118263 labor dispute/ termination of contract of employment/ notice

አሠሪው ሠራተኛው በሚፈጽመው የሥራ ጥፋት  ማስጠንቀቂያ     በሰጠው ጊዜ የስራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጥ የሚችለው በ30 ቀናት ውስጥ ሲሆን ይህ ቀን ካለፈ በኋላ የሚያደርገው ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ማቋረጥ የሥራ ውል የሚቋረጥባቸውን ሕጋዊ ሥርዓቶች ያላገናዘበ ስለመሆኑ፣

 

አዋጅ ቁ.377/96 አንቀፅ 27(3)

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27/1/ሀ/3/፣43/2/

 

የሰ/መ/ቁ. 118263

ቀን ጥር 18/2008ዓ.ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመስል እንደሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- ወ/ሮ ሙሪዳ ኑረዲን ቀረቡ

 

ተጠሪ፡- አቡልኬስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር የቀረበ የለም

 

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩን ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ ጉዳይ በሰበር እንዲታይ የቀረበው መሰረታዊ የክርክር ነጥብ የአሁኑ ተጠሪ የወሰደው ከስራ የማሰናበት እርምጃ በሕጉ አግባብ መሆን ያለመሆኑን ነው፡፡ ጉዳዩ የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአሁኗ አመልካች በአሁኑ ተጠሪ በመ.ቁ. 39053 ባቀረቡት ክስ መነሻነት ነው፡፡ ጉዳዩ በየደረጃው የተመለከቱት የስር ፍ/ቤቶች በአሁኑ ተጠሪ የተወሰደው ከስራ የማሰናበት ተግባር በሕጉ መሰረት ነው በማለታቸው በሰበር እንዲታረም ያቀረበው አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን የቀረበ ነው፡፡

 

የአሁኗ አመልካች በስር ፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ያቀረቡት ክስ ባጭሩ፡- በተጠሪ ድርጅት በመጋዘን ሃላፊነት ከታህሳስ 06 ቀን 2004ዓ.ም ጀምሮ የስራ ውላቸው እስከተቋረጠበት ግንቦት 21ቀን 2006ዓ.ም ድረስ በወር 3386.32 (ሶስት ሺህ ሶስት መቶ ሰማንያ ስድስት ከሰላሳ ሁለት ሳንቲም) እየተከፈላቸው ስራቸውን ሲሰሩ እንደነበር፤ የአሁኑ ተጠሪ የስራ ውላቸው ከሕግ ውጪ ያቋረጠው በመሆኑ ስንብቱ ሕገወጥ ነው ተብሎ የስራ ስንብት ካሳ፣ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፣ የግንቦት ወር የ21ቀን ደመወዝ፣ የ4ቀን የዓመት ረፍት ክፍያ እንዲከፈላቸው እንዲወሰንላቸው ዳኝነት መጠየቃቸው የሚያሳይ ነው፡፡


ተጠሪ የመከላከያ መልስ ያቀረበ ሲሆን ዋና ፍሬ ነገሩ፡- አመልካች እቃ እያለ የለም እያሉ፤ ከድርጅቱ ሰራተኞች ባለመግባባት እና በተደጋጋሚ ከስራ በማርፈድ ጥፋት ፈጽመው ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም አላሻሻሉም፡፡ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ አይገባቸውም የ4ቀን እረፍት ወስደውታል፤ የግንቦት የ21ቀን ደመወዝ በሂሳብ ቁጥራቸው ገቢ ሆነዋል፡፡ ስንብቱ በሕግ አግባብ የተከናወነ ነው በማለት ተከራክሯል፡፡

 

የስር ፍ/ቤትም የተጠሪ ምስክሮች አድምጧል፡፡ የሰነድ ማስረጃም ተመልክተዋል፡፡ በተጠሪ የቀረቡ ምስክሮች አመልካች የድርጅቱ የስራ መግቢያ ሰዓት አያከብሩም፡፡ ከ2፡00 – 2፡30 ሰዓት ድረስ የስራ መግቢያ መሆኑን እየታወቀ ከ3፡00 - 3፡30 ይገባሉ፡፡ ከጥበቃና  ሌሎች ሰራተኞች ይጋጫሉ፡፡ ፈጸሙት ለተባለው ጥፋት በ03/03/2005ዓ.ም ፣ በ12/03/2005ዓ.ም እና በ29/02/2006ዓ.ም ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው በ12/03/2005ዓ.ም የሁለት ቀን ደመወዝ ተቀጥቷል፡፡ አመልካች የተጠሪ ማስረጃ አላስተባበሉም፡፡ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 27(1(ሀ) እና (ረ) መሰረት ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው በተደጋጋሚ ከስራ የቀሩ በመሆኑ ስንብቱ ህጋዊ ነው፡፡ የስራ ስንብት ካሳ እና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ አይገባቸውም፡፡ የእረፍት ጊዜ በተመለከተ መውሰዳቸው የተረጋገጠ ሲሆን የግንቦት ወር 21ቀን ደመወዝ ፈርመው መውሰዳቸው አልተረጋገጠም ብር 2370.59 ይክፈላቸው በማለት ወስኗል፡፡

 

የአሁኑ አመልካች በስር ፍ/ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ያቀረቡ ቢሆንም ግራቀኙ በማከራከር የስር ፍ/ቤት ውሳኔ አጽንቷል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች አቤቱታ ተመርምሮ ለሰበር ይቅረብ በመባሉ ተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ግራቀኙ የጽሑፍ ክርክር አድርጓአል፡፡ አመልካች በሰበር አቤቱታቸው ለስንብቱ ምክንያት የተባለው ነገር በስንብት ደብዳቤ እንዳልተገለጸ፤ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላ ከስራ የሚያሰናብት ጥፋት መፈጸማቸው ሳይረጋገጥ የስራ ውል መቋረጡ ሕገወጥ ነው ሊታረም ይገባል በማለት የተከራከሩ ሲሆን ተጠሪ በበኩላቸው በስንብት ደብዳቤው ላይ ምክንያት አለመገለጹ ስንብቱ ሕገወጥ አያደርገውም ውሳኔው ሊነቀፍ አይገባም የሚል መልስ አቅርበዋል፡፡ የመልስ መልስም ቀርቧል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከለይ የተገለጸው ሲሆን እኛም ጉዳዩን መርምረናል፡፡ እንደመረመርነውም የዚህ ችሎት ምላሽ የሚጠይቀው ጭብጥ የአሁኑ ተጠሪ ከአመልካች ጋር የነበራቸው የስራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጡ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 መሰረታዊ ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገ ነው ወይስ አይደለም? የሚል ሆኖ አግኝቶታል፡፡

 

አመልካች የስራ ውሉ የተቋረጠው ከሕግ ውጪ በሆነ አግባብ ነው በማለት አጥብቀው ሲከራከሩ ተጠሪ በበኩሉ የአመልካች የስራ ውል የተቋረጠው በፈጸሙት ጥፋት ነው የሚል መልስ


ማቅረቡን መዝገቡን ያሳያል፡፡ በስር ፍ/ቤት በፍሬ ነገር ደረጃ ተረጋገጠ የተባለው አመልካች እቃ የለም እንደሚሉ፤ ከስራ ባደረቦቻቸው እንደማይግባቡ እና በ03/05/2005 ፣ በ12/03/2005 ፣ እና በ29/02/2006 ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው የሚገልጽ ነው፡፡ ከዚህ መዝገብ ጋር የተያያዘው እና በተጠሪ ተጻፈ በተባለው ደብዳቤ የአመልካች የስራ ውል ከ21/09/2006ዓ.ም ጀምሮ የሁለት ወር ደመወዝ ተከፍሏቸው እንደሚቋረጥ የሚገልጽ ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪ በስንብት  ደብዳቤው ምክንያት ሳይገልጽ ፍሬ ነገሩ በማስረዳት የስራ ውል ማቋረጥ እንደሚችል ግልጽ ቢሆንም ለስንብቱ ምክንያት የሆነው ጥፋት መቼ እንደተፈጸመ ማጣራትና ግልጽ ማድረግ ግን የአሰሪው ግዴታ ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ የአሁኑ ተጠሪ አመልካች ጥፋት ፈጽመዋል በማለት የተከራከረ ቢሆንም እስከ ጥቅምት 29ቀን 2006ዓ.ም ተፈጸሙ የተባሉ ጥፋቶች መሰረት በማድረግ ቅጣት ወስኖ እንደነበር የስር ፍ/ቤት መዝገብ የሚያሳይ ቢሆንም ለመጨረሻ ጥፋት ቅጣት ከተወሰነ በኋላ ያለማስጠንቀቂያ ከስራ የሚያሰናብት ጥፋት ስለመፈጸማቸው በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ ጉዳይ አይደለም፡፡

 

በመሰረቱ አንድ አሰሪ ሰራተኛው ያለበቂ ምክንያት ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው በመደጋገም የስራ ሰዓት የማያከብር ሰራተኛ የስራ ወሉ ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጥ እንደሚችል በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 27(1)(ሀ) ስር ተመልክቷል፡፡ ከዚህ በተያያዘ እንደጥፋቱ ክብደት በስራ ቦታ አምባጓሮ መፍጠር ወይም ጠብ አጫሪነት ያለማስጠንቀቂያ ከስራ እንደሚያሰናብት ከላይ በተመለከተው ሕግ አንቀጽ 27(1(ረ) ስር ተደንጓል፡፡ በተያዘው ጉዳይ የስር ፍ/ቤት አመልካች በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው አርፍደዋል ከተቋሙ ሰራተኞች አይግባቡም ያለ ቢሆንም ድርጊቱ የተፈጸመበት ጊዜ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው ጊዜ በኋላ ስለመሆኑ አላረጋገጠም፡፡ አንድ አሰሪ በሰራተኛው ተፈጸመ ያለው ያለማስጠንቀቂያ ከስራ የሚያሰናብት ድርጊት የስራ ውሉ ለማቋረጥ ያለው መብት ድርጊቱ መከሰቱ ከታወቀበት ከ30ቀናት በኋላ በይርጋ እንደሚታገድ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 27(3) ላይ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ የአሁኑ ተጠሪ በአመልካች ተፈጸመ ያለው በተደጋጋሚ ማርፈድ፤ ከድርጅቱ ሰራተኞች ያለመግባባት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው ከጥቅምት 2006ዓ.ም በኋላ የተፈጸሙ እና ድርጊቱ መከሰቱ በታወቀ በ30ቀናት ውስጥ ህጋዊ እርምጃ ስለመወሰዱ ያቀረበው ክርክር የለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ተጠሪ የአመልካች የስራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ያቋረጠው የአዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 27(1)(ሀ)፣ (ረ) እና (3) ድንጋጌዎች መሰረታዊ ይዘትና መንፈስ ሳይከተል ነው ብለናል፡፡ የስር ፍ/ቤቶችም በተጠሪ የተወሰደው የስራ ውል ማቋረጥ ተግባር በሕጉ አግባብ ነው ማለታቸው በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ የተደነገጉትን የስራ ውል የሚቋረጥባቸው ሕጋዊ ስርዓቶች ያላገናዘበ እና መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ብለናል፡፡


የአመልካች የስራ ውል የተቋረጠው በሕጉ ከተዘረጋው ስርዓት ውጪ ነው ከተባለ የሕገወጥ ሥራ ውል ማቋረጥ ሕጋዊ ውጤት ምንድነው? የሚለው ነጥብ ቀጥሎ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ሰራተኛ የስራውሉ በሕገወጥ መንገድ ሲቋረጥ በሕጉ የተቀመጠው መፍትሔ በሕጉ የተፈቀደው ውዙፍ ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ስራ መመለስ ወይም ልዩ ልዩ ክፍያዎች ተፈጽመውለት ከስራ ማሰናበት ናቸው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 43(1) እንደተመለከተው የስራ ውሉ ከሕግ ውጭ የተቋረጠበት ሰራተኛ ወደ ስራ የመመለስ መብት አሰሪው ደግሞ የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ ሰራተኛው ወደስራ የመመለስ ካልፈለገ/ች ካሳ እንዲከፈለው የመጠየቅ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ይሁንና ፍርድ ቤት አንድ ሰራተኛ ወደስራ ሊመለስ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለው አንኳር ነጥብ ሲወሰን የስራው ባህሪ የግራቀኙ ግንኙነት እና የኢንዱስትሪ ሰላም ታሳቢ መደረግ አለባቸው፡፡ ፍ/ቤቱ ሰራተኛው ወደስራ ቢመለስ ከአሰሪው ጋር ከፍተኛ ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ብሎ ካመነ ሰራተኛው በሕጉ አግባብ ካሳ ተከፍሎት ከስራ እንዲሰናበት ሊወሰን እንደሚችል ከላይ በተመለከተው አዋጅ አንቀጽ 43(2) ስር ተመልክቷል፡፤ በተያዘው ጉዳይ የአሁኗ አመልካች በድርጅቱ ሲኒየር እስቶር ኪፐር /የመጋዘን ኃላፊ/ የነበሩ ስለመሆኑ የተካደ ጉዳይ አይደለም፡፡ የመጋዘን ሃላፊ የሚሆነው ሰራተኛ ከፍተኛ የሆነ እምነት የሚጣልበት ስራ ከመሆኑ አንጻር ከአሰሪው ጋር ጥሩ የስራ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል፡፡ አመልካች እና ተጠሪ አሁን ያላቸው ግንኙነት ከፍተኛ እምነት በሚጠይቀው የስራ መደብ አመልካች በነበሩት የስራ መደብ እንዲቀጥሉ ማድረግ በኢንዱስትሪ ሰላም እና የድርጅቱ ውጤታማነት የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ሊፈጠር እንደሚች ግምት ወስደናል፡፡ በመሆኑም አመልካች ወደ ስራ ከሚመለሱ ይልቅ በሕጉ የተፈቀዱላቸው ክፍያዎች ተከፍሏቸው ከስራ ቢሰናበቱ ለሁለቱም ተከራካሪዎች ጠቃሚ ነው ብለናል፡፡

 

የአመልካች የስራ ውል ከሕግ ውጭ በመቋረጡ ምክንያት በሕጉ የተፈቀዱ ክፍያዎች የስራ ስንብት ክፍያ፣ የካሳ ክፍያ እና የማስጠንቀቂያ ክፍያ ስለመሆናቸው ከላይ በተመለከተው አዋጅ አንቀጽ 39፣40፣43 እና 44 ተመልክቷል፡፡ የአመልካች የወር ደመወዝ 3386.38  መሆኑ በቀረቡት ክስ የተጠቀሰ ሲሆን ተጠሪም የደመወዝ መጠኑ በመካድ ያቀረበው ክርክር የሌለ በመሆኑ ለሚወሰነው ካሳ መነሻው ይህንን የደመወዝ መጠን ይዘናል፡፡ አመልካች በተጠሪ ድርጅት ከታህሳስ 06 ቀን 2004 እስከ ግንቦት 21ቀን 2006ዓ.ም የሰሩ መሆናቸውም አላከራከረም፡፡ የአመልካች የአገልግሎት ዘመን 3 አመት ከ 7 ወር ከ 16 ቀን ነው፡፡ በመሆኑም የስራ ስንብት ክፍያ በአንቀጽ 40(1) እና (2) መሰረት ብር 6,349.44፤ የካሳ ክፍያ በአንቀጽ 43(4)(ሀ) መሰረት 20,318.28 ብር፤ ተጠሪ የአመልካች የስራ ውል ያለማስጠንቀቂያ በማቋረጡ በአንቀጽ 35(1)(ለ) መሰረት የሁለት ወር ደመወዝ ለመክፈል የሚገደድ ይሆናል፡፡ ይሁንና የአሁኑ ተጠሪ የሁለት ወር ደመወዝ እንዲወስዱ በደብዳቤ የገለጸ በመሆኑ ይህንን በደብዳቤው የገለጸውን መጠን  ገንዘብ


ካልከፈለ ይክፈል ብለናል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የስር ፍ/ቤቶች በተጠሪ የተወሰደው የማሰናበት እርምጃ በሕጉ አግባብ ነው በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ሊሻር የሚገባው ሁኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ.ቁ.  39053  በ14/04/2007ዓ.ም የሰጠው ፍርድ፤ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ. 156383 በ4/12/2007ዓ.ም የሰጠው ፍርድ ተሽሯል፡፡

2. ተጠሪ የአመልካች የስራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ያቋረጠው ከሕግ ውጭ ነው በማለት ወስነናል፡፡

3. ተጠሪ የአመልካች የስራ ውል ከሕግ ውጭ በማቋረጡ የስራ ስንብት ክፍያ፣ ብር

6,349.44፤ የካሳ ክፍያ ብር 20,318.28 እና የማስጠንቀቂያ የሁለት ወር ደመወዝ ያልተከፈለ ከሆነ እንዲከፈላቸው ተወስኗል፡፡ በድምር ብር 26,667.72 (ሃያ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስድሳ ሰባት ከሰባ ሁለት ሳንቲም) እንዲሁም በስንብት ደብዳቤ የተገለጸው የሁለት ወር ደመወዝ ስራ ማፈላለጊያ የተባለው የ2ወር የማስጠንቀቂያ ደመወዝ የሚተካ ነው ብለናል፡፡ ገንዘቡ ያልተከፈለ ከሆነ ተጠሪ አሁን ከተወሰነው ገንዘብ ደምሮ መክፈል አለበት ብለናል፡፡

4. ወጪና ኪሳራ ግራቀኙ የየራሳቸው ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘጋ ወደ መ/ቤት ተመለሰ፡፡

 

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 

መ/ይ