101020 labor law dispute salary

በሠራተኛው የሚጠየቅ የውዝፍ ደመወዝ ክፍያ ጥያቄ በአሠሪው የይርጋ መቃወሚያ ካልቀረበበት በስተቀር ተከፋይ ስለመሆኑ።-

የሰ/መ/ቁ. 101020

መስከረም 29 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

ሱልጣን አባተማም መኰንን ገ/ህይወት ሙስጠፋ አህመድ ተኸሊት ይመስል

 

አመልካች፡- አቶ ዳዊት ገ/ማርያም - የቀረበ የለም፡፡ ተጠሪ፡- አቶ ሣህለማርያም ደግፌ - የቀረበ የለም፡፡

መዝገቡ ተመርምሯል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

የሰበር አቤቱታው የሶማሌ ክልል መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.05-0- 60/06 መጋቢት 19 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት ተፈፅሟል ይታረምልን የሚል ሲሆን፤ይግባኝ ባይ በጠበቃቸው በኩል ግንቦት 18 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት ሦስት ገጽ ቅሬታ፡-

በሥር ፍርድ ቤት ከሳሽ የአሁኑ የሰበር አመልካች በተጠሪ ላይ በ17/10/2005 ዓ.ም በተፃፈ ክስ ከተጠሪ ጋር በ3ዐ/09/2004 ዓ.ም በተዋዋሉት የሥራ ቅጥር ውል መሠረት አመልካች ሲሰሩ የቆዩ ቢሆንም ተጠሪ ክፍያ ባለመፈፀማቸው እና አመልካችን ከሥራ አላግባብ በማሰናበታቸው ተጠሪ ውዝፍ ደመወዝ፣ ካሣ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅም ለአመልካች እንዲከፍሉ ይወሰንላቸው ዘንድ ጠይቀዋል፡፡

ተጠሪ ለቀረበባቸው ክስ ከአመልካች ጋር የሥራ ቅጥር ውል የለንም ከማለት አልፈው በፍሬ ነገር ክርክሩ መልስ ባለመስጠታቸው ክሱ የቀረበለት የጅጅጋ ወረዳ ፍርድ ቤት በግራ ቀኙ መካከል የሥራ ቅጥር ውል አለ ተጠሪ ውዝፍ ደመወዝ ብር 42,000 /አርባ ሁለት ሺህ/ አመልካች ይክፈሉ ሲል ወስኗል፡፡

ተጠሪ በውሣኔው ቅር በመሰኘት ለፋፈን ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቁት ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙ አከራክሮና ማስረጃ ሰምቶ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን በማፅናት ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት ወስኗል፡፡

የአሁኑ ተጠሪ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቅርበው ግራ ቀኙን ያከራከረ ቢሆንም በሥር ፍርድ ቤት ያልቀረበ የይርጋ ክርክር በማንሳት የአመልካች ክስ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 162/3 መሠረት በይርጋ ቀሪ ሆኗል በማለት የሥር ፍርድ ቤቶች ውሣኔ በመሻር መሠረታዊ የሕግ ሥህተት የፈፀመ በመሆኑ ችሎቱ የሥር ሰበር ችሎት ስህተት በማረም የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲያፀናልኝ እና ወጪና ኪሣራዬን ይተካልኝ ዘንድ በመወሰን ያስናብተኝ የሚል ነው፡፡

የሰበር አቤቱታ አጣሪ ችሎቱ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ሰኔ 20 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት መርምሮ፡፡


“የሱማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በይርጋ ላይ ተመርኩዞ የሰጠው ዳኝነት አግባብነት ከፍ.ሥ.ሥ.ሕግ ቁጥር 244/3 አንፃር ለመመርመር ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ይቅረብ” ሲል አዟል፡፡

ተጠሪ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ደርሷቸው በጠበቃቸው በኩል ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ጽፈው ያቀረቡት መልስ፤ ተጠሪ በሥር ፍርድ ቤት የቀረበባቸው ክስ ችግር የተሞላበት የነበር ቢሆንም በይግባኝ ደረጃ የሥር ፍርድ ቤት ውሣኔ ህገወጥነት ከመግለጽ አልፎ በቃል ክርክር ስለይርጋ በማንሳት ተከራክረዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሥር ፍርቤት ውሣኔ ቢያጸናውም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የአመልካች ክስ በይርጋ ቀሪ ነው በማለት መወሰኑ የሚነቀፍ ባለመሆኑ ውሳኔው ስህተት የለበትም ተብሎ ችሎቱ ከበቂ ወጪና ኪሣራ ጋር ያሰናብተን የሚል ነው፡፡

አመልካች ሀምሌ 25 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ ያቀረቡ ሲሆን የሰበር አቤቱታውን በሚያጠናክር መልክ የቀረበ ነው፡፡

እኛም በሰበር አቤቱታው ያስቀርባል ሲባል የተያዘውን ጭብጥ መሠረት በማድረግ የግራ ቀኙ ክርክር አግባብ ካላቸው ህጐች አንፃር መርምረናል ፡፡

አመልካች ለሰበር አቤቱታቸው ምክንያት ያደረጉት በሥር ፍርድ ቤት በተጠሪ ላይ ያቀረብኩት ክስ በይርጋ ቀሪ አይሆንም፣ በሥር ፍርድ ቤትም ያልቀረበ መቃወሚያ በሰበር ደረጃ ሊቀርብ አይገባም በሚል ሲሆን ተጠሪ መቃወሚያ በቃል ክርክር አቅርቤያለሁ ውሳኔው አግባብ ነው ባይ ናቸው፡፡

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 244/3 መሠረት መቅረብ ከሚገባቸው መቃወሚያዎች ውስጥ ተጠቃለው ካልቀረቡ ያልቀረበው መቃወሚያ ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት የሚያሰናክል ከሆነ ባለጉዳዩ ራሱ ሆነ ብሎ ለማቅረብ ባለመፈለግ እንደተወው የሚቆጠር ለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ ተጠሪ መቃወሚያ በመጀመሪያ ቀነ ቀጠሮ አጠቃለው አለማቅረባቸው አሁን በሰበር ክርክር ያመኑ ሲሆን በሥር መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና ውሳኔም ስለመቅረቡም አልተመዘገበም፡፡ መቃወሚያ ካልቀረበም ተከሳሹ ሆነ ብሎ እንደተወው የሚቆጠር ከመሆኑም በላይ በሥር ፍርድ ቤት ያልተነሳ ክርክር ኋላ በማንሣት ለውሣኔ መሠረት ማድረግ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 329/1 የሚፃረር ነው፡፡

የክልሉ ሰበር በሥር ፍርድ ቤት ያልቀረበውን መቃወሚያ በማንሳት የአመልካች ክስ በይርጋ ቀሪ ሆኗል ሲል መወሰኑ የህግ ስህተት ሲሆን፤ አመልካች ሥራ ከተቀጠርኩ ጊዜ ጀምሮ ደመወዝ አልተከፈለኝም ውዝፍ ደመወዜ ይከፈለኝ በሚል ነው፡፡ አመልካች አስራ ሦስት ወር ለተጠሪ መስራታቸው ተረጋግጧል፡፡ አመልካች የጠየቁት የውዝፍ ደመወዝ ክፍያ የይርጋ መቃወም በተጠሪ ካልቀረበበት የማይከፈልበት ምክንያት የለም፡፡

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአሁኑ ተጠሪ የተነሳ የይርጋ ጥያቄ ሳይኖር የአመልካች ክስ በይርጋ ቀሪ ማድረጉ የሕግ ስህተት ስለሆነ የሚከተለው ውሣኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሣ ኔ

 

1. በሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቁጥር 05/1/60/06 ግንቦት ዐ5 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ በፍ.ብ.ሥ.ሥ.ሕግ ቁጥር 348/1 መሠረት ተሽሯል፡፡

2.  የሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፈፋን ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ.ቁ.19-05-06 ጥር

29 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጡት ውሳኔ እና የጅጅጋ ወረዳ ፍርድ ቤት   በመ.ቁ.M/D/J746/05


ሐምሌ ዐ4 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ በፍ.ብ.ሥ.ሥ.ሕግ ቁጥር 348/1 መሠረት ፀንቷል፡፡

3.  ግራ ቀኙ ወጪና ኪሣራቸው ይቻሉ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 


 

ብ/ግ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡