Labor dispute
Internal regulation and directive of organization
Vacancy promotion
በአንድ አሰሪ ድርጅት መተዳደሪያ ደንብና መመሪያ መሠረት በአንድ የሥራ መደብ ላይ የውጪ ሰው የሚቀጠረው መጀመሪያ ለቦታው የሚመጥን የውስጥ ሠራተኛ ካለ ለውስጥ ሠራተኛው እድል ከሰጠ ለኋላ ከሆነ አሠሪው ድርጅት ይኽን ደንብና መመሪያ ተላልፎ የውስጥ ዕድገት ማስታወቂያ ሣያወጣና ለሠራተኞች ዕድል ሳይሰጥ የውጪ ቅጥር ቢፈጸም ድርጊቱ ህገወጥ ተግባር ስለመሆኑና ቅጥሩ ሊሠረዝ የሚገባው ስለመሆኑ፣
የሰ/መ/ቁ. 107002
ግንቦት 14 ቀን 2007ዓ.ም
ዳኞች፡- አልማው ወሌ
ዓሊ መሐመድ
ሱልጣን አባተማም
ሙስጠፋ አህመድ
ተኸሊት ይመሰል
አመልካች፡- ሲስተር ትዕግስት ፈቃድ - ቀረቡ
ተጠሪ፡- የኤድስ መከላከያ ማህበራዊ አገልግሎት ድርጅት አልቀረበም
ፍ ር ድ
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 177544 መስከረም 22 ቀን 2007 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔና የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 197235 ህዳር 17 ቀን 2007 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበችውን የሰበር አቤቱታ አጣራቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ የሥራ መደብ ሊሰጠኝ ይገባል በማለት የቀረበን ጥያቄ የሚመለከት ነው፡፡ ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በምዕራብ ኦሮሚያ አሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ ነው፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ ውሳኝ ቦርዱ አመልካች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል ፡፡
1- አመልካች በተከሳሽ (ተጠሪ) ድርጅት በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በነርስ ካውንስለር ሰባተኛ ደረጃ ተቀጥሬ በመሥራት ላይ እያለሁኝ የቤተሰብ ችግር ስላጋጠመኝ በራሴ አቤቱታ አቅራቢነት በደረጃ ሶስት የነርስ ካውንስለር የሥራ መደብ ወደ ነቀምት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ተዛውሬና ተመድቤ በመሥራት ላይ እገኛለሁ ፡፡ ሆኖም ተከሳሽ እኔ በፊት ተቀጥሬበት የነበረው ሰባተኛ ደረጃ ነርስ ካውንስለር ለመመደብ መስፈርቱን የሚያሟላ የውስጥ ሠራተኛ የለም አግባብ ባልሆነ መንገድ የመሥሪያ ቤቱን መተዳደሪያ ደንብ በመጣስ ከአምስት ዓመት በፊት የሥራ ስንብት ክፍያና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን ከፍሎ ያሰናበታትን ሠራተኛ በመጥራት ያለምንም ውድድር በመቅጠር ደረጃ ሰባት ነርስ ካውንለር አድርጎ መድቧታል፡፡ ከሳሽ መስፈርቱ የሟማላ የውስጥ ሠራተኛ እያለሁ የውስጥ ሠራተኞች ተወዳድረው በእድገት በሚመደቡበት የሥራ መደብ ላይ የነቀምቴ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እኔን በቦታው ላይ መመደብ ሲገባው የውጭ ማስታወቂያ በማውጣት ቅጥር መፈፀሙ የድርጅቱን መተዳደሪያ ደንብ የሚጥስና የእኔን መብት የሚያጣብብ መሆኑ፣ቅጥሩን በመሰረዝ እኔን በቦታው ላይ እንዲመድቡኝ ውሣኔ ይሰጥልኝ በማለት የምዕራብ ኦሮሚያ አሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ ክስ አቅርባለች፡፡
2- ተከሳሽ (ተጠሪ በበኩሉ ከሳሽ በሶስተኛ ደረጃ ነርስ ካውንስለር የሥራ መድብ ተመድባ የምትሠራ ሠራተኛ ናት ከሳሽ አራት ደረጃዎችን በመዝለል ደረጃ ሰባት ነርስ ካውንስለር ሥራ መደብ ላይ መመደብ አለብኝ በማለት ያቀረበችው ክስ የህግ ስህተት የለውም ፡፡ ከሳሽ ለደረጃ ሰባት የሚመጥን የሙያ ብቃት ስነምግባርና የሥራ አፈፃፀም የላትም ፡፡ ባለው የሥራ መደብ ፤ሥራውን ለመሥራት የሚችል ሠራተኛ በዕድገት ወይም በቅጥር የመመደብ መብት ያለው አሠሪው (ድርጅቱ) እንጅ ሠራተኛው አይደለም ፡፡ ከሳሽ ያለምንም ውድድር የሥራ መደቡ እንዲሰጣት ያቀረበችው ክስ ተገቢ ባለመሆኑ ውድቅ ይደረግልኝ በማለት ተከራክሯል፡፡
3- የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ የግራቀኙን ክርክር ከመረመረ በኃላ ከሳሽ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በደረጃ ሰባት የሥራ መደብ ፣ተመድባ ስትሠራ የነበረ መሆኑ በተከሳሽ አልተካደም ከሳሽ ወደ ወለጋ ቅርንጫፍ የተዛወረችውና በደረጃ ሶስት የሥራ መደብ ላይ ተመድባ ለመሥራት የተስማማችው በቤተሰብ ችግር ምክንያት መሆኑ ተረጋግጧል ፡፡ተከሳሽ ከሳሽ በዲሲፒሊን ችግር ምክንያት ወደ ደረጃ ሶስት ብቅ ብላ የተመደበች ስለመሆኑ ያቀረበው ማስረጃ የለም፡፡ስለዚህ ተከሳሽ ደረጃ ሰባት የሥራ መደብ ተመድባ ስትሠራ የነበረችውን ተከሳሽን ሣያሳውቅ ከውጭ ሌላ ሰው የቀጠረው ከሳሽ ቦታውን እንዳታገኘ ለማድረግ በማስብ በክፋ ልቦና ነው፡፡ ስለዚህ ተከሳሽ ከሳሽን በደረጃ ሰባት የሥራ መደብ መድቦ የደመውዝን ልዩነት አስቦ ሊከፍል ይገባል በማለት በድምፅ ብልጫ ውሣኔ ሰጥቷል፡፡
4- የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ በሰጠው ውሣኔ ቅር በመሠኘት ተጠሪ ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቧል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ መልስ ሰጭ (አመልካች) ያለውድድር በደረጃ ሰባት የሥራ መደብ እንድትመደብ የሰጠው ውሳኔ የመሥሪያ ቤቱን የሥራ አመዳደብ መመሪያ መሠረት ያላደረገ ነው በማለት ቦርዱ የሰጠውን ውሣኔ ሽሮታል ፡፡አመልካች ይግባኝ ሰሚው ችሎት በሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት አቅርባለች ፡፡ የክልሉ የሰበር ችሎት የአመልካችን የሰበር አቤቱታ አልተቀበለውም ፡፡
5- አመልካች ህዳር 18 ቀን 2007 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ በአንድ የሥራ መደብ ላይ የውጭ ሰው የሚቀጠረው በመጀመሪያ ለቦታው የሚመጥን የውስጥ ሠራተኛ ካለ እድል ከሰጠ በኃላ መሆን እንዳለበት በግልፅ ያስቀምጣል ፡፡ አመልካች በደረጃ ሰባት የሥራ መደብ ተመድቤ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ስሰራ እንደነበር ተረጋግጧል ፡፡ይህ ሆኖ እያለ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት አመልካች በደረጃ ሰባት የሥራ መደብ ልትመደብ አይገባትም በማለት የሰጡት ውሳኔ የድርጅቱን መተዳደሪያ ደንብ ያላገናዘበና መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልክታለች ፡፡ ተጠሪ መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም በተፃፈ መልስ አመልካች ያለውድድር በቀጥታ ለመመደብ ጥያቄ ያቀረበችበት ደረጃ ሰባት የሥራ መደብ ለመወዳደር የሚስፈልገው የትምህርት ደረጃ አድቫንስድ ዲፕሎማ ሲሆን አመልካች ያላት ድፕሎማ በመሆኑ ለቦታው ለመወዳደር አትችልም አመልካች አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ደረጃ ሰባት ተመድባ የነበረው በድሮው መዋቅር ነው፡፡ ስለዚህ ያለምንም ውድድር በደረጃ ሰባት እንድትመደብ የተሰጠውን ውሣኔ መሻሩ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክሯል፡፡ አመልካች ሚያዚያ 8/ቀን 2007 ዓ.ም በተፃፈ የመልስ መልስ በነርስ ሙያ ዲፕሎማና ዲግሪ የትምህርት መርሃ ግብር እንጂ አድቫንስድ ዲፕሎማ የሚባል የትምህርት መረሃ ግብር የለም በነርስ በአድቫንስ ዲፕሎማ የተመረቀ ባለሙያ የለም ፡፡ ተጠሪ ዕውነትነት የሌላቸውን መስፈርቶች በማንሣት የቀረበው ክርክር ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም በማለት ተከራክራለች፡፡
6- ከሥር የክርክሩ አመጣጥና ለዚህ ሰበር ችሎት ግራቀኙ በፅሑፍ ያቀረቡት ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት አመልካች በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት መስፈርቱን የማሟላው ሠራተኛ ሣልወዳደር የደረጃ እድገት ሣይሰጠኝ ተጠሪ ቅጥር በመፈፀም የሥራ መደቡን ማስያዙ ሕገ ወጥ ስለሆነ ቅጥሩ ተሰርዞ እኔ በቦታው ላይ እንድመደብ በማለት ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የሰጡት ውሳኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም ? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ መርምረናል ፡፡
7- ጉዳዩን እንደመረመርነው በተጠሪ ድርጅት ውስጥ ክፍት የሥራ መደብ ሲኖር ድርጅቱ ሌላ ሠራተኛ ከመቅጠሩ በፊት መስፈርቱን የሚያሟሉ የድርጅቱ ሠራተኞች ካሉ ተወዳድረው በእድገት በቦታው ላይ እንዲመደቡ እድል መስጠት ያለበት መሆኑ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብና የሰው ሀይል አመዳደብ መመሪያ በግልፅ የተደነገገ በመሆኑን አመልካችና ተጠሪ የሚተማመኑበት ነጥብ ነው፡፡ አመልካችና ተጠሪ የሚከራከሩበት ጭብጥ አመልካች ተጠሪ የመተዳደሪያ ደንቡንና መመሪያውን በመጣስ ለደረጃ ሰባት የሚያስፈልገውን መስፈርት የማሟላ ሠራተኛ እኔ እያለሁ ለእኔ እድል ሣይሰጠኝ ከውጭ ሠራተኛ በመቅጠር የስራ መደቡን ማስያዙ ህገወጥ ነው በማለት ያቀረበችውን ክስ ተጠሪ ሙሉ በሙሉ በመካድ በነቀምት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የነበረውን ደረጃ ሰባት የስራ መደብ በቅጥር ሰው ያሟላሁት ካሉኝ ሠራተኞች ለሥራ መደቡ የሚያስፈልገውን መስፈርት የሚያሟላ ሠራተኛ ስለሌለኝ ነው፡፡ አመልካችም ለደረጃ ሰባት የሚያስፈልገውን መስፈርት አታሟላም የሚል ክርክር በማቅረቡ ነው፡፡ ይህም የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 246 በሚደነግገው መሠረት ፣ተጠሪ ደረጃ ሰባት የሥራ መደብ በውጭ ቅጥር ያሟላው የሥራ መደቡ የሚያስፈልገውን መስፈርት የሚያሟሉ ሠራተኞች እንዲወዳደሩ እድል ከሰጠ በኋላ መስፈርቱን የሚያሟላ ሠራተኛ ባለማግኘቱ ነው ወይስ አይደለም ? የሚለው አከራካሪ ነጥብ መታየት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል ፡፡
8- ተጠሪ በደረጃ ሰባት የሥራ መደብ ላይ የውጭ ቅጥር በመፈፀም በሥራ መደቡ ላይ ሠራተኛ ከመመደቡ በፊት የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብና የሰው ሀይል ምደባ አፈፃፀም መመሪያ በሚደነግጉት መሠረት በሥራ መደቡ የሚያስፈልገውን የትምህርት ዝግጅት፣የሥራ ልምድና ሌሎች መስፈርቶች የሚያሟሉ ሠራተኞች ማስረጃውን በማቅረብ እንዲወዳደሩ እና እንዲመዘገቡ የእድገት ማስታወቂያ ያላወጣና መስፈርቱን የሚያሟሉ ሠራተኞች እንዲወዳደሩ እድል ያልሠጠ መሆኑን የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ከሰጠው ውሣኔ ተረድተናል ፡፡ ከዚህ አንፃር ተጠሪ አመልካችና ሌሎች የድርጅት ሠራተኞች ለደረጃ ሰባት የሥራ መደብ ለመወዳደር የሚያስችላቸውን ማስረጃ በማቅረብ እንዲወዳደሩ የውስጥ የእድገት ማስታወቂያ ሣያወጣና መስፈርቱን ለሚያሟሉ ሠራተኞች እድሉን ሣይሰጥ ፣ሠራተኛ በመቅጠር በደረጃ ሰባት ላይ መመደቡ የድርጅቱን መተዳደሪያ ደንብና የሰው ሀይል አመዳደብ መመሪያ መሠረታዊ መርህ የሚጥስና ህጋዊ ዕውቅና ሊሰጠው የማይገባው ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል ፡፡
9- ተጠሪ የራሱ የሆነ የሥራ መዋቅር ፣አደረጃጀትና የሥራ መደብ ያለው ድርጅት መሆኑ አያከራክርም፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ተጠሪ በተለያዩ አካባቢዎች በራሱ የሆኑ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ያሉት መሆኑንና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቹም ያላቸው ተመሳሳይ የሥራ መደቦች የሚያስፈልገው የትምህርት ዝግጅት፣የሥራ ልምድና ሌሎች መስፈርቶች ተመሣሣይነት ያላቸው እንደማይሆኑና በተመሣሣይ የሥራ መደብ ተመድበው ለሚሠሩ ሠራተኞች የሚከፈለው ደመወዝና ሌሎች ሁኔታዎች ተመሣሣይነት ያላቸው እንደሚሆኑ ከተጠሪ ድርጅታዊ ተፈጥሮአዊ ባህሪና መተዳደሪያ ደንብ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ደረጃ ሰባት ነርስ ካውንስለር የሥራ መደብ ላይ ለመመደብ የሚያስፈልገው መስፈርትና በነቀምት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ደረጃ ሰባት ነርስ ካውንስለር የሥራ መደብ የሚያስፈልገውን መስፈርት አንድ አይነትና ተመሣሣይ መስፈርቶች መሆናቸውን በመካድ ተጠሪ ያቀረበው ክርክር የለም፡፡ አመልካች በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ደረጃ ሰባት የሥራ መደብ መስፈርት በሟሟላት ተመድባ ስትሠራ እንደነበር ተረጋግጧል፡፡ ተጠሪ አዲስ አበባ የነበራትን ደረጃና ደሞወዟን በመቀነስ ወደ ነቀምት ቅርንጫፍ የተዛወረችው በነበረባት የቤተሰብ ችግር ምክንያት አመልካች ጥያቄ በማቅረቧ ምክንያት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ከዚህ አንፃር በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ተመድባ ስትሠራበትና ደመወዝ ስትበላበት ለነበረው ደረጃ ሰባት የሥራ መደብ ለመወዳደር የሚያስፈልገውን መስፈርት አታሟላም በማለት የሚያቀርበው ክርክር የሕግ መሠረት ያለው መከራከሪያ ሆኖ አላገኘነውም ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪ ለአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ ያላቀረበውን አዲስ የፍሬ ጉዳይ መከራከሪያ በዚህ ሰበር ችሎት በማንሣት ለደረጃ ሰባት የሚያስፈልገው የነርስ አድቫንስድ ዲፕሎማ ነው የሚልና መዋቅሩ ስለተለወጠ መስፈርቱም ተለውጧል በማለት ያቀረባቸው መከራከሪያዎች በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 329 ንዑስ አንቀፅ/1/ የሚጥስ በመሆኑ ተቀባይነት ያለው መከራከሪያ ሆኖ አግኝተነዋል ፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ አመልካች ተጠሪ የነቀምት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ባለው ደረጃ ሰባት ክፍት የሥራ መደብ ለመወዳደር አትችልም በማለት ያቀረበው ክርክር ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም፡፡
10- አመልካች በተጠሪ ድርጅት ደረጃ ሰባት የሥራ መደብ ላይ ተመድባ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስትሠራ የነበሩ መሆኑንና አመልካች ይህንን የሥራ መደብ ለቅቃ በነቀምት ጽ/ቤት በደረጃ ሶስት የሥራ መደብ የተመደበችው በራሷ ጥያቄ አቅራቢነት መሆኑ ፣ተጠሪ በነቀምት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ደረጃ ሰባት የሥራ መደብ ላለው ከፍት ቦታ ለመወዳደር የሚያስችላት ቢሆንም ፣ከሌሎች ሠራተኞች ጋር ሣትወዳደር የሥራ መደቡን ለማግኘት የሚያስችላት አይደለም ፡፡ ከዚህ አንፃር የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ አመልካች ከሌሎች ሠራተኞች ጋር በደረጃ ሰባት የሥራ መደብ የመወዳደር እድል እንዲሰጣት ውሣኔ መስጠት ሲገባው አመልካች ያለምንም ውድድር ደረጃ ሰባት ላይ እንድትመደብ የሰጠው ውሳኔ የተጠሪን መተዳደሪያ ደንብና የሰው ሀይል አመዳደብ መመሪያ ያልተከተለ በመሆኑ ነው፡፡በሌላ በኩል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና ሰበር ችሎት አሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ አመልካች ደረጃ ሰባት የሥራ መደብ ላይ ያለምንም ውድድር እንድትመደብ የሰጠውን ውሣኔ መሻራቸው ተገቢ ቢሆንም ፣ተጠሪ አመልካችና ሌሎች ሠራተኞችን በማወዳደር የውስጥ እድገት ማስታወቂያ ሣያወጣና ለሠራተኞች እድል ሣይሰጥ የውጭ ቅጥር መፈፀሙ ህገወጥ ተግባር በመሆኑ ፣ተጠሪ የፈፀመው ቅጥር ተሰርዞ አመልካችንና ሌሎች ሠራተኞችን በማወዳደር በደረጃ ሰባት የሥራ መደብ በእድገት እንዲመደብ ውሣኔ ሣይሰጡ ማለፋቸው አመልካች ያቀረበችውን ግልፅ የዳኝነት ጥያቄና የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 182 ንዑስ አንቀፅ 2 ያላገናዘበና በከፊል መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል፡፡
ው ሳ ኔ
1. የምዕራብ ኦሮሚያ የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት የሰጡት ውሣኔ ተሻሽሏል፡፡
2. ተጠሪ የውስጥ እድገት ማስታወቂያ ሣያወጣና አመልካችና ሌሎች ሠራተኞች ተወዳድረው በደረጃ ሰባት የሥራ መደብ ለማደግና ለመመደብ የሚያስችላቸውን እድል ሣይሰጥ የውጭ ቅጥር በመፈፀም ደረጃ ሰባት የሥራ መደብ ላይ መመደቡ ሕገወጥ ተግባር በመሆኑ ተጠሪ በደረጃ ሰባት ላይ የፈፀመው ቅጥር ሊሠረዝ ይገባዋል በማለት ወስነናል፡፡
3. አመልካች በደረጃ ሰባት የስራ መደብ ለመወዳደር የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን የምታሟላ በመሆኑ ፣ተጠሪ አመልካችንና ሉሎች መስፈርቱን የሚያሟሉ ሠራተኞችን በማወዳደር የውስጥ እድገት ሊሰጥ ይገባዋል በማለት ወስነናል፡፡
4. በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራቀኙ ለያራሳቸው ይቻሉ ፡፡
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡