105997 Labor dispute Transfer of employees Collective agreement

Labor dispute

Transfer of employees

Collective agreement

 አንድ ሠራተኛ መብትና ጥቅሙን ሳይነካ ከአንድ የሥራ ቦታ ወደ ሌላ የሥራ ቦታ ወይም የስራ መደብ በማዛወር ማሠራት የአሰሪው አስተዳደራዊ ሥልጣን ነው ሲባል ዝውውሩ ያለህጋዊ ምክንያትና በህብረት ስምምነቱ ከሠፈረው አሰራር ውጪ ይከናወናል ተብሎ ሊተረጎም የማይገባው ስለመሆኑ፣ 

የሰ// 105997

ሚያዚያ 26 ቀን 2ዐዐ7 .

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

ሱልጣን አባተማም

ሙስጠፋ አህመድ

ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- /ሪት ሉሊት አያሌው ማሞ - ቀረቡ 

ተጠሪ፡የኢትዩጵያ መድን ድርጅት - /ፈጅ ማህሌት ዓለሙ - ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

ጉዳዩ ከሰራተኛ የስራ መደብና ቦታ ዝውውር ጋር ተያይዞ የተነሳውን ክርክር የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች ባሁኑ ተጠሪ ላይ በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡ የአመልካች የክስ ይዘትም፡- የተጠሪ ድርጅት አመልካች የኢንዲስትሪ ሰላም አላግባብ ንትርክ እየፈጠሩ መረባሻቸውን ሳያረጋግጥ 26/08/2005 / በፃፈው የአመልካችን የግል ታሪክ በሚያጎድፍ ደብዳቤ ከኦዲት ወደ ማርኬቲንግ ክፍል ያላግባብ በማዘዋወር እርምጃ መውሰዱን ጠቅሰው የተወሰደው እርምጃ እንዲነሳና ወደ ኦዲት ክፍል እንዲመለሱ እንዲሁም የዝውውሩ ደብዳቤ እንዲሰረዝላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ 

የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም፡- አመልካች ከኦዲት ሰራተኞች ጋር ባላቸው አለመግባባት የተነሳ የኢንዲስትሪ እና የስራ ቦታ ሰላም ለመጠበቅ ሲባል የአመልካች የስራ ደረጃ እና ደመወዝ ሳይነካ ዝውውሩ መፈፀሙንና ክሱ ከተመሰረተ በኋላም የአመልካችን ደመወዝ ብር 10,759.00 ማድረጉን ገልፆ ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል በማለት ተከራክሯል፡፡

ጉዳዩ በዚህ መልክ የቀረበለት ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ሰምቶ ጉዳዩን በመመርመር የሥራ መደብ ዝውውሩ ሕጋዊ ነው፣ የዝውውር ደብዳቤም ሊሰረዝ አይገባም በማለት ወስኗል፡፡

በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸው ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- አመልካች ለኢንዲስትሪ ሰላም የፈጠሩት ችግር ስለመኖሩ ሳይረጋገጥ እና በስራው ላይ ያስከተሉት ችግር መኖሩ በተጠሪዎች ምስክሮች ባልተነገረበት ሁኔታ ዝውውሩ ህጋዊ ነው ተብሎ መወሰኑ ያላግባብ ነው የሚል ነው፡፡

ቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡ 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክርና ለሰበር አቤቱታው መነሻ የሆነውን ውሳኔ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡ ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ሲቀርብ የተያዘው ጭብጥ ዝውውሩ ሕጋዊ ነው ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት አመልካች ከአቀረበው ክርክር ይዘትና ከሕጉ ጋር አገናዝቦ ለማየት ይቻል ዘንድ ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩን ከዚሁ ጭብጥ አንጻር ብቻ እንደሚከተለው ተመልክተናል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የአሁን አመልካች ሥራዬን በአግባቡ እየተወጣሁ እያለ አሠሪው ወደ ሌላ የሥራ መደብ ተዛውረሻል በማለት ደብዳቤ ጽፎልኛል፣ ዝውውሩ ከፍላጎቴና ከህብረት ስምምነቱ ውጪ የተደረገ ከመሆኑም በላይ በግል ማህደሬ ላይ ከፍተኛ ችግር የሚያስከትል ነው በማለት ገልጸው ተከራከረው ተጠሪ ዝውውሩ የተደረገበትን ምክንያቶችን ዘርዝሮ በሕግ ከተሠጠው ስልጣን የመነጨ መሆኑንም ጭምር ጠቅሶ መከራከሩን ነው፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር በመጀመሪያ ደረጃ የሰማው የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም የተጠሪ ምስክሮች ቃል አመልካች ከሰራተኞች ጋር ብሎም ከሃላፊዎች ጋር ግጭት የሚፈጥሩ፣የሚሰጣቸውን ስራውም በአግባቡ የማይሰሩ ስለመሆኑ፣የስራ ባልደረቦቻቸው አብረዋቸው ለመስራት የማይመርጧቸው ሰው እንደሆኑ፣ ስራቸውን በአግባቡ ስለማይሰሩ የጊዜ ብክነት፣ አላስፈላጊ ውጪና ያልተቃና ስራ መከሰቱን መመስከራቸውን፣ የአመልካች ምስክር ደግሞ አመልካች በስተመጨረሻ የኦዲት ስራ የሰሩባቸው ሶስት ቅርንጫፎች አስመልክቶ የተፈጠረ ችግር ሳይኖር ስራውን ከአመልካች ጋር መስራታቸውን ገልጸው መመስከራቸውን በውሳኔ ላይ ከአሰፈረ በኋላ የአመልካች ምስክር የሰጡት የምስክርነት ቃል አመልካች አሉባቸው የተባሉትን ከስራው ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮችን ፈጽሞ የሌሉባቸው ስለመሆኑ አስረድተዋል ለማለት የሚያስችል አይደለም፣ አመልካች ስራው ላይ ያሳያሉ የተባሉት ባህርይ በስራ ቅልጥፍና፣ በውጤታማነትና በኢንዲስትሪ ሰላም ላይ አሉታዊ ተእፅኖ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ተጠሪ ድርጅት የአመልካችን ደመወዝ፣ የስራ ደረጃና ሌሌች ጥቅማጥቅሞችን ሳይነካ የፈፀመው የሥራ መደብ ዝውውር ሕጋዊ ነው በማለት ደምድሟል፡፡

ከተጠሪ የሥር ክርክርም ሆነ በዚህ ሰበር ደረጃ ከሰጠው መልስ መገንዘብ የተቻለው ደግሞ በአንድ በኩል ዝውውሩ የተፈጸመው በአመልካች ጥያቄ መነሻ መሆኑን ጠቅሶ የተሻለ ደመወዝ አመልካች እንዲያገኙ ማድረጉን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአመልካችን ተገቢ ያልሆነ ባህርይ  መነሻ በማድረግ ለኢንዱስትሪና ለስራ ቦታ ሰላም የተደረገ ነው በማለት የሚከራከር መሆኑን ነው፡፡

በመሰረቱ አንድ አሰሪ አንድን ሰራተኛ ከአንድ የስራ መደብ ወደ ሌላ የስራ መደብ የማዛወር አስተዳደራዊ ስልጣኑ ነው ተብሎ የሚታመነው አሰሪው ስራንና ሰራተኛን ለማገናኘት የሚችልበት አግባብ ነው በሚል ምክንያት ሆኖ ዝውውሩም ተቀባይነት የሚያገኘው የሰራተኛውን መብትና ጥቅም በማይነካ መልኩና ተመሳሳይ ወደሆነው የስራ መደብ ተከናውኖ ሲገኝ እንጂ ይህንኑ በሚቃረን መልኩ ሊሆን እንደማይገባ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት አግባብነት ያላቸውን የአዋጅ ቁጥር 377/1996 ድንጋጌዎችን በመመርመር በሰ//ቁጥር 40938 እና በሌሎች በርካታ መዛግብት በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት በየትኛውም እርከን የሚገኝ የፍርድ ቤትን የሚያስገድድ የህግ ትርጉም የሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡

በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ አመልካችን ከኦዲት ክፍል ወደ ማርኬቲንግ የስራ መደብ ያዛወራቸው መሆኑን ሳይክድ አዲሱ የስራ መደብ አመልካች ቀድሞ ይሰሩበት ከነበረው የስራ መደብ ጋር ተመሳሳይ የሆነና የአመልካችን መብትና ጥቅም በማይነካ መልኩ መከናወኑንና ለዝውውሩ አብይ ምክንያትም የአመልካች ባህርይ ሁኖ ለኢንዲስትሪ ሰላም ሲባል አመልካች እንዲዛወሩ ከተደረገበት የስራ ቦታ በጡረታ የወጣ ሰራተኛ አመልካች እንዲተኩ ለማድረግ ሲባል መከናወኑን ጠቅሷል፡፡ ሆኖም ተጠሪ ድርጅት ለዝውውሩ ምክንያት ያደረጋቸው እነዚህ ምክንያቶች ባንድ በኩል ከአመልካች ባህርይ ጋር እንደተያያዙ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአመልካች ጥያቄ መነሻና በጡረታ የተገለሉ ሰራተኛን የሥራ መደብ እንዲሸፈኑ ለማድረግ ታሰቦ የተደረገ መሆኑን የሚገልጹ በመሆናቸው ይዘታቸው ሲታይ እርስ በራሳቸው የሚቃረኑ ምክንያቶች መሆናቸውን የሚያስገነዝብ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ አንድ ሰራተኛ በባህርይ ችግር ለኢንዲስትሪ ሰላም አስቸጋሪነቱ ከተረጋገጠ በሕጉ አግባብ ተገቢው ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠው ተደርጎ እንዲታረም ማድረግ የሚቻልበት አግባብ መኖሩ የሚታወቅ ሲሆን በባህርይ ችግር ተዛወረ የተባለን ሰራተኛ ደግሞ የስራ መደቡ ክፍት በመሆኑ እንዲዛወር ተደርጓል በሚል የሚቀርብ ክርክር ዝውውሩ ስራንና ሰራተኛን ለማገናኘት የተደረገ ነው ብሎ ለመደምደም የማያስችል ነው፡፡ ተጠሪ አመልካችን በየጊዜው የሚያዛውራቸው ስለመሆኑ በክርክሩ ሂደት መገለጹም ሲታይ ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ ስራንና ሰራተኛን ለማገናኘት ሲባል ባልተደረገ የሥራ ውል ደግሞ የስራ ውል የሚሻሻልበት አግባብ ያለመኖሩን ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 15 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡

በመሆኑም ተጠሪ የስራ መደቡ ዝውውሩ ሕጋዊ ነው ብሎ የሚያቀርባቸው ምክንያቶች እርስ በራሳቸው የሚቃረኑ በመሆናቸው ተጠሪ ዝውውሩ በህጉ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ያከናወነው ነው በማለት ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ አልተገኘም፡፡

ዝውውሩ ሕጋዊ መሆኑን ያሳያሉ የተባሉት የተጠሪ ምክንያቶች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ናቸው ከተባለ የአሰሪው የዝውውሩ እርምጃ የአስተዳዳሪነት ሥልጣኑን በዘፈቀደ ለማከናወን መነሳቱን ያሳያል ከሚባል በስተቀር የዝውውሩን ህጋዊነት በምንም መመዘኛ አያሳዩም፡፡

ስለሆነም አንድን ሰራተኛ መብትና ጥቅሙን ሳይነካ ከአንድ የስራ ቦታ ወደ ሌላ የሥራ ቦታ ወይም የስራ መደብ በማዛወር ማሰራት የአሰሪው አስተዳደራዊ ሥልጣን (Administrative prerogative) ነው ሲባል ዝውውሩ ያለ ሕጋዊ ምክንያትና በሕብረት ስምምነቱ ከሰፈረው አሰራር ውጪ ይከናወናል ተብሎ ሊተረጎም የማይገባው ስለመሆኑ ከአሰሪና ሰራተኛ ሕጉ አጠቃላይ መሰረታዊ አላማና ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ//ቁጥር 5711777113 እና በሌሎች በርካታ መዛግብት ከሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ሁኖ ስለአገኘን ተጠሪ አመልካችን ያዛወረበት ሁኔታ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ መሰረዝ ሲገባው በስር ፍርድ ቤቶች ተቀባይነት ማግኘቱ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ሁኖ አግኝተናል፡፡ ተጠሪ ያከናወነው ዝውውር ሕገ ወጥ ነው ከተባለም የአመልካችን ባህርይ በተመለከተ በዝውውር ደብዳቤው የገለፀበት አግባብ ከአመልካች የግል ማህደር ጋር ሊኖር የማይገባ በመሆኑ ሊሰረዝ የሚገባው ሁኖ አግኝተናል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ተከታዩን ወስናል፡፡

   

1.    በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 10179 መጋቢት 09 ቀን 2006 / ተሰጥቶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 139826 ነሐሴ 07 ቀን 2006 / የፀናው ውሳኔ በፍ///// 348 (1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2.    የአመልካች ዝውውር ሕገ ወጥ ነው፣ ሊሰረዝ ይገባል ብለናል፡፡ አመልካች ይሰሩበት ከነበረው የኦዲት የስራ መደብ ወደ ማርኬቲንግ የስራ መደብ ሊዛወሩ አይገባም፣ የዝወውሩ ደብዳቤም ሙሉ በሙሉ ሊሰረዝ ይገባል ከአመልካች ማህደር ሊያያዝ አይገባም ብለናል፡፡

3.    በዚህ ሰበር ችሎት በተደረገው የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ

 

ማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡