111839 Labor dispute Termination of contract of employment without notice Negligence

Labor dispute

Termination of contract of employment without notice

Negligence

Proclamation no. 377/96 አንቀፅ 13/3/፣27/1/g/

 አንድ በሹፌርነት የተቀጠረ ሠራተኛ አሰሪው ጋር በተያያዘ ሁኔታ ጥንቃቄ ማድረግ ከሚገባው ነገር አንዱ መኪናውን የሚያሽከረክርበት አግባብ ከአካባቢው አየር ሁኔታና ከመልከዓ ምድሩ ጋር ባገናዘበ መልኩ መሆን ያለበት ስለመሆኑና ይህንን ሳያደርግ ቀርቶ አደጋና ጉዳት ቢደርስ ከባድ ቸልተኝነት እንዳደረሰ ተቆጥሮ የስራ ውሉ ያለማስጠንቀቂያ ሊቋረጥ የሚችል ስለመሆኑ፣  

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 13/3/፣27/1/ሸ/ 

 

የሰ//. 111839

ግንቦት 28 ቀን 2ዐዐ7 .

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

ሡልጣን አባተማም

ሙስጠፋ አህመድ

ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- .ኤስ አይ ኢትዩጵያ - ጠበቃ አላምነህ ስንሻው ቀረቡ

ተጠሪ፡- አቶ እሸቱ ካሳ - የቀረበ የለም፡፡ 

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ጉዳዩ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅን መሠረት ያደረገ ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ሐምሌ  24 ቀን 2ዐዐ6 . በተፃፈ ክስ በአመልካች ድርጅት በሹፌርነት ተቀጥረው እየሠሩ ባለበት ሁኔታ ያላግባብ ከስራ መሰናበታቸውን ገልፀው ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሏቸው ወደ ስራ እንዲመለሱ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የአሁኑ አመልካችም በተከሣሽነቱ ቀርቦ በሰጠው መልስ ተጠሪ የድርጅቱን መኪና ባግባቡ የመንዳት ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት ግንቦት 05 ቀን 2006 . ሰው ገጭቶ ጉዳት ማድረሱንና ከዚህ በኋላም ሰኔ 08 ቀን 2006 / ከደሴ ወደ መቐሌ በሚሄድበት ጊዜ በግድየለሽነት በማሸከርከር በመኪናው ላይ ጉዳት ከማድረሱም በላይ በተሽከርካሪው ውስጥ በነበሩት የድርጅቱ ሰራተኞች ላይ ቀላል የመቁሰል አደጋ ማድረሱንና ይህም በክፍሉ የትራፊክ ፖሊስ መረጋገጡንና አመልካችም ተገቢውን ኮሚቴ አቋቁሞ በማጣራት ከአረጋገጠ በኋላ ስንብቱን ያከናወነ መሆኑን ዘርዝሮ ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የደሴ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ግንቦት 05 ቀን 2006 / ደረሰ የተባለው አደጋ በሰላሳ የስራ ቀናት ውስጥ የስራ ስንብት ማከናወኛ ምክንያት ያልሆነ በመሆኑ በይርጋ እንዲሚታገድ፣ ሰኔ 08 ቀን 2006 / ደረሰ የተባለው አደጋ ደግሞ በተጠሪ በኩል ቸልተኝነት በመኖሩ የደረሰ ነው ቢባልም በከባድ ቸልተኝነት የደረሰ ነው ሊባል የሚችል ያለመሆኑን ጠቅሶ የአመልካችን የስንብት እርምጃ  ሕገወጥ መሆኑን በመደምደም ተጠሪ የአምስት ወር ከስድስት ቀናት ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሏቸው ወደ ስራ እንዲመለሱ በማለት ወስኗል፡፡ የአሁኑ አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለደቡብ ወሎ መስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ አፅንቶታል፡፡

የአሁኑ የሠበር አቤቱታው የቀረበውም ይህንኑ ውሣኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

የአመልካች ጠበቃ መጋቢት 24 ቀን 2ዐዐ7 . በፃፉት የሰበር አቤቱታ በበታች /ቤቶች ውሣኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶችን ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ፡- የተጠሪ ድርጊት በሕጉ አግባብ ሲጣራ ቆይቶ ተጠሪ ከባድ ቸልተኝነት ያለባቸው መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ለተፈፀመው እርምጃ ድርጊቱ በይርጋ የታገደ ነው መባሉ አሰሪ የሰራተኛውን ጥፋት በትክክል አወቀ ሊባል የሚችልበትን አግባብና በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27/1//1/ ስር ስለ ከባድ ቸልተኝነት የተመለከተውን የህጉን ድንጋጌ ባላገናዘበ መልኩ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ሊታረም የሚገባው ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሣይ ነው፡፡ የሰበር አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ሊታይ ይገባዋል በመባሉ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡ 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር የሠበር አቤቱታው ከቀረበበት ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም ሰኔ 08 ቀን 2006 . ደረሰ ለተባለ አደጋ የተጠሪ ቸልተኝነት ከባድ ሊባል የሚችል አይደለም ተብሎ የስንብቱ እርምጃ ሕገወጥ ነው መባሉ ባግባቡ መሆን አለመሆኑን በጭብጥነት ሊመረመር የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ በአመልካች ድርጅት በሹፌርነት ተቀጥረው እየሠሩ ባለበት ወቅት ግንቦት 05 ቀን 2006 . መንገደኛ በነበረው ሰው ላይ ጉዳት አድርሰዋል፣ሰኔ 08 ቀን 2006 . ደግሞ የአመልካች ድርጅት ሰራተኞችን ከደሴ ወደ መቐሌ ለስራ ይዞ በመሄድ ላይ እያለ መንገዱ ጠመዝማዛና የአየሩ ሁኔታም ዝናብማ ሁኖ እያለ ከጥንቃቄ ጉድለት መኪናውን እንዲወድቅ በማድረግ በመኪናው ላይ ጉዳት አድርሷል፣በሰራተኞች ላይም ቀላል የመቁሰል አደጋ አድርሷል ተብሎ ስንብቱ የተከናወነ መሆኑንና የስር ፍርድ ቤቶች ግንቦት 05 ቀን 2006 . ተፈጸመ የተባለው ጥፋት በሰላሳ ቀን የይርጋ ጊዜ መታገዱን፣የሰኔ 08 ቀን 2006 . ጥፋት ግን በወቅቱ ዝናባማ የአየር ሁኔታ በነበረበትና መንገዱ እርጥበታማና ቁልቁለታማ በሆነበት አካባቢ የተፈፀመ ቢሆንም በተጠሪ በኩል ቸልተኝነት ነበር ከሚባል በስተቀር በአዋጁ በተመለከተው አግባብ ከባድ ቸልተኝነት ነበር ሊባል የሚችል አይደለም በሚል ምክንያት የበታች ፍርድ ቤቶች የወሰኑ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ የተጠሪ አድራጎት በከባድ ቸልተኝነት ስር ሊወድቅ ይችላልን? የሚለው ነው፡፡

በመሠረቱ አንድ ሠራተኛ ለስራው የተሰጡትን መሣሪያዎችና እቃዎች ሁሉ በጥንቃቄ የመጠበቅ ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 13/3/ ስር የተመለከተ ሲሆን በአሠሪው ንብረት ወይም ከድርጅቱ ስራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባለው ማናቸውም ንብረት ላይ ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ ሠራተኛውን ያለማስጠንቀቂያ ከስራ ለማሰናበት የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያት ስለመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ 27/1/ሸ/ ድንጋጌ ያሣያል፡፡ ሆኖም ከባድ ቸልተኝነት የሚለውን ቃል መለኪያ በተመለከተ ሕጉ በግልጽ አያሣይም፡፡ ይሁን እንጂ ቸልተኝነት የጥንቃቄ ጉድለት እንደመሆኑ መጠን የጥንቃቄ ዓይነትና ደረጃ እንደየድርጊቱና አድራጊው የስራ ድርሻ አኳያ በመመልከት ምላሽ ለማግኘት እንደሚገባ ይህ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር 41115 አስገዳጅ የህግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ በመሆኑም የተጠሪ የጥፋት ደረጃ "ከባድ ቸልተኝነትን" ሊያቋቁም የሚችል መሆን አለመሆኑን ከስራቸው ባህርይ አንፃር መመልከቱ የግድ የሚል ነው፡፡ ተጠሪ ስራቸው ሹፌር ሲሆኑ ከስራቸው በተያያዘ ሁኔታ ጥንቃቄ ማድረግ ከሚገባቸው ነገሮች አንዱ መኪናውን የሚያሽከረክሩበትን አግባብ ከአከባቢው አየር ሁኔታ እና ከመልክዓ ምድሩ ጋር በአገናዘበ መልኩ መሆን ያለበት መሆኑን የሚመለከት ነው፡፡በመሆኑም በዝናባማ የአየር ሁኔታና ጠመዝማዛና ቁልቁለታማ በሆነ መንገድ በዝግታና በጥንቃቄ ተሽከርካሪን ማሽከርከር ከአንድ አሽከርካሪ የሚጠበቅ ሙያዊ ግዴታ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ መኪናውን ዝናባማ በሆነ የአየር ሁኔታ ውስጥ በጠመዝማዛና ቁልቁለታማ በሆነ መንገድ ላይ ተጠሪ ማርሹን በተመጣጣነ ማርሽ አስሮ ባለማሽከርከሩ አደጋው መደረሱ በክፍሉ ፖሊስና አመልካች ባቀረባቸው ሌሎች ማስረጃዎች የተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ ተጠሪ ማስተባበያ ማስረጃ ያላቀረበበት ጉዳይ ስለመሆኑ ከክርክሩ ሂደት ተገንዝበናል፡፡ ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው የበታች ፍርድ ቤቶችም ተጠሪ ሲያሽከረክሩት የነበረው መኪና በተጠቀሰው የአየር ሁኔታና መልክዓ ምድር ላይ ሲሽከረከር ተጠሪ ተገቢውን ማርሽ አስሮ ሲሽከረክር ነበር በማለት የደመደሙት ፍሬ ነገር ያለመኖሩን የውሳኔያቸው ይዘት ያስገነዝባል፡፡

ተጠሪ መኪናውን ሲያሽከረክሩ የነበረበት ሁኔታ ከላይ የተገለጸው ነው ከተባለ ደግሞ  ትክክለኛ አእምሮ ባለው ሰውና በተጠሪ የግል ሁኔታ መመዘኛ መሠረት ከባድ ቸልተኝነትን ሊያሣይ የሚችል አይደለም ሊባል የሚችልበትን አግባብ አላገኘንም፡፤፡፡ በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች የተጠሪ ጥፋት ከባድ ቸልተኝነት አይደለም ማለታቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት ሁኖ  ስለተገኘ የሚከተለውን ወስነናል፡፡

ው ሣ ኔ

1.    በደሴ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/.10762 ታህሳስ 06 ቀን 2007 . ተሰጥቶ በደቡብ ወሎ መስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/.19554 የካቲት 19/ 2007 .ም፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 03-10681 መጋቢት 18 ቀን 2ዐዐ7 . በትእዛዝ የፀናው ውሣኔ በፍ/////. 348/1/መሠረት ተሽሯል፡፡

2.    አመልካች ተጠሪን ያሰናበተው በሕጉ አግባብ ነው ብለናል፡፡

3. በዚህ ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ /ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡