107838 civil procedure/ amendment of pleading/ summon

አንድ ተከሳሽ በከሳሽ በመጀመሪያ ክስ ሲቀርብበት መጥሪያ ደርሶት በተከራከረበት እና ከሳሽ ክስ ያሻሽል ተብሎ በተዘጋ መዝገብ ላይ ክሱ ተሻሽሎ መዝገቡ ከተከፈተ በኋላ ለተከሳሽ በተገቢው መንገድ መጥሪያ ሳይደርስ የሚሰጥ ውሳኔ ስነ- ስርዓታዊ ስላለመሆኑ፣

የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. አንቀጽ 94-110

 

የሰ/መ/ቁ. 107838

ቀን 19/4/2008 ዓ.ም

 

 

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሱ ሲርጋጋ ፈይሳ ወርቁ

አመልካች፡-   1. አቶ ታከለ አርአያ - አልቀረቡም 2. አቶ አብርሃ ተክሉ - ቀርበዋል

ተጠሪ፡-  አቶ ደጀን ገ/እግዚአብሔር - ቀርበዋል

 

መዝገቡን ተመርምሮ የሚከተለውን ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ የሰበር አቤቱታ መዝገብ ክርክር አመልካች 1.አቶ ታከለ አረአያ 2.አቶ አብረሃ ተክሉ በቀን 23/3/2007 ዓ.ም በተፃፈ አቤቱታ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ. 05504 አከራክሮ በቀን 11/2/2007 ዓ.ም የሰጠውን ፍርድ በመቃወም የቀረበ ነው፡፡ ቅሬታቸውም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የአሶሳ ከፍ/ፍ/ቤት መጀመሪያ የቀረበው ክስ መጥሪያ ደርሶን ከቀረብን በኃላ በፍ/ቤቱ ክሱ እንዲሻሻል ታዞ መዝገቡን ዘግቶታል፡፡ ክሱ ተሻሽሎ መዝገቡ ሲንቀሳቀስ ግን የአሁን ተጠሪ (ከሳሽ) አድራሻችንን እያወቀ የሁመራ ቤት ሲታገድ መጥሪያ ሊሰጠን ሲችል በቤታችን ላይ መለጠፍ ሲቻል ፍ/ቤት ግቢ ውስጥ መጥሪያውን በመለጠፍና በጋዜጣ ጥሪ ማስደረጉ ሆን ብሎና ተገቢ አለመሆኑን መገንዘብ ሲቻል የስር ፍ/ቤት በሌለንበት የተሰጠው ውሳኔ ይነሳልን ብለን ያቀረብነውን ማመልከቻ ውድቅ ማድረጉ ስህተት በመሆኑ ይታረምል የሚል ነው፡፡ መዝገቡ ተመርምሮ አመልካቾች መጀመሪያ ክስ ሲቀርብባቸው ቀርበው መልስ የሰጡ ሲሆን በሌሉበት ይታይ የሚል ትዕዛዝ የተሰጠው ተጠሪ ክስ አሻሽሉ ተብለው መዝገቡ ከተዘጋባቸው በኃላ ባቀረቡት የተሻሻለ ክስ ጊዜ አመልካቾች ከአካባቢው አልተገኙም ተብለው በፍ/ቤት ቅጥር ግቢ እና በጋዜጣ ተጠርተው አልቀረቡም በማለት   ክርክሩ


በሌሉበት ተካሂዶ ውሳኔ የተሰጠውና አመልካቾች ይህንኑ ገልፀው ሲያመለክቱ ማመልከቻቸውን ውድቅ ማድረጉ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/አን. 94-110 ጋር ለመመርመር ሲባል ቀርቧል፡፡ መልስና የመልስ መልስም ተሰጥቶበታል፡፡

 

ተጠሪ በቀን 25/7/2007 ዓ.ም በተፃፈ መልስ አመልካቾች በአሶሳ ከፍ/ፍ/ቤት በመ.ቁ.37304 የተወሰነልኝን ውሳኔ በመ.ቁ.08505 የአፈፃፀም መዝገብ ከፍቼ መጥሪያ ላለመቀበል ከተሰወሩ በኃላ ንብረታቸው ከታገደ ከ2 ወር በኃላ ቀርበው ገንዘቡን ገቢ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ በሌለንበት የተወሰነ ውሳኔ ነው በማለት በአፈፃፀም መዝገብ ላይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/አን. 78 መሠረት አመልክተዋል እኔም ይህንኑ አንስቼ ተከራክሬያለሁ፡፡ መጀመሪያ መዝገቡ ክስ  ተሻሽሎ እንዲቀርብ ፍ/ቤቱ አዞ መዝገቡን ዘጋው ይበሉ እንጅ የተዘጋ መዝገብ የለም፡፡ አመልካቾች በሚኖሩበት ሁሉ ፈልጌ በማጣቴ ለፍ/ቤቱ አመልክቼ መጥሪያው ተለጥፏል በጋዜጣም ጥሪ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ አቤቱታቸው ውድቅ ይሁንልን ብለው ተከራክረዋል፡፡ አመልካችም በቀን 16/8/2007 ዓ.ም በተፃፈ የመልስ መልስ አቤቱታቸውን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡

 

በዚሁ መሠረት መዝገቡን እንደመረመርነው ክርክሩ የጀመረው ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት አሶሳ ከፍ/ፍ/ቤት ሲሆን አመልካች (የከፍ/ፍ/ቤት ተከሣሾች)  ለአሶሳ ከፍ/ፍ/ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ከሳሽ አቶ ደጀን ገ/እግዛብሄር በተከሳሾች (የአሁን አመልካቾች) ላይ በቀን 7/3/2005 ዓ.ም በተፃፈ ክስ አቅርቦብን እኛም ቀርበን ክርክር ከተጀመረ በኃላ ፍ/ቤቱ ከሳሽ ክስህን አሻሽል ተብሎ መዝገቡ ተዘጋ ከዚህ በኃላ መዝገቡ ሲንቀሳቀስ እኛ ያልሰማንና  ከሳሽ የኛን አድራሻ እያወቀ ሆን ብሎ ላገኛቸው አልቻልኩም በማለት በፍ/ቤት ቅጥር  ግቢ ውስጥ በመለጠፍና በጋዜጣ ጥሪ በማስደረግ ሲሆን ባለመስማታችን በሌለንበት ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ በሌለንበት መወሰኑን የሰማነው በቀን 6/8/2006 ዓ.ም በመሆኑና እንደሰማንም ቀርበን ያመለከትን ስለሆነ በሌለንበት የተሰጠው ውሳኔ እንድነሣልን በማለት አመልክተዋል፡፡ የአሁኑ ተጠሪም (የከፍ/ፍ/ቤት ከሳሽ) የሰጠው መልስ የተከሳሾች ማመልከቻ የቀረበው ለፍርድ ቤቱ በመሆኑ እኔ መልስ እንድሰጥ አይጠበቅብኝም፡፡ ፍ/ቤቱ ከሳሽ ክሱን ያሻሽል ብሎ መዝገቡን ቢዘጋም በተለዋጭ ቀጠሮ ክሱ ተሻሽሎ የሚቀርብ እንጂ መዝገብ እንድዘጋ የሚያዝ ሥነ ሥርዓትም የለም፡፡ ተከሳሾቹ መጥሪያ እንዳይደርሳቸው ሆን ብለው ከአካባቢው በመሰወራቸው ተፈልገው በአድራሻቸው ስላልተገኙ መጥሪያውን ሊያዩት በሚችሉበት ቦታ  ተለጥፏል ስለዚህ ማመልከቻቸው ውድቅ ይሁንልኝ ብሏል፡፡

 

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የአሶሳ ከፍ/ፍ/ቤት በመ.ቁጥር 08505 በቀን 21/9/2006 ዓ.ም በቀረበው ማመልከቻ ላይ የሰጠው ብይን ተከሳሾች ያቀረቡት ማመልከቻ ክርክሩ ተጀምሮ ክሱ  እንዲሻሻል  ከተደረገ  በኃላ  ከአካባቢው  ቢሰወሩም  ይኖራሉ  በሚባልበት  ቦታና  ህዝብ


በሚሰበስብበት ቦታ ሁሉ በፍ/ቤት አጥር ግቢ እና በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው አልቀረቡም ተከሣሾች (አመልካቾች) ክሱ እንዲሻሻል የታዘዘ ቢሆንም በቀጣዩ የሚቀጥል ጉዳይ መሆኑን አያውቅም ተብሎ አይታሰብም፡፡ ስለዚህ ያቀረቡት ምክንያት በቂ አይደለም በማለት ማመልከታቸውን አልተቀበልነውም ሲል መዝገቡን ዘግቷል፡፡ የአሁን አመልካቾች ለቤንሻንጉል ጉሙዝ ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርበው የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ.ቁጥር 05445 በቀን 10/10/2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/አን. 337 መሠረት የሚያስቀርብ ሆኖ አልተገኘም ሲል መዝገቡን ዘግቶታል፡፡ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም በመ.ቁ. 05504 አከራክሮ በቀን 11/2/2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ፍርድ አመልካቾች የተሻሻለው ክስ ከመጥሪያ ጋር እንዲደርሳቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ታዞ ከአካባቢው በመሰወራቸው ሌሎች የመጥሪያ አደራረስ ምርጫዎችን በመጠቀም አመልካቾች ሊመለከቱት ይችላሉ በተባሉ ግልፅ ቦታዎች እና በፍ/ቤት ቅጥር ግቢ  በመለጠፍና  በጋዜጣ ቢጠሩም ስላልቀረቡ በሌሉበት መወሰኑ እና የስር ፍ/ቤት ማመልከቻቸውን በዚህ ሁኔታ ውድቅ ማድረጉ ስህተት ያለበት ሆኖ አላገኘነውም በማለት የስር ፍ/ቤትን ትዕዛዝና ብይን በማፅናት ወስኗል፡፡ የአሁኑ አመልካቾች ይህንን ውሳኔ በመቃወም ቀርበዋል፡፡

 

በዚህ ሰበር ችሎት የተያዘው ጭብጥ አመልካቾች በመጀመሪያ ክስ ሲቀርብባቸው መጥሪያ ደርሷቸው ቀርበው ተከራክረዋል፡፡ የአሁን ተጠሪ ክስ ያሻሽል ተብሎ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ክሱ ተሻሽሎ መዝገቡ ከተከፈተ በኃላ አመልካቾች በአካባቢው አልተገኙም በማለት መጥሪያ በፍ/ቤት ግቢ በመለጠፍና በጋዜጣ ጥሪ በማድረግ አልቀረቡም በማለት በሌሉበት የተወሰነው ተጠሪና አመልካቾች ጎን ለጎን በእርሻ እንቨስትመንት የተሠማሩ መሆኑ እየታወቀ በፍ/ቤት ቅጥር ግቢ መለጠፉና በጋዜጣ ጥሪ የተደረገላቸው እየታወቀ በፍ/ቤት ቅጥር ግቢ መለጠፉና በጋዜጣ ጥሪ የተደረገላቸው መሆኑ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/አን 94-110 ካለው የመጥሪያ አሰጣጥ ድንጋጌና ከመጥሪያ አሠጣጥ አላማ ጋር ለመመርመር ነው፡፡ በተያዘው ጭብጥ መሠረት አመልካቾች መጀመሪያ በአሁን ተጠሪ ክስ ሲቀርብባቸው መጥሪያ አድርሷቸው ቀርበዋል፡፡ የሥር ፍ/ቤት ተጠሪ (የሥር ፍ/ቤት ከሣሽ) ክሱን ያሻሽል ብሎ መዝገቡን ዘግቶታል፡፡ ክሱ ተሻሽሎ መዝገቡ ሲከፈት ለአመልካቾች መጥሪያ ሊደርሣቸው ይገባል፡፡ የስር ፍ/ቤት የአመልካቾች አቤቱታ መጥሪያ ሣይደርሰን በሌለንበት የተሰጠው ውሳኔ ይነሣልን ጥያቄ ውድቅ ያደረገበት ምክንያት አመልካቾች መጥሪያ እንዳይደርሳቸው ተሸሽገዋል በሚልና መዝገቡ ተዘግቶ በሚቀጥለው ቀጠሮ ክርክሩ እንዲቀጥል ማወቅ ይችላሉ ሲል ነው፡፡ የሥር ፍ/ቤት ተከሣሾች (የአሁን አመልካቾች) በሚቀጥለው ቀጠሮ ክርክሩ ይቀጥላል ለማለት የሚችሉት መዝገቡ ባይዘጋና ቀጠሮ ቢሰጥ እንጂ መዝገቡ ተዘግቶ ቀጠሮ ባልተሰጠበት የሚቀጥለውን ቀጠሮ ሊያውቁ የሚችሉበት መንገድ የለም፡፡ አመልካቾች መጀመሪያ መጥሪያ ደርሷቸው ቀርበው እያለ መጥሪያ እንዳይደርሳቸው    የተሸሸጉ


ወይም መሰናክል ያደረጉ መሆኑን የሥር ፍ/ቤት ተረድቻለሁ የሚለው ተጠሪ ከገለፀላቸው ውጪ በሌላ መንገድ የተረጋገጠ ስለመሆኑ የተገለፀው ነገር የለም፡፡ አመልካቾች ከተጠሪ ጋር ጎን ለጎን የእርሻ ኢንቨስትመንት ሥራ ይሰራሉ በዚህ የሥራ ቦታቸው መጥሪያ እንዲደርሳቸው የተደረገ መሆኑ ወይም የተለጠፈ መሆኑ የተገለፀ ነገር የለም፡፡ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ.አንቀጽ 100 ይገልፃል፡፡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 105 በተደነገገው መሠረት በመኖሪያ ቤታቸው ወይም  በመጨረሻ ጊዜ ይኖሩበት በነበረ ሥፍራ መጥሪያ የተለጠፈ መሆኑ የተገለፀ የለም፡፡ ይህ በቅድሚያ የሚወሰድ የመጥሪያ አደራረስ ዘዴ እያለ የሥር ፍ/ቤት የመጨረሻ አማራጭ በጋዜጣ ጥሪ መጥሪያ ማድረግ ዘዴ ተጠቅሞ እና ተከሳሾች (የአሁን አመልካቾች) መጥሪያ ሣይደርሰን ሳንሰማ በሌለንበት የተሰጠ ውሳኔ ይነሳልን አቤቱታ ውድቅ ማድረጉ ተገቢ ሆኖ አልታየንም፡፡ በመሆኑም አመልካቾች ተዘግቶ የነበረው መዝገብ ተከፍቶ ክርክር የጀመረ መሆኑን ባልሰሙበት የሥር ፍ/ቤት የመጥሪያ አስፈላጊነት ተከራካሪዎች ቀርበው እንዲከራከሩ ያላቸውን ህጋዊ መብት ለማክበር ፍ/ቤቱም እውነቱን እንዲደርስበት ለማስቻል በመሆኑ መጥሪያ ለአመልካቾች ሲያደርሳቸው በቅድሚያ ሊጠቀም የሚገባውን የመጥሪያ አደራረስ መንገድ በመተው የመጨረሻ አማራጭ በጋዜጣ ጥሪ በመጠቀሙና አመልካቾች ይህንኑ ገልፀው መጥሪያውን ያልሰሙና በሌለንበት የተሰጠው ውሳኔ ይንሣልን ብለው ሲያመለክቱ ውድቅ ማድረጉ መሠረታዊ የህግ ሥህተት የተፈፀመበት ነው ብለናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1.  የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የአሳሳ ከፍ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 08505 ግንቦት 21  ቀን

2006 ዓ.ም የሰጠው  ውሳኔ፣ የቤ/ጉ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ.ቁ. 05454 ሰኔ 10    ቀን

2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ፣ የቤ/ጉ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.

05504    ጥቅምት    11   ቀን   2007   .ም   በዋለው    ችሎት    የሰጠው   ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/አንቀጽ 348(1) መሠረት ተሽሯል፡፡

2. የአሁን አመልካቾች ክስ እንዲሻሻል ተብሎ የተዘጋ መ.ቁጥር 07304 ተከፍቶ ክርክር የጀመሩ መሆኑን ሳያውቁ መጥሪያ በአግባቡ ሳይደርሳቸው የተሰጠ ውሳኔ እንዲነሳላቸው ያቀረቡት ምክንያት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/አንቀጽ 78(2) መሠረት ውሳኔውን ለማንሳት በቂ በመሆኑ በመ.ቁጥር 07304 የተሰጠው ውሳኔ ተነስቷል የቤ/ጉ/ክ/መ/የአሶሳ ከፍ/ፍ/ቤት የተሻሻለውን ክስ ለአመልካቾች አድርሶ ካከራከረ በኃላ ውሳኔ እንዲሰጥበት መልሰናል፡፡

3.  በዚህ መዝገብ ወጪና ኪሣራ ተቻቻሉ ብለናል፡፡

4.  በ17/6/2007 ዓ.ም የተሰጠ እግድ ተነስቷል፡፡ ይፃፍ፡፡

5.  መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መ/ቤት ተመልሷል፡፡የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

የ/ማ