112927 civil procedure/ admission/ procedure when claim admitted

ከሳሽና ተከሳሽ ያልተካካዱበትና ከሳሽ በክሱ ገልፆ ተከሳሽ ባመነው ነጥብ ላይ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ማስረጃ በመመዘን ሳይሆን ተከሳሹ በሰጠው የእምነት ቃል ወይም መልስ መሰረት መወሰን ያለበት ስለመሆኑ

የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.242

የሰ/መ/ቁ. 112927

ቀን የካቲት 16/2008 ዓ.ም

 

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሀመድ ተኽሊት ይመሰል እንደሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- የማርዘነብ ዕቁብ ዳኛ አቶ ባዬ አጥናፉ - ጠበቃ አለጌታ መርሻ - ቀረቡ

ተጠሪዎች፡- 1. አቶ ዋለልኝ ተመስገን - ቀረቡ

2. አቶ አዲሱ ጥሩነህ

 

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

1. ጉዳዩ ላልተከፈለ የዕቁብ ገንዘብ የተሰጠ የዋስትና  ግዴታ የሚመለከት  ነው፡፡ የአመልካች ዕቁብ አባል የሆነ ወርቁ ሚናስ የተባለና የሥር አንደኛ ተከሳሽ የሆነ ሰው የዕቁብ እጣ ደርሶት ብር 465,000 /አራት መቶ ስልሣ አምስት ሺ ብር/ ተቀብሎ ሲወስድ ቀሪውን የዕቁብ እጣ በየጊዜው የሚከፍል ስለመሆኑ፣ አቶ ወርቁ ሚናስ የዕቁብ ገንዘብ መጣሉን ቢያቋርጥ፤ ተጠሪዎች ገንዘቡን የሚከፍሉ ስለመሆኑ ተጠሪዎች የዋስትና ግዴታ ገብተው ፈርመዋል፡፡ አቶ ወርቁ ሚናስ መክፈል የነበረበትን ብር 222,000 /ሁለት መቶ ሃያ ሁለት ሺ ብር/ ሣይከፍል የዕቁብ ገንዘቡን መጣሉን በማቋረጡ አመልካች አንደኛ ተከሳሽ ወርቁ ሚናስና እሱ የዕቁብ ገንዘቡን ሲወስድ ዋስ የሆኑት ተጠሪዎች ገንዘቡን እንዲከፍሉ ውሣኔ ይሰጥልን በማለት ለምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ አቅርቧል፡፡

2. ተጠሪዎች የዕቁብ አባላትና የዕቁብ ገንዘብ በእጣ ደርሶት የወሰደው አቶ ወርቁ ሚናስ ዋስ እንደሆነ ገልፆም በዕቁብ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የዚህ አይነት የዕቁብ ገንዘብ ለዕቁብተኛ ሲሰጥ የዕቁቡ ኃላፊዎች አራት ዋሶችን አስጠርተው ገንዘቡን መስጠት ነበረባቸው፡፡ የዕቁብ ኃላፊዎች ሁለት ዋሶችን አስጠረተው ገንዘብ መስጠታቸው የዕቁቡን መተዳደሪያ ደንብ ያልተከተለ መሆኑን ስለማያሳይ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ተከሳሾች እያንዳንዳችን ክስ የቀረበበትን


ገንዘብ አንድ አራተኛውን ብቻ ነው የመክፈል ኃላፊነት ያለብን በማለት መልስ የሰጡ መሆኑን የሥር ፍርድ ቤት በውሣኔው አስፍሮታል፡፡

3. የሥር ፍርድ ቤት ዕቁብ የደረሰው ሰው የደረሰውን የዕቁብ ገንዘብ ከመውሰዱ በፊት የዕቁብ አባላት የሆኑ ስንት ዋሶችን የመጥራት ኃላፊነት እንዳለበት በጭብጥነት ይዞ ለማጣራት የዕቁቡን መተዳደሪያ ደንብና የምስክሮችን ቃል ከሰማ በኃላ የዕቁቡ ኃላፊዎች የዕቁቡን ገንዘብ የወሰደውን አቶ ወርቁ ሚናስ አራት ዋሶችን የማስጠራት ኃላፊነት የለባቸውም ስለዚህ አንደኛ ተከሳሽ ወርቁ ሚናስ ያልከፈለውን የዕቁብ ገንዘብ ይክፈል፡፡ የዕቁቡን ገንዘብ አንደኛ ተከሳሽ ካልከፈለ፣ ሁለተኛ ተከሳሽና ሶስተኛ ተከሳሾች ይክፈሉ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

4. ተጠሪዎች የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ በመቃወም ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው የተጠሪዎችን ይግባኝ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 መሠረት ሰርዞታል፡፡ ተጠሪዎች የሰበር አቤቱታ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የሰበር አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የግራ ቀኙ ክርክር ከሰማ በኃላ ተጠሪዎች የፈረሙት የዋስትና ውል በፍታብሔር ሕግ ቁጥር 1725 እና በፍታብሔር ህግ ቁጥር 1723 የተደነገገውን መሰረት የሚያሟላ ባለመሆኑ ዋስትናው ህጋዊ ውጤት የለውም፡፡ ተጠሪዎች አንደኛ ተከሳሽ የዕቁብ ገንዘብ ሲወስድ በሰጡት ዋስትና አይገደዱም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

5. አመልካች ለዚህ ሰበር ችሎት ባቀረበው የሰበር አቤቱታ ተጠሪዎች በሥር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ የዕቁብ ገንዘብ ደርሶት ቢወሰድ ዋስ መሆናቸውን በግልፅ ክደው አልተከራከሩም፡፡ በአንፃሩ ተጠሪዎች ዋስ እንደነበሩ አምነው ክስ ከቀረበበት ገንዘብ አንድ አራተኛውን ብቻ እንደሆነ ገልፀው ተከራክረው እያለ የዋስትና ውሉ የህጉን ፎርማት አያሟላም በማለት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የሰጠው ትርጉምና ውሣኔ የህግ መሠረት የሌለው በመሆኑ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል፡፡ ተጠሪዎች በሥር ፍርድ ቤት የዋስትና ውሉን በመቃወምና በመካድ የተከራከርን በመሆኑ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የዋስትና ውሉ ህጋዊ መስፈርቶችን ያሟላ መሆኑን በመመርመር የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡ አመልካች የመልስ መልስ ሰጥተዋል፡፡

6. ከሥር የክርክሩ አመጣጥና ግራ ቀኙ በሰበር ያቀረቡት የፅሑፍ ክርክር ከላይ  የተገለፀው ሲሆን እኛም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ተጠሪዎች የፈረሙት የዋስትና ውል የህጉን ፎርም አያሟላም በማለት ተጠሪዎች ክስ ያቀረበበትን የዕቁብ ገንዘብ የመክፈል ኃላፊነት የለባቸውም በማለት የሰጠው ውሣኔ አግባብነት ያላቸውን  የህግ ድንጋጌዎች መሠረት ያደረገ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡ ጉዳዩን እንደመረመርነው ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለመወሰን በመጀመሪያ ተጠሪዎች  በሥር


አንደኛ ተከሳሽ የሆነው አቶ ወርቁ ሚናስ ለደረሰው የዕቁብ ገንዘብ ዋስ መሆናቸው በሥር ፍርድ ቤት አከራካሪ ጭብጥ ሆኗል ወይስ አልሆነም? የሚለውን ነጥብ ማየት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

7. ተጠሪዎች ለሥር ፍርድ ቤት በሰጡት መልስ የአመልካች የዕቁብ አባላት መሆናቸውንና እነርሡም በስማቸው የዕቁብ ገንዘብ የሚጥሉ መሆኑን፣ አቶ ወርቁ ሚናስ የተባለ ዕቁብተኛ የዕቁብ ገንዘብ ሲደርሰው ዋስ ሆነው ያፈረሙ መሆኑን በማመን ለሥር ፍርድ ቤት መልስ የሰጡ መሆኑ የሥር ፍርድ ቤት በውሣኔው በግልፅ አስፍሯል፡፡ ተጠሪዎች በሥር  ፍርድ ቤት አቶ ወርቁ ሚናስ ለወሰደው የዕቁብ ገንዘብ የዋስትና ግዴታ የገቡ መሆኑን ሣይክዱ፣ አከራካሪ ነጥብ አድርገው ያቀረቡት በገቡት የዋስትና ግዴታ መሠረት ሊከፍሉ የሚገባውን የገንዘብ መጠን እንደሆነና ተጠሪዎች የቁብ ኃላፊዎች በአቶ ወርቁ ሚናስ የዕቁብ ገንዘቡን ከመስጠታቸው በፊት አቶ ወርቁ ሚናስ አራት ዋስ እንዲጠራ ማድረግ ሲገባቸው በእኛ ዋስትና ብቻ የዕቁቡን ገንዘብ የከፈሉት ከዕቁቡ መተዳደሪያ ደንብ ውጭ ስለሆነ እኛ የምንገደደው እያንዳንዳችን አቶ ወርቁ ሚናስ የወሰደውንና ሣይከፍል የቀረውን የዕቁብ ገንዘብ 1/4ኛ ብቻ ነው በማለት እንደሆነ የሥር ፍርድ ቤት በውሣኔው አስፍሯል፡፡

8. የአንድ ጉዳይ አከራካሪ ጭብጥ ከሳሽ በክስ የገለፀውንና ተከሳሽ በመልሱ ክዶ የተከራከረበት ነጥብ እንደሆነ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 246 ንዑስ አንቀጽ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተከራካሪዎች ክርክራቸውን የሚያስረዳ ማስረጃ እንዲያቀርቡ የሚገደዱትና ፍርድ ቤቱን በተከራካሪዎች ያቀረበውን ማስረጃ ተዓማኒት ክብደት የሚመዝነው ግራ ቀኙ ተካክደው በሚከራከሩበት ጭብጥ ላይ ብቻ እንደሆነና ከሳሽና ተከሳሽ ያልተካካዱበትና ከሳሽ በክሱ ገልፆ ተከሳሽ ባመነው ነጥብ ላይ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ማስረጃ በመመዘን ሣይሆን በተከሳሹ በሰጠው የዕምነት ቃል ወይም መልስ መሠረት መወሰን እንዳለበት በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 242 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ይዘትና መሰረታዊ ዓላማ በመመርመር ለመረዳት  ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር ተጠሪዎች አቶ ወርቁ ሚናስ የዕቁብ እጣ ወጥቶለት በቁብ ያደረሰውን ገንዘብ ከዕቁቡ የሥራ ኃላፊዎች ሲወስድ እነርሱ የዋስትና ግዴታ የገቡ መሆኑ ያልተካደና አከራካሪ ጭብጥ ባለመሆኑ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተጠሪዎች የታመነውን ወርቁ ሚናስ ላልተከፈለው የዕቁብ ገንዘብ የገቡት የዋስትና ግዴታ መኖሩን ለማስረዳት አመልካች ያቀረበው የውል ሰነድ የህጉን ፎርም አያሟላም በማለት የሰጠው ውሣኔ ከላይ የጠቀስናቸውን የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 246 (1) የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 242 ድንጋጌዎችና አመልካቾች ያለበት የማስረዳት ግዴታ እስከምን ድረስ እንደሆነ ያላገናዘበና መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

9. የሥር ፍርድ ቤት የአመልካች የዕቁብ ኃላፊዎች ተጠሪዎችን በሰጡት ዋስትና ብቻ የዕቁቡን ገንዘብ በዕቁቡ ባለዕድል /ባለ እጣ/ አቶ ወርቁ ሚናስ መክፈላቸው ተገቢ ነው ወይስ


አይደለም? ተጠሪዎች በዋስትናው መክፈል የሚገባቸው ወርቁ ሚናስ የወሰደውን የዕቁብ ገንዘብ ሙሉውን ነው ወይስ እያንዳንዳቸው አንድ አራተኛ (ግማሹን ገንዘብ) የሚለውን አመልካችና ተጠሪዎች የተካከደበትን ጭብጥ በመያዝ የሰውና የፅሑፍ ማስረጃ ሰምቶ ተጠሪዎች ወርቁ ሚናስ የወሰደውን ሣይከፍል ያቀረበውን የዕቁብ ገንዘብ እያንዳንዳቸው 1/2ኛውን (ሙሉ ገንዘቡን) የመክፈል ኃላፊነት አለባቸው በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡ ይህም የሥር ፍርድ ቤት የደረሰበት የፍሬ ጉዳይና የማስረጃ ምዘና መደምደሚያ በይግባኝ ሰሚው ችሎት ፀንቷል፡፡ በመሆኑም የክልሉ ሰበር ችሎት አከራካሪ የፍሬ ጉዳይ ጭብጥ ያልሆነ ተከራካሪዎች ያልተካካደበት ነጥብ ጭብጥ አድርጎ በመያዝ የዋስትና ውሉ የህጉን ፎርም ስለማያሟላ ተጠሪዎች የዕቁብ ዋስ በመሆን ለገቡት ግዴታ ተጠያቂ አይደሉም በማለት የሰጠው ውሣኔ ከላይ የተጠቀሱትን የህግ ድንጋጌዎች የሚጥስና መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

1. የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 44853 መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ ተሽሯል፡፡

2. የምስራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 7630 ጥቅምት 19 ቀን 2007 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ

ቁጥር 39054 ታህሣሥ 23 ቀን 2007 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ ፀንቷል፡፡ 3.  በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የራሳቸው ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 


 

 

የ/ማ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡