96378 criminal procedure/ appeal/ application of appeal decision on co-accuseds

ከስር ተከሳሾች መካከል ፍ/ቤት የሠጠው ውሣኔ ለአንዱየሚጠቅም
በሆነ ጊዜና ይግባኝ ባዩ ጋር ተከሠውጥፋተኛ ተብለው የተቀጡ
ሠዎች ይግባኝ ቢያቀርቡ ኖሮ በይግባኝ ሠሚው ፍቤት ውሣኔ
ሊጠቅሙ ይችሉ የነበረ መሆኑ ከተረጋገጠ ይግባኝ ሠሚዉ ፍ/ቤት
የሠጠው ውሣኔ ይግባኝ ላላቀረቡት ተከሳሾች ጭምር ተፈፃሚነት
ሊኖረው የሚገባ ሥለመሆኑ፣
የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁጥር 196/1/ /ሀ/ /ለ/

የሰ//.96378

ህዳር 25 ቀን 2007 ዓ.ም

ዳኞች፡-አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- ሀቢብ ጀማል

 

ተጠሪ፡- የደ/ብ/ብ/ሕ/ብ/ክ/መንግስት ዐ/ሕግ -

 

አቤቱታ አቅራቢዎች፡- 1.ረዳት ሳጅን መሐመድ እንድሪስ      ጉዳዩን ተከታታዮች ተስፋዬ 2. አብዱ ኡመር                                   አለሙ እና ወሰላ ከድር

3. ደግፌ አለሙ                     ቀረቡ

 

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የወንጀል ክርክርን የሚመለከት ሲሆን መዝገቡ የተከፈተው በሀቢብ ጀማል አመልካችነት ሁኖ ከተጠሪ ጋር ክርክሩ ተካሂዶ ይህ ችሎት ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ/ም በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበው ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ/ም በዚህ ችሎት የተሰጠው ውሳኔ በስር ፍርድ ቤት ከሀቢብ ጀማል ጋር ተከሳሽ የነበሩትን የአሁኑ አቤቱታ አቅራቢዎችንም የሚጠቅም በመሆኑ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 196 ድንጋጌ መሰረት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል በማለት ህዳር 02 ቀን 2007 ዓ/ም ማመልከቻ ስለአቀረቡ ነው፡፡ ይህ ችሎትም ይህንኑ የአቤቱታ አቅራቢዎችን ጥያቄ ለማስተናገድ ይቻለው ዘንድ ተጠሪ አስተያየት እንዲሰጥበት ያደረገ ሲሆን ተጠሪ ህዳር 19 ቀን 2007 ዓ/ም ባቀረበው አስተያየት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ/ም በተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ተጠቃሚ መሆን ያለባቸው መሆኑን የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 196 ከአስቀመጠው ድንጋጌ የሚገነዘበው መሆኑን ዘርዝሮ አቤቱታ አቅራቢዎች አቶ ሀቢብ ጀማል ጥፋተኛ በተባሉበት በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 422(1) ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ ተብለው በስር  ፍርድ ቤት የቀረቡባቸው የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች መሰረት ተደርገው  ቅጣት ሊወሰንባቸው እንደሚገባ ገልፆ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

 

እኛም ጉዳዩን ከሕጉ ጋር አገናዝበን ተመልክተናል፡፡


የጉዳዩ መነሻ በደ/ብ/ብ/ሕ/ብ/ክልላዊ መንግስት የስልጤ ዞን ዐ/ሕግ ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ/ም በዋለው ችሎት ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት የጥፋተኝነት እና ተገቢውን የቅጣት ውሳኔ በሰጣቸው አቶ ሃቢብ ጀማልና በአሁኑ አቤቱታ አቅራቢዎች ላይ አራቱም ተከሳሾች በወ/ህ/ቁ 32/1//ሀ/፣ 37፣ 27/1/ እና 671/1/ሀ/ ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የማይገባቸውን ብልፅግና ለማግኘትና ለሌላውም ለማስገኘት በማሰብ በስልጤ ወረዳ ውስጥ አሻኖ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ከወራቤ ወደ ቡታጅራ በሚወስደው አስፋልት መንገድ ላይ ሚያዚያ 08 ቀን 2005 ዓ/ም ከምሽቱ 5፡00 ሰኣት እስከ 7፡30 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ የውንብድና ወንጀል ተግባር ለመፈፀም አስቀድመው በማሰብ በቡድን /ህብረት/ ሁነውና ተደራጅተው የጦር መሳሪያና ለዚሁ ተግባር የሚያግዛቸውን ተሽከርካሪ ጭምር በማዘጋጀት በመንገዱ ላይ ከአዲስ አበባ ወደ ወራቤ ምርጥ ዘር እና ሰዎችን ጭኖ ይጓዝ የነበረውንና በአቶ አብዱረዛቅ ዑመር አማካኝነት የሚሽከረከረውን ኤፍ.ኤስ.አር መኪና በማስቆም ከባድ የሆነ የውንብድና ወንጀል ለመፈፀም ሞክረዋል የሚል ሁኖ እያንዳንዱ ግብረ አበር በወቅቱ ፈፀመ የተባለውን ድርጊትም ክሱ ይዘረዝራል፡፡

 

የአሁን አቤቱታ አቅራቢዎች በተከሳሻነታቸው ቀርበው ድርጊቱን አልፈፀምነም፤ ጥፋተኛም አይደለንም በማለት ክደው ተከራክረዋል፡፡ በአቃቤ ሕግ በኩል በማስረጃነት የሰው ማስረጃና የሰነድ ማስረጃዎች ቀርበዋል፡፡ ከዚህም በኋላ ሁሉም ተከሳሾች እንዲከላከሉ ተደርጎ የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን አሰምተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ ተካሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው በአቃቤ ሕግ ተነግሮባቸው በመከላከያ ማስረጃዎቻቸው አላስተባበሉም በሚል ምክንያት በአቃቤ ሕግ በተጠቀሰው ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ አድርጎአል፡፡ ቅጣቱን በተመለከተም የግራ ቀኙን አስተያየት ተቀብሎ ከቅጣት አወሳሰን መመሪያ ጋር  አገናዝቦ መመርመሩን በማጣቀስ አቶ ሀቢብ ጀማልንና የአሁኑ አቤቱታአቅራቢ ከሆኑት 1ኛውን (የሥር 1ኛ ተከሳሽ) እና 2ኛውን (የሥር 2ኛ ተከሳሽን) እያንዳንዳቸውን በሰባት ዓመት፣ የስር 3ኛ ተከሳሽን (የአሁኑን ሶስተኛ አቤቱታ አቅራቢን) ደግሞ በስድስት አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ አቶ ሀቢብ ጀማል ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣ የሰበር አቤቱታቸውን ደግሞ ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የአሁኑ አቤቱታ አቅራቢዎች ግን በዚህ አግባብ የይግባኝና የሠበር አቤቱታቸውን ስለማቅረባቸው የክርክሩ ሂደት አያሳይም፡፡

 

ሆኖም ከአቤቱታ አቅራቢዎች ጋር በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ4ኛ ተከሳሽነት ተሰይሞ የነበረውና በበታች ፍርድ ቤቶች የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ የተሰጠበት አቶ ሃቢብ ጀማል በሕጉ አግባብ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ለዚህ ችሎት የሠበር አቤቱታ አቅርቦ ጉዳዩ ተጠሪ ባለበት ከተጣራ በኋላ ተጠሪ አድራጎቱ የሚሸፈንበትን የሕግ ድንጋጌ በመለየትና የበታች ፍርድ ቤቶች የጥፋተኝነት ውሳኔ የሰጡበት ድንጋጌ ለስር ተከሳሾች አድራጎት አግባብነት የሌለው መሆኑን ዘርዝሮ በሰጠው መልስ መነሻ ይህ ችሎት ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት የስር ተከሳሾች አድራጎት የሚያቋቁመው በወ/መ/ሕግ አንቀጽ 32(1(ለ)፣ 33 እና 422(1) ድንጋጌ መሆኑን ገልፆ አቶ ሀቢብ ጀማልን በዚሁ ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ አድርጎ የቅጣት ውሳኔውንም በዚሁ ድንጋጌ አግባብ ወስኗል፡፡ ይህ ውሳኔ በሕግ አተገባበርና አተረጓጎም ረገድ የበታች ፍርድ ቤቶች የፈጸሙበትን ስህተት ከማረሙም በላይ በውጤቱ ደግሞ አቶ ሀቢብ ጀማልን የጠቀመ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከስር ተከሳሾች መካከል አንዱ ይግባኝ ጠይቆ የይግባኝ ሰሚው ፍርድ  ቤት የሰጠው  ውሳኔ ለይግባኝ ባዩ የሚጠቅም በሆነ ጊዜና ከይግባኝ ባዩ    ጋር


ተከሰው ጥፋተኛ ተብለው የተቀጡ ሰዎች ይግባኝ ቢያቀርቡ ኑሮ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔ ሊጠቀሙ ይችሉ የነበረ መሆኑ ከተረጋገጠ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ይግባኝ ላላቀረቡት ተከሳሾች ጭምር ተፈፃሚነት ሊኖረው እንደሚገባ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 196(1(ሀ) እና(ለ) ድንጋጌዎች ስር በግልፅ ተመልክቷል፡፡ ይህ ድንጋጌ ለዚህ ችሎት የዳኝነት አሰጣጥ ስርዓትም ተፈፃሚነት ያለው ነው፡፡ ምክንያቱም ችሎቱ የሚመራበት የተለየ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ የለምና፡፡ ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ስንመለከተው የአሁኑ አቤቱታ አቅራቢዎች ከአቶ ሀቢብ ጀማል ጋር ለዚህ ችሎት አቤቱታ ቢያቀርቡ ኑሮ የፍርዱ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችሉ የነበረ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ በመሆኑም አቶ ሀቢብ ጀማልን በተመለከተ ይህ ችሎት ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ.ም የሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 196(1))(ሀ) (ለ) መሰረት ለአሁኑ አቤቱታ አቅራቢዎች ላይም ተፈጻሚነት አለው ብለናል፡፡

 

ቅጣቱን በተመለከተ ግን አቶ ሀቢብ ጀማል ላይ የተሠጠው እንዳለ ተግባራዊ ይሁን የሚል ግልፅ ድንጋጌ ከወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 196 ድንጋጌ ስር አለ ለማለት ስለማይቻልና በመርህ ደረጃም እያንዳንዱ አጥፊ ሊቀጣ የሚገባው በተሳትፎውና ግላዊ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ ስለመሆኑ ከወ/መ/ሕጉ አንቀጽ 40 ድንጋጌ እና ከወንጀል ቅጣት አወሳሰን መርሆዎች የምንገነዘበው በመሆኑ የአሁኑ አቤቱታ አቅራቢዎች ላይ የሚጣለው የቅጣት  መጠንን መመልከቱ ተገቢ ሁኖ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ስንመለከተው ከአሁኑ  ጥያቄ አቅራቢዎች ውስጥ 1ኛው ረዳት ሳጅን መሀመድ እንድሪስ፣ እና 2ኛው አብዲ አሙር ከሀቢብ ጀማል ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ የተቀጡ በመሆኑ በአቶ ሀቢብ ጀማል ላይ በዚህ ችሎት የተጣለው ቅጣት ሙሉ በሙሉ ተፈፃሚነት ያለው ሁኖ አግኝተናል፡፡ ዐቃቤ ሕግ በጥያቄ አቅራቢዎች ላይ በቅጣት ማክበጃነት በስር ፍርድ ቤት የተያዙት ምክንያቶች እንዲያዙ የጠየቀ ቢሆንም ይህ ችሎት በአቶ ሀቢብ ጀማል ላይ የቅጣት ውሳኔ ሲሰጥ በከፊል ውድቅ ያደረጋቸው በመሆኑ በአሁኑ ጥያቄ አቅራቢዎች ላይም ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሚያገኙበትን ሕጋዊ ምክንያት አላገኘም፡፡

 

3ኛውን ጥያቄ አቅራቢ አቶ ደግፌ አለሙን በተመለከተ በስር ፍርድ ቤት የተያዙለት የቅጣት ማቅላያ ምክንያቶች ሁለት ናቸው፡፡ ይሄውም ሪኮርድ የሌለበት መሆኑና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑ ናቸው፡፡ ይህንኑ ይዘን የቅጣት እርከኑን ስንመለከተው በአንድ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት ከእርከን 11 ወደ እርከን 12 ከፍ የሚል ሲሆን ጥያቄ አቅራቢው አቶ ደግፌ አለሙ ሁለት የቅጣት ማቅላያ ምክንያት ስላላቸው በመመሪያው አንቀፅ 13(5) መሰረት በጥያቄ አቅራቢው ላይ ሊጣል ይችል የነበረው ቅጣት በአራት እርከን እንዲወርድ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ ስሌት መሰረትም ከእርከን 12 ወደ እርከን 8 የሚወርድ ሁኖ በዚሁ መጨረሻ እርከን  ስር የተመለከተው የቅጣት አይነትና የመጠን ሬንጅ ከአንድ አመት ከሁለት ወር እስከ አንድ አመት ከስድስት ወርበመሆኑ ለፍ/ቤቱ በተሰጠው ፍቅድ ስልጣን መሰረት አቶ ደግፌ አለሙ ለፈፀሙት ጥፋት ተመጣጣኝ፣ ለመሰል አጥፊዎችን ደግሞ አስተማሪ ነው ብለን ያገኘነው አንድ አመት ከሁለት ወር ፅኑ እስራት ነው፡፡ ሲጠቃለልም የበታች ፍርድ ቤቶች በጥያቄ ባሁኑ ጥያቄ አቅራቢዎች ላይ የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ከላይ በተመለከቱት ሕጋዊ ምክንያቶች መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ተከታዩን ወስነናል፡፡


 ው ሳ ኔ

 

1. በስልጤ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 09466 ሰኔ 28 ቀን  2005  ዓ/ም የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 196/1/ /ሀ/ እና /ለ/ መሰረት ተሻሽሎ ጥያቄ አቅራቢ በሆኑት፡-

ሀ/ ረዳት ሳጅን መሐመድ እንድሪስ ለ/ አብዱ ኡመር

ሐ/ ደግፌ አለሙ ይህ ችሎት ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ/ም በአቶ ሀቢብ ጀማል በሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ተፈፃሚነት አለው ብለናል፡፡ ስለሆነም ጥያቄ አቅራቢዎቹ ሊጠየቁ የሚገባው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 33፣ 32(1(ለ) እና 422(1) ድንጋጌ ስር ነው ብለናል፡፡

 

2. ቅጣቱን በተመለከተም ረዳት ሳጅን መሐመድ እና እንድሪስ አብዱ ኡመር እያንዳንዳቸው በጉዳዩ የታሰሩት ማናቸውም ጊዜ የሚታሰብላቸው ሁኖ ሊቀጡ የሚገባው በአንድ አመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት ነው በማለት ወስነናል፡፡ ደግፌ አለሙን በተመለከተ ደግሞ የታሰሩት የሚታሰብላቸው ሁኖ በአንድ አመት ከሁለት ወር ፅኑ እስራት ነው ብለናል፡፡

3. በዚህ ችሎት ውሳኔ መሰረት ተከታትሎ እንዲያስፈፅም ለወራቤ ማረሚያ ተቋም ይገለጽለት ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

እ/ተ