103704 contract law/ rent/ government houses/ sub leting

አንድ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነ ሰው ከመንግስት የተከራየውን ቤት ለሌላ ሰው አከራይቶ መጠቀምየሚችለው በመመሪያው የተመለከቱት ምክንያቶች ተጣምረው የተገኙ እንደሆነ ስለመሆኑ፡-

 

መመሪያ ቁጥር 3/2004 አንቀጽ 6 መመሪያ ቁጥር 4/2004 አንቀጽ 12

 

የሰ/መ/ቁ. 103704 ጥር 20/ቀን 2007ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

ዓሊ መሀመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኸሊት ይመሰል

 

አመልካች፡- -------ቀረቡ

ተጠሪ፡- --------ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ  ር ድ

ይህ ጉዳይ የተጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን አመልካች ተከሳሽ ተጠሪ ከሳሽ ነበሩ፡፡ ተጠሪ ባቀረቡት ክስ በአራዳ ክ/ከተማ ወረዳ 2 ቤት.ቁ 1314 (ለ)የሆነውን የመንግስት ቤት አመልካች የተከራየውን ንግድ ቤት ለሶስት በመሸንሸን አንዱን በ8000 ብር አከራይቶኝ ሙዝ የመሸጥ ስራ እየሰራሁበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በመመሪያ ቁ.3/2004 መሰረት የከተማው ግብረ ሀይል ተጠሪ አንዱን ክፍል በመያዝ  ለአመልካች አንደኛውን ክፍል በመክፈል እንዲሰጠኝ ተወስኗል፤ ሆኖም የስር አንደኛ ተከሣሽ እኔ በሌለሁበት ዕቃዬን የታሽገውን ቤት በውስጡ ያለውን ንብረት ተጠሪ እንዲጠቀምበት አድርጓል ፤ንብረቴንም እየተጠቀመበት ነው፡፡ ቤቱንም ወደ መኖሪያ ቤት በመቀየር ይዟል ንብረቴን መረከብ እና የተቋረጠብኝ ገቢን ማስከፈል አልቻልኩም ስለዚህ የንብረት ግምት 4000 እና የተቋረጠ ገቢ ተከፍሎኝ የንግድ ቤቱን ያስረክቡኝ በማለት ጠይቋል፡፡ አመልካች ባቀረቡት መልስ ለተጠሪ ቤት ሸንሽኜ በ8000 አላከራየውም የሀሰት ክስ ነው፡፡ በመመሪያ ቁ.3/2004 መሰረት የኪራይ ውሉ ከእርሳቸው ጋር እንድቀጥል ጉዳዩን የሚመለከተው አካልም የተሳሳተ ግንዛቤ ውስጥ በመክተት ቢጠየቅም አመልካች ለማስፈጸም የተዋቀረውን ግብረሀይል ከቫይረሱ ጋራ መኖሬን የሚያስረዳ ማስረጃ በማቅረቤ የኪራይ ውሉን ከእኔ ጋርእንዲቀጥል ተደርጓል፤ በተጨማሪም ሌላ ገቢ የሌለኝና ወረዳው የወሰነልኝ በመሆኑ ቤቱን ለተጠሪ ላስረክብ አይገባም ፣ ቤት ውስጥ የነበረውን ንብረት ወይም ግምት እና ያጣሁትን ገቢ ይከፈለኝ ለተባለው ማስረጃ ያልቀረበበት በመሆኑ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲል መልሱን ሰጥቷል ፡፡ ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን በማከራከር አመልካች የኤች አይ ቪ ታማሚ በመሆናቸው ብቻ በመመሪያው ልዩ ድንጋጌ ተጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም፤ በንግድ ቤቱ ቁጥር 1314 በአንደኛው ክፍል እየሰሩበት ገቢ በማግኘት ላይ መሆናቸውን በማረጋገጥ ተጠሪ የአከራካሪውን ቤት አንዱን ክፍል ሊያገኙ ይገባል በማለት ወስኗል፡፡ ሌላውን የንብረት ግምትና የታጣ ገቢ ጥያቄ በማስረጃ አልተረጋገጠም ሲል ውድቅ አድርጎታል ፡፡ በቀጣይነት ጉዳዩን በይግባኝ ያዩት ፍርድ ቤቶችም የስር ውሳኔ የሚነቀፍ አይደለም በማለት አጽንቶታል፡፡

የአመልካች አቤቱታም የቀረበው ይህንኑ ውሳኔ ለማሳረም ነው፡፡ አመልካች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ ቅሬታቸውን ሲገልጹ ፡- በመመሪያ ቁ. 3/2004 መሰረት የኤች.አይ.ቪ ታማሚ እና  ሌላ


ገቢ የሌለኝ መሆኔን አረጋግጫለሁ፤1314(ሀ)(ለ) ሆኖ (ሀ) ለመኖሪያ እየተጠቀምኩበት የትኛውን እንደምካፈል እንኳ አልተለየም ፤በአጠቃላይ ሌላ የገቢ ምንጭ እንዳለኝ የቀረበ ማስረጃ ሳይኖር የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ ሊታረም ይገባል በማለት ጠይቀዋል፡፡

በዚህ መሰረት ችሎቱም አመልካች ኤች አይ ቪ ታማሚ እና የገቢ ምንጭ የለኝም ሲሉ ያነሱት ጥያቄ ውድቅ መሆኑን ከመመሪያ ቁ. 3/2004 እና 4/2002 አንቀጽ 6 መሰረት ለማጣራት በጭብጥነት በመያዝ የግራቀኙን መልስና የመልስ መልስ በጽሑፍ በማቀባበል ተከራክረዋል ፡፡ ተጠሪ በሰበር አቤቱታቸው የሚከራከሩት አመልካች የቤት ቁ.1314ን ለመኖሪያነት ከተከራዩ በኃላ ሀ፣ለ፣ሐ በማለት ለተጠሪ 1314(ለ)”ን” አከራይቶኝ ለራሳቸውም ሲሰሩ ነበር ስለዚህ በመመሪያው ቁ.6 አንፃር ጠቅላላውን ያከራዩ ሳይሆን በሌላኛው ቤት ሲነግዱና የገቢ ምንጫቸው ያደረጉት በመሆኑ ኤች አይ ቪ ታማሚ በመሆናቸው ብቻ ተጠቃሚ ሊሆኑ አይገባም ተብሎ አመልካች የያዙትን እንዲሰሩበት ተደርጎ እኔም በተከራየሁት ተጠቃሚ እንድሆን መወሰኑ ሊጸና ይገባዋል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ አመልካች በበኩላቸው በሽተኛ መሆኔ አልተካደም በይዞታዬ ስር አድርጌ ከምጠቀምበት ንግድ ቤት በቀር ሌላ የገቢ ምንጭ የለኝም ፣በመሆኑም ውሳኔው ሊሻር ይገባዋል በማለት ክርክራቸውን አጠናክረዋል ፡፡

በአጠቃላይ የክርክሩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተጠቀሰው ሲሆን እኛም የግራቀኙን ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔና አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች አንጻር መርምረናል ፤ በዚህ መሰረት ከተያዘው ጭብጥ በመነሳት እንዳየነው ከተጠቃሾቹ መመሪያዎች አንጻር ልዩ ተጠቃሚ ለመሆን መመሪያ 3/2004 እና ቁ.4/2004 የኤች አይ ቪ ታማሚን አስመልክቶ የተለያየ ድንጋጌ አይታይባቸውም ፡፡ አንድነታቸው ጎልቶ ከመታየቱ በቀር የመመሪያ ቁ.3 አንቀፅ 6 እና መመሪያ ቁ. 4/2004 አንቀጽ 12 የሚሉት ከመንግስት የተከራየው ሰው የኤች አይ.ቪ ታማሚ ሆኖ እና ሌላ የገቢ ምንጭ ሳይኖረው እና ሲጠቀምበት የነበረውን ቤት አከራይቶ ከተገኘ ይህንኑ አረጋግጦ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል በተያዘው ጉዳይ በተጠቃሹ ቤት ቁ.1314 “ን“ አስመልክቶ አመልካች ሸንሸኖ ለተጠሪ አከራይቶና የቀረውን ክፋይ አመልካች ሲጠቀሙበት የነበረ መሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ በስር ፍርድ ቤቶች የተረጋገጠ እውነታ ነው፡፤ ይህ ከሆነ ደግሞ አመልካች በአንደኛው ክፍል ቤት ላይ እየነገዱ መሆናቸውን ሳይክዱ ከዚህ የተለየ ሌላ የገቢ ምንጭ የለኝም ያለኝ ለመሆኑም አልተረጋገጠም በማለት የሚያቀርቡት ክርክር መመሪያውን ያላገናዘበ ነው፡፡ በመሆኑም አመልካች ይዘውት ባሉት ክፍል ተከራይነታቸው ሲቀጥል ተጠሪም የአንደኛውን ክፍል ሊያገኙ ይገባል መባሉን ይህ ችሎትም የሚቀበለው ይሆናል ፡፡

በመጨረሻም ጉዳዩን ያዩት የአዲስ አበባ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና የይግባኝ ሰሚው አመልካች ሌላ የገቢ ምንጭ ያላቸው መሆኑን በማረጋገጥ የመመሪያው ልዩ ተጠቃሚ ሊሆኑ አይገባም በማለት የደረሱበት መደምደሚያ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት አልተቻለም ፡፡ በመሆኑም ተከታዩ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 ው  ሳ ኔ

 

1. በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ.ቁ 06479 በ 03/7/06 ዓ.ም ተሰጥቶ በከተማው ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በመ.ቁ.21839 በቀን 29/8/06 እና በከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት  በመ.ቁ.22278 በሀምሌ 11 ቀን /2006 ዓ/ም የፀናው ውሳኔ ጸንቷል፡፡


2. አመልካች የገቢ ምንጭ ስላላቸው የኤች.አይ.ቪታማሚ በመሆናቸው የመመሪያው ልዩ ተጠቃሚ ሊሆኑ አይገባም መባሉ በአግባቡ ነው ብለናል፡፡

3.  ግራቀኙ የወጪ ኪሳራቸውን ይቻቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ውሳኔ ስላገኘ ተዘግቷል፡፡

 

 ት ዕ ዛ ዝ

በነሀሴ 08 ቀን 2006 ዓ.ም በዚህ ችሎት ተሰጥቶ የነበረው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡