በጊዜያዊ ትእዛዝ ላይ በሚሰጥ ብይን ቅር የተሰኘ አካል የስረ ነገሩ ክርክር የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ እስካልተገኘ ድረስ ይግባኝ (የሰበር) አቤቱታ ሊቀርብ የማይችል ስለመሆኑ
የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.320(3)
የሰ/መ/ቁ. 116209
የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ
ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ
ሸምሱ ሲርጋጋ ፈይሳ ወርቁ
አመልካች - የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን - አልቀረቡም
ተጠሪ - ወ/ሮ ምፅላል አብርሃ - አልቀረቡም
መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡
ፍ ር ድ
ጉዳዩ የቀረበው በግራ ቀኙ መካካል ባለው የንብረት ካሳ ክርክር በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በማዕከላዊ ዞን ማዕከላዊ ፍርድ ቤት የአብይ አዲ ምድብ ችሎት በመ/ቁ 02634 ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ያሳለፈውን ብይን በመቃወም ነው ፡፡ አመልካች ይግባኝ የቀረበበት የገንዘብ መጠን ብር 791,225.00 (ሰባት መቶ ዘጠና አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሃያ አምስት) በመሆኑ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመወሰን ስልጣን የለዉም፤ እንዲሁም በስር በተደረገ ክርክር ተካፋይ አልነበርኩም የሚሉ መቃወሚያዎችን አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱም መቃወሚያዎችን ከመረመረ በኋላ ባሳለፈው ብይን ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 455/1997 አንቀጽ 11(4) እንዲሁም የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 29(4) ስር እንደተደነገገው ካሳን በተመለከተ በተሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ተከራካሪ ወገን ለሚመለከተው የከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ወይም የከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በሌለበት ለሚመለከተው መደበኛ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሊያቀርብ እንደሚችል ከሚደነግጉ በቀር የተጠቀሱት አዋጆች በካሳዉ ግምት መጠን ወደተለያየ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚቀርብ የሚደነግጉ ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን አለው ብሏል፡፡ ሁለተኛውን መቃወሚያ በተመለከተም የአሁን አመልካች እየተሰራ ያለው መንገድ ባለቤት በመሆኑ ለመንገድ ስራ ስለተወሰደው መሬት እና በመሬቱ ላይ ስለነበረው ንብረት ካሳ የመክፈል ግዴታ እንዳለበት
በአዋጁ በግልፅ ስለተደነገገ፤ በሚመለከተው የአስተዳደር አካል ፊት ተከራካሪ አልነበርኩም የሚል ክርክር ቢያቀርብም በስር የተወሰነውን ካሳ ከፋይ ከሆነ በካሳው መጠን ላይ ለቀረበው ይግባኝ መልስ እንዲሰጥ እና እንዲከራከር መደረጉ በአግባቡ ነው በማለት መቃወሚያውን ውድቅ አድርጓል፡፡ ይህን ተከትሎም የግራ ቀኙን ክርክር ለመስማት ቀጠሮ ለውጧል፡፡
የሰበር አቤቱታዉ የቀረበው አመልካች ያነሳቸውን መቃወሚያወች ውድቅ በማድረግ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን በመቃወም ነው ፡፡ አመልካች ሀምሌ 20 ቀን 2007 ዓ.ም ያቀረበው የሰበር ማመልከቻ ተመርምሮ መቃወሚያዎቹ ውድቅ ተደርገው ወደ ክርክሩ ለመግባት የተሰጠውን ብይን ስነስርዓታዊነት ለመመርመር ሲባል ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጓል ፡፡ በዚሁ መሰረት ግራ ቀኙ ክርክራቸውን በጽሁፍ ተለዋዉጠዋል፡፡
ከላይ ባጭሩ የገለጽነው የጉዳዩን አመጣጥ ሲሆን በበኩላችን በመጀመሪያ በሰበር የተያዘውን ጭብጥ ከመወሰናችን በፊት ጉዳዩ የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠበትና በሰበር መታየት የሚችል ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ማየቱ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ከላይ እንደተገለፀው የሰበር አቤቱታ የቀረበው የክልሉ የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአመልካች የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ ብይን ሰጥቶ ክርክር ለመስማት ቀጠሮ መያዙን በመቃወም ነው ፡፡ ነገር ግን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በዳኝነት አይቶ ውሣኔ የሚሰጠው የመጨረሻ ውሣኔ ባገኙ ጉዳዮች ላይ ስለመሆኑ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 80 ንኡስ አንቀፅ 3/ሀ/ ተደንግጓል ፡፡ ከዚህም ሌላ ማናቸውም ፍርድ ቤት ክርክሩን በሚሰማበት ጊዜ በመጀመሪያ በሚቀርብ መቃወሚያ ላይ ተገቢ መስሎ የታየውን ብይን ሲሰጥ ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊት ይግባኝ (የሰበር አቤቱታ) ሊቀርብ እንደማይችል ፤ ስለሆነም ለክርክሩ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በመቃወሚያው ላይ በተሰጠው ብይን ያለውን ቅሬታ ጨምሮ ከስረ ነገሩ ጋር ይግባኝ (የሰበር አቤቱታ) ለማቅረብ እንደሚቻል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 320(3) ስር ተደንግጓል
ቅሬታ የቀረበበት ብይን ይዘትና ተገቢነት ያላቸው የህጉ ድንጋጌዎች ከላይ የተመለከተው በመሆኑ አመልካች በተሰጠው ብይን ላይ ቅሬታ ካለውም በስረ-ነገሩ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ፍርድ ከተሰጠ በኋላ ይህንን ቅሬታም ጨምሮ በአንድ ላይ በማጠቃለል ያቀርባል እንጂ ክርክሩ እንዲቀጥል በተደረገበት ሁኔታ በብይኑ ላይ የሰበር አቤቱታ ማቅረቡ ህጉን መሠረት ያደረገ ሆኖ አላገኘነውም በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡
ው ሳ ኔ
1. አመልካች ጉዳዩ የመጨረሻ ውሣኔ ሳያገኝ ለሰበር ችሎት ያቀረበውን አቤቱታ ለማስተናገድ የሚቻልበት የህግ መሠረት የሌለ በመሆኑ አቤቱታውን አልተቀበልነውም፡፡
2. በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በማዕከላዊ ዞን ማዕከላዊ ፍርድ ቤት የአብይ አዲ ምድብ ችሎት በመ/ቁ 02634 ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ባሳለፈው ብይን ላይ ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊት የሰበር አቤቱታ ሊቀርብበት የሚቻል አይደለም ብለናል፡፡
3. በዚህ መዝገብ በ05/01/2008 ዓ.ም ተሰጥቶ የነበረው የአፈፃፀም ዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል ይፃፍ፡፡
4. ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፣ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡
የ/ማ