112583 labor dispute/ leave /conversion of leave to payment

አንድ ሠራተኛ ከአንድ ዓመት በታች አገልግሎት የሰጠ እንደሆነ
ተመጣጣኝ የሆነ የረፍት ጊዜ በአገልግሎት ጊዜው ልክ
(proportion to the length of his service) የሚሰጠው ስለመሆኑ
አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 77(6)

 

የሰ/መ/ቁ. 112583

 

ጥቅምት 5 ቀን 2008 ዓ.ም

 

 

 

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ብርሃኑ አመነው ተፈሪ ገብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መለሰ

አመልካች፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጅማ ቅ/የቀረበ የለም ተጠሪ፡- አቶ ብሩክ አበራ- ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ መዝገብ የቀረባቸውን ጉዳይ የሥራ ውል መቋረጥ ተከትሎ ሊከፈል የሚገባ ልዩ ልዩ ክፍያ ክርክር የሚመመለከት ነው፡፡

 

ተጠሪ ከአመልካች ጋር የነበረው የሥራ ውል ማቋረጥ ተከትሎ ልዩ ልዩ ክፍያዎችን የጠየቀ ሲሆን የጅማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን ካከራከረ በኃላ ተጠሪ የሠራበት የእሁድ ቀን ክፍያ የ2006 ዓ.ም የአመት ዕረፍት እና የጥር ወር 2006 ዓ.ም ሙሉ ደመወዝ እንዲከፈለው ወስኗል፡፡

 

ይግባኙ ለጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአመልካች በኩል የቀረበ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኘም

 

አመልካች ለኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት አቤቱታ በማቅረቡ ችሎቱም ግራቀኙን ካከራከረ በኃላ የጥር ወር 2006 ዓ.ም ደመወዝ ለተጠሪ የተከፈለ መሆኑ ተረጋግጧል በማለት በዚህ ረገድ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር ፕሮፊደንት ክፍያ ጉዳይ እንዲጣራ ለሥር ፍርድ ቤት በነጥብ እንዲመለስ ሌላው የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ በማፅናት ፍርድ ሰጥቷል ፡፡


ለዚህ ሰበር ችሎት አቤቱታ የቀረበው በዚሁ ላይ ሲሆን የአመልካች የቅሬታ ነጥብ የእሁድ ቀን ሥራ ተጠሪ ሳይሰራ እንዲከፈለው መወሰኑ እና የ2006 ዓ.ም ተጠሪ አገልግሎት (የሥራ ውል) የተቋረጠው ጥር ወር 2006ዓ.ም አገልግሎት እንደሰጠ ተቆጥሮ የዓመት እረፍት ሙሉ ታስቦ እንዲከፈል መወሰኑ አግባብ አይደለም የሚል ነው፡፡

 

የሰበር ችሎቱ አቤቱታውን ከመረመረ በኃላ የእሁድ ቀን ክፍያ ለተጠሪ እንዲከፈል መወሰኑን እና የ2006ዓ.ም ሙሉ የዓመት እረፍት ተብሎ በሥር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ አግባብነት ለመመርመር ተጠሪ መልስ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡

 

ተጠሪ በበኩሉ የሥር ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ የሰጡት ውሳኔ በሕግ አግባብ የተወሰነ ነው በማለት ተከራክሯል ፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ በአጭሩ ከላይ የተገለፀ ሲሆን እኛም ለሰበር ያስቀርባል ሲባል የተያዘውን ጭብጥ መሠረት በማድረግ ከሕጉ ጋር በማገናዘብ መርምረናል፡፡

 

የአመልካች አንደኛው የቅሬታ ነጥብ እሁድ ቀን ተጠሪ ይሰራበት የነበረው ፋርማሲ ዝግ ስለነበር ተጠሪ እሁድ ቀን መሥራቱን ሳያረጋግጥ የሥር ፍርድ ቤት እሁድ ቀን ለሰራበት ይክፈሉ ማለቱ አግባብ አይደለም የሚል ሲሆን በዚህ ረገድ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ይዘት ላይ እንደተገነዘብነው የአመልካች ነ/ፈጅ በወረዳ ፍርድ ቤት በቃል ክርክርና ሲያደርግ ተጠሪ ለስራው ተከፍሎታል በማለት ስለመሆኑ የወረዳው ፍርድ ቤት በመዝገቡ አስፍሯል፡፡ የወረዳው ፍርድ ቤትም ተጠሪ እሁድ ቀን መሥራቱን የአመልካች ነ/ፈጅ ሳይክድ ነገር ግን ተከፍሎታል እያለ ስለተከራከረ የክፍያ ፔሮል አስቀርቦ መርምሮ በፔሮል የተከፈለው ወርሃዊ የደመወዝ እንጂ የትርፍ ቀን ክፍያ ስለመክፈሉ አላስረዳም በሚል በእሁድ ቀን ለሰራበት እንዲከፈል ወስኗል፡፡

 

ስለሆነም አመልካች በዚህ ረገድ ለዚህ ሰበር ችሎት ያቀረበው ቅሬታ የፍሬ ነገር ክርክር ከመሆኑም ባሻገር ተጠሪ እሁድ ቀን አልሰራም በማለት በሥር ፍርድ ቤት ያላቀረበውን የክርክር ነጥብ በዚህ ችሎት ደረጃ አጉልቶ ማቅረቡ ሲታይ ለዚህ ሰበር ችሎት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ.ሕገ መንግስት ከተሰጠ የሰበር ሥልጣን እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ ውጪ ከመሆኑም ባሻገር በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ 329/1/ መሠረትም በሥር ፍርድ ቤት ያልተነሳም የክርክር ነጥብ በየትኛውም ደረጃ ባለው የበላይ ፍርድ ቤት ተቀባይነት ስለሌለው ቅሬታው የሕግ መሠረት የለውም ብለናል፡፡

 

በሁለተኛ ደረጃ የቀረበው ነጥብ ተጠሪ ከአመልካች ጋር የነበረው የሥራ ውል ጥር ወር 2006 ዓ.ም መቋረጡ ተረጋግጦ እያለ በ2006ዓ.ም በጀት ዓመት ሙሉ አገልግሎት እንደሰጠ ታስቦ የዓመት እረፍት በገንዘብ ተሰልቶ እንዲከፈል መደረጉ አግባብ መሆን አለመሆኑን ነው፡፡


የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 77 (1)(ሀ) ላይ እንደተመለከተው ለአንድ ዓመት አገልግሎት የ14 የሥራ ቀናት በቃድ ይሰጣል፡፡አንድ ሰራተኛ ከአንድ አመት በታች አገልግሎት የሰጠ እንደሆነም በዚሁ ልክ ተመጣጣኝ የሆነ የእረፍት ጊዜ እንደሚሰጠው አንቀጽ 77(6) ላይ ተደንግጓል፡፡

 

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ ተጠሪ በ2006 ዓ.ም የበጀት ዓመት በአመልካች መ/ቤት ያገለገለው እስከ ጥር ወር 2006ዓ.ም ሲሆን የአገልግሎት ጊዜው በበጀት ዓመቱ ሲሰላ 7 ወራት ብቻ ያገለገለ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡

 

በመሆኑም አገልግሎት በሰጠበት ጊዜ ልክ ያልተጠቀመበት የዓመት እረፍት ወደ ገንዘብ ተለውጦ ሊከፈለው የሚገባው በ2006 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሙሉ እንዳገለገለ ሳይሆን በአዋጅ አንቀጽ 77(6) በተደነገገው አግባብ በአገልግሎት ጊዜው ልክ (proportion to the length of his service) የሚለውን መርህ ተከትሎ መሆን አለበት፡፡

 

በዚህ ረገድ የሥር ፍርድ ቤቶች ይህንኑ በአግባቡ ሳይመለከቱ የአንድ ዓመት ሙሉ አገልግሎት እንደሰጠ በመቁጠር የሙሉ ዓመት ፈቃድ በገንዘብ ተለውጦ እንዲከፈል መወሰናቸው የሕጉን ይዘትና ዓላማ ያላገናዘበ ሆኖ ስላገኘነው ሊታረም ይገባል ብለናል፡፡

 

ስለሆነም ተጠሪ በ1/2006ዓ.ም በአመልካች መ/ቤት የሰጠው አገልግሎት 7 ወራት ብቻ በመሆኑ ይኸው አገልግሎቱ የሚያሰጠው የዓመት ፈቃድ 8 ቀናት ብቻ ሲሆን ከሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ መረዳት እንደተቻለው ተጨማሪ የሁለት ዓመት አገልግሎት ስላለው ሁለት ቀናት ሲደመርለት ሊያገኝ የሚገባው የዓመት ፈቃድ አሥር ቀናት (10) ይሆናል ፡፡

 

በዚሁ መሠረት ስዓቱ ሲሰራ (2576*30) X10 = 858.66 ያልተጠቀመው የዓመት እረፍት ክፍያ ሆኖ በገንዘብ ተለውጦ ሊከፈለው ይገባል ብለናል ፡፡

 

በዚሁ መሠረት ተከታዩ ተወስኗል ፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የኦሮሚያ   ጠቅላይ   ፍርድ   ቤት   ሰበር   ሰሚ   ችሎት   በሰበር   መ/ቁጥር   1202

153በ07/07/07ዓ.ም የሥር ፍርድ ቤት ቤቶችን ውሳኔ በማሻሻል የሰጠው ፍርድ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 348(1) መሠረት ተሻሽሏል ፡፡


2. ለተጠሪ ሊከፈል የሚገባው የዓመት እረፍት ክፍያ ብር 1,373.86 ተብሎ በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ፍርድ ክፍል ብቻ ተሻሽሎ ብር 858.66( ስምንት መቶ ሃምሳ ስምንት ብር ከ66/100) ነው ተብሎ ተወስኗል ፡፡

3.  ሌላው የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ክፍል ፀንቷል ፡፡

4. በዚህ ፍርድ ቤት ለተደረገው ክርክር ግራቀኙ የየራሳቸውን ወጪና  ኪሣራ  ይቻሉ ብለናል ፡፡


 

 

 

ት/ጌ


መዝገቡ ተዘግቷል ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡