Labor dispute
Absence for 5 consecutive days
Termination of contract of employment
Art. 27 of Proclamation no. 377/2004
አንድ ሰራተኛ በመደዳው ለአምስት የስራ ቀናት ካለበቂ ምክንያት ከስራ መቅረቱ የተረጋገጠ እስከሆነ ድረስ አሰሪው በዚሁ ምክንያት ሰራተኛውን ካለማስጠንቀቂያ ከስራ ያሰናበተው ስለመሆኑ በደብዳቤ ሳይገልፅ መቅረቱ የሥራ ውሉ በሕግ አግባብ አልተቋረጠም ወደሚል መደምደሚያ የሚያደርስ ስላለመሆኑ
አዋጅ ቁ.377/96 አንቀፅ 27(1) (ለ)
የሰ/መ/ቁ.104862
መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.
ዳኞች፡- መድሕን ኪሮስ
አልማው ወሌ
ሡልጣን አባተማም
ሙስጠፋ አህመድ
ተኽሊት ይመስል
አመልካች፡-አቶ መልካሙ አረጋ - ቀረቡ
ተጠሪ፡-ተስፋዬ ለገሠ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ - ጠበቃ ይትባረክ መኮንን ቀረቡ
መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል፡፡
ፍ ር ድ
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ አመልካች በአሁኑ ተጠሪ ላይ በ09/12/2005 ዓ.ም አዘጋጅተው ባቀረቡት ክስ ነው፡፡ የክሳቸውም ይዘት ባጭሩ፡-ከሳሽ ከጥር 30 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ በወር ብር 8,076 ደመወዝ እና ብር 100 አበል እየተከፈላቸው በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ በዶዘር ኦፕሬተርነት የስራ መደብ ተቀጥረው በመስራት ላይ እያሉ ተከሳሽ ከ01/11/2005 ዓ.ም ጀምሮ በእርሳቸው ምትክ ሌላ ሰራተኛ በመቅጠር የስራ ውላቸው በቃል ያቋረጠባቸው መሆኑን የሚገልጽ ሆኖ የስንብት እርምጃው ሕገወጥ ነው ተብሎ ሕገ ወጥ የስራ ስንብት የሚያስከትላቸውን ክፍያዎች እና ያልተጠቀሙበትን የዓመት ዕረፍት ክፍያ በድምሩ ብር 106,381.00 ተከሳሽ እንዲከፍላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው፡፡
ተከሳሽ ድርጅት በበኩሉ በ11/02/2006 ዓ.ም በሰጠው መልስ ከሳሽ በራሳቸው ከስራ ከመቅረታቸው ውጪ ተከሳሽ ያላሰናበታቸው መሆኑን፣ሁሉም ሰራተኞች ለተረከቡት የድርጅቱ ንብረት ዋስትና እንዲያቀርቡ ተከሳሽ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ከሳሽ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን፣ዋስትና ለማቅረብ ያላቸውን ፈቃደኝነት ከ21/10/2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 30/10/2005 ዓ.ም ድረስ እንዲያስታውቁ በቃልም ሆነ በጽሁፍ ቢገለጽላቸውም ከሳሽ ይህንን ከማድረግ ፋንታ ከ21/10/2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 30/10/2005 ዓ.ም ድረስ በተከታታይ ከስራ መቅረታቸውን፣በ03/11/2005 ዓ.ም ቢሮ ተገኝተው ተመሳሳይ መልዕክት ቢነገራቸውም ያልፈጸሙ እና እንደገና ከ03/11/2005 ዓ.ም እስከ 08/12/2005 ዓ.ም ድረስ ስራ ላይ አለመገኘታቸውን፣ከዚህ በኃላ ከሳሽ በ08/12/2005 ዓ.ም ቢሮ ቀርበው ስራቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን በመግለጻቸው የተዘጋጀላቸውን ክፍያ እና የስራ ልምድ እንዲወስዱ ተጠይቀው ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን፣በከሳሽ ምትክ ሌላ ሰራተኛ የተቀጠረው ከዚህ ሁሉ በኃላ በ05/01/2006 ዓ.ም. መሆኑን በዝርዝር በመግለጽ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ተከራክሯል፡፡
ፍርድ ቤቱም ክሱን እና የግራ ቀኙን ምስክሮች ከሰማ በኃላ አጠቃላይ ክርክሩን መርምሮ የከሳሽ ምስክሮች ቃል ተከሳሽ ከሳሽን በቃል ከስራ እንዳሰናበተ የሚያስረዳ አለመሆኑን፣ከሳሽ ዋስ የሚጠሩ መሆን አለመሆኑን እስከ 30/10/2005 ዓ.ም ድረስ እንዲያስታውቁ፣ይህ ካልሆነ ግን ስራቸውን በራሳቸው ፈቃድ እንደለቀቁ ተቆጥሮ የስራ ግንኙነቱን እንደሚያቋርጥ ተከሳሽ በ21/10/2005 ዓ.ም የሰጠው ማስታወቂያ በይዘቱ ከሳሽ እስከተባለው ቀን ድረስ ሀሳባቸውን ካልገለጹ ተከሳሽ ከ30/10/2005 ዓ.ም ጀምሮ የስራ ውሉን እንደሚያቋረጥ የሚያመለክት መሆኑን፣የስራ ውላቸው ከ30/10/2005 ዓ.ም ጀምሮ እንደተቋረጠ የሚቆጠር ከሆነ ደግሞ ከዚህ ቀን በኃላ ከሳሽ በስራ ቦታው የሚገኙበት ምክንያት ስለማይኖር ከሳሽ በተጨማሪ ከ03/11/2005 ዓ.ም እስከ 08/11/2005 ዓ.ም ድረስ ስራ ላይ አልተገኙም በማለት ተከሳሽ ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን፣ከሳሽ ከ21/10/2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 30/10/2005 ዓ.ም ድረስ በመደዳው ከስራ መቅረታቸው የተረጋገጠ ቢሆንም ተከሳሽ ይህንን ድርጊት የማሰናበቻ ምክንያት አድርጎ በደብዳቤ እስካልገለጸ ድረስ ከሳሽ የተሰናበቱት በመደዳው ከአምስት የስራ ቀናት በላይ ከስራ በመቅረት በራሳቸው አነሳሽነት ነው ሊባል የሚችል አለመሆኑን፣በአጠቃላይ ከሳሽም በራሳቸው አነሳሽነት ሰራቸውን ስላልለቀቁ እና ተከሳሽም ስላላሰናበታቸው ስንብቱ ሕገወጥ መሆኑን ገልጾ በክሱ ከተጠየቀው ክፍያ ውስጥ ተከሳሽ ብር 79,189.66 ግብር ከተቀነሰ በኃላ ለከሳሽ እንዲከፍል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ተከሳሹ ባቀረበው ይግባኝ ሳቢያ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ተከሳሽ በ21/10/2005ዓ.ም የሰጠው ማስታወቂያ በማስረጃነት የቀረበው በከሳሽ ሳይሆን በተከሳሽ በኩል ሆኖ እያለ እና የማስታወቂያው ይዘትም የስራ ውሉ በተከሳሽ አነሳሽነት መቋረጡን የማያረጋግጥ ሆኖ እያለ እንዲሁም ከሳሽ በመደዳው ከአምስት የስራ ቀናት በላይ ከስራ መቅረታቸው ተረጋግጦ እያለ የስር ፍርድ ቤት የስራ ውሉ የተቋረጠው በተከሳሽ አነሳሽነት ነው፣ስንብቱም ሕገወጥ ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ገልጾ ውሳኔውን በማሻሻል ተከሳሽ ከሕግ ውጪ የስራ ውሉን አቋርጧል በሚል የተሰጠውን እና ሕገወጥ የስራ የስንብት እርምጃ የሚያስከትላቸውን ክፍያዎች ተከሳሽ ለከሳሽ እንዲከፍል የተሰጠውን የውሳኔ ክፍል ሽሮ የዓመት ዕረፍት በገንዘብ ተቀይሮ እንዲከፈል የተሰጠውን የውሳኔ ክፍል ብቻ በማጽናት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡አመልካች አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡት ይዘቱ ከላይ የተመለከተው የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ አመልካች ዋስ ካልጠሩ ተጠሪው የስራ ውላቸውን እንደሚያቋርጥ ገልጾ የጻፈላቸው መሆኑ በተረጋገጠበት እና አመልካች ዋስ አለማቅረባቸው ባልተካደበት ሁኔታ ስንብቱ ሕጋዊ ነው ተብሎ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የመወሰኑን አግባብነት ተጠሪው ባለበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምረናል፡፡
በዚህም መሰረት አመልካች ክስ ያቀረቡት ተጠሪው ከ01/11/2005 ዓ.ም ጀምሮ በእርሳቸው ምትክ ሌላ ሰራተኛ በመቅጠር የስራ ውላቸውን በቃል ያቋረጠባቸው መሆኑን በመግለጽ ሲሆን ተጠሪው በበኩሉ አመልካችን እንዳላሰናበተ እና በራሳቸው ከስራ እንደቀሩ በመግለጽ ተከራክሯል፡፡በመሰረቱ ማንኛውም ተከራካሪ ወገን ለክርክሩ ምክንያት የሚያደርጋቸውን ፍሬ ነገሮች የማስረዳት ሸክም እንዳለበት የሚታወቅ ነው፡፡በተያዘው ጉዳይ የአመልካች የምስክሮች ቃል ተጠሪው አመልካችን በቃል ከስራ እንዳሰናበተ የሚያስረዳ አለመሆኑን የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ተቀብሎ በውሳኔው ላይ አስፍሯል፡፡እንዲህ ከሆነ ደግሞ አመልካች በክሳቸው መሰረት አስረድተዋል ሊባል የሚችልበት ሕጋዊ ምክንያት አይኖርም፡፡በአሰሪው በቃል ከስራ ተሰናብቻለሁ በሚል ክስ የሚያቀርብ ሰራተኛ ይህንኑ የማስረዳት ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 43610 የተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ለተያዘው ጉዳይ ተፈጸሚነት ሊኖረው የሚገባው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡
በሌላ በኩል ተጠሪው ከ 01/11/2005 ዓ.ም ጀምሮ ከስራ እንደሚያሰናብተኝ በ 21/10/2005 ዓ.ም በጻፈው ማስታወቂያ አረጋግጦ እያለ ስንብቱ ሕገወጥ አይደለም ተብሎ የተወሰነው በአግባቡ አይደለም በማለት አመልካች ተከራክረዋል፡፡ ይሁን እንጂ አመልካች ከ21/10/2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 30/10/2005 ዓ.ም ድረስ ከስራ መቅረታቸው የተረጋገጠ በመሆኑ፣በመደዳው ለአምስት የስራ ቀናት ያለበቂ ምክንያት ከስራ መቅረት ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 27(1)(ለ) መሰረት ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውል ለማቋረጥ የሚያስችል ምክንያት በመሆኑ፣በዚህ ምክንያትም አመልካች የስራ ውላቸውን ከ30/10/2005 ዓ.ም በፊት በራሳቸው አነሳሽነት እንዳቋረጡ የሚቆጠር በመሆኑ እና ይህም ተጠሪው በ21/10/2005 ዓ.ም የሰጠው ማስጠንቀቂያ ከ01/11/2005 ዓ.ም ጀምሮ የአመልካችን የስራ ውል እንዳቋረጠው የሚያመለክት ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጥያቄ የማንሳትን እና የመመርመርን አላስፈላጊነት የሚያስከትል በመሆኑ ተጠሪው የስራ ውሌን ከ01/11/2005 ዓ.ም ጀምሮ እንዳቋረጠው ሊቆጠር ይገባል በማለት አመልካች ያቀረቡት ክርክር ሕጋዊ መሰረት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡አንድ ሰራተኛ በመደዳው ለአምስት የስራ ቀናት ካለበቂ ምክንያት ከስራ መቅረቱ የተረጋገጠ እስከሆነ ድረስ አሰሪው በዚሁ ምክንያት ሰራተኛውን ካለማስጠንቀቂያ ከስራ ያሰናበተው ስለመሆኑ በደብዳቤ ሳይገልጽ መቅረቱ በአዋጁ አንቀጽ 27 (1) (ለ) መሰረት የስራ ውሉ በሕግ አግባብ አልተቋረጠም ወደሚል መደምደሚያ የሚያደርስ አይደለም፡፡በመሆኑም በዚህ ረገድ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተደረሰበትን የተሳሳተ መደምደሚያ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ማረሙ ሕጉን መሰረት ያደረገ ነው ከሚባል በቀር የሚነቀፍበት ሕጋዊ ምክንያት የለም፡፡
ሲጠቃለል ይግባኝ ሰሚው ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተሰጥቶ የነበረውን ውሳኔ በማሻሻል የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ ስላልተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ው ሳ ኔ
1. በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 80816 በ 30/03/2006 ዓ.ም. የተሰጠውን ውሳኔ በማሻሻል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 139450 በ 12/12/2006 ዓ.ም. የሰጠው ውሳኔ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል፡፡
2. እንዲያውቁት የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍርድ ቤቶች ይላክ፡፡
3. የሰበር ክርክሩ ያስከለተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡
4. ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቶአል፡፡