90713 civil procedure property law immovable property intervention by third party title deed

civil procedure

property law

immovable property

intervention by third party

title deed

 

 

ቤትና ይዞታን በሚመለከት በሚደረግ ክርክር አንድ ጣልቃ ገብ አመልካች ክርክር በሚደረግበትቤትና ይዞታ ላይ ጣልቃ ገብቶ ለመከራከር መብት አለኝ በማለት መብቱን የሚያሳዩ ሰነዶችን አቅርቦ እያለ የባለይዞታነት ወይም የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር አላቀረብክም ተብሎ ከወዲሁ ጣልቃ ገብተህ ልትከራከር አትችልም ተብሎ አቤቱታውን ውድቅ ማድረግ አግባብነት የሌለው ሥለመሆኑ

የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 41

 የሰ//. 90713

 

 

መስከረም 29 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- ወ/ሮ አሚና ሰይድ ጠበቃ ይርሳው ጌትነት ቀረቡ ተጠሪዎች፡-1 ወ/ሮ ወለላ ንጋቱ - ጠበቃ ዘርፉ ካብትይመር ቀረቡ

2. የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት - ነ/ፈጅ ማዴቦ ዋንጐ ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ መዝገብ አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት በፍትሐ ብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 41 መሰረት ያቀረቡትን የጣልቃ ገብነት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡

የጉዳዩን አመጣጥ በተመለከተ ከሳሽ የነበሩት የአሁኗ 1ኛ ተጠሪ በዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአሁኑ 2ኛ ተጠሪ ላይ ክስ መመስረታቸውን፣ የክሳቸው ይዘትም ከሳሽ ለኢንቨስትመንት ዓላማ ለማዋል በጨረታ ተወዳድረው እና አሸንፈው የገዙትን 602 ካሬ ሜትር የቦታ ይዞታ ተከሳሽ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር ሊያስረክባቸው ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን የሚገልጽ ሆኖ ይህንኑ ቦታ ነጻ አድርጎ እንዲያስረክባቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት መሆኑን፣ተከሳሹም ርክክቡ የዘገየው የአሁኗ አመልካች በፈጠሩት ችግር ምክንያት መሆኑን እና በክሱ መሰረት ቦታውን ለማስረከብ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጾ መልስ መስጠቱን፣አመልካች የጣልቃ ገብነት አቤቱታ ያቀረቡትም ጉዳዩ በዚህ ደረጃ ላይ እያለ መሆኑን፣ፍርድ ቤቱም የጣልቃ ገብነት ማመልከቻውን እና አባሪ ሰነዶችን ከመረመረ በኃላ አመልካች በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው ለመከራከር የሚያስችላቸውን በቂ ምክንያት አላቀረቡም በማለት የጣልቃ ገብነት ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉን እና አመልካች አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡትም ለክልሉ የበላይ ፍርድ ቤቶች ያቀረቡት ይግባኝ እና የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት በማጣቱ መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡

የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በተጠሪዎች መካከል ክርክር የተነሳበት ንብረት በሟች ባለቤታቸው ሐጅ መሐመድ ዑመር ስም ተመዝግቦ የሚታወቅ መሆኑን እና የአመልካች ሚስትነት እና የልጆች ወራሽነት በፍርድ የተረጋገጠ መሆኑን የሚያሳዩ የተለያዩ ሰነዶችን አመልካች ከአቤቱታቸውጋር አያይዘው አቅርበው እያለ በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው ለመከራከር የሚያስችላቸውን በቂ ምክንያት አላቀረቡም በማለት የስር ፍርድ ቤቶች የአመልካችን የጣልቃ ገብነት አቤቱታ ውድቅ የማድረጋቸውን አግባብነት ከፍትሐ ብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 41 ድንጋጌ   አንጻር


ተጠሪዎች ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ ተደርጎ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን መርምረናል፡፡

በዚህም መሰረት በአንድ ክስ ሌሎች ተከራካሪ ወገኖች በክርክር ላይ ባሉበት ጊዜ ማናቸውም ሶስተኛ ወገን በጉዳዩ ያገባኛል የሚል ሲሆን ከፍርድ ውሳኔ በፊት ጣልቃ ገብ ሆኖ ለመከራከር እንደሚችል እና የጣልቃ ገብነት ማመልከቻው በክሱ ውስጥ ያገባኛል የሚልበትን ምክንያት የሚዘረዝርና በተለይም የመብቱን ሁኔታ የሚገልጽ መሆን እንዳለበት፣እንዲሁም የጣልቃ ገብነት ጥያቄ አቅራቢው በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ ለመከራከር የሚያስችል መብት ያለው መሆን አለመሆኑ በቅድሚያ ሊወሰን እንደሚገባው፣ጣልቃ ለመግባት የሚያስችል መብት የለውም በተባለ ጊዜ መሰናበት እንደሚገባው እና መብት አለው በተባለ ጊዜ ግን የክርክሩ ተካፋይ እንዲሆን ከተደረገ በኃላ ከጣልቃ ገቡ መብት አንፃር ጭምር አጠቃላይ ክርክሩ ተመርምሮ ተገቢ ነው  የሚባል ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን ከፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 41 (1)፣ (2) እና (3) ድንጋጌዎች ይዘት መገንዘብ ይቻላል፡፡

በተያዘው ጉዳይ አመልካች ከቤተሰቦቻቸውጋር የሚኖሩበት በሟች ባለቤታቸው  ስም እንደሚታወቅ እና 189 ካሬ ሜትር ይዞታ እንዳለው የተገለጸው ቤት የሚገኘው 1ኛ ተጠሪ በጨረታ ከ2ኛ ተጠሪ ገዝቸዋለሁ በሚሉት 602 ካሬ ሜትር የቦታ ይዞታ ውስጥመሆኑ በተጠሪዎቹም ያልተካደ ጉዳይ ሲሆን የጣልቃ ገብነት ማመልከቻው የቀረበለት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአመልካችን ጥያቄ ሳይቀበል የቀረው አመልካች ከግብር ደረሰኞች በስተቀር ባለይዞታ ወይም ባለቤት መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የባለቤትነት  ሰነድ አላቀረቡም፣ደረሰኞቹም የሚታወቁት በአመልካች ስም አይደለም፣ሰነዶቹ የሚያመለክቱት ክስ ያስነሳውን ይዞታ ስለመሆኑም የቀረበ ማረጋገጫ የለም በማለት መሆኑን የብይኑ ግልባጭ ያመለክታል፡፡

ይሁን እንጂ አመልካች ለጣልቃ ገብነት ማመልከቻው ምክንያት ያደረጉት ቤትና ይዞታ በግብር ደረሰኞች የሚታወቀው በሟች ባለቤት ስም ቢሆንም አመልካች ሚስትነታቸውን እና የልጆችን ወራሽነት በፍርድ ቤት ያረጋገጡ መሆኑ በተረጋገጠበት እና የባለይዞታነት  ወይም የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ማቅረብ ያልቻለ ተከራካሪ ወገን ክርክር ባስነሳው ቤት እና ይዞታ ላይ አለኝ የሚለውን መብት የባለይዞታነት ወይም የቤት ባለቤትነት ማረጋጫ ሰነድ በማቅረብ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ማስረጃ ማስረዳት የማይችል ስለመሆኑ ግልጽ የሆነ የሕግ ክልከላ በሌለበት ሁኔታ የጣልቃ ገብነት ጥያቄው የቀረበለት ፍርድ ቤት አመልካች በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው ለመከራከር የሚያስችላቸውን በቂ ምክንያት አላቀረቡም በማለት የሰጠው እና በክልሉ የበላይ ፍርድ ቤቶች ተቀባይነት ያገኘው ብይን ከላይ ከተጠቀሰው የፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 41 ድንጋጌ ይዘት እና መንፈስ አንጻር ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡ የአመልካች የጣልቃ ገብነት ጥያቄ መሰረት የሚያደርገው የካሳ እና የምትክ ቦታ መብትን ብቻ ሳይሆን የኢንቨስትመንት የቅድሚያ መብትን ጭምር  ስለመሆኑ ከመዝገቡ መገንዘብ የተቻለ ሲሆን አመልካች በጣልቃ ገብነት ሊያቀርቡ የሚችሉትን ክርክር ይዘት እና አድማስ በተሟላ ሁኔታ መገንዘብ የሚቻለው ጥያቄአቸው ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ጉዳዩ እንዲገቡ ሲደረግ ነው፡፡

በሌላ በኩል በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 41 መሰረት በጣልቃ ገብነት መከራከር የሚቻለው ከፍርድ ውሳኔ በፊት መሆኑ በድንጋጌው ንዑስ ቁጥር (1) የተመለከተ ሲሆን ጉዳዩ የፍርድ ውሳኔ ካገኘ በኃላ በሆነ ጊዜ ግን በክርክሩ ውስጥ ተካፋይ መሆን የሚገባውና ተካፋይ ባልሆነበት ክርክር የተሰጠው ፍርድ መብቴን ይነካል የሚል ሰው ተነክቶብኛል የሚለውን መብት


ማስከበር  የሚችለው    በፍትሐብሔር    ስነ  ስርዓት   ሕግ   ቁጥር   358   ድንጋጌ   መሰረት ነው፡፡በመሆኑም አመልካች የጣልቃ ገብነት አቤቱታ ያቀረቡበት ጉዳይ በተጠሪዎች መካከል ክርክሩ ቀጥሎ ውሳኔ ተሰጥቶበት ከሆነ የአመልካች አቤቱታ ሊስተናገድ የሚገባው በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር   358 ድንጋጌ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ሲጠቃለል የአመልካችን የጣልቃ ገብነት ማመልከቻ ውድቅ በማድረግ በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 ው ሳ ኔ

1. የአመልካችን የጣልቃ ገብነት ማመልከቻ ውድቅ በማድረግ በዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 09114 በ05/03/2005 ዓ.ም ተሰጥቶ በጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና በደ/ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት እንደቅደም ተከተሉ በመዝገብ ቁጥር 06769 በ05/06/2005 ዓ.ም. በውሳኔ እና በመዝገብ  ቁጥር 58897 በ13/07/2005 ዓ.ም. በትዕዛዝ የፀናው ብይን በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር

348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2. አመልካች በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 41 በተደነገገው መሰረት በጉዳዩ በጣልቃ ገብነት ለመከራከር የሚያስችል መብት ነበራቸው በማለት ወስነናል፡፡

3. አመልካች የጣልቃ ገብነት ማመልከቻ ያቀረቡበት ተጠሪዎች ከሳሽ እና ተከሳሽ በመሆን የሚከራከሩበት ጉዳይ የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሚደርስበት ቀን ውሳኔ ያላገኘ ከሆነ አመልካች በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 41 ድንጋጌ መሰረት የተሟላ ክርክር እንዲያቀርቡ በማድረግ፤ጉዳዩ ውሳኔ አግኝቶ ከሆነ ደግሞ አመልካች በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 358 ድንጋጌ በተዘረጋው ስርዓት መሰረትየመቃወም አቤቱታቸውን አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ በማድረግ የሶስቱንም ተከራካሪ ወገኖች አጠቃላይ ክርክር መርምሮ ተገቢ ነው የሚለውን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩ ለዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲመለስ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር  341(1) መሰረት ወስነናል፡፡

4. በዚሁ መሰረት መፈጸም ያስችለው ዘንድ የውሳኔው ግልባጭ ለዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤እንዲያውቁት ደግሞ ለጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ለደ/ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ይላክ፡፡

5.  የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

6.  ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::

90713