109055 Labor dispute Cost of litigation Civil procedure code

Labor dispute

Cost of litigation

Civil procedure code art. 463, 464(1)

Proclamation no. 377/2004 art. 161

 አንድ ሰራተኛ ለአሠሪው በሥራ ክርክር ምክንያት ያወጣውን ወጭና ኪሳራ የመክፈል ግዴታ የሚጣልበት በክርክሩ ተረች በመሆኑ ምክንያት ብቻ ሳይሆን ሠራተኛው በአሠሪው ላይ ያቀረበው ክስ ሀሰተኛና በተጭበረበረ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ስለመሆኑ 

የፍትሐ ብሔር ሥነ ስርዓት ህግ ቁጥር 463 ፣465 (1) አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 161 

 

የሰ//.109055

ሐምሌ 29 ቀን 2007 .ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

ዓሊ መሀመድ

ተኽሊት ይመሰል

አዳነ እንደሻው

ቀነአ ቂጤታ

አመልካች - አቶ ጌትነት ከበደ - ቀረቡ  

ተጠሪዎች ሃያት ሜድካል ከሌጅ  አልቀረቡም፡፡

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

   

1.    ጉዳዩ የቀረበው የአመልካች የጠበቃ አበልና ወጭና ኪሳራ ብር 6000/ስድስት ብር/እንዲከፍል የተሰጠው ውሳኔ በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች የስራ ውሉ ከህግ አግባብ ውጭ ተቋርጧል የሚል ክስ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቅርቦ፣ተጠሪ የአመልካች የስራ ውል የተቋረጠው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ በሚደነግገው መሰረት መሆኑን ገልጾ በመከራከሩ፣ የስር /ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ተጠሪ የአመልካችን የስራ ውል ያቋረጠው በህግ አግባብ ነው በማለት አመልካች /ከሳሽ/ ለተጠሪ ለተከሳሽ የጠበቃ አበል ብር 5000 / አምስት ብር/ እና ኪሳራ ብር 1000 /አንድ ብር/ በድምሩ ብር 6000 /ስድስት ብር/ ይክፈል ማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

2.    አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ይግባኝ አቅርቧል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሽ /ተጠሪ/ ለአመልካች የሁለት ወር ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ የስራ ውሉን አቋርጧል፡፡ ስለዚህ መልስ ሰጭ /ተጠሪ/ ለአመልካች የሁለት ወር ደመወዝ ብር 10,697.96 /አስር ስድስት መቶ ዘጠና ሰባት ብር ከዘጠና ስድስት ሳንቲም/ ግብር ተቀንሶ የመክፈል ሃላፊነት አለበት፡፡ በሌሎች ነጥቦች የስር /ቤት የሰጠው ውሳኔ አልተነካም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

3.    አመልካች ጥር 17 ቀን 2007 / በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የስራ ውሉ የተቋረጠው በህግ ከተደነገገው ውጭ መሆኑን ካረጋገጠ በኃላ የሁለት ወር ደመወዝ የማስጠንቀቂያ ክፍያ ብቻ እንዲከፈለኝ የሰጠው ውሳኔና የስር ፍርድ ቤት ለተጠሪ እንዲከፍል የተወሰነብኝን የጠበቃ አበል እና ኪሳራ ሳይሻር መቅረቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ  በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልክቷል፡፡ ተጠሪ ግንቦት 13 ቀን 2007 / በሰጠው መልስ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 161 ሰራተኞቹን የዳኝነት ክፍያ ከመክፈል ነፃ የሚያደርግ እንጂ በአሰሪው ወጭና ኪሳራ እንዳይከፍሉ የሚያደርግ ድንጋጌ አይደለም በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ አመልካች ግንቦት 25 ቀን 2007 / የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡

4.    ጉዳዩ በዚህ ሰበር ችሎት የተያዘው ጭብጥ፤ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ ይዘትና ግራ ቀኙ ያቀረቡት የጽሁፍ ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ሲቀርብ የተያዘውን ጭብጥ ማለትም አመልካች ለተጠሪ ብር 6000 /ስድስት ብር/ የጠበቃ አበልና ኪሳራ እንዲከፍል የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ የህግ መሰረት አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጭብጥ ነጥብ መርምረናል፡፡

5.    ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለመወሰን ለያዝነው ጉዳይ አግባብነት ያላቸውን የፍታብሔር ስነ ስርዓት ህግ እና የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 ድንጋጌዎች መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ በፍርድ ቤት በሚደረግ ክርክር  ተራቸው ስራቸው ኪሳራና ወጭ እንዲከፍል ፍርድ ቤቱ ሊያዝ እንደሚችልና ኪሳራ በቁጥር የተወሰነለት ወገን የተወሰነለትን የኪሳራ ገንዘብ፣ የወጭ ዝርዝር እንደሚያቀርብ የተፈቀደለት ደግሞ የወጭና ኪሳራ ዝርዝር አቅርቦ ለመጠየቅ የሚችል መሆኑን ከፍትሐብሔር ስነ-ስርዓት ህግ ቁጥር 463 ድንጋጌዎች ይዘት መረዳት ይቻላል፡፡ ይኸ የሥነ - ሥርዓት ህጉ ድንጋጌ አዋጅ 377/96 ቁጥር 161 ንዑስ አንቀጽ 2 “ማንኛውም ሰራተኛ ወይም የሰራተኛ ማህበር ፍርድ ቤት ለሚያቀርበው የስራ ክርክር ጉዳይ ከክፍያነፃ ነው በማለት ካስቀመጠው ድንጋጌ ጋር ተጣጥሞ መታየት ያለበት ነው፡፡

6.    የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 162 ንዑስ አንቀጽ 2 ድንጋጌ ከዳኝነት ክፍያ ነፃ ነው በሚል መንገድ ሳይሆንከክፍያ ነፃ ነውበማለት የሚደነግግ መሆኑን ከድንጋጌው አቀራረጽና አውድ ንባብ ለማየት ይቻላል፡፡ ድንጋጌው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 ህጋዊና ሰላማዊ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት የመፍጠር፤ የኢንዱስትሪ ሰላምን የመፍጠር፤ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል የሚነሳ ክርክር በተቀላጠፈ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ የማድረግ አላማዎቹን በሚያሳካ ሁኔታ መተርጎምና ስራ ላይ መዋል ይኖርበታል፡፡ ከላይ የተገለጹትን አላማዎች ለማሳካት፤ ሠራተኞች በግልም ሆነ በጋራ መብታችን በአሠሪው ተጥሶብናል ብለው ሲያስቡ ጉዳዩን አይቶ ውሳኔ ለሚሰጥ ፍርድ ሰጭ አካል ከህግ አግባብና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲታይላቸው ለመጠየቅ የሚችሉበትን ተደራሽና ቀልጣፋ የዳኝነት ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ 

7.    ከዚህ አንፃር ሲታይ ሠራተኛው በፍትሐብሄር ሥነ-ሥርዓት ህግ 465 ንኡስ አንቀጽ 1 በተደነገገው መሰረት ሠራተኛው ሀሰተኛና የተጨበረበረ ክስና ማስረጃ በአሰሪው ላይ ማቅረቡ ካልተረጋገጠ በስተቀር ከህግ አግባብ ውጭ ተጥሶብኛል የሚለውን የመብት ጥያቄ ለፍ/ቤት ወይም በህግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል /አሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ/ አቅርቦ በሙሉ ወይም በከፊል ተረች በሆነ ጊዜ ሁሉ አሰሪው ለክርክሩ ያወጣውን ወጭና ኪሳራ እንዲከፍል በሚያስገድድ መንገድ የአዋጅ አንቀጽ 161 ድንጋጌዎች ከተተረጎሙት ሠራተኞች ተጥሶብናል የሚሉትን መብት ለማስከበር ክስ አቅርበን በፍርድ ቤት ተከራክረን ብንረታ አሰሪው ለጠበቃና ለክርክሩ የወጣውን ወጭ እንድንከፍል ሊወሰንብን ይችላል በሚል ፍራቻና ስጋት መብታቸውን በፍርድ ከመጠየቅ የሚገደቡበትን ሁኔታ የሚፈጥር ይሆናል፡፡ ይህም ከላይ የገለጽናቸውን የአዋጁን መሰረታዊ ዓላማዎች የሚያሳካ አይደለም፡፡ በመሆኑም ሰራተኛ ለአሰሪው በስራ ክርክር ምክንያት ያወጣውን ወጭና ኪሳራ የመክፈል ግዴታ የሚጣልበት በክርክሩ ተረች በመሆኑ ምክንያት ብቻ ሳይሆን ሰራተኛው በአሰሪው ላይ ያቀረበው ክስ ሀሰተኛና በተጭበርበረ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ሆኖ ሲገኝ መሆን እንዳለበት የፍታብሔር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 463 የፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 465 ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌዎች ከአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 161 ድንጋጌ ጋር በሚጣጣም መንገድ በመተርጎም ለመረዳት ይቻላል፡፡

8.    በያዝነው ጉዳይ  አመልካች ከህግ አግባብ የስራ ውሉ ተቋርጦብኛል በሚል እምነት ክስ ያቀረበ መሆኑና በክርክር ሂደት አሰሪው /ተጠሪ/ያቀረበው ማስረጃ ከሰራተኛው /አመልካች/ የተሻለ ሆኖ ስለተገኘ የስር ፍርድ ቤት ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት የወሰነ መሆኑን ተረድተናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አመልካችንና የተጠሪን ክርክር በይግባኝ ያየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ አመልካችን የስራ ውል ከማቋረጡ በፊት የሁለት ወር ማስጠንቀቂያ መስጠት ነበረበት በማለት ተጠሪ ለአመልካች የሁለት ወር ደመወዝ የማስጠንቀቂያ ክፍያ እንዲከፍል የወሰነ መሆኑን ይግባኝ ሰሚው /ቤት ከሰጠው ውሳኔ ተረድተናል፡፡ ይህም አመልካች በክርክሩ ሙሉ ለሙሉ ተረች አለመሆኑንና  በከፊል መብት ያለው መሆኑ ተረጋግጦ ውሳኔ የተሰጠለት መሆኑን ያሳያል፡፡

9.    ከላይ በዝርዝር ከሰጠነው የህግ ትርጉምና አመልካችና ተጠሪ በስር ፍርድ ቤት እና በይግባኝ ካቀረቡት ክርክር መሰረታዊ ባህሪ አንፃር ሲታይ፣ አመልካች ለተጠሪ የጠበቃ አበል ብር 5000/ አምስት ብር/ ኪሳራ ብር 1000 /አንድ ብር/ በድምሩ ብር 6000 /ስድስት ብር/ እንዲከፍል የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል፡፡ 

1.     የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 139696 ታህሳስ 8 ቀን 2007 / የሰጠው ውሳኔ ተሻሽሏል፡፡

2.     የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ ለአመልካች የሁለት ወር ደመወዝ ብር 10697.96/ አስር ስድስት መቶ ዘጠና ሰባት ብር ከዘጠና ስድስት ሳንቲም/ ግብር ተቀንሶ እንዲከፍል በማለት የሰጠው የውሳኔ ክፍል ጸንቷል፡፡

3.     የፌዴራል ከፍተኛ /ቤት አመልካች በተጠሪ የጠበቃ አበል ብር 5000 /አምስት ሺህ ብር/ኪሳራ ብር 1000 /አንድ ብር/ በድምሩ ብር 6000 /ስድስት ሺብር/እንዲከፍል የሰጠው የውሳኔ ክፍል ተሸሯል፡፡ አመልካች ይህንን ገንዘብ ለተጠሪ የመክፈል ኃላፊነት የለበትም በማለት ወስነናል፡፡

4.     በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ በየራሳቸው ይቻሉ ፡፡

መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡