110150 civil procedure/ security for cost

 

ከሳሽ በተከሳሽ ላይ ለሚደርሰው ኪሳራ ዋስ እንዲያሲዝ የሚጠየቀው ከሳሽ በክሱ ምክንያት በተከሳሽ ላይ የሚደርሰውን ኪሳራ ለመክፈል የሚያስችሉ ሁኔታዎች የሚያጠራጥር ሲሆንና ኪሳራውንም ለመክፈል የሚያስችል ሃብት ወይም ገንዘብ የሌለው በሆነ ጊዜ ስለመሆኑ

የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 200

 

የሰ/መ/ቁጥር 110150

 

የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀንዓ ቂጣታ

አመልካች፡- አቶ ገ/መድህን ወ/ሚካኤል - ጠበቃ አብይ ጌታቸው ቀረቡ ተጠሪዎች፡- 1. አቶ ግርማይ ፍትዊ - ጠበቃ ወርቅነሽ መንግስቱ ቀረቡ

2. የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ፅ/ቤት - ነ/ፈጅ ሙሴ ዳዊት ቀረቡ

 

3. የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅ/ቤት

 

- ዐቃቤ ሕግ ታደሰ አንዳርጌ ቀረቡ

 

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

1. ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የውጭ አገር ዜጋ በመሆናቸው ተከራክረው በለቱ  አንደኛ ተጠሪ ለሚደርስባቸው ኪሳራ ዋስትና የሚሆን ብር 5‚500 /አምስት ሺ አምስት መቶ ብር/ እንዲያስይዙ የተሰጠውን ትዕዛዝ አልፈፀመም በሚል የስር ፍርድ ቤት አመልካች በተከሳሾች ላይ ያቀረበውን ክስና መዝገብ መዝጋቱ የሕግ መሰረት ያለው ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ የክርክሩ መነሻ አመልካች ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያቀረበው ክስ ነው፡፡ አመልካች ለስር  ፍርድ ቤት ያቀረበው ክስ ይዘትም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ኤርትራዊያን ከአገር ሲወጡ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ 13 የሚገኘውን ቁጥሩ 3018 የሆነ ቤት ለአንደኛ ተከሳሽ /አንደኛ ተጠሪ/ አከራይቸው ነበር ሁለተኛ ተከሳሽ ይህንን ቤት በአንደኛ  ተከሳሽ


ሸጦለታል፡፡ የከሳሽ ዕዳ ነው በሚል ከቤቱ ዋጋ በመቀነስ ለሶስተኛ ተከሳሽ ከከፈለ በኋላ ቀሪውን ገንዘብ በብሔራዊ ባንክ በኩል ሲሳብ በስሜ አስቀምጧል፡፡ ከሳሽ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በመንግስት ፈቃድ ከተመለስኩ በኋላ ለሶስተኛ ተከሳሽ በድጋሜ ክፍያ ፈፅሜለሁ፡፡ ስለዚህ ከሳሽ ከመንግስት መመሪያ ውጭ አከራይቸው ለሄድኩት አንደኛ ተከሳሽ ቤቴን ለመሸጥ ሁለተኛ ተከሳሽ ያደረገው ውል ፈራሽ እንዲሆንልኝ፡፡ ይህ የማይቻል ከሆነ ከቤቱ ዋጋ አላግባብ ያስቀነሰው ገንዘብና ለሶስተኛ ተከሳሽ በድጋሜ የከፈልኩት ገንዘብ እንዲመለስልኝ በማለት ክስ አቅርቧል፡፡

2. አንደኛ ተጠሪ /አንደኛ ተከሳሽ/ አመልካች በዚህ አገር ዜጋና ኗሪ ባለመሆኑ በክርክሩ ለሚደርስብኝ ኪሳራ ዋስትና ያስብልኝ በማለት ተከራክሯል፡፡ የስር ፍርድ ቤት ከሳሽ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ ለሚያደርሰው ኪሳራ ብር 5‚500 /አምስት መቶ ሺ አምስት መቶ ብር/ ዋስትና እንዲያስይዝ፣ በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የስር ፍርድ ቤት ሰኔ 10 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት አመልካች በዋስትና እንዲያሲዙ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠበትን የዋስትና ገንዘብ ያላስያዙና በሁለተኛ ተከሳሽና በሶስተኛው ተከሳሽ ላይ የቀረበው ክስ በአንደኛ ተከሳሽ ጋር ከቀረበው ክስ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልፆና የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 201 ጠቅሶ መዝገቡን ዘግቶታል፡፡ አመልካች በዚህ ትዕዛዝ ቅር በመሰኘት ያቀረበውን የይግባኝ ቅሬታ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 መሰረት ሰርዞታል፡፡

3. አመልካች አንደኛ ተጠሪ ከጠየቀው የዋስትና ገንዘብ በላይ በብሔራዊ ባንክ በስሜ በግል አካውንት የተቀመጠ ገንዘብ እንዳለ በክስ ማመልከቻየ ገልጨ እያለ፣ ከዚህ ገንዘብ ለኪሳራ የሚሆን ገንዘብ እንደታገደ በማድረግ ክርክሩን መቀጠል ስችል  የስር  ፍርድ ቤት የዋሰትና ገንዘብ እስዲያስይዝ የሰጠው ትዕዛዝና ትዕዛዙን አልፈፀምክም በማለት መዝገቡን መዝጋቱ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት የካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም የተፃፈ የሰበር አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ተጠሪዎች በተናጥል አመልካች የስር ፍርድ ቤት በሕግ በተደነገገው  መሰረት እንዲያስይዝ ትዕዛዝ የተሰጠበትን የዋስትና መዝገብ ያላስያዘው በመሆኑ አመልካች ትዕዛዙን እስኪፈፀም ድረስ የስር ፍርድ ቤት መዝገቡን መዝጋቱ የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 201 መሰረት ያደረገ በመሆኑ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በሚል ይዘት ያለው መልስ አቅርበዋል፡፡ አመልካች የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡

4. ከስር የክርክሩ አመጣጥና ግራ ቀኙ ያቀረቡት የፅሁፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም ጉዳዩን መርምረናል፡፡ ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች ክስ ያቀረበው ሁለተኛ ተጠሪ ለአንደኛ ተከሳሽ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በነበረው ጦርነት ምክንያት እኔ ከአገር ስወጣ፣ ከመመሪያ ውጭ የፈፀመው የቤት ሽያጭ ውል ፈራሽ ይደረግልኝ፡፡


የሽያጭ ውሉ አይፈረስም ከተባለ፣ በብሔራዊ ባንክ በከሳሽ ስም  በግል አካውነት የተቀመጠ ገንዘብ፣ ከቤቱ ሽያጭ አንደኛ ተከሳሽ ከሳሽ የግብር እዳ ያለብኝ መሆኑን ሣያረጋግጥ ቀንሶ ለሶስተኛ ተከሳሽ የከፈው ክፍያ እና ከሳሽ ለሶስተኛ ተከሳሽ ከቤቱ ዋጋ ተቀንሶ ለሶስተኛ ተከሳሽ የተከፈለ መሆኑን ሣላውቅ በድጋሜ የከፈልኩት ገንዘብ እንዲመለስ ውሳኔ ይሰጥልኝ በማለት እንደሆነ ግራ ቀኙ ካቀረቡት ክርክር ተረድተናል፡፡

5. የከሳሽ ክስ በመሰረታዊ ባህሪውን ይዘቱ ከሳሽ በክርክሩ ረች ወይም ተረች ቢሆን አንደኛ ተጠሪ በክርክሩ ምክንያት የሚያደርስበትን ኪሣራ ለመሸፈን የሚያስችል  ገንዘብ የሚያሳጣ አይደለም፡፡ ከሳሽ በአንደኛ ተጠሪና ሁለተኛ ተጠሪ መካከል የአመልካች ቤት ለመሻሻጥ የተዋዋሉት ውል ፈራሽ ነው ቢባል፣ አመልካች ለተጠሪዎች ኪሳራ መክፈል እንደማይገደዱ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ 463 ንዑስ አንቀፅ 2 ይደነግጋል፡፡ በሌላ በኩል አመልካች አንደኛ ተጠሪና ሁለተኛ ተጠሪ የተዋዋሉት የቤት ሽያጭ ውል ይፍረስልኝ ጥያቄ ውድቅ ቢሆንበትና አመልካች በክርክሩ ተረቶ ቢሆን፣ በክርክሩ ምክንያት በተጠሪዎች ላይ ያደተሰውን ኪሳራ ለመክፈል የሚችል ሁለተኛ ተጠሪ ቤቱን በአንደኛ ተጠሪ ሸጦ በአመልካች ስም በብሔራዊ ባንክ በግል አካውንት ያስቀመጠው ጥሬ ገንዘብ ያለ መሆኑን አመልካች ካቀረበው ክስ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ አንደኛ ተጠሪ አመልካች በክርክሩ ለሚያደርስበት ኪሳራ የዋስትና ገንዘብ እንዲያሲዝ ያቀረበውን ጥያቄ የስር ፍርድ ቤት በብሔሪዊ ባንክ ከሚገኘውና በአመልካች ስም በዝግ አካውንት ከተቀመጠው ገንዘብ፣ በአንደኛ ተጠሪ በክርክር ምክንያት ለሚደረስበት ኪሳራ መከፈያ እንዲሆን ብር 5‚500 /አምስት ሺ አምስት መቶ ብር/ ብሔራዊ ባንክ አግዶ እንዲያቆይ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 155 ንዑስ አንቀፅ 2 መሰረት ትዕዛዝ መስጠት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ሰምቶና አከራክሮ ውሳኔ ለመስጠት እየቻለ፣ አመልካች የኪሳራ ገንዘብ እንዲያስይዝ የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 200 ንዑስ አንቀፅ 1 እና ንዑስ አንቀፅ 2 የተደነገጉትን ድንጋጌዎች መስፈርት የሚያሟላ አይደለም፡፡

6. በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 200 ንዑስ አንቀፅ 1 እና ንዑስ አንቀፅ 2 መሰረት ከሳሽ በተከሳሽ ላይ ለሚደርሰው ኪሳራ ዋስ እንዲያስይዝ የሚጠየቀው፣ ከሳሽ በክሱ ምክንያት በተከሳሽ ላይ የሚደርሰውን ኪሳራ ለመክፈል የሚችሉ ሁኔታ የሚያጠራጥር ሲሆንና ኪሳራውንም ለመክፈል የሚያስችል ሀብት ወይም ገንዘብ የሌለው በሆነ ጊዜ እንደሆነ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 200 ንዑስ አንቀፅ 2 እና ንዑስ አንቀፅ 3 ተደግጓል፡፡ ከዚህ አንፃር የስር ፍርድ ቤት አንደኛ ተጠሪ በክርክሩ ለሚደርስበት ኪስራ አመልካች ዋስትና እንደሰጠው ያቀረበውን ጥያቄ፣ በአመልካች ስም በዝግ አካውነት በብሔራዊ ባንክ ከተቀመጠው ገንዘብ በአንደኛ ተጠሪ ላይ ሊደረስ ይችላል ተብሎ የገመተውን ኪሳራ ማለትም ብር 5‚500 /አምስት ሺ አምስት መቶ ብር/ ባንኩ ይዞ እንዲቆይ በማዘዝ የአመልካችን ሕገ መንግስታዊ   ፍትሕ


የማግኘት መብት በማያጣብብ ሁኔታ ለማስፈፀም እየቻለ፣ አመልካች የዋስትና ገንዘብ እንዲያሰጥ የሰጠው ትዕዛዝ የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 200 ንዑስ አንቀፅ 2 እና ንዑስ አንቀፅ 3 እና የሕገ መንግስቱን አንቀፅ 37 ንዑስ አንቀፅ 1 ድንጋጌዎች የሚጥስና መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

7. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤት አመልካች ከሕግ አግባብ ውጭ የዋስትና ገንዘብ እንዲያስይዝ የሰጠውን ትዕዛዝ እንዳልፈፀመ ገለፆ መዝገቡን መዝጋቱ ከላይ የጠቀስናቸውን የሕግ ድንጋጌዎች፣ የሚጥስ መሆኑን ገልፆ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ መሻር ሲገባው፣ የአመልካችን ይግባኝ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 መሰረት መሰረዙ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል፡፡

 ው ሳ ኔ

1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 212488 ሰኔ 10 ቀን

2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር

157449 ታህሳስ 16 ቀን 2007 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ ተሽሯል፡፡

2. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በብሔራዊ ባንክ በአመልካች ስም በዝግ አካውንት ከተቀመጠው ገንዘብ ብር 5‚500 /አምስት ሺ አምስት መቶ ብር/ ወጭ እንዳይሆን የዕግድ ትዕዛዝ በመስጠትና የተዘጋውን የመዝገብ ቁጥር 212488 በማንቀሳቀስ የአመልካችን እና የተጠሪዎችን ክርክርና ማስረጃ በመስማትና በመመርመር ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 341/1/ መሰረት መልሰን ልከንለታል፡፡

3. በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 


 

 

ብ/ይ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡