108785 Labor dispute Dependents’ benefit in case of death Period of limitation in labor dispute

Labor dispute

Dependents’ benefit in case of death

Period of limitation in labor dispute

Proclamation no. 377/2004 art (1)

 

 

ሰራተኛው በስራ ላይ በደረሰበት የሞት አደጋ ምክንያት የሰራተኛው ባለቤትና ሌሎች ጥገኞች የሚያቀርቡት የካሣ ክፍያ ጥያቄ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መቅረብ ያለበት ስለመሆኑ 

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 162 ንዑስ አንቀፅ 1  

የሰ// 108785

ሀምሌ 21 ቀን 2ዐዐ7 .ም

ዳኞች  - አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

ተኸሊት ይመስል

እንደሻው አዳነ

ቀነአ ቂጣታ

አመልካች - ዩሴፍ ተክሌ ህንፃ ሥራ ተቋራጭ ጠበቃ ብሥራት መኮንን  ቀረቡ

ተጠሪ -   / ወርቅነሽ ጌታቸው በራሳቸው  እና ሞግዚት በሆነችላቸው  እነ ሕፃን ረዲኤት ታምራት ከጠበቃ አቶ ፋንቱ አስፋው ጋር ቀረቡ፡፡

መዝገቡን መርምረን  የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል ፡፡

ፍርድ

1.    ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሠጠው ውሣኔ መሠረታዊ  የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ በሥራ ላይ በሚደርስ ጉዳት ለሚስትና በሌሎች ጥገኞች የሚከፈል የካሣ ገንዘብ ጥያቄ የይርጋ የጊዜ ገደብ የሚመለከት ነው ተጠሪ ባለቤቷ የሁለት ልጆች አባት የሆነው ታምራት ሀይሌ አሠሪው በመደበው መኪና ከሌሎች ሠራተኞች ጋር ሲጓጓዝ መኪናው ተገልብጦ ሚያዝያ 23 ቀን 2ዐዐ5 . ህይወቱ ያለመሆኑን ገልፆ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት ለእርሷና ለህፃናቱ ካሣ እንዲከፈላቸው ውሣኔ እንዲሰጥላት ጥር 25 ቀን 2ዐዐ6 . ጠይቃለች ፡፡

2.    አመልካች በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 162 ንሁስ አንቀፅ 4 የተደነገገው የስድስት ወር የይርጋ የጊዜ ገደብ አልፏል በማለት መቃወሚያ አቅርቧል ፡፡ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አመልካች ያቀረበውን መቃወሚያ በመቀበል ክሱ በይርጋ ቀሪ ይሆናል በማለት ብይን ሰጥቷል ፡፡ ተጠሪ ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርባ፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ለጉዳዩ አግባብነት ያለው በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 162 ንዑስ አንቀጽ 1 የተደነገገው የይርጋ ጊዜ ገደብ ነው ፡፡ ስለዚህ ክሱ የቀረበው በዚህ ድንጋጌ የተጠቀሰው ይርጋ የጊዜ ገደብ ከማለፉ በፊት በመሆኑ በይርጋ አይታገድም በማለት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን ሽሮታል ፡፡

3.    አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረበው ይህንን የይግባኝ ሰሚውን ፍርድ ቤት ውሣኔ በመቃወም ሲሆን ተጠሪ ይግባኝ  ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን የሕግ ስህተት የሌለበት መሆኑን ገልፃ ተከራክራለች እኛም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ጉዳዩ በይርጋ አይታገድም በማለት የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 162 ንሁስ አንቀፅ /1/ ድንጋጌ መሠረት በማድረግ የሰጠውን ብይን ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል ፡፡

4.    ጉዳዩን አንደመረመርነው በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 162 ንሁስ አንቀፅ  4 የተደነገገው የስድስት ወር ይርጋ ተፈፃሚ የሚሆነው አሠሪው በሠራተኛው ላይ ወይም ሠራተኛው በአሠሪው ላይ ለሚያቀርበው የደመወዝ፣ የትርፍ ሠዓት ሥራ ክፍያ፣በአል ቀናት ክፍያ ጥያቄና ለመሳሰሉት የክፍያ ጥያቄዎች መሆኑን ከድንጋጌው አቀራረፅና ይዘት ለመረዳት ይቻላል በአዋጅ አንቀፅ 4 በይዘቱም ሆነ በአቀራረፅ ፣የሰራተኛው በስራ ላይ የደረሰበት የሞት አደጋ የሰራተኛው ባለቤትና ሌሎች ጥገኞች በአዋጁ አንቀጽ 110 መሠረት የሚያቀርቡትን የካሣ ክፍያ ጥያቄ በስድስት ወር የይርጋ የጊዜ ገደብ ለመገደብ ታስቦ የተደነገገ ድንጋጌ አይደለም ፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለጉዳዩ አግባብነት ያለው በአዋጅ አንቀፅ 162 ንዑስ አንቀፅ 1 የተደነገገው የይርጋ የጊዜ ገደብ ነው፡፡ተጠሪ ክስ ያቀረበችው በአዋጁ አንቀጽ 162 ንዑስ አንቀጽ 1 የተደነገገው የይርጋ ጊዜ ገደብ  ከማለፉ በፊት በመሆኑ የተጠሪ ክስ በይርጋ አይታገድም በማለት የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የሌለበት ነው በማለት ወስነናል ፡፡

1.    የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 139907 ህዳር 25 ቀን 2007 . የሰ ጠውን ውሣኔ ፀንቷል ፡፡

2.    ተጠሪዎች ያቀረበት ክስ በይርጋ ቀሪ አይሆንም በማለት ወስነናል ፡፡

3.    በዚህ ፍርድ ቤት የወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራቀኙ ይቻቻሉ

መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡