104028 civil procedure/ review of judgment/ period of limitation

የዳግም ዳኝነት ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለሟሉ ስለሚገባቸው  ጥብቅ መስፈርቶች;-

አንድ   ክስ  በይርጋ   መዘጋቱ   ዳግም   ዳኝነት  ጥያቄውን   ለማስተናገድ እንደበቂ ምክንያት/እንደመመዘኛ/ የማይወሰድ ስለመሆኑ:-

 

 የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.6

 

የሰበር መዝገብ ቁጥር 104028

የካቲት 17 ቀን 2008 ዓ/ም

ዳኞች፡-1.አልማው ወሌ

 

2.ዓሊ መሐመድ

 

3.ተኽሊት ይመስል

 

4. እንዳሻው አዳነ

 

5.ቀነዓ ቂጣታ

 

አመልካች፡- ወ/ሮ ብዙአየሁ ያለው - ቀረቡ ተጠሪ፡-አቶ ሲሳይ ካሴ   - ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የገጠር እርሻ መሬት መብት መሰረት አድርጎ የቀረበውን ይዞታ ይለቀቀልኝ ጥያቄን የሚመለከት የቀረበውን ክርክር በግራ ቀኙ ማስረጃና ከሚመለከተው አካል በቀረበው ማረጋገጫ መሰረት ይዞታው የተጠሪ ነው ተብሎ ከተወሰነ በኋላ ለውሳኔው መሰረት የሆነውና ከሚመለከመተው አስተዳደር አካል የተሰጠው የሰነድ ማስረጃ ሐሰተኛነቱ ከውሳኔው በኋላ ማስረጃውን በላከው አካል ተረጋግጧል በሚል የቀረበውን የዳግም ዳኝነት ይታይልን ጥያቄ የሚመለከት ነው፡፡ ክርክሩ የጀመረው በላይ ጋይነት ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 02162 ሲሆን ጉዳዩ በመጀመሪያ ሲጀመር የአሁኑ ተጠሪ ከሳሽ፣ አመልካች ደግሞ ተከሳሾች ነበሩ፡፡ የአሁኑ ተጠሪ ከሳሽ አመልካችና አመልካች እና አቴ ብርሃን ደመቀ ደግሞ ተከሰሽ ነበሩ የአሁን ተጠሪ ያቀረቡት ክስ ይዘትም፡- ቁበላይ ገይንት 01 ቀበሌ አስተዳደር መኮቢያ ገብሬኤል ገብር ውሥት ጥሩ 498/ለ እና 501 የሆኑ ቤቶች ግማሹ የሟች አባታችን የአቶ ገብሬ ድንቅነህ ሲሆኑ ወረሾች ነን፣ ግማሹን ደግሞ ሟች ወ/ሮ ብዙነሽ አደራ በኑዛዜ ሰጥተውናል በማለት ቤቱን ተጠሪዎች ያላግባብ መያዛቸውን ዘርዝረው ቤቱ እንዲለቀቅ ይወሰን  በማለት ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚሳይ ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪዎችም ለክሱ በሰጡት መከላከያ መልስ ክሱ በይርጋ የታገደ ነው በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ከማቅረባቸውም በተጨማሪ በፍሬ ነገሩም ተገቢ ነው ያሉትን ክርክር አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያውን መሰረት


አድርጎ ጉዳዩን በመመርመር የአመልካቾች ክስ ከሰላሳ ሶስት አመት በኋላ የቀረበ ነው በማለት በይርጋ ቀሪ ነው በማለት ቤቱን ሊያስረክቡ አይገባም ሲል በመ/ቁጥር 75780 የተከፈተውን መዝገብ ዘግቶታል፡፡ ከዚህም በኋላ የአሁኑ አመልካቾች  የአሁኑ  3ኛ ተጠሪ  የሟች ወ/ሮ ብዙነሽ አደራ ወራሽነትን በመጠየቅ የሟቿ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ ናቸው ተብሎ በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 147267 የተሰጠውን ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 መሰረት ተቃውመው ፍርድ ቤቱን ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪው የሟቿ ልጅ ሳይሆኑ የወራሽነት ማስረጃ መውሰዳቸውን አመልካቾች አረጋግጠዋል ተብሎ የቀደመው የወራሽነት ማሰረጃ እንዲረዝ ታህሳስ 09 ቀን 2006 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተሰጥቶአል፡፡ ከዚህ በኋላ የአሁኑ አመልቾች የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 75780 የተሰጠውን ብይን በሕገ ወጥ መንገድ በተገኘ የወራሽነት ማስረጃ ምስክር  ወረቀት ያሰጡት  ብይን ነው በማለት በድጋሚ እንዲታይ ዳኝነት ጠይቀው ፍርድ ቤቱም በይርጋ የተዘጋ ክስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 6 መሰረት በድጋሚ የሚታይበት አግባብ የለም በማለት ሳይቀባላቸው ቀርቶአል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ብይን በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡-3ኛ ተጠሪ ያገኙት የወራሽነት ማስረጃ ሐሰተኛ ነው ከተባለ ተጠሪዎች ይህንኑ የሚያስተባብል ማስረጃ ባላቀረበቡት ሁኔታ የውርስ ንብረቱን አይለቁም ተብሎ የተሠጠው ብይን በዳግም ዳኝነት የሚታይ አይደለም ተብሎ  የአመልካቾች ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ያላግባብ ነው የሚል ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም የአመልካቾች የቀደመው ክስ በይርጋ የታገደ ን በሚል ምክንያት የዳግም ዳኝነት ጥያቄው ሳይታይ የመታለፉን አግባብነት ለመመርመር ተብሎ ጉዳዩ ለዚህ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን 1ኛ፣2ኛ እና 4ኛ ተጠሪዎች ሊቀርቡ ስላልቻሉ በፅሑፍ መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፎአል፡፡ 3ኛ ተጠሪ ግን ቀርበው በሠጡት መልስ፡-የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ አቀራረብ ስርዓቱን ያልጠበቀ መሆኑን፣ የአመልካቾች የቤት ይለቀቅልኝ ጥያቄ በይርጋ ውድቅ የሆነበት መ/ቁጥር 75780 እና የተጠሪን የወራሽነት ማስረጃ ያሰረዙበት መዝገብ ቁጥር 147267 ግንኙነት የሌላቸው በመሆኑ የዳግም ዳኝነት ጥያቄው የሚቀርብበት አግባብ የሌለ መሆኑን ዘርዝረው የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ አመልካቾችም የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካለቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም በጉዳዩ ላይ ዳኝነት የተሰጠው ተገቢው የክርክር አመራር ስርዓት ተፈፅሞና ተገቢው ጭብጥ ተይዞ፣ በሕጉ   አግባብ


መጣራት   ተደርጎ   ነው?   ወይስ  አይደለም?   የሚሉት   ነጥቦች  ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር    6 ድንጋጌዎች ይዘት መመልከቱ ተገቢ ሁኖ አግኝቶታል፡፡

 

በዚህም መሰረት የአሁኑ አመልካቾች ለወረዳው ደረጃ ፍርድ ቤት አቤቱታ ያቀረቡት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 6 መሰረት ዳግም ዳኝነት እንዲታይላቸው በመጠየቅ ሲሆን የስር ፍርድ ቤትም አቤቱታውን በጉዳዩ ላይ ቀድሞ ፍርድ ቤት ከተሠጠበት መዝገብ ቁጥር 02162 ውጭ በመቀበል ተጠሪዎችን ያቀረቡት አቤቱታ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 6 መሰረት ሊስተናገድ እንደማይችል በማመን የአመልካቾች የቀድሞ ክስ በይርጋ የታገደ ነው ተብሎ ብይን  የተሰጠበት በመሆኑ በዳግም ዳኝነት ስርዓት ሊታይ የሚችል አይደለም በማለት አቤቱታው ውድቅ አድርጎታል፡፡

 

ይህ ችሎት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 6 ይዘቱንና መንፈሱን ከሌሎች የፍተሓብሔር ሥነ ስርአት ውስጥ ከተመለከቱት የማስረጃ አቀራረብ ደንቦች እና የፍርድ መቃወሚያ ስርዓቶች ጋር በማገናዘብ እንዲሁም የድንጋጌው ዓላማ በእውነት ላይ የተመሰረተ ዳኝነት እንዲሠጥ ማድረግ ከመሆኑ አኳያ በመመርመር ለተጠቀሰው ድንጋጌ በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(1) ድንጋጌ መሰረት አስገዳጅ የሆነ የሕግ ትርጉም በመ/ቁጥር 43821 እና በመ/ቁጥር 32269 ሠጥቶበታል፡፡በሰ/መ/ቁጥር 43821 ላይ በቀረበው ጉዳይም ይህ ሰበር ችሎት በመ/ቁጥር 16624 የያዘውን አቋም ማለትም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 6 መሰረት የዳግም ዳኝነት ጥያቄ መቅረብ ያለበት ይግባኝ ከመቅረቡ በፊት እንጂ በይግባኝ ቀርቦ ውሳኔ ባገኘ ጉዳይ አይደለም በማለት የሠጠው የሕግ ትርጉም በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(1) መሰረት ተለውጧል፡፡ በዚህም መሰረት የዳግም ዳኝነት ጥያቄ ጉዳዩ በይግባኝ ታይቶ ውሳኔ ከተገኘ በሁዋላም ቢሆን በቁጥር 6 ስር የተመለከቱት መመዘኛዎች ተሟልተው እስከተገኙ ድረስ መቅረብ እንደሚችል ተግለጾ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ተሰጥቷል፡፡

አሁን በተያዘው ጉዳይ አከራካሪው የሕግ ነጥብ /ጉዳይ/ የአመልካቾች ጥያቄ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 6(2) ስር የሚወድቅ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ስለሆነ ይህን ድንጋጌ ማየቱ ለጉዳዩ አወሳሰን ይጠቅማል፡ ይህ ድንጋጌ ይግባኝ ሊቀርብበት የሚችል የመጨረሻ ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ  ከተሰጠ በኋላ ውሳኔው ወይም ትዕዛዙ የተሰጠው በሃሰት ተዘጋጅቶ በቀረበ ሰነድን ሃሰተኛ የምስክርነት ቃልን፣ ወይም መደለያን ወይም ወንጀል ጠቅሶ የሆነ ተግባርን መሰረት አድርጎ መሆኑን አቤት ባዩ ሲረዳው ጉዳዩ በይግባኝ ከመታየቱ በፊት ውሳኔውን የሰጠው ፍ/ቤት ራሱ ዳኝነቱን በድጋሚ እንዲያይ ጥያቄ ለማቅረብ መብት የሚሰጠው ነው፡፡ የድንጋጌው ሙሉ ይዘትና መንፈስ የሚያሳየው የመጨረሻው ፍርድ ከተሰጠ በሁዋላ ሀሰተኛ ሰነድ ወይም ሀሰተኛ የምስክርነት ቃል ወይም መደለያ እንደተደረገና አቤት ባዮም ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት አስፈላጊውን ትጋት አድርጎ ለማወቅ ያለመቻሉን በሚገባ ለማስረዳት የሚችል የሆነ እነደሆነ፣እነዚህ ጉዳዮች መኖራቸው  ወይም መፈጸማቸው ታውቆና ተገልጾ ቢሆን ኖሮ ለፍርድ መለወጥ ወይም መሻሻል በቂ ምክንያት ሊሆኑ ይችል እንደነበር ለማስረዳት የቻለ እንደሆነ፣ የተሰጠ ፍርድ ሊያስለውጥ የሚችል አዲስ ማስረጃ ማግኘቱ ብቻ  ፍርድ


እንደገና እንዲታይ የማያደርግ መሆኑን፣ ማስረጃው ፍርዱን በማሳሳት ውጤቱን ያበለሸና ተገቢ ያልሆነ ድርጊትን የሚያሳይ መሆን ያለበት መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም  ማስረጃውም በሐሰት ተዘጋጅቶ የቀረበ ሰነድን፣ ሀሰተኛ የምስክርነት ቃልን ወይም መደለያን ወይም ወንጀል ጠቀስ ተግባርን መሰረት ያደረገ መሆንና ማስረጃው ፍርዱ በሚሰጥበት ጊዜ ፍርዱ እንደገና ይታይልኝ የሚለው ተከራካሪ ወገን ማስረጃው መኖሩን ያውቀው የነበረ ያለመሆኑ፣ ይግባኝ ቀርቦበት ከሆነ አዲስ ማስረጃው ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ግምት ውስጥ እንዲያስገባ ይግባኙ ለቀረበለት ፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑ፣ የተገኘው አዲስ ማስረጃ የሀሰት ሰነድን፣ ሀሰተኛ ምስክርነትን፣ መደለያንና የመሳሰሉትን የሚመለከት ለመሆኑ ማረጋገጫ መኖሩን በሚጠቅስ ቃለመሐላ የተደገፈና ማስረጃው አስፈላጊው ትጋት የተደረገበት ቢሆንም ፍርዱ በተሰጠ ጊዜ በአመልካቹ ያልታወቀ መሆኑን የሚገልፅ መሆን ያለበት መሆኑ በቅድመ ሁኔታነት ሊሟሉ የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ድንጋጌው ያስገነዝባል፡፡ የዳግም ዳኝነት ጥያቄ ጥብቅ መለኪያዎች ያሉት መሆኑን ከድንጋጌው ይዘት መንፈስ መገንዘብ የምንችለው ጉዳይ ሲሆን የድንጋጌው ጥብቅ የመሆን አይነተኛ አላማም የተሰጡ ውሳኔዎችን አጣራጣሪነት ለማስወገድ መሆኑ ይታመናል፡፡ ስለሆነም የዳግም ዳኝነት ጥያቄ የቀረበለት ፍርድ ቤት ለውሳኔው መሰረት የሆነው ሰነድ ወይም ማስረጃ ሐሰተኛ መሆኑን ብቻ ሳይሆን በሕጉ የተመለከቱት ሁሉም  መመዘዎችን  አቤቱታ አቅራቢው ማሟላቱን በቅድሚ ሊያረጋገጥ ይገባል፡፡

በተያዘው ጉዳይ አመልካቾች የሚከራከሩት 3ኛ ተጠሪ አለኝ የሚሉት የወራሽነት ማስረጃ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሰረዝ ተደርጎአል በሚል ነው፡፡ይሁን እንጂ የስር ፍርድ ቤት ይህ የሰነድ ማስረጃ ሐሰተኛ ነው ከተባለ 3ኛ ተጠሪ በመ/ቁጥር 75780 በነበረው ክርክር የክርክሩ ተሳታፊ መሆን ይችል ነበር ወይስ አልነበረም?፣ በአመልካቾች ላይ የይርጋ መቃወሚያውን ሊያነሳ የሚችልበት ሕጋዊ መብትና ጥቅም አለው ወይስ የለውም?፣ ይርጋ ለማንሳት የሚችል ከሆነስ ለግራ ቀኙ ክርክር አግባብነት የሚኖረው የይርጋ ጊዜ ምን ያህል ነው፣ አግባብነት ያለው የይርጋ ጊዜ ከተለየ በኋላስ የአመልካች የቤት ይለቀቅልኝ ጥያቄ ውድቅ ለማድረግ የሚያስችል ነው ወይስ አይደለም? የሚሉትንና ይህ ሁሉ የሚታለፈ እና ወደ ፍሬ ነገሩ የሚገባ ከሆነ ደግሞ አከራካሪ ቤቶች የውርስ ንብረት መሆን ያለመሆናቸውንና ለአመልካቾች የሚለቀቁበት አግባብ መኖር ያለመኖሩ በጭብጥነት ተይዞ በፍሬ ጉዳዩ ላይ ተገቢው ዳኝነት የሚሠጠበት ይሆናል፡፡ ስለሆነም አንድ ክስ በይርጋ መዘጋቱ የዳግም ዳኝነት ጥያቄውን ላለማስተናገድ እንደበቂ ምክንያት የማይወሰድና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 6 ድንጋጌም በመመዘኛነት ያልተቀመጠ በመሆኑ በዚህ ረገድ የስር  ፍርድ ቤት ያስቀመጠውን ምክንያት አልተቀበልነውም፡፡

ሲጠቃለልም የአመልካቾች የዳግም ዳኝነት ጥያቄ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 6 ሰር የተመለከቱትን ጥብቅ መመዘኛዎችን ያማሏ መሆን ያለመሆኑ በቅድሚያ ከታዬ በኋላና ጥያቄያቸው በሕጉ የተመለከተውን መስፈርት የሚያሟላ ነው የሚባል ከሆነም በመልካቾች   እና


በተጠሪዎች መካከል ተፈፃሚነት ያለው የይርጋ ጊዜ ተለይቶ ክሱ አግባብነት ባለው የይርጋ ጊዜ ቀሪ የማይሆን ከሆነም ግራ ቀኙ በፍሬ ነገሩ ክርክር አድርገውበትና በተገቢው መንገድ ሁሉ ፍርድ ቤቱ በራሱ አነሳሽነትም በተጨማሪ ማስረጃዎች አጣርቶ እንዲሁም ወደ ክርክሩ ሊገባ የሚገባው አስፈላጊ አካል ካለም ወደ ክርክሩ እንዲገባ አድርጎ ክርክሩን ከመራው በኋላ በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ዳኝነት ሊወሰንበት የሚገባው ሁኖ ስለአገኘን  በጉዳዩ ላይ  የበታች  ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል፡፡በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሣ ኔ

 

1. በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 75780 ሐምሌ 23 ቀን 2006 ዓ.ም የተሰጠው ብይን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሸሯል፡

2. የአመልካቾች የዳግም ዳኝነት ጥያቄ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 6 ስር የተመለከቱትን ጥብቅ መመዘኛዎችን ያሟላ መሆን ያለመሆኑ ሳይጣራ ክሱ በይርጋ ውድቅ የሆነ ነው በሚል ምክንያት ብቻ ተቀባይነት የሚያጣበት አግባብ የለም፣ አቤቱታቸው በሕጉ  የተመለከተውን መመዘኛ ያሟላል ከተባለም ለጉዳዩ አግባብነት ያለው የይርጋ ጊዜ ተለይቶና በስነ ስርዓት ሕጉ አግባብ ክርክሩ ተመርቶ ተገቢው ዳኝነት ሊሰጥበት ይገባል ብለናል፡፡

3. የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ክርክሩን በመ/ቁጥር 75780 ቀጥሎ በፍርድ ሐተታው ላይ ስለዳግም ዳኝነት አቀራረብ ስርዓትና መመዘኛዎች እንዲሁም ለጉዳዩ ተፈፃሚነት ያለውን ይርጋ ጊዜ በመለየት እና የአመልካቾችን ክርክርና ማስረጃ እንዲሁም የተጠሪዎችን ክርክርና ማስረጃ በመመርመርና እውነታውን ለማወቅ የሚረዱ የሰነድ ማስረጃዎችን  በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 145(1) መሠረት በማስቀረብ፣ የክርክሩ አስፈላጊ ወገን ካለም ወደ ክርክሩ በማስገባት አከራካሪውን ቤት የማን ነው? በሚለው ላይ ተገቢውን ሁሉ በማጣራት ውሣኔ እንዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 341(1) መሠረት መልስን ልከንለታል፡፡ ይፃፍ፡፡

4.  በዚህ ችሎት ክርክር ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ ብለናል፡፡

 

 

መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡