110615 labor law dispute/ termination of contract of employment/ brawl at work place

Labor dispute

Termination of contract of employment without notice

Brawl at work place

Proclamation no 377/2004 art. 32/1/a, 13/2/ and 27

 

የሰ//. 110615

ግንቦት 28 ቀን 2007 ዓ/ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

ሱልጣን አባተማም

ሙስጠፋ አህመድ

ተኸሊት ይመስል

አመልካች፡- ኃብተሚካኤል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር -

   ሥራ አስኪያጅ አቶ ተካልኝ ሁንዴ ቀረቡ

ተጠሪ፡- አቶ ታመነ ታደሰ ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 22279 ሐምሌ 10 ቀን 2006 . የሰጠው ውሳኔና የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 187457 የካቲት 9 ቀን 2007 . የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ሥህተት ያለበት በመሆኑ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው የሰበታ ሀዋሳ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በወረዳው ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሕግ አግባብ ውጭ የሥራ ውሌ ተቋርጧል በማለት ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ አመልካች ሆነው ተከራክረዋል፡፡

1.   ከሳሽ (ተጠሪ) ከተከሳሽ (አመልካች )ድርጅት ጋር በሠራተኝነት ተቀጥሮ ሲሰራ ተከሳሽ ከሕግ አግባብ ውጭ የሥራ ውሉን ያቋረጠው መሆኑን ገልፆ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ መሠረት የተለያዩ ክፍያዎችን ተከሳሽ እንዲከፍል ይወሰንልኝ በማለት ክስ አቅርቧል፡፡አመልካች በተከሳሽነት ቀርቦ ከሳሽ በጥቅምት 2 ቀን 2006 ዓ.ም አደም ገረመው ከሚባል ሠራተኛ ጋር በመደባደብ በሥራ ቦታ ሁከት የፈጠረ መሆኑንና ህዳር 25 ቀን 2006 ዓ.ም የድርጅቱን ሥራ አስኪያጅ አልታዘዝም ከማለቱም በላይ “ዝም በል አንተ አሽሻም ፡፡ አሽሽ አጭስህ መጥተሕ አፍህን አትክፈት፡፡ አእምሮ የሚያደነዝዝ አሽሽ ወስደህ ደንዝዘህ መጥተህ አታደንዝዘን” በማለት የተሳደበና ችግር የፈጠረ መሆኑ ከሥራ የተሠናበተ መሆኑን ገልፆ ተከራክሯል ፡፡ የወረዳው ፍርድ ቤት የከሳሽንና የተከሳሽን ምስክሮች ሰምቷል የከሳሽ አንደኛው ምስክር ከሳሽ ከቅርብ አለቃው ጋር መጣላቱን የመሰከረ መሆኑንና የተከሳሽ ምስክሮች ጥቅምት 7 ቀን 1986 ዓ.ም ከሳሽ የድርጅቱን አንድ ሠራተኛ የደበደበ መሆኑንና 25/03/2006 ዓ.ም ከሳሽ የቅርብ አለቃውን ሀሽሻም ሀሽሽ አጭሰህ መጥተህ ትናገረናለህ ጠብ እና ግርግር ያነሳ መሆኑን በማረጋገጥ እንደመሰክሩ የሥር ፍርድ ቤት በውሣኔው አስፍሮ ተጠሪ /ከሳሽ/ አለቃውን አልታዘዘም ማለቱንና መስደቡ የተረጋገጠ በመሆኑ የሥራ ውሉ የተቋረጠው በሕግ አግባብ ነው በማለት የተጠሪ /ከሳሽን/ ክስ ውድቅ አድርጎታል ፡፡

2.   ተጠሪ በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል ፡፡ የልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክረክር ከሰማ በኃላ አመልካች የተጠሪን የስራ ውል ያቋረጠው ተጠሪ አለቃውን ሰብዓዊ መብቱን በሚነካ መልኩ ስለሰደበው መሆኑ እንደተረጋገጠ ገልፆ አመልካች ተጠሪው ለፈፀመው ለዚህ ጥፋት ማስጠንቀቂያ መስጠት ሲገባው ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውሉን ማቋረጡ የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 27 ንዑስ አንቀጽ 1 እና ንዑስ አንቀፅ 4 ድንጋጌ መስፈርት የሚያሟላ አይደለም በማለት ስንብቱ ከሕግ አግባብ ውጭ የተፈፀመ ነው ተብሎ አመልካች ብር 8,284.24 /ስምንት ሁለት መቶ ሰማንያ አራት ብር ከሃያ አራት ሳንቲም ) ለተጠሪ እንዲከፍል ውሣኔ ሰጥቷል ፡፡ አመልካች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት አቅርቧል ፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የተጠሪ አድርጎትጠብናአንባጓሮ ማንሣት ነው ተብሎ ሊያዝ አይገባም በማለት የልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ አፅንቶታል ፡፡

3.   አመልካች የካቲት 24 ቀን 2007 . በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ የቅርብ ኃላፊውን አንድ ሠራተኛ ወደሌላ ቦታ ሄዶ እንዲሠራ ትዕዛዝ ሲሰጥ ትዕዛዙን ከመቃወም አልፈው የቅርብ አለቃውን አንተ ሀሽሻም በማለት የተሳደበና አምባጓሮ የፈጠረ፤ በዚህ ምክንያት የምርት ሥራው እንዲገታ ያደረገ መሆኑን በማስረጃ ተረጋግጧል ፡፡ ይህ የተጠሪ አድራጎት የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 27/1/ መስፈርት አያሟላም በማለት የልዩ ዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጡት የሕግ ትርጉም መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል ፡፡ተጠሪ በበኩሌ ሚያዚያ 6 ቀን 2007 . በተፃፈ መልስ እኔ አለቃዬን አልተሳደብኩም ፡፡ ሁከትም አልፈጠርኩም ፡፡ ስለዚህ ስንብቱ ህገ ወጥ ነው ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ ሰጥቷል ፡፡ አመልካች ሚያዝያ 20 ቀን 2007 / የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡

4.   ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ግራቀኙ ያቀረቡት የፅሑፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት አመልካች የተጠሪን የሥራ ውል ያቋረጠው ከሕግ አግባብ ውጭ ነው በማለት የሰጡት ውሣኔ የሕጉን ድንጋጌዎች መሠረት ያደረገ ነው ወይስ አይደለም ? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

5.   ጉዳዩን እንደመረመርነው ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለመወሰን በመጀመሪያ ተጠሪ ህዳር 25 ቀን 2006 . በሥራ ቦታ ያሳየውን ባህሪይና የፈፀመውን አድራጎት በተመለከተ ፍሬጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ያላቸው የወረዳው ፍርድ ቤትና የልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የደረሱበትን የፍሬ ጉዳይና የማስረጃ ምዘና ድምዳሜ መመርመር አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል ፡፡ ህዳር 25 ቀን 2006 . ተጠሪና ሌሎች አራት ሠራተኞች ሥራ እየሰሩ እያለ የቅርብ አለቃቸው ከእነሡ መካከል አንድ ሠራተኛ ወደ ሌላ የሥራ ክፍል እንዲሄድና ቀሪዎች አራቱ ቀሪውን ሥራ እንዲያከናውኑ ትዕዛዝ የሰጠ መሆኑ በዚህ ጊዜ ተጠሪ የቅርብ አለቃውን የሥራ ትእዛዝ ከመቃወም አልፎ ሀሽሻም ሀሽሽ አጭስህ መጥተህ ትናገረናለህ በማለት የተሳደበ መሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑንና የተጠሪ ማስረጃ ይህንን በአመልካች ማስረጃ የተረጋገጠውን ፍሬ ጉዳይ ያላስተባበለ መሆኑን የወረዳው /ቤት በውሣኔው በግልፅ አስፍሮታል ፡፡

6.   አመልካች ተጠሪን ከስራ ያሰናበተው ተጠሪ የሥራ ትዕዛዝ ባለመቀበሉና የቅርብ አለቃውን ክብረ ነክ የሆነ ስድብ በመሳደቡ ምክንያት ነው በማለት የወረዳው ፍርድ ቤት የደረሰበትን የፍሬ ጉዳይ ማጣሪትና የማስረጃ ምዘና መደምደሚያ ሙሉ በሙሉ ትክክል ነው በማለት የልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተቀበለው መሆኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 22279 ሀምሌ 10 ቀን 2006 . በሰጠው ውሣኔ በአራተኛው ገፅ የግራቀኙን ክርክርና ማስረጃ ይዘት ከተነተነ በኃላ ‹‹ በአጠቃላይ የመልስ ሰጭ ድርጅት ይግባኝ ባይን ከሥራ ያባረረው እሱ አለቃውን ሰብዓዊ ክብሩን መንካቱን በሚነካ መልኩ ስለሰደበው እንደሆነ ከመዝገቡ ውስጥ የምንረዳው ጉዳይ ነው በማለት በመጨረሻው ፓራግራፍ ካሰፈረው የፍሬ ጉዳይና የማስረጃ ምዘና መደምደሚያ ለመረዳት ይቻላል፡፡

7.   ከዚህ አንፃር ሲታይ ተጠሪ ህዳር 25 ቀን 2006 . በቅርብ አለቃው የተሰጠውን የሥራ ትዕዛዝ ከመቃወም አልፎ የቅርብ አለቃውን አንተ ሀሽሽ አጭሰህ መጥተህ አትናገረንበማለት የተሣደበ መሆኑን ፍሬጉዳይ ያማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው የወረዳው ፍርድ ቤትና የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልዩነት የላቸውም፡፡ የወረዳው ፍርድ ቤትና የዞኑ ከፍተኛ /ቤት የተለያዩት ይኸ የተጠሪ አድርጎት አመልካች ህዳር 26 ቀን 2006 . ከተጠሪ ጋር ያለውን የሥራ ውል ያለማስጠንቀቂያ በማቋረጥ ለወሰደው እርምጃ በቂና ህጋዊ ምክንያት ነው ወይስ አይደለም ? የሚለው የህግ ጥያቄ በሚመረምሩበትና መዝነው ውሣኔ በሰጠበት ጊዜ እንደሆነ ከውሣኔያቸው ለመረዳት ችለናል ፡፡

8.   ሠራተኛው ከሥራ ውል የተመለከተውን ሥራ ራሱ የመሥራትና የሥራ ውሉና ደንቡ መሠረት በአሠሪው የሚሰጠውን ትዕዛዝ የመፈፀም ግዴታ ያለበት መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 13 ንዑስ አንቀፅ 1(1)እና ንዑስ አንፅ 2 ተደንግጓል ፡፡ከዚህ በተጨማሪ አንድ ሰራተኛ እንደጥፋቱ ክብደት በስራው ቦታ አንባጓሮ ወይም ጠብ አጫሪነት ጥፋት በፈፀመ ጊዜ አሰሪው ሰራተኛውን ያለማስጠንቀቂያ ከስራ ሲያሰናብተው የሚችል መሆኑን የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 27 ንዑስ አንቀፅ(1)ተደንግጓል፡፡ ተጠሪ የቅርብ አለቃው ከተጠሪ ጋር ከሚሠሩት አምስት ሠራተኞች አንድ ሠራተኛ ወደ ሌላ ሥራ ክፍል ለማሰማራት የሰጠውን ትዕዛዝ የተቃወመና በአዋጅ አንቀፅ 13 ንዑስ አንቀጽ 2 አሠሪው በሥራ ውሉና ደንቡ መሠረት የሰጠውን የሥራ ትዕዛዝ የመፈፀም ግዴታውን ያልተወጣ መሆኑን አሠሪው ሌሎች ሠራተኞች የሥራ ትዕዛዝና ስምሪት የመስጠት መብት በመጋፋት የቅርብ አለቃውንአንተ ሀሽሻም ሀሽሽ አጭሰህ መጥተህ አትናገረንበማለት የተሳደበ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

9.   አመልካች የቅርብ አለቃው ላይ የስድብና ማዋረድ ተግባር የፈፀመው በወንጀል ሕግ ማንም ሰው እንዳይዘውና እንዳይጠቀም ክልከላ የተደረገበትን ሀሽሽ አጭሰህ መጥተህ ነው የምትናገረን በማለት እንደሆነ ተረጋግጧል ፡፡ ተጠሪ በቅርብ አለቃው ላይ የፈፀመው የስድብና ማዋረድ ተግባር፣በህግ የተከለከለ ተግባር ፈጽመሀል በማለት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡም የሚያወግዘውንና የሚጠየፈውን ተግባር የቅርብ አለቃው ፈጽሞ መጥቶ ሰራተኞችን እንደሚበጠብጥ አድርጎ ሌሎች ሰራተኞች እየሰሙ በመግለፅ እንደሆነና ይህም የተጠሪ አድርጎትና ተግባር የአሠሪው ወኪል የሆነውን የቅርብ አለቃውን ሰብዓዊ ክብር በሚነካ ሁኔታ ተጠሪ የስድብና ማዋረድ ተግባር የፈፀመና በዚህ ምክንያት የተጠሪ የቅርብ አለቃ ስሜት ውስጥ እንደገባና ለጠብና ለድብድብ እንዲነሳሳ ለማድረግ አስቦና መርጦ የተናገረው መሆኑን ከግራቀኙ ክርክርና ከሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ለመረዳት ይችላል ፡፡ይህንን የተጠሪ አድርጎት በአዋጅ ቁጥር 32 ንዑስ አንቀጽ 1() ድንጋጌ ጋር በማነፃፃር ስንመለከተውአሠሪው የሠራተኛውን ሰብዓዊ ክብርና ሞራልን የሚነካ ወይም በወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሠረት የሚያስቀጣ ሌላ አድርጎት የፈፀመ እንደሆነ ሠራተኛው የሥራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውሉን ለማቋረጥ እንደሚችል ይደነግጋል

10. በዚህ መዝገብ እየታየ ያለው ጉዳይ ከላይ የተጠቀሰው ድንጋጌ የተገለፁት ተግባራት በአሠሪው ሣይሆን በሠራተኛው የተፈፀመ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ተጠሪ የቅርብ አለቃው የሠጠውን የሥራ ትዕዛዝ አልፈፅምም ከማለት አልፎ አንተ ሀሽሻም ሀሽሽ አጭሰህ መጥተህ አትናገረን በማለት የቅርብ አለቃውን የሰደበና ያዋረደ መሆኑን በዚህ ምክንያት ከቅርብ አለቃው ጋር ጠብ የተፈጠረ መሆኑ የስር ፍርድ ቤት ውሣኔ ያሳያል ከዚህ አንፃር በአዋጅ ቁጥር 32 ንዑስ አንቀፅ 1(ሀ) የተገለፀ ሁኔታ ሠራተኛው የቅርብ አለቃውን ሰብዓዊ ክብርና ሞራል የሚነካ የስድብና የማዋረድ ተግባር በመፈፀሙ ወይም ሌላ ህገወጥ ተግባር በመፈፀሙ ምክንያት በሥራ ቦታ በሠራተኛውና በቅርብ የሥራ ሀላፊው መካከል ጠብ የተነሳ መሆኑ ከተረጋገጠ አሠሪው በአዋጅ ቁጥር 27 ንዑስ አንቀጽ 1(ረ) በተደነገገው መሠረት የሥራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ እንደሚችል የአዋጁን አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 2፣የአዋጅ አንቀጽ 32(2) ሀ ከሚደነግገው በሚቃረን ሁኔታ ሠራተኛው የቅርብ የሥራ ሀላፊውን ሰብዓዊ ክብርና ሞራል የሚነካ ተግባር መፈፀም ሊያስከትል የሚችለውን ህጋዊ ውጤትና የአዋጁን አንቀፅ 27 ንዑስ አንቀፅ 1(ረ) ድንጋጌ ይዘትና መሠረታዊ ዓላማ በማገናዘብ ለመረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ተጠሪ በቅርብ አለቃው የተሰጠውን የሥራ ትዕዛዝ ከመቃወም አልፎ የቅርብ የሥራ ሃላፊውን አንተ ሀሽሻም ሀሽሽ አጭሰህ መጥተህ እኛን አትናገረን በማለት በመሳደቡና ከቅርብ አለቃው ጋር መጣላቱ የሥራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ የሚያስችል በቂና ህጋዊ ምክንያት አይደለም በማለት የሰጡት የሕግ ትርጉምና ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል፡፡

ው ሣ ኔ

1. የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔና የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ተሸሯል፡፡

2. የሰበታ ሀዋሳ ወረዳ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ፀንቷል፡፡

3. አመልካች የተጠሪን የሥራ ውል የቋረጠው በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀፅ 2 እና በአንቀፅ 27 ንዑስ አንቀፅ 1() መሠረት በመሆኑ የሥራ ስንብቱ በሕግ አግባብ የተከናወነ ነው በማለት ወስነናል ፡፡

4. በዚህ ፍርድ ቤት የወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ

መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡