101632 civil procedure interlocutory appeal attachment

ሌሎች ሰዎች በሚከራከሩበት መዝገብ ለክርክሩ መነሻ ከሆነው ንብረት ውስጥ በአንደኛው ወገን ጠያቂነት የታገደን ንብረት ሌላ ሶስተኛ ወገን ለሌላ እዳ አፈፃፀም ንብረቱን ሥለምንፈልገው በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 158 መሰረት የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ይነሳልኝ ብሎ አቤቱታ አቅርቦ ዕግዱ ሊነሳ አይገባም ተብሎበሚሰጠው ብይን ላይ ይግባኝ በሚጠየቅበት ወቅት ከስረ ነገር ውሳኔ በፊት ይግባኝ የሚባልበት አይደለም ሊባልየማይቻል ስለመሆኑ፡-

 

የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 320(3)

 

የሰ/መ/ቁ.101632 መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም.

ዳኞች፡- መድሕን ኪሮስ

 

አልማው ወሌ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- አቢሲኒያ ባንክ አ.ማ. - ነገረ ፈጅ ብርሃኑ አሰፋ ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ ዘይቱ ከማል - የቀረበ የለም

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ መዝገብ አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረበው ተጠሪ እና የተጠሪ ባለቤት ናቸው የተባሉት አቶ ኑሪ ከማል እንደቅደም ተከተላቸው ከሳሽ እና ተከሳሽ በመሆን ከፍቺ ጋር ተያይዞ ክርክር እያካሄዱ በነበረበት መዘገብ የአሁኑ አመልካች በተከሳሹ ግለሰብ ላይ በሌላ መዝገብ ላስፈረደው የብድር ዕዳ በንብረቱ ላይ አፈጻጸሙን መቀጠል ያስችለው ዘንድ ከፍቺ ክርክር ጋር ተያይዞ በተከሳሹ ስም ተመዝግቦ በሚታወቀው ቤት ላይ በከሳሽ ጠያቂነት የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ እንዲነሳለት በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 158 መሰረት ያቀረበውን አቤቱታ እና በአቤቱታው ላይ የተሰጠውን መልስ የመረመረው የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዕግዱ ሊነሳ አይገባም በማለት የሰጠው ብይን እና ብይኑ ጊዜያዊ አገልግሎት ያለው በመሆኑ ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊት ይግባኝ የሚባልበት አይደለም በማለት ይግባኝ ሰሚው የፌዴራል ከፍተኛ  ፍርድ ቤት የሰጠው ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመባቸው በመሆኑ ሊታረሙ ይገባል በማለት ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮ ጉዳዩን በተመሳሳይ ጉዳይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት አስቀድሞ በመዝገብ ቁጥር 86400 በ21/09/2005 ዓ.ም. ከተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም አንጻር ተጠሪዋ ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በጉዳዩ እልባት ማግኘት የሚገባው ዕግዱ ሊነሳ አይገባም በማለት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተሰጠው ብይንጊዜያዊ አገልግሎት ያለው በመሆኑ ከስረ ነገሩ በፍርድ በፊት ይግባኝ የሚባልበት አይደለም በማለት በይግባኝ ሰሚው ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠው ትዕዛዝ ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው ወይስ አይደለም? የሚል ነጥብ መሆኑን በመገንዘብ አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ከዚሁ ነጥብ አንፃር መርምረናል፡፡


በዚህም መሰረት በአንድ ፍርድ ቤት በተሰጠ የማገጃ ትዕዛዝ ላይ ቅሬታ የተሰማው ወይም አላግባብ ነው የሚል ወገን ለፍርድ ቤቱ አቤቱታውን ያቀረበ እንደሆነ እና የቀረበውም አቤቱታ በቂ ምክንያት የሚያስገኝ መሆኑን የተረዳው እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ሰጥቶት የነበረውን የማገጃ ትዕዛዝ እንዲሻሻል፣እንዲነሳ ወይም ጨርሶ እንዲሰረዝ ለማድረግ እንደሚችል በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 158 ስር ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን የማገጃ ትዕዛዝ ይነሳልኝ ጥያቄው በመዝገቡ ተከራካሪ በሆነ ወገን ወይም የክርክሩ አካል ባልሆነ 3ኛ ወገን ጭምር ሊቀርብ የሚችል ነው፡፡በተያዘው ጉዳይ የዕግድ ይነሳልኝ ጥያቄው የቀረበው በአመልካች ባንክ ሲሆን ተጠሪዋ ባለቤቴ ናቸው ከሚሏቸው ግለሰብ ጋር በሚከራከሩበት መዝገብ ባንኩ ተከራካሪ ወገን አይደለም፡፡ይግባኝ ሰሚው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በትዕዛዙ ላይ እንደገለጸው በድንጋጌው  ንዑስ ቁጥር (4) ስር በተጠቀሱት ትዕዛዞች ላይ ካልሆነ በቀር ማናቸውም ፍርድ ቤት ክርክሩን በሚሰማበት ጊዜ በጉዳዩ ላይ ጊዜያዊ አገልግሎት ያለው ትዕዛዝ ሲሰጥ፣ቀነ ቀጠሮ ሲወስን፣በመጀመሪያ ደረጃ በሚቀርብ መቃወሚያ ላይ ተገቢ መስሎ የታየውን ትዕዛዝ ሲሰጥ በእንደእነዚህ ዓይነቶቹ ትዕዛዞች ላይ ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊት ይግባኝ ማለት የማይቻል ስለመሆኑ እና ነገር ግን ለክርክሩ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ከተሰጠ በኃላ ከዚህ በላይ በተገለጹት ትዕዛዞች ላይ ቅሬታ ያለው ሰው ቅሬታውን በስረነገሩ ፍርድ ላይ ከሚያቀርበው ቅሬታ ጋር አጠቃሎ የማቅረብ መብት ያለው ስለመሆኑ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር  320(3) ስር ተደንጓል፡፡

 

ከድንጋጌው አነጋገር በግልጽ መገንዘብ እንደሚቻለው ድንጋጌው ጊዜያዊ አገልግሎት ባላቸው ትዕዛዞች ላይ ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊት ይግባኝ ማቅረብን የከለከለው የስረ ነገሩ ጉዳይ ውሳኔ ባገኘ ጊዜ በስረ ነገሩ ፍርድ ላይ ቅሬታ ያለው ወገን በስረ ነገሩ ፍርድ ላይ ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ በተሰጠበት ጊዜያዊ አገልግሎት ባለው ትዕዛዝ ላይም ቅሬታውን አጠቃሎ የማቅረብ መብት ስለተጠበቀለት ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ አመልካች ባንክ የስረ ነገሩ ጉዳይ ተከራካሪ ወገን ስላልሆነ የስረ ነገሩ ክርክርም ሆነ በክርክሩ መጨረሻ የሚሰጠው ውሳኔ አይመለከተውም፡፡ የዕግድ ትዕዛዙ ሊነሳ ይገባል ወይስ አይገባም? በሚለው ጭብጥ ላይ የሚሰጠው ትዕዛዝ ከአመልካች አንጻር እንደመጨረሻ ፍርድ የሚቆጠር እንጂ ጊዜያዊ አገልግሎት ያለው ትዕዛዝ ነው የሚባል አይደለም፡፡በመሆኑም ይግባኝ ሰሚው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ከዚህ አንጻር በመገንዘብ የቀረበለትን የይግባኝ ቅሬታ መርምሮ ተገቢ ነው የሚለውን ትዕዛዝ ሊሰጥበት ሲገባ ብይኑ ጊዜያዊ አገልግሎት ያለው በመሆኑ ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊት ይግባኝ የሚባልበት አይደለም በማለት መዝገቡን ዘግቶ መመለሱ የፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 320(3) ድንጋጌን እና ዓላማ እና ይዘት ያገናዘበ ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

ሲጠቃለል የእግድ ትዕዛዙ ሊነሳ አይገባም በማለት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተሰጠው ብይን ጊዜያዊ አገልግሎት ያለው በመሆኑ ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊት ይግባኝ የሚባልበት አይደለም በማለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የዕግድ ትዛዙ ሊነሳ አይገባም በማለት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 206422 በ03/07/2006 ዓ.ም. የተሰጠው ብይን ጊዜያዊ አገልግሎት ያለው ስለሆነ ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊት ይግባኝ የሚባልበት አይደለም በማለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ


ቤት በመዝገብ ቁጥር 150681 በ15/08/2006 ዓ.ም. የሰጠው  ትዕዛዝ    በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሮአል፡፡

2. የዕግድ ትዛዙ ሊነሳ አይገባም በማለት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 206422 በ03/07/2006 ዓ.ም. የተሰጠው ብይን ከአመልካች ባንክ አንጻር የመጨረሻ እንጂ ጊዜያዊ አገልግሎት ያለው ትዕዛዝ አይደለም በማለት ወስነናል፡፡

3. ይህንኑ ተገንዝቦ የቀረበለትን ይግባኝ በፍሬ ጉዳዩ ረገድ መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲመለስ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 341(1) መሰረት ወስነናል፡፡በዚሁ መሰረት ተገቢውን መፈጸም ያስችለው ዘንድ የውሳኔው ግልባጭ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይላክ፡፡

4.  የሰበር ክርክሩን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

5.  ውሳኔ ያገኘ በመሆኑ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

 


 

ብ/ይ


የማይነበብ አምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::