ፍ/ቤት በተዋዋዮች መሃል የተደረገን ውል (የእርቅ ስምምነት) ህጋዊነታቸውን ሳይረጋገጥ ሊያፀድቅበት የሚችልበት አግባብ የሌለ ስለመሆኑ
የፍ/ሕ/ቁ.1731
የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.277
የሰ/መ/ቁ. 109497
የካቲት 3 ቀን 2008ዓ.ም
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ
ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ
አብርሃ መሰለ ፈይሳ ወርቁ
አመልካች፡- አቶ አግማስ ኡመር እና ወ/ሮ ሰብረና ጌታቸው ጠበቃ ይትባረክ መኮንን ቀርበዋል
ተጠሪ፡- አቶ ኡመር አሳዬ እና ወ/ሮ አሰገድ ሃሰን -ጠበቃ መስፍን እሼቱ ቀርበዋል መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
በዚህ የሰበር አቤቱታ መዝገብ ክርክር አመልካቾች አቶ አግማስ ኡመር እና ወ/ሮ ስብርና ጌታቸው ጥር 26ቀን 2007ዓ.ም በተጻፈ አቤቱታ የፌ.ከፍ/ፍ/ቤት በመ.ቁጥር 156998 ታህሳስ 20 ቀን 2007ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው ትእዛዝ ቅር በመሰኘት የቀረበ ነው፡፡ ቅሬታቸውም የውል ስምምነት በተዋዋዮች መሀከል ሕግ መሆኑ ተደንግጎ እያለ የውል ስምምነት የህግና የሞራል ጥሰት እንዲሁም ሌሎች ህጋዊ ምክንያቶች የተጓደሉበት ሁታዎች የተካተቱበት ሲሆን እና እነዚህ ምክንያቶች ከተዋዋዩ በአንዱ ወገን ላይ የመብት ሆነ የግዴታ ተጽእኖ የበለጠ የሚያበዛበት ሆኖ የተገኘ ከሆነ ተቀባይነት የለውም ሊባል ካልተቻለ በቀር የስር ፍ/ቤት ካለበቂ ምክንያት ስምምነታችንን ውድቅ ማድረጉ ተገቢ ባለመሆኑ ይታረምልን የሚል ነው፡፡
በስር ፍ/ቤት የተደረገው ክርክር በአፈጻጸም የፍ/ባለመብቶች (የአሁን አመልካቾች) በፍ/ባለእዳ (የአሁን ተጠሪዎች) ላይ ብር 480,000 እንዲከፍሉን ተወስኖልናል ሲሉ የአፈጻጸም መዝገብ በፌ.የመ.ደረጃ ፍ/ቤት ይከፍታሉ፡፡ ፍ/ቤቱም የአ.ፍ/ባለእዳዎች በውሳኔው መሰረት እንዲፈጽሙ
ያዛል፡፡ የፍርድ ባለመብቶች (የአሁን አመልካቾች) ከፍ/ባለእዳዎች ጋር ሰኔ 13 ቀን2006ዓ.ም በአፈጻጸም ስምምነት አድርገናል፡፡
በዚሁ ስምምነት መሰረት ፍርዱ እንዲፈጸም ስምምነቱን ፍ/ቤቱ አጽድቆ የፍ/ቤት ማህተም አርፎበት እንዲሰጠን ሲሉ ያመለክታሉ፡፡ የፍ/ባለእዳዎችም ተስማምተዋል፡፡
የፌ.የመ.ደረጃ ፍ/ቤት በመ.ቁ. 215541 አከራክሮ ሐምሌ 11ቀን 2006ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ትእዛዝ የቀረበው አቤቱታ በተመለከተ ፍ/ቤት የተሰጠ ፍርድ፣ ውሳኔ ያስፈጽማል፡፡ የተሰጠው ውሳኔ ብር 480,000 እንዲከፍል ነው የቀረበው ስምምነት ደግሞ ቤት ለማስረከብ የተዋዋሉ መሆኑን ያሳያል፡፡ እንዲፈጸም ከቀረበው ፍርድ የተለየ ነው፡፡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 396(1) መሰረት ተስማምተው ፈጽመው ከቀረቡ ተቀብሎ ትእዛዝ ይሰጣል ይሁንና እንደዋና ክስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 277 መሰረት ውል ተመዝግቦ ውሳኔ መስጠት ግን የሚቻል ባለመሆኑ አልተቀበልነውም ሲል አዟል፡፡ የአሁን አመልካቾች ለፌ.ከፍ/ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርበው ከፍ/ፍ/ቤት በመ.ቁጥር 156998 ታህሳስ 20ቀን 2007ዓ.ም በዋለው ችሎት የስር ፍ/ቤት የሰጠው ትእዛዝ ስህተት የተገኘበት አይደለም ሲል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 337 መሰረት ይግባኙን ሰርዞታል፡፡
የአሁን አመልካች ይህን ትእዛዝ ቅር በመሰኘት ቀርበዋል፡፡ መዝገቡ ተመርምሮ የስር ፍ/ቤት ግራቀኙ ስለፍርዱ አፈጻጸም ከፍርድ ውጪም ቢሆን የተስማሙበትን ውል በተመለከተ ተቀብሎ አልመዘግብም ያለበትን አግባብ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 277 እና 396 እንዲሁም ከፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1731 ድንጋጌዎች አንጻር ተገቢነቱን ለማጣራት ሲባል ቀርቧል፡፡ መልስና የመልስ መልስም ተሰጥቶበታል፡፡ ተጠሪዎች ሰኔ 5 ቀን 2007ዓ.ም በተጻፈ መልስ የፍ/ባለእዳዎች ከፍ/ባለመብቶች ጋር ተስማምተን ስምምነቱን ለፍ/ቤት አቅርበን እያለ በተጠሪነት መጠራታችን ተገቢ ባመሆኑ በነጻ እንሰናበት ሲል ተከራክረዋል፡፡ የአሁን አመልካቾችም ሐምሌ 3 ቀን 2007ዓ.ም በተጻፈ መልስ አቤቱታቸውን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ከተያዘው ጭብጥ አኳያ መዝገቡን እንደመረመርነው የአሁን አመልካች ግንቦት 26 ቀን 2006ዓ.ም በተሰጠው ውሳኔ መሰረት እንዲፈጸምላቸው ያቀረቡት የአፈጻጸም ክስ ብር
480,000 እንዲከፈላቸው ነው፡፡ ፍ/ቤት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 277 መሰረት ተዋዋዮቹ በእርቅ መጨረሳቸውን ገልጸው እንዲጸድቅላቸውና ከመዝገቡ ጋር ተያይዞ በእርቁ መሰረት እንዲፈጸም ትእዛዝ እንዲሰጥላቸው የጠየቁት ፍርዱ የባለእዳ (የአሁን ተጠሪ) ቤት ላይ እንዲፈጸም ነው፡፡ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 277(1) ተከራካሪዎቹ ነገሩን በእርቅ ለመጨረስ ለፍ/ቤቱ ሲያቀርቡ የእርቁ ስምምነት ሕግንና ሞራልን የማይቃረን መሆኑን ፍ/ቤቱ ስረዳው እርቁን ተቀብሎ በማጽደቅ ከመዝገቡ ጋር ማያያዝ እንደሚገባው ይደነግጋል፡፡ የአሁን አመልካችና የተጠሪ የእርቅ ስምምነት በገንዘብ እንዲከፈል የተወሰነን ውሳኔ የአሁን ተጠሪን ቤት ለአመልካች ለማስተላለፍ (ለመፈጸም)
የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ ለአሁን አመልካች የሚፈጸም ቤት የእርቅ ስምነነቱ ህጋዊነት የማረጋገጥ ጉዳይ በተመለከተ ሊነሳበት የሚችል ክርክር ጋር በተያያዘ እራሱን የቻለ ማጣራት የሚፈልግና ውሳኔ የሚያስፈልገው ጉዳይ በመሆኑ ፍ/ቤት በተዋዋዮች መሃል የተደረገ ውል በፍ/ብ/ሕ/አንቀጽ 1731 እንደሚደነግገው ውሎች ባቋቋማቸው ሰዎች ላይ ሕግ በመሆናቸው ብቻ ህጋዊነታቸው ሳይረጋገጥ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 277 በሚደነግገው አንጻር የእርቅ ስምምነቱን ተቀብሎ በአፈጻጸም መዝገብ ላይ የሚያጸድቅበት አግባብ የለም፡፡ ለአፈጻጸም ተብሎ የተደነገው ስርዓት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 396 በሚደነግገው መሰረት አመልካችና ተጠሪዎች ከፍ/ቤት ውጭ በተደረገ ስምምነት በውሳኔው መሰረት ለፍ/ባለመብቱ የተከፈለ መሆኑን ለፍ/ቤቱ ካሳወቁት ፍ/ቤቱ ስምምነቱን ተቀብሎ ትእዛዝ የሚሰጥበት አካሄድ ተገቢነት ያለው ነው፡፡ በመሆኑም የስር ፍ/ቤት ይህንኑ በማተት የሰጠው ትእዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አላገኘነውም፡፡
ው ሳ ኔ
1. የፌ.ከፍ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 156998 ታህሳስ 20ቀን 2007ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ትእዛዝ፣ የፌ.የመ.ደረጃ ፍ/ቤት በመ.ቁ. 215541 ሐምሌ 8 ቀን 2006ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ትእዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348(1) መሰረት ጸንቷል፡፡
2. በዚህ መዝገብ ወጪና ኪሳራ ተቻቻሉ ብለናል፡፡
3. መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መ/ቤት ተመልሷል፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡