101040 labor law dispute payment instead of annual leave

የዓመት ዕረፍት ክፍያ አስፈላጊው የገቢ ግብር ተቀንሶ ለሠራተኛው ሊከፈለውየሚገባ ስለመሆኑ:-አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 27(ሐ)፣36፣37

 

የገቢ ግብር አዋጅ 286/94 እና ደንብ ቁጥር 78/94 አንቀፅ 3

የሰ/መ/ቁ. 101040

 

መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ሡልጣን አባተማም መኮንን ገ/ሕይወት ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

አመልካች፡- አቶ አየለ መንግሥቱ

 

ተጠሪ፡- የኢትዮጲያ እህል ንግድ ድርጅት

 

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሠጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ይህ ጉዳይ የተጀመረው በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ነገሌ ወረዳ ፍ/ቤት ሲሆን የአሁን አመልካች ከሣሽ ሲሆን    ተጠሪ  ተከሣሽ  ነበሩ አመልካች                     ባቀረበው ክስ  ተጠሪ  ያለምንም ምክንያት ያለማስጠንቀቂያ ከሥራ ስላሰናበተኝ የአገልግሎት ካሣና ጉዳት ፣የስድስት ወር ደሞዝ፣ የአመት ዕረፍት ክፍያ እና የሥራ ልምድ ጨምሮ 51,778 ብር እንዲከፈለኝ በማለት ጠይቋል፡፡ ተጠሪም በሰጠው መልስ አመልካች የመጋዘን ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ 41.01 ኩንታል በቆሎ በጆንያ መሐከል ተደብቆ በፅዳት ሠራተኛ በኩል ተደረሶበት ይህንንም ያደረጉት ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል በማሰብ ነው፣በድርጊቱም ተጠይቀው በቀን ሰራተኛ ሲጫን ተዛብቶ ይሆናል በማለት ተናግሯል፡፡ ይሁንና ይህ ተግባራቸው ያለቅድሚያ ማስጠንቀቂያ የሚያሰናብት ነው በማለት ተከራክሯል፡- ጉዳዩ የቀረበለት ፍ/ቤትም ተገኘ የተባለው በቆሎ ማን እንደደበቀው በግልፅ ባልተረጋገጠበት ያለማስጠንቀቂያ መሰናበቱ ህገ ወጥ ነው በመሆኑም በአዋጅ ቁ. 377/96 አንቀፅ 36፣37 ሣያሟላ እርምጃ መወሰዱ አግባብ ስላልሆነ በአዋጅ አንቀጽ 43(1) መሰረት ካሳና ደሞዝ ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ክፍያዎች ጨምሮ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 40(1-3) ባጠቃላይ 49,998.50 ይከፈለው ሲል ወሰነ ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለትም የከፍተኛው ፍ/ቤት በፍ/ህ/ስ/ስ/ቁ.337 ሰርዞታል፡፡ የክልሉም የሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን በማየት ጠፋ የተባለው በቆሎ በመጋዘን ውስጥ  ተደብቆ እና ቁልፉም ከተጠሪ ሌላ ማንም እንማይዘው ተረጋግጧል፣ በመሆኑም ተጠሪ የማጭበርበር ድርጊት የፈጸመ በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(ሐ) መሰረት ያለማስጠንቀቂያ የሚያሰናብት ነው ሲል የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ሽሮታል፡፡

የአመልካች የሰበር አቤቱታም ይህንን ውሳኔ ለማስቀየር ነው፡፡ አመልካች ባቀረቡት አቤቱታ በስር ፍ/ቤት ተጠሪ በሰጠው መልስ በመጋዘን ውስጥ የተደበቀ በቆሎ  በመገኘቱ እንዳሰናበተኝ ቢገልጽም የደረሰ ጉዳት የለም በማለት አጣርቶ ስንብቱ ህገ ወጥ ነው በማለት የተለያዩ ክፍያ እንዲከፈለኝ ቢወሰንም የክልሉ ሰበር ሰሚ ፍ/ቤት የአመልካችን የመጋዘን ኃላፊ መሆኑን በመገልጽና ቁልፉም በእኔው እጅ እንደሚቀመጥ  በመጥቀሰ የማጭበርበር ድርጊት   ተፈጸሟል


በማለት በአዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 27(ሐ) መሰረት ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት የተወሰነልኝን የዓመት ዕረፍት ጭምር የሰረዘ ውሳኔን መሰጠቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ጠይቋዋል፡፡

በዚህ መሰረት ይህ ችሎትም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ስንብቱ ህጋዊ ነው ሲል ሲሽረው ወደ ገንዘብ ተቀይሮ እንዲከፈል የተወሰነውን የዓመት ዕረፍት ክፍያ ጭምር መሻሩን እንደ ጭብጥ በመያዝ የግራ ቀኙን አስቀርቦ መልስና የመልስ መልስ በማቀባበል እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡ ተጠሪ ለአመልካች የዓመት እረፍት ሊከፈል እንደሚገባ ሳይክድ በትርፍነት የተከፈላቸውን ገንዘብ እንዲከፍሉ (እንዲመልሱ) በማለት ሲከራከር አመልካች በበኩላቸው የሚፈለግባቸው ገንዘብ የሌለና አዲስ ክርክር ሊነሳ አይገባም ሲሉ ክርክራቸውን አጠናክረዋል፡፡

በመሆኑም የግራ ቀኙ ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና አግባብነት ካለው ህግ አኳያ አገናዝበን መርምረናል፡፡

በመሆኑም የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተጠቀሰውን ሲመስል እኛም ጉዳዩን እንዳየነው አመልካች በወረዳው ፍ/ቤት ከህግ ውጭ ተሰናበትኩ ሲል የዓመት ዕረፍትን ጨምሮ የተለያዩ ክፍያ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡

በዚሁ መሰረት ግራ ቀኙን በማከራከር ስንብቱ ሕገ ወጥ በመሆኑ የስራ ከህግ ውጭ መሰናበት ውጤት የሆኑት ክፍያ እንዲከፈል ወስኗል፡፡በይግባኝ ሰሚውም ይኸው ውሳኔ ጸንቷል፡፡ በቀጣይነት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የስር ውሳኔን በመሻር አመልካች የመጋዘን ኃላፊ ሆኖ በሚሰሩበት ወቅት ተደብቆየተገኘ በቆሎ መኖሩ የተረጋገጠ በመሆኑ ድርጊቱ በአዋጅ 377/96 አንቀፅ 27(1(ሐ) ስር የሚወድቅ የማጭበርበር ድርጊት በመሆኑ ስንብቱ ህጋዊ ነው ሲል ወስኗል፡፡

ይህ ችሎትም የክልል ሰበር ሰሚ ችሎት ስንብቱ ህጋዊ ነው ሲል የደረሰበትን ድምዳሜ የሚቀበለው ሲሆን በስር ፍርድ ቤት የተጠየቀው የዓመት ዕረፍት ክፍያ ጥያቄን አስመልከቶ ሳይለይ በጠቅላላ መሻሩ ሊታረም የሚገባ ሆኖ አግኝተናል፡፡

በመሠረቱ የዓመት ዕረፍት ክፍያ ሠራተኛ በሥራ ዘመኑ ሊጠበቁለት ከሚገቡ መብቶች መሀከል አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ክፍያ የሠራተኛው ውል በህግ ወይም ከህግ ውጭ እንዲሁም ሠራተኛው በራሱ ጊዜ ሲያቋርጥየዓመት ዕረፍትክፍያ ሊታለፍበት (ሊነፈግ) የሚችል አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ጥያቄው ከሚቀጥለው ሁለት አመት በላይ ሊራዘም እንደማይችል በአዋጅ አንቀጽ 79(5) ላይ ተመልክቷል፡፡ ይህም የሆነው ሰራተኛው ወደ ገንዘብ ተቀይሮ እንዲሰጠው ከሚጠይቅ ዕረፍቱን በአይነት ወስዶ በተሟላና አካሉን አሳርፎ በአዲስ ሀይል ሥራውን እንዲያከናውን ታስቦ እንደሚሆን ብዙ አያከራክርም፡፡ የህጉ አንቀጽ 76(1) ይህንኑ ሲያጠናክር በዚህ ረገድ ሰራተኛው የዕረፍት ጊዜውን ለመተው ሊስማማ የማይችል መሆኑን ክልከላ ያስቀመጠው፡፡ ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመጣም የክልሉ የሰበር ሰሚ ችሎትም የአመልካችን የአመት እረፍት ክፍያ ውድቅ ያደረገበት ምክንያት ግልፅነት የጐደለው ሲሆንአመልካችም ውሳኔው ቢሻርም በሥር ፍ/ቤትየታመነው የአመት እረፍት ክፍያ የ85 ቀን (5468.5) ብር ሊከፈለኝ ይገባል በማለት ይከራከራሉ፡፡ ተጠሪም በበኩሉ ይህ ክፍያ ለአመልካች ሊከፈል እንደሚገባው በማመን መጠኑን አስመልክቶ የ48 ቀን ብቻ ነው ሊከፍለው የሚገባው ሲል መነሻው ግብር ተቀንሶ ሊከፍል ይገባዋል በማለት ይከራከራል፡፡ እንግዲህ የቀኑን ብዛት  አስመልክቶ የተነሳው ክርክር በሥር ፍ/ቤት ጐልቶ መከራከሪያ ሆኖ ያልመጣ በመሆኑ አልተቀበልነውም ሌላው ተጠሪ የሚያነሣው ክርክር የዓመት ዕረፍት ክፍያው ግብር ተቀንሶ ሊከፈል ይገባል የሚል ነው፡፡ በዚሁ ውሳኔ ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው የዓመት ዕረፍትን ለሰራተኛው መክፈል የማስፈለጉ አላማ ግልፅ ነው


በመርህ ደረጃ በዓይነት የእረፍት ቀናትን ወስዶ እንዲወጣ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ በህግ የተፈቀደለትን የዓመት ዕረፍቱን ወስዶ ከመውጣት በቀር ሌላ ሊያሟላ የሚጠበቅበት ነገር የለም፡፡ በሌላበኩል በተለያዩ በህጉ በተቀመጡት ምክንያቶች የዓመት ዕረፍት ወደ ገንዘብ ተቀይሮ  ሲከፈል እንደሌሎች ከአሰሪና ሰራተኛ ህጉ የሚመነጩ መብቶች (ክፍያ) የዓመት ዕረፍት ክፍያም የገቢ ግብር ከተቀነሰ በኋላ የሚከፈል ክፍያ መሆኑን ይህ ችሎት የሚቀበለው ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የገቢ ግብር የአዋጅ ቁ.286/94 እና ደንብ ቁ.78/94 አንቀፅ 3 የዓመት እረፍትን ያለማግለሉ ይህንኑ የሚያጠናክሩ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል አመልካች እንዲከፈላቸው የጠየቁትን የገንዘብ መጠን በሥር ውሳኔ በግልፅ ተጠቅሶ ባይቀመጥም ተጠሪ ለመጠንና ስሌት ክርክር ውጭ አመልካች የአመት ዕረፍት ክፍያ የላቸውም የሚል ክርክር አላቀረቡም በመሆኑም በአዋጅ ቁ. 377/96 አንቀፅ 77፣78 እና 79 በተደነገጉት መሠረት አመልካች ያቀረቡትን የገንዘብ መጠን በሌላ ማስረጃ አላስተባበለም፡፡

በአጠቃላይ የክልሉ ሠበር ሰሚ ችሎት የሥር ውሳኔን ሲሽር የአመልካችን  የአመት ዕረፍት ክፍያ ጭምር መሻሩ መሠረታዊ የህግ ሥህተት የተፈፀመበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በመሆኑም የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 ው ሳ ኔ

1.  የአርሲ ነገሌ ወረዳ /ቤት በመ/ቁ 20962 በቀን 20/12/05 የከፍተኛው /ቤት በመ/ቁ

18732 በቀን 27/01/06 እና የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ 74447 በቀን 01/07/06 በማሻሻል ፀንቷል፡፡

2.  አመልካች የጠየቁትን የዓመት ዕረፍት ክፍያ በህጉ መሰረት አስፈላጊው የገቢ ግበር ተቀንሶ ይከፈላቸው ብለናል፡፡

3.  ተጠሪ ለአመልካች በትርፍነት ከወሰዱት ገንዘብ   ሊመልሱልኝ   ይገባል የሚለውን በህግ አግባብ ከመጠየቅ ይህ ውሳኔ አያግድም፡፡

4.  የወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ይቻቻሉ፡፡

 

 

መዝገቡ ውሳኔ አግኝቷል ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

እ/ኢ