103209 labor law dispute body injury by employee-teacher on student termination of contract of employment

አንድ ተማሪ በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ ህገመንግስታዊ መብት ያለው ስለመሆኑ፡-

 

አንድ አስተማሪ የሚያስተምራቸውን ተማሪዎች በአግባቡ የመቆጣጠርና የመከታተል ህጋዊ ግዴታ ያለበት ስለመሆኑና ይህንን ግዴታውን ተላልፎ ተማሪን ቢደበድብ ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውሉን ሊያቋርጥ የሚችል በቂ ምክንያት ስለመሆኑ፡

 

የኢ.ፌ.ዲ.ሬ ህገ መንግስት በአንቀፅ 16 የፍ/ሕ/ቁ 2124 እና 2125

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 27(1)(ቀ) ፣አንቀፅ 14(2)(ሀ)

የሰ/መ/ቁ 103209

 

የካቲት 16 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

 

 

አመልካች፡- አትላስ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት - ጠበቃ መልካም ዓለማየሁ ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሪት መስታወት ስመኝ - ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት የቀረበውን የግል የሥራ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመሰረቱት ክስ ነው፡፡ ተጠሪ በአመልካች ላይ ያቀረቡት ክስም፡- ከአመልካች ጋር በሕግ አግባብ ያደረጉት የስራ ቅጥር ውል ከሕግ ውጪ የተቋረጠባቸው መሆኑን ገልፀው የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፍሏቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መከላከያ መልስም፡- ተጠሪ ከስራ የተነሰናበቱት በአመልካች ንብረት ያላግባብ በመገልገላቸው ከስራ ባልደረባቸው ጋር በክፍል ውስጥ ግጭት በመፍጠራቸው ማስንጠቀቂያ እየተሰጣቸው ከስራ ገበታቸው ያለበቂ ምክንያት በመቅረታቸው እና ተጠሪ በሚያስተምሯቸው የክፍል ተማሪዎች ላይ የመግረፍና የማስደንገጥ ተግባር እየፈፀሙ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የስነ ልቦና ችግር በማድረሳቸው ምክንያት ነው በማለት ስንብቱ ሕጋዊ ነው ሲል ተከራክሯል፡፡

የስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና የአመልካችን ምስክሮችን ከሰማ በኋላ ጉዳዩን በመመርመር አመልካች ተጠሪን ያሰናበተው ከሕግ ውጪ ነው ወደሚለው ድምዳሜ ደርሶ ውጤቱን በተመለከተም የክፍያዎችን አይነትና መጠን በመዘርዘር በድምሩ ብር 14,988.33 (አስራ አራት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ስምንት ብር ከሰላሳ ሶስት ሳንቲም) አመልካች ለተጠሪ ሊከፍል ይገባል በማለት ወስኗል፡፡በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም፡፡የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡-የስር ፍርድ ቤት ተጠሪ ከአስተማሪ ጋር በስራ ቦታ ተጣልተው በማስጠንቀቂያ የመታለፉቸውን ሁኔታ ለስንብት ምክንያት ሊሆን የሚችል


አይደለም በማለት ማለፉም ሆነ ተጠሪ ተማሪዎችን መደብደባቸውን በማስረጃ በአረጋገጠበት ሁኔታ ጥፋቱ ያለማስጠንቀቂያ ከስራ የሚያሰናብት አይደለም በማለት ስንብቱን ሕገ ወጥ ሲል መወሰኑና ይህም በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት መጽናቱ ያላግባብ ነው የሚል ነው፡፡

አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ተጠሪ ቀርበው በሰጡት መልስም ጥፋቶቹ ያለመረጋገጣቸውንና ያለማስጠንቀቂያ ከስራ ሊያሰናብቱ የሚችሉበት አግባብ የሌለ መሆኑን ጠቅሰው በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም በማለት ተከራክረዋል፡፡አመልካችም የሰበር አቤቱታውን በማጠናከር የመልስ መልሱን አቅርቧል፡፡ይህም ችሎት ግራ ቀኙ በስር ፍርድ ቤት የተከራከሩበትን መዝገብ እንዲቀርብ አድርጎ በአመልካች ምስክሮች የተነገረውንና የተረጋገጠውን የምስክርነት ቃል ይዘት ተመልክቷል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡እንደመረመረውም የችሎቱን ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ ሁኖ ያገኘውን በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ለማለት ይቻላል? ወይስ አይቻልም? የሚለው ጭብጥ ነው፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት በዚህ ችሎት የሚከራከረው ተጠሪን ከስራ ባልደረባቸው በስራ ቦታ ጠብ ፈጥረው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል በተማሪዎች ላይ ሕገ ወጥ የሆነ የድብደባ ተግባር ፈጽመዋል በማለት መሆኑን ነው፡፡ተጠሪ በበኩላቸው ጥፋቶቹን መፈፀሜ በማስረጃ አልተረጋገጠም በማለት የሚከራከሩ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡

ከዚህ ሁሉ መገንዘብ የሚቻለው ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የፌዴራሉ መጀመሪያ ፍርድ ቤት አመልካች ስንብቱን ሕጋዊ ያደርጋሉ በማለት በመከላከያ መልሱ የጠቀሷቸውን ፍሬ ነገሮች ውድቅ ያደረጋቸው መሆኑን ሲሆን ለዚህም ያስቀመጣቸው ምክንያቶች ተጠሪ ከስራ ባልደረባቸው በስራ ቦታ ጠብ ፈጥረዋል ለተባለው አድራጎት በአመልካች በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ከታለፉ በኋላ ይኼው በማስጠንቀቂያ የታለፈው ጥፋት ለስንብቱ ምክንያት ሊሆን እንደማይችል ተማሪዎችንመደብደባቸውም ያለማስጠንቀቂያ ከስራ የሚያሰናብት ጥፋት ስላለመሆኑ በሕጉ አልተመለከተም የሚሉ ናቸው፡፡

የአዋጅ ቁጥር 377/1996 የስራ ውል ስለሚቋረጥበት ምክንያቶችና ሁኔታዎችን በአንቀጽ 23 ከአንቀጽ 26 እስከ 30 ተደንግገው ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ሕብረት ስምምነት መሰረት ያለማስጠንቀቂያ ውሉን ለማቋረጥ የሚያበቃ ምክንያት ተደርጎ የተወሰደ ጉዳይም በአሰሪው ተነሳሽነት ያለማስጠንቀቂያ ውሉን ሊያቋርጥ የሚችል መሆኑ በአንቀጽ 27/1/ተ/ ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 24 እንደተመለከተው ውሉ በሕግ የሚቋረጥበት ምክንያቶች በአብዛኛው ከሁለቱም ወገን ቁጥጥር ውጭ ያሉ ሲሆን የስራ ውል በሁለቱም ፈቃደኝነት የሚገቡበት እንደመሆኑ ሁሉ ሁለቱም በፈቃደኝነት ከተስማሙ ውሉን ሊያቋርጡ የሚችሉበት ሁኔታም በአንቀጽ 25 ስር ሰፍሮ ይገኛል፡፡ስለዚህ ከላይ በተገለጹት ቁጥሮች በተደነገጉት ምክንያቶችና ሁኔታዎች የሚፈጸም የስራ ውል መቋረጥ ሕጋዊ የስራ ውል መቋረጥ ሲሆን ከነዚህ ውጭ የሚደረጉ የስራ ውል መቋረጥ በሕገ ወጥነት የሚፈረጁ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 42 ድንጋጌ ስር ተመልክቷል፡፡ በዚህም ላይ በመመስረት የሚያስከተሉት ውጤቶች የሚለያዩ በመሆኑ በተናጥል የሚያስከትሉትን ውጤት ከሕጉ አግባብ በማየት ዳኝነትን መስጠት የሚጠይቅ መሆኑም ግልፅ ነው፡፡

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመጣ አመልካች ከተጠሪ ጋር በሕግ አግባብ የመሰረተው የስራ ውል መኖሩንና  ስንብት  ማድረጉን  ሳይክድ  አጥብቆ  የሚከራከረው  ስንብቱ  ሕጋዊ  ነው በሚል


ነው፡፡ለዚህም ተጠሪ በአመልካች ንብረት ያላግባብ መገልገላቸውን ከስራ ባልደረባቸው  ጋር በክፍል ውስጥ ግጭት መፍጠራቸውን ተጠሪ ማስንጠቀቂያ እየተሰጣቸው ከስራ  ገበታቸው ያለበቂ ምክንያት መቅረታቸውንና ተጠሪ በሚያስተምሯቸው የክፍል ተማሪዎች ላይ በመግረፍና በማስደንገጥ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የስነ ልቦና ችግር ማድረሳቸውን የሚገልጹ ምክንያቶች ጠቅሶ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቷል፡፡አመልካች ያቀረባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ተጠሪ ከስራ ባልደረባቸው ጋር በስራ ቦታ ፈጠሩ ለተባለው ጸብ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው የታለፉ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በስራ ቦታ ጠብ መፍጠር በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1(ረ) ድንጋጌ መሰረት እንደጥፋቱ ክብደት እየታየ ያለማስጠንቀቂያ  ከስራ የሚያሰናብት ተግባር መሆኑ የተደነገገ ሲሆን በተያዘው ጉዳይ ግን ተጠሪ  ለጥፋቱ በማስጠንቀቂያ የታለፉ መሆኑን በሚገባ ተረጋግጧል፡፡በመሆኑም በማስጠንቀቂያ የታለፉበት ጉዳይ የማስጠንቀቂያውን ተደጋጋሚነትን በመግለጽ ሌላ ጥፋት መፈጸሙ ሲረጋገጥ ለስንብት መሰረት ከሚሆን በስተቀር ራሱ በማስጠንቀቂያ ቀሪ የሆነ ጥፋቱ ግን ለስንብት መሰረት የሚደረግበት አግባብ የለም፡፡በመሆኑም አመልካች በዚህ ረገድ ያቀረበው ክርክር የሕግ መሰረት የሌለው በመሆኑ ተቀባይነት የሚያገኝበትን አግባብ አላገኘንም፡፡

ሌላው አመልካች አጥብቆ የሚከራከረው ተጠሪ የሚያስተምሯቸውን ተማሪዎች መደብደባቸው በፍሬ ነገር ደረጃ ተረጋግጦ እያለ አድራጎቱ ያለማስጠንቀቂያ ከስራ የሚያሰናብት አይደለም መባሉ ተገቢነት የለውም በሚል ነው፡፡በእርግጥ አንድ ተማሪ በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ ሕገ መንግስታዊ መብት ያለው መሆኑን የኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት  አንቀፅ 16 በግልጽ ያስቀመጠው ጉዳይ ሲሆን ይህን ህገ መንግስታዊ መብት መጣስ ሕገ ወጥ ድርጊት በመሆኑ በሕግ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑም የሚታመን ነው፡፡በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1(ቀ)) ድንጋጌ ስር በተመለከተው አግባብም በአዋጁ አንቀጽ 14(2(ሀ)) ድንጋጌ ጋር ተጣምሮ ሲታይ ከስራ ያለማስጠንቀቂያ ለማሰናበት የሚያስችል ምክንያት ነው፡፡

በሌላ በኩል አንድ አስተማሪ የሚያስተምራቸውን ተማሪዎች በአግባቡ የመቆጣጠርና የመከተታል ህጋዊ ግዴታ ያለበት መሆኑን ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2124 እና 2125 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡በመሆኑም እነዚህ የሕግ ድንጋጌዎች ተጣጥመው በአግባቡ ተግባራዊ መሆን ያለባቸው መሆኑ እሙን ነው፡፡ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ስንመለከተው ተጠሪ ተማሪዎችን ደብድበዋል የተባለው ከአስተማሪነታቸው ከሚጠበቀው ኃላፊነት በላይ ስለመሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ ያልተረጋገጠ መሆኑን የስር ፍርድ ቤት ዋና መዝገብ ላይ የቀረቡትን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ይዘት በመመልከት ተገንዝበናል፡፡ ከሁሉም በላይ የአመልካች ሁለተኛ ምስክር በስር ፍርድ ቤት ቀርበው በሠጡት የምስክርነት ቃል ተማሪዎችን መግረፍ ክልክል መሆኑን ገልፀው እንደዚህ አይነት አድራጎት የፈፀመ አስተማሪ ለጥፋቱ ከምክር እስከ ማጠንቀቂያ የሚሰጥበት ሂደት መኖሩን መጨረሻ ላይም አስተማሪው ካልታረመ ጉዳዩን የበላይ አካል እንዲያውቀው ተደርጎ ተገቢው የሚወሰን መሆኑና ይህም በትምህርት ቤት መተዳደሪያ ደንብ ያለ መሆኑን ጭምር ዘርዝረው መግለጻቸው ሲታይ ትምህርት ቤቱ ሕገ ወጥ ተግባር ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን ተገንዝቦ ይህንኑ ህገ ወጥ ተግባር ለመከላከልና ተፈጽሞ ሲገኝም አስተማሪው በዲሲፕሊን የሚጠይቅበትን ስርዓት ዘርግቶ እየሰራበት መሆኑ የሚያሳይ በመሆኑ አመልካች ተጠሪ ፈፀሙ የተባሉት አድራጎት ከአስተማሪነታቸው ኃላፊነት እና ግዴታ በላይ መሆኑንና ከትምህርት ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ መሆኑን ጭምር ያለማስረዳቱን የክርክሩ ሂደት የሚያሳይ መሆኑን የሚያስገነዝብ ሁኖ አግኝተናል፡፡ ስለሆነም የስር ፍርድ ቤት ተማሪን መደብደብ ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውሉን ለማቋረጥ የሚያስችል አይደለም በማለት ያስቀመጠው ምክንያት ከሕገ መንግስቱ አንቀጽ 16 ከአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1(ቀ) እና 14(2(ሀ)


ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ውጪ ቢሆንም ተጠሪ ፈጸሙ የተባለው ድርጊት ከአስተማሪነት ኃላፊነት እና ግዴታቸው የወጣና ያልተገባ ስለመሆኑ ባለመረጋገጡ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ሲል የደረሰበት ድምዳሜ ግን በውጤት ደረጃ ተቀባይነት የሚሰጠው ሁኖ አግኝተናል፡፡በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

 ው ሳ ኔ

1. በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 36072 ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ 140064 ሐምሌ 14 ቀን 2006 ዓ/ም በትዕዛዝ የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348(1) መሰረት ጸንቷል፡፡

2. የአመልካች እርምጃ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ በውጤት  ደረጃ ሲታይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት የሚቻል ሁኖ አልተገኘም ብለናል፡፡

3. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር ግራ ቀኙ የሰበር  ክርክር ወጪና  ኪሳራን የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

 

 ት ዕ ዛ ዝ

ሐምሌ 16 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል፡ይፃፍ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

 

 

 

 

መ/ይ