናቸው፡፡
የ መጀ መሪያ ውን ጭብጥ በተመ ለከተ ፡- አንድ የመጨረሻ ፍርድ ባገኘ ጉዳይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት የሚል ወገን ለዚህ ችሎት የሰበር አቤቱታውን ማቅረብ ያለበት በአዋጅ ቁጥር 25/1998 አንቀጽ 22(4) ባተመለከተው አግባብ በዘጠና ቀናት ውስጥ መሆኑን ሕጉ ያሳያል፡፡ በተያዘው ጉዳይ አመልካች የክልሉ ፍርድ ቤቶች የሰጡት የመጨረሻ ፍርድ በመ/ቁጥር 03- 08770 ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ/ም መሰጠቱን የሚያሳይ የትዕዛዝ ግልባጭ አያይዘው ያቀረቡ ሲሆን ለዚህ ችሎት የሰበር አቤቱታቸውን ያቀረቡት ደግሞ ሐምሌ 03 ቀን 2006 ዓ.ም ነው፡፡ ይህም የሰበር አቤቱታው በሕጉ የተመለከተው የዘጠና ቀናት የጊዜ ገደብ ከማለፉ በፊት የቀረበ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ ተጠሪ በጉዳዩ ላይ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 28950 መጋቢት 18 ቀን 2006 ዓ.ም ነው ውሳኔ የሰጠው በማለት የአመልካችን የሰበር አቤቱታ አቀራረብ ለመቃወም ያቀረቡት ምክንያት የክርክሩን ሂደት ያላገናዘበ በመሆኑ አልተቀበልነውም፡፡
ሁ ለተ ኛ ውን ጭብጥ በተመለ ከተ ፡- ከስር ጀምሮ ከተደረገው ክርክር መገንዘብ እንደሚቻለው አመልካች ከተጠሪ ገንዘብ ሲበደሩ ለገንዘቡም አመላለስ አመልካች ያላቸውን ቤትና ባህርዛፍ በመያዣ ለተጠሪ መስጠታቸውን ነው፡፡ ሆኖም መያዣ ውሉ በማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ላይ አለመመዝገቡን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ በማናቸውም ዓይነት ሰነድ ላይ የተመሰረተ ቢሆን ከተፃፈበት ቀን አንስቶ የማይነቀሳቀሰው ንብረት በሚገኝበት አገር ባለው በማይንቀሳቀስ ርስት መዝገብ ካልተፃፈ በቀር በማንኛውንም ዓይነት ውጤት እንደማያስገኝ በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 3052 ስር በማያሻማ ሁኔታ ተደንግጐ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ህጉ
በግልጽ የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚመሰረተው መያዣ መመዝገብ እንዳለበት የደነገገውን አለመከተል የመያዣው አመሰራረት ጉድለት ያለበት መሆኑን ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል በመያዣ ውሉም አመልካች የተበደሩትን ገንዘብ እስከ ጥር 14 ቀን 2001 ዓ/ም ባይመልሱ ተጠሪ በመያዣነት የያዙትን ቤትና ባህርዛፍ እንደሚረከቡ በግልጽ ተዋውለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ውሉ በህጉ አግባብ የተደረገ ሆኖ አላገኘንም፡፡ ምክንያቱም በፍ/ህ/ቁ 3060/1/ በተደነገገው መሰረት ዕዳው እንዲከፈል በተወሰነበት ጊዜ ሳይከፈል የቀረ እንደሆነ ገንዘብ ጠያቂው የመያዣ መብት ያገኘበትን የማይንቀሳቀስ ንብረት ይወስዳል በሚል የተደረገ ውል ፈራሽ ስለመሆኑ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ የዚህ ድንጋጌ አይነተኛ አላማ ሰዎች ለጊዜው የገጠማቸውን የገንዘብ ወይም ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማቃለል ሲሉ ተገቢውን መደራደር አድርገውና ነፃ የመዋዋል መብታቸውን ተጠቅመው ወደ ግዴታው በነፃ ፍላጎታቸው ይገባሉ ተብሎ ስለማይታሰብ በዚህ ሁኔታ ውሉ ተፈጽሞ ሲገኝ ሕጉ ለስምምነቱ ጥበቃ ባለማድረግ የተዋዋይ ወገኖችን የንብረት መብት ለመጠበቅ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለሆነም የበታች ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ከዚህ ድንጋጌ መሰረታዊ አላማ በማየት የተጠሪን የአመልካች ቤትና ባህር ዛፍ ልረከብ ጥያቄን ውድቅ ማድረግ ሲገባቸው አመልካች አምነዋል በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተናል፡፡
ቀጥሎ መታየት ያለበት የህግ ነጥብ ተጠሪ ያላቸው መፍትሔ ምንድነው? የሚለው ነው፡፡ በአመልካችና በተጠሪ መካከል የገንዘብ ብድር ውል መደረጉ የተካደ ፍሬ ነገር አይደለም ፡፡ አመልካች ከተጠሪ ብር 8000,00 (ስምንት ሺህ) ተበድረው ወስደው በውሉ በተመለከተው የጊዜ ገደብ አልመለሱም፡፡ በመሆኑም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1731፣በፍ/ብ/ህ/ቁ.2471 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሰረት አመልካች ለተጠሪ የተበደሩትን ገንዘብ መመለስ ግዴታ አለባቸው፡፡አመልካች ይህንኑ ገንዘብ መመለስ ያለባቸው ከምን ያህል ወለድ ጋር ነው የሚለውን ስንመለከትም ወለድን በተመለከተ ገዥው መርህ በፍ/ብ/ህ/ቁ.2478 የተቀመጠው ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌው ተበዳሪው ወለድ እንዲከፍል የውሉ ቃል ካልሆነ በቀር ለተበዳሪው ወለድ መክፈል የለበትም ተብሎ አስገዳጅነት ባለው ሁኔታ ተደንግጓል፡፡ ስለዚህ ወለድ የሚከፈለው በውሉ ወለድ ይከፈላል የሚል ቃል ሲኖር መሆኑን ድንጋጌው ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ ተዋዋዬች በወለድ የሚከፈለውን ገንዘብ በዓመት ከመቶ አስራ ሁለት በላይ እንዲሆን ለመዋዋል እንደማይችሉ የፍ/ብ/ህ/ቁ. 2479(1) ድንጋጌ በኃይለ ቃል አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም ተዋዋይ ወገኖች በገንዘብ ብድር ወለድን ገልጸው መስማማት እንደሚችሉና መጠኑ ግን በአመት ከመቶ አስራ ሁለት በላይ ሊሆን አይችሉም፡፡ ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስ አመልካችና ተጠሪ ባደረጉት የውል ስምምነት ወለድ ለመክፈል ስምምነት የተደረገ ቢሆኑም የወለዱ መጠን ግን በወር ከመቶ አምስት ሁኖ የሚታሰበውም በወር መሆኑን በግልጽ ስምምነቱ እንደሚያሳይ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ህጉ ለብድር ገንዘብ ሊከፈል የሚችል የወለድ መጠን በአመት ከመቶ አስራ ሁለት ነው በማለት ከደነገገው ጣሪያ በላይ ስምምነት መደረጉን ነው፡፡ ህጉ ወለድ በአመት ጊዜ እንዲታሰብ እንጂ በወር ጊዜ እንዲታሰብ አልፈቀደም፡፡ ስለሆነም አመልካች በወር አምስት ከመቶ ወለድ እየከፈሉ የብድር ገንዘቡን ለመመለስ ያደረጉት ስምምነት ከፍ/ብ/ህ/ቁ. 1711 እና 2479(1) ድንጋጌዎች አንጻር ሲታይ በህግ ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ አለመሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይም አመልካች ለተጠሪም በወር አምስት በመቶ እየታሰበ እንዲከፍሉ የሚገደዱበት የህግ አግባብ አላገኘንም ፡፡ ሆኖም አመልካች የብድር ገንዘቡን በጊዜ ገደቡ ያልመለሱ በመሆኑ በአመት የሚታሰበው ህጋዊ ወለድን (9%) ለተጠሪ የማይከፈሉበትን አግባብ ግን አላገኘንም፡፡ ሲጠቃለልም
የስር ፍርድ ቤቶች የመያዣ ውሉ ህጋዊ አድርገው በሰጡት ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ ህግ ስህተት የተፈፀመበት ሁኖ ስላገኘን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡
ው ሳ ኔ
1. የላስታ ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 00256 በ10/07/2002 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ፍርድ፣ የሰሜን ወሎ አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 12151 ሰኔ 25 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ እንዲሁም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 03-08770 ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 348/1/ መሠረት ተሻሽለዋል፡፡
2. አመልካች እና ተጠሪ የመሰረቱት የማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ ውል ሕጋዊ ስላልሆነ ተጠሪ ቤትና ባህርዛፍ ሊረከቡ አይገባም ብለናል፡፡
3. አመልካች ለተጠሪ ሊከፍሉ የሚገባው ዋናውን የብድር ገንዘብ ብር 8000.00 (ስምንት ሺህ) ገንዘብ መመለስ ከነበረበት ከጥር 14 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ ተከፍሎ እስከሚያልቅ ድረስ ከሚታሰብ ህጋዊ ወለድ (9%) ነው ብለናል፡፡
4. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡
መዝገቡ የተዘጋ ስለሆነ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡
እ/ተ