101795 labor law dispute promotion of employee

“ስለሠራተኛ ዕድገት አሰጣጥ ስርዓት” በሚል በአዋጁ የተገለፀው ሀረግ ሊተረጎም የሚገባው ከአንድ የሠራተኛ የስራ መደብ ወደ ሌላ የሠራተኛ የስራ መደብ የሚፈፀም የዕድገት አሰጣጥ ስርዓት በሚል መልኩ ስለመሆኑ፣

 

በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 142(1)(ሠ)

የሰ/መ/ቁ. 101579

 

ህዳር 24 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመስል

አመልካቾች፡-

 

1.  አቶ ገ/መድህን አስፋው           13. አቶ ዓለማየሁ ተሾመ

2.  አቶ ተ/ፃዲቅ ደምሴ               14. አቶ ላቀው እርገጤ

3.  አቶ ዳኜ አየለ                   15. አቶ ተሾመ አግዴ

4.  አቶ ወ/ሚካኤል ዋቄ              16. አቶ አየለ ይግለጡ

5.  አቶ አምሃ ኃ/ስላሴ17. አቶ ይትባረክ ሰሜ                              ከጠበቃ

6.  አቶ አመሃ መላኩ ኃ/ማሪያም       18. ወ/ሮ ፀሐይ አእምሮ              መስፍን

7.  አቶ ደምሴ ድጋፌ              19.ወ/ሮብዙነሽ ማሞ                አለማየሁ

8.  አቶ ግዛው አስረስ               20. ወ/ሮ በቀለች ጐዳና              ጋር ቀረቡ

9.  አቶ ታደሰ ገ/መድህን21. አቶ ኃ/ማሪያም ገና

10. አቶ ወረደወርቅ ጥላሁን           22. አቶ ገብረ ተ/ኃይማኖት

11. አቶ ከበደ አወቀ                 23. አቶ ፍቃደስላሴ ርዳው

12. አቶ ይልማ ጨርቆስ              24. አቶ ሞገስ ኃ/መስቀል

 

 

ተጠሪ፡- ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ነ/ፈጅ ሳህለማሪያም ወዳጆ ቀረቡ፡፡

 

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

የሰበር አቤቱታው የቀረበው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍ/ብ/ይ/መ/ቁጥር 128430  ታህሳስ 7 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ.96927 ግንቦት 05 ቀን 2006 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተሽሮ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በማለት አመልካቾች የሰበር አቤቱታ ስላቀረቡ ነው፡፡ ጉዳዩ የጡረታ ደመወዝ ማስተካከያ አስተዳደራዊ ውሳኔ ተግባራዊ ይሁንልን ጥያቄ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በዚህ ፍርድ ቤት የአሁኑ አመልካቾች ከሳሾች ተጠሪ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ተከሳሾች ነበሩ፡፡


የአመልካቾች የክስ ይዘትም፡- መንግስት ለመንግስት ሰራተኞች እና ጡረተኞች ህዳር 23 ቀን 2003 ዓ/ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ የደመወዝ ማስተካከያ ማድረጉን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርተዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅድስ ሲኖዶስም በስሩ ላሉት ሰራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ እንዲደረግ ወስኖ ባለበት ሁኔታ የአሁኑ ተጠሪ እምቢተኛ መሆኑን ዘርዝረው የጡረታ ደመወዝ ማስተካከያ እንዲከፈል ይወሰንልን የሚል ነው፡፡ የስር ተከሳሾች ጉዳዩ በፍርድ ሊታይ የማይችልበትን ምክንያትና አመልካቾች ክሱን ለማቅረብ መብትና ጥቅም የሌላቸው መሆኑን የሚያሳዩ ነጥቦችን በመጥቀስ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት የተከራከሩ ሲሆን በፍሬ ነገር ደረጃም ለአመልካቾች የጡረታ ደመወዝ እንዲስተካከል የሚደረግበት የህግ ወይም የህብረት ስምምነት የሌለ መሆኑን ዘርዝረው ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

 

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ጉዳዩን መርምሮ የአመልካቾች ጥያቄ ተቀባይነት የለውም ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካቾች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ከሰማ በኃላ ጉዳዩን መርምሮ የአመልካቾች ጥያቄ በፍርድ ቤት ሊታይ እንደሚችል፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ/ም ባደረገው ስብሰባ ማስተካከያውን ለሰራተኞችና ለጡረተኞች በወሰነው መሰረት የአሁኑ ተጠሪም ለአሁኑ አመልካቾች ማስተካከያው ሊከፍል ይገባል በማለት ደምድሞና ሊጨመር የሚገባውን ማስተካከያ በመቶኛ ገልጾና ይኼው ማስተካከያ የሚመለከተውን የጡረታ ደመወዝ መጠን ለይቶ ለአመልካቾች ተጠሪ የጡረታ ማስተካከያውን ሊከፍል ይገደዳል በማለት ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኃላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስር የሚተዳደር ነገር ግን በራሱ ገቢ ራሱን የሚያስተዳድር  ስለመሆኑ ግራ ቀኙን ያላከራከረ ጉዳይ መሆኑን፣ ለአመልካቾች ክስም ሆነ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሠራተኞቹና ጡረተኞቹ የደሞዝ ማስተካከያ አስመልክቶ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ.ም ያስተላለፈው ውሳኔ መሆኑን በዚህ ውሳኔ ጥናት ተደርጐ የቀረበውን ጉባኤው ያፀደቀላቸው ሲሆን ሌሎቹ ማለትም በትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤትና ጐፋ ጥበበ እድ ካህናት ማሰልጠኛ ለሚገኙት ሠራተኞችና ጡረተኞች እንደየገቢያቸው መጠን እየወሰኑ ለአስተዳደሩ አቅርበው  እያስፀደቁ  ተግባራዊ እንዲሆን ሲል ቋሚ ሲኖዶሱ መወሰኑን የስብሰባ ቃለ ጉባኤ ይዘት በግዴታ የማያመላክት መሆኑን ከዚህ መረዳት የሚቻለው የጉባኤው ውሳኔ የአሁኑን ተጠሪን በተመለከተ ቀጥተኛ ተፈጻሚነት እና አስገዳጅነት ያለው የደመወዝ ማስተካከያ ያለማድረጉ መሆኑን ይልቁንም ተጠሪ በራሱ ገቢ የሚተዳደር ከመሆኑ አንፃር እንደራሱ ገቢ መጠን ጥናት አድርጐ በአስተዳደሩ አፅድቆ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ የተቀመጠለት መሆኑን እንጂ አስገዳጅ የሆነ ውሳኔ ያልተሰጠ መሆኑን የሚያስገነዝብ መሆኑን ደምድሞ አመልካቾች ባለው የቤተክርስቲያን መዋቅር መሰረት አቤቱታቸውን ከማቅረብ ውጪ በፍርድ ሃይል ተፈጻሚ የሚሆን ውሳኔ የላቸውም በማለት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮ የፌደራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በውጤት ደረጃ በመቀበል አፅንቶታል ፡፡ የአሁኑ  የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡


የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ/ም ያሳለፈው ውሳኔ ተጠሪ ገቢውን መሰረት በአደረገ መልኩ ለሰራተኞቹም ሆነ ለጡረተኞቹ በተሰራው ስኬል መሰረት ማስተካከያውን እንዲያደርግ የሚል ሁኖ እያለ ተጠሪ ለሰራተኞቹ ብቻ ማስተካከያውን አድርጐ ለጡረተኞቹ ሳያደርግ ሲቀር የቀረበውን ክስ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያላግባብ ተርጐሞ ተጠሪ የሚገደድበት ውሳኔ የለም በማለት መወሰኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ነው የሚል ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል ፡፡እንደመረመረውም ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ሲቀርብ በጭብጥነት የተያዘው ነጥብ ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ/ም በሰጠው ውሳኔ የአሁኑን ተጠሪ በስም ጠቅሶ ለሠራተኞቹና ጡረተኞቹ እንደየገቢያቸው መጠን እየወሰኑ ለአስተዳደሩ እያስፀደቁ ክፍያው እንዲፈፀም በማለት በሰጠው ውሳኔ መሰረት ለሰራተኞቹ የጭማሪውን ክፍያ እንደአደረገ ተጠሪ ግንቦት 27 ቀን 2005 ዓ/ም በሰጠው መልስ ማመኑ ከተረጋገጠ የሲኖዶሱ ውሳኔ ለጡረተኞች ብቻ ተፈፃሚነት የለውም በሚል የተሰጠውን ውሳኔ አግባብነት ለመመርመር ተብሎ ነው፡፡ እኛም ጉዳዩን ከዚሁ ጭብጥ አንፃር ብቻ መመርመሩን ተገቢነት ያለው ሆኖ አግኝተናል፡፡

 

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥር የሚተዳደር ነገር ግን በራሱ ገቢ ራሱን የሚያስተዳድር ስለመሆኑ ግራ ቀኙን ያላከራከ ጉዳይ መሆኑን፣ ለአመልካቾች ክስም ሆነ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሠራተኞቹና ጡረተኞቹ የደሞዝ ማስተካከያ አስመልክቶ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ.ም ያስተላለፈው ውሳኔ መሆኑን፣ በዚህ ውሳኔ ጥናት ተደርጎ የቀረበውን ጉባኤው ያፀደቀላቸው ሲሆን ሌሎቹ ማለትም በትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤትና በጎፋ ጥበብ እድ ካህናት ማሰልጠኛ ለሚገኙት ሠራተኞችና ጡረተኞች እንደየገቢያቸው መጠን እየወሰኑ ለአስተዳደሩ አቅርበው እያፀደቁ ተግባራዊ እንዲሆን ሲል ቋሚ ሲኖዶሱ መወሰኑና ይህንኑ ተከትሎም ተጠሪ ለሠራተኞቹ የጭማሪውን አስተካክሎ ክፍያውን ሲፈፅም ለአሁኑ አመልካቾች፤ የድርጅቱ ጡረተኞች ግን ማስተካከያውን ሳያደርግ የቀረ መሆኑን አምኖ የሚከራከር መሆኑን ነው፡፡ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተጠሪ ለክሱ ኃላፊነት የለበትም ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰው የሲኖዶሱ የስብሰባ ቃለ ጉባኤ ይዘት ተጠሪ ለጡረተኞች ማስተካከያ እንዲያደርግ በግዴታየሚያመላክት አይደለም የሚለውን ምክንያት በመያዝ መሆኑን ከውሳኔው ይዘት ተረድተናል፡፡

 

በመሰረቱ ተጠሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስር የሚተዳደር ከሆነ የቤተክርስቲያኗ የበላይ የሆነው አካል የሰጠውን ውሳኔ ያለምንም ልዩነት ተግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡ ተጠሪ ለአመልካቾች የጡረታ ደመወዝ የሚከፍለው በግራ ቀኙ መካከል በነበረው የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ሲሆን ይህ ክፍያ የሚፈፀመውም የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነቱ በጡረታ ምክንያት በመቋረጡ ምክንያት በመሆኑና ገንዘቡም ከአሰሪውና ከሠራተኞቹ ደመወዝ ተቆርጦ ሲጠራቀም ከነበረው መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የጡረታ ደመወዝ ሕጋዊ በሆነ የአስተዳደራዊ ውሳኔ መሰረት እንዲስተካከል ሲደረግ በሠራተኛው ስም የተቀመጠው ገንዘብ መኖሩን ብቻ በማረጋገጥ ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡ ጡረታ አግባብነት ላላቸው የህብረተሰቡ ክፍሎች የኑሮ ዋስትና


ለመስጠት እንዲያስችል ተብሎ ተግባራዊ የሚደረግ ማህበራዊ መድህን መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የኑሮ ዋስትና የመስጠት መሰረታዊ አላማው የሚሳካው ደግሞ ተጨባጭነት ያለውን ወይም የሕብረተሰቡን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ማስተካከያው ሲደረግ መሆኑ የሚታመን ነው፡፡ በዚህ አግባብ የጡረታም ሆነ የደመወዝ ማስተካከያም ተግባራዊ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ መኖሩም ግንዛቤ የሚወሰድበት ነው፡፡ የተጠሪ መስሪያ ቤት ባለቤት የሆነውና የበላይ የአስተዳደር አካሉ መንግስት ለሠራተኞቹና ለጡረተኞቹ ያደረገውን ማስተካከያ መነሻ በማድረግና በራሱ ፍላጎት ለተጠሪ ሠራተኞቹና ጡረተኞች ማስተካከያውን እንዲያደርግ፣ ማስተካከያው ደግሞ የተጠሪን ገቢ መሰረት አድርጎ ሊሰራእንደሚገባና በሚመለከተው አካል  እየጸደቀ ተግባሪዊ እንዲሆን የሚገልፅ ውሳኔ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ/ም መወሰኑም ይህንኑ የሚያሳይ ነው ፡፡ ተጠሪ የሲኖዶሱ ውሳኔ በተጠሪ ላይ አስገዳጅነት የለውም በማለት የሚያቀርበውና በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተቀባይነት ያገኘው መከራከሪያ ነጥብ ሲታይም ተጠሪው ገቢውን መሰረት ያደረገ ጥናት አደርጎ ለቋሚ እና ለኮንትራት ሰራተኞቹ ማስተካከያውን አድርጎ ክፍያውን መፈጸሙን ያመነበትን አግባብ ክፍያውን ለጡረተኞቹ ላለማድረግ ህጋዊ ምክንያት የነበረው መሆን ያለመሆኑን አጣምሮ ያላገናዘበ ሆኖ አግኝተናል፡፡ምክንያቱም የተጠሪ የበላይ አስተዳደር የሆነው አካል ለተጠሪ የሰጠው አስተዳደራዊ አቅጣጫ የማስተካከያው ክፍያ ተጠቃሚዎችን ሠራተኞች ወይም ጡረተኞች በሚል ጭምር ተለይቶ እንዲፈፀም የሚያሳይ ሳይሆን ለሠራተኞቹም ሆነ ለጡረተኞቹ ልዩነት ሳይደርግ የድርጅቱን ገቢ መሰረት አድረጎ ማስተካከያውን እንዲሰራና ተግባራዊ እንዲያደርግ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ስለሆነም ተጠሪ የበላይ አካልን ውሳኔ ተግባራዊ ላለማድረግ ሕጋዊ መከራከሪያ ሊሆነው የሚችለው የድርጅቱ የገቢ ሁኔታ ብቻ ነው፡፡ሆኖም ተጠሪ ለሰራተኞቹ ማስተካከያውን ያደረግው የድርጅቱን ገቢ መሰረት አድርጎ ስላለመሆኑ ያቀረበው ክርክርና ማስርጃ የለም፡፡የተጠሪ የበላይ አካል የሆነው ሲኖዶሱ ማስተካከያው ለተጠሪ ድርጅት ሰራተኞች ጡረተኞች እንዲደረግ ውሳኔ ከሰጠና ለሠራተኞቹ የተጠሪን ገቢ መሰረት ባደረግ መልኩ ማስተካከያው መደረጉ እስከተረጋገጠ ድረስ ደግሞ ተጠሪ ጡረተኞችን ብቻ በመለየት የማስተካከያው ተጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም የሚልበት አግባብ የለም፡፡ተጠሪ የበላይ አካሉን ውሳኔ ተቀብሎ ለሠራተኞቹ ብቻ ማስተካከያ አድርጎ ለጡረተኞቹ ብቻ ማስተካከያውን የተወበት አካሄድ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ በውጤት የጡረታ መብት ለኑሮ ዋስትና ያለው ሕጋዊ ፋይዳ ዋጋ የሚያሳጣው ነው፡፡

 

አመልካቾች ተጠሪ ላይ በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ የመሰረቱት ከተጠሪ ጋር መስርተው የነበሩት ሕጋዊ የአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነት ተቋርጦ የአመልካቾች የጡረታ መብት ተከብሮላቸው የጡረታ መብት ተካፋይ ሁነው ባሉበት ሁኔታ በአስተዳደራዊ ውሳኔ መሰረት የተከበረላቸው የጡረታ ማስተካከያ ክፍያ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም በሚል በመሆኑ ጉዳዩ ኃይማኖታዊ ስርዓትን ተከትሎ ትርጉም የማያስፈልገው በመሆኑ ጉዳዩ በፍርድ ቤት መታየቱ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 11 ስር የተደነገገውን መርህ የማይነካ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ሕጋዊ የሆነ አስተዳደራዊ ውሳኔ ተግባሪዊ ሳይሆን ሲቀር በፍርድ ቤት ውሳኔ አስገዳጅነትእንዲኖረውማድረግም በኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 37 እና 25 የተረጋገጡትን ፍትህ የማግኘት መብትና የእኩልት መብት ውጤታማ የሚያደረግ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ስለሆነም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተጠሪ የበላይ አካል የሆነው ሲኖዶስ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ.ም በሰጠው ውሰኔ የአሁኑን ተጠሪ በስም ጠቅሶ ለሠራተኞቹና ጠረተኞቹ እንደየገቢያቸው መጠን እየወሱነ ለአስተዳደሩ እያስፀደቁ ክፍያው እንዲፈፀም በማለት በሰጠው ውሳኔ መሰረት ተጠሪ ለሰራተኞቹ የጭማሪው  ክፍያ  እንደ  አደረገ  ግንቦት  27  ቀን  2005  ዓ/ም  በሰጠው  መልስ  ማመኑ


በተረጋገጠበት ሁኔታ የሲኖዶሱ ውሳኔ ለጡረተኞች ብቻ ተፈፃሚነት የለውም የሚል ትርጉም የሚያሰጥ ውሳኔ መስጠቱ በክርክሩ ሂደት የተረጋገጡትን ፍሬ ነገሮችን ያላገናዘበ  ሆኖ ስለአገኘነው በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1.  የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 96927 ግንቦት 05 ቀን

2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 128430 ታህሳስ 07 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል፡፡

3. ተጠሪ ለአመልካች ጥያቄ ኃላፊ ነው ተብሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ/ም በወሰነው መሰረት ከጥር ወር 2003 ዓ/ም ጀምሮ የጡረታ ማስተካከያ አበል ሊከፈላቸው ይገባል በማለት ወስነናል፡፡ ስሌቱን በተመለከተ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባስቀመጠው መሰረት ነው ብለናል፡፡

4. ለክርክሩ የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 


 

እ/እ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማአለበት፡፡