96858 contract law/ rent/ rent increase

አንድ ቤት የተከራየ ሠው የኪራይ ዘመኑ ሲያልቅ አከራዩ    ኪራዮን መጨመሩን ማስጠንቀቂያ ከሠጠውና ተከራዩም ዝም ብሎ ቤቱን መጠቀም ከቀጠለአዲሱን የኪራይ ተመን ተከራዩ እንደተቀበለው የሚቆጠር ስለመሆኑ፣

 

 

የፍ/ህ/ቁ.  1684፣ 2952/2/

//.96858 ቀን 26/03/2007 ዓ/ም

ዳኞች፡-  አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- ወ/ሮ አብቢልክሽ ገለታ - ቀረቡ ተጠሪ፡- ዶ/ር ትግስት ቦርጋ - ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የኪራይ ገንዘብ ይከፈለኝ ጥያቄን መሰረት ያደረገ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአሁኑ ተጠሪ በአሁኑ አመልካች ላይ በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡ የተጠሪ ክስ መጋቢት 10 ቀን 2004 ዓ/ም የተጻፈ ሆኖ ይዘቱም ህዳር 19 ቀን 2003 ዓ/ም በተደረገ የኪራይ ውል አመልካች /የስር ተከሳሽ/ የተጠሪ /የስር ከሳሽ/ የሆነውን ንብረት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ 522 የሆነ መኖሪያ ቤት በየወሩ ብር 2000.00 /ሁለት ሺህ ብር/ እየከፈሉ ለሶስት ወር ተጠቅመው ሊለቁና የተጠቀሙበትን የውሃና የመብራት ወጪ ከፍለው ቤቱን ለማስረከብ ግዴታ የገቡ መሆኑን ገልጸውና በግዴታው መሰረት ቤቱን ለማስረከብ ፈቃደኛ ያለመሆናቸውን፣ በዚህም ምክንያት ተጠሪ በህጋዊ ወኪላቸው በኩል ለአመልካች ታህሳስ 19 ቀን 2004 ዓ/ም ቤቱን አመልካች እንዲለቁ፣ የማይለቁ ከሆነ ደግሞ በየወሩ ብር 5000.00 /አምስት ሺህ ብር/ እንዲከፍሉ ማስጠንቀቂያ የሰጧቸው ቢሆንም ቤቱን ያልለቀቁላቸው መሆኑን ዘርዝረው  አመልካች ያለባቸውን የሁለት ወር ከአስር ቀናት ውዝፍ ኪራይ ብር 13,499.00 እንዲከፍሉና ቤቱን እንዲያስረክቧቸው፣ ቤቱን እስከሚያስረክቡ ድረስ ያለውን ኪራይም እንዲከፍሉ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የአሁኗ አመልካች ለክሱ በሰጡት መልስም ህዳር 19 ቀን 2003 ዓ/ም የተደረገው የኪራይ ውል መኖሩን ሳይክዱ የቤቱን የኪራይ መጠን ብር 5000.00 ስለመሆኑ ተሰጠ የተባለውን ማስጠንቀቂያ ግን ከተጠሪ ህጋዊ ወኪል ያልተሰጣቸውና አስገዳጅነት የሌለው መሆኑን ዘርዝረው ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማና ለአመልካች ታህሳስ 19 ቀን 2004 ዓ/ም ተሰጠ የተባለው ማስጠንቀቂያ በተጠሪ ህጋዊ ወኪል የተሰጠ መሆን ያለመሆኑን ከአጣራ በኃላ ጉዳዩን መርምሮ ማስጠንቀቂያ ለአመልካች ሲሰጥ የተጠሪ ጠበቃ ህጋዊ ውክልና ነበራቸው ባይባልም አመልካች የተጠሪ ፍላጎት መሆኑን ያወቁ መሆኑ መረጋገጡን ደምድሞ እና ከታህሳስ 19 ቀን 2004 ዓ/ም ጀምሮ ያለው ግንኙነት ላልተወሰነ ጊዜ እንደታደሰ የሚቆጠር መሆኑን


በፍ/ብ/ህ/ቁ.2968(1) መደንገጉን ፣ በአከራይ ለተከራይ በፈለገው ጊዜ ቤቱን የማስለቀቅ ህጋዊ መብት ያለው መሆኑ በህጉ የተጠበቀለት መብት መሆኑ በፍ/ብ/ህ/ቁ.2966 የተደነገገ መሆኑ በዋቢነት ጠቅሶ አመልካች ለተጠሪ ከታህሳስ 19 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ  ቤቱን እስከሚያስረክቡበት ጊዜ ድረስ የሚታሰብ ወርሃዊ ኪራይ ብር 5000.00/አምስት ሺህ/ እንዲከፍሉ፣ የተጠቀሙበትን የውሃና የመብራት ወጪም እንዲከፍሉ ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኗ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኃላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ታህሳስ 19 ቀን 2004 ዓ.ም የተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ የተጠሪ መሆኑን በጊዜው ማወቃቸው በሚገባ የተረጋገጠ በመሆኑ አመልካች ማስጠንቀቂያው ከተጠሪ ህጋዊ ወኪል አልተሰጠኝም የሚሉት ክርክር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጾ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ አጽንቶታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ለአመልካች በህጉ አግባብ ማስጠንቀቂያ ባልተሰጠበት ሁኔታ የቤቱ ኪራይ በወር 5000.00 /አምስት ሺህ ብር/ ነው ተብሎ መወሰኑ ያላግባብ ነው የሚል ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮ የኪራይ ገንዘቡ በወር ከብር 2000.00 ወደ ብር 5000.00 ብር ከፍ ማለቱ ተረጋግጧል ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርበው ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካችና ተጠሪ ህዳር 19 ቀን 2003 ዓ/ም ያደረጉት የኪራይ ውል የተወሰነ የኪራይ ዘመን የተቀመጠለትና ይህ ጊዜም ያለፈ መሆኑን፣ ጊዜው ካለፈ ስለ ኪራዩ መጨመር ማስጠንቀቂያ ከደረሳቸው በኃላም አመልካች የተጠሪን መኖሪያ ቤት መጠቀም መቀጠላቸውን፣ ተጠሪ አመልካች የኪራይ ጊዜው ከአለፈ በኃላ መኖሪያ ቤቱን ለተጠቀሙበት ጊዜ በአዲሱ የኪራይ ተመን መሰረት ኪራይ አልተከፈለኝም በማለት የሚከራከሩ መሆኑንና አመልካች አዲሱ የኪራይ ተመን ተጠሪ በወኪሉ በኩል አሳውቄአለሁ ቢሉም ወኪሉ ህጋዊ ውክልና ስላልነበራቸው አመልካች አዲሱን የኪራይ ተመን አውቀዋል ለማለት የሚቻልበት አግባብ የሌለ መሆኑን ጠቅሰው የሚከራከሩ መሆኑን ነው፡፡

አመልካችና ተጠሪ ህዳር 19 ቀን 2003 ዓ/ም ለሶስት ወራት ያደረጉት የኪራይ ውል ዘመን ተጠናቆ አመልካች የተጠሪን ቤት መጠቀም የቀጠሉ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ይህ ግንኙነት የፍ/ብ/ህ/ቁ.2968/1/ ድንጋጌን የሚያሟላ የኪራይ ውል ግንኙነት መኖሩን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ችሎትም በዚህ ረገድ የበታች ፍርድ ቤቶች የደረሱበትን ድምዳሜ ሲመለከተው የፍ/ብ/ህ/ቁ.2968/1/ ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ያገናዘበ በመሆኑ እና አመልካችም በዚህ ረገድ ያቀረቡት ቅሬታ ስለሌለ የሚመለከተው ሆኖ አላገኘውም፡፡

በዚህ ችሎት መታየት ያለበት አቢይ ነጥብ አመልካች እና ተጠሪ ላልተወሰነ ጊዜ የተደረገ የኪራይ ውል ግንኙነት ነበራቸው ተብሎ ድምዳሜ ከተያዘ አመልካች መኖሪያ ቤቱን ለተጠቀሙበት ጊዜ ሊከፍሉ የሚገባው የኪራይ ገንዘብ መጠን ምን ያህል ነው? የሚል ነው፡፡ አመልካች የኪራይ መጠኑንን ያሻሻለው የታህሳስ 19 ቀን 2004 ዓ/ም ማስጠንቀቂያ ከተጠሪ ህጋዊ ወኪል የተሰጠኝ አይደለም ቢሉም ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው አመልካች የኪራዩ መጠን እንዲጨመር የተደረገው በአከራዩ ፍላጎት መሆኑን ከማስጠንቀቂያው በኃላ ያወቁ መሆኑ በማስረጃ መረጋገጡን ደምድመዋል፡፡ ይህ ችሎት ደግሞ ይህን የፍሬ ነገር ማጣራትና የማስረጃ ምዘና ስልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች የያዙትን   ድምዳሜ


እንዳለ የሚቀበለው መሆኑን ከኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም አመልካች የኪራይ ተመኑ ከብር 2000.00 ወደ ብር 5000.00/አምስት ሺህ/ ከፍ ስለማለቱ ተገቢው ማስጠንቀቂያ አልደረሰኝም በማለት የሚያቀርቡት ክርክር ተቀባይነት የሚሰጠው ሁኖ አልተገኘም፡፡

አመልካች ወርሃዊ የኪራይ ተመኑ ከፍ መደረጉን አከራይ ያሳወቃቸው መሆኑን በሚገባ ያውቁ ነበር፣ ቤቱንም መጠቀም ቀጥለዋል ከተባለ ደግሞ አዲሱን የኪራይ ተመን መቀበላቸውን ከፍ/ብ/ህ/ቁ.1684(1) ድንጋጌ ይዘት የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ አመልካች በዚህ አግባብ የኪራይ ተመን መሻሻሉን ከአወቁ በኃላ ቤቱን መጠቀም የቀጠሉ በመሆኑ በፍ/ብ/ህ/ቁ.2952 (2) ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ መሰረት በአዲስ የቤት ኪራይ ተመን መሰረት ለቤቱ ባለቤት ኪራዩን ለመክፈል የማይገደዱበት ህጋዊ ምክንያት የለም፡፡ በአጠቃላይ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት ስላልተቻለ ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

1. በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ.70432 ጥር 20 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ.131903 ጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.348(1) መሰረት ፀንቷል፡፡

2. በግራ ቀኙ መካከል የህዳር 2003 ዓ/ም የኪራይ ውል ካበቃ በኃላ የኪራይ ውሉ ላልተወሰነ ጊዜ ተደርጓል ፣ የኪራይ ተመኑም ወደ ብር 5000.00 /አምስት ሺህ/ ከፍ ማለቱን አመልካች አውቀውታል ተብሎ ይህንኑ ገንዘብ ከታህሳስ 19 ቀን 2004 ዓ/ም ጀምሮ ቤቱን እሰከሚያስረክቡ ድረስ ለተጠሪ እንዲከፍሉ ተብሎ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የለም ብለናል፡፡

3.  በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸው ይቻሉ ብለናል፡፡

 

 ት ዕ ዛ ዝ

 

ጥር 19 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል፡፡ ይፃፍ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት