105054 family law/ common property/ agreement on partition of common property

አንድ ጋብቻ ሲፈርስ ንብረት ክፍፍልን በሚመለከት በእርቅ ውል ስምምነት በሽማግሌ የተደረገው እርቅ በፍ/ቤት ተመዝግቦ ከተዘጋ በኋላ እንደገና እንደ ባልና ሚስት አብረን እየኖርን ስለነበር በድጋሚ የንብረት ክፍፍል ይደረግ የሚል ጥያቄ አግባብነት ያለው ስላለመሆኑ፣

 

የሰ/መ/ቁ. 105054

ታህሳስ 22 ቀን 2008ዓ/ም

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ሙስጠፋ  አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

አመልካች፡- ወ/ሮ ጌጤ እጅጉ -ቀርበዋል ተጠሪ፡-አቶ ብርሃኑ ተሰማ   -ቀርቧል

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የባልና ሚስት አፈፃፀም የሚመለከት ነው፡፡ ክርክሩ የተጀመረው በሌሙና ቢልቢሎ ወረዳ ፍርድ ቤት ተጠሪ ባቀረቡት የአፈፃፀም ክስ ነው፡፡ የአቤቱታውን ይዘትም ባጭሩ በመ/ቁ.343/96 በቀን 21/8/1996 ዓ/ም የነበረው ጋብቻ ሲፈርስ ንብረት ክፍፍል በሚመለከት በእርቅ ውል ስምምነት በሽማግሌ የተደረገው እርቅ በፍርድ ቤት ተመዝግቦ ተዘግተዋል፡፡ በዚሁ መሰረትም አንድ ወፍጮ ቤት፤ አንድ የዘይት መጭመቂያ ቤት እና አንድ ፒፒሻ ሽጉጥ የተጠሪው እንደሆነ ፍርድ ቤት በውሳኔው አረጋግጠዋል፡፡ ከውሳኔ በኃላ ታርቀን በባልና ሚስት ሆነን ስንኖር የዲገሉና ጢጆ ወረዳ ፍርድ ቤት መ/ቁ.19963 በቀን 9/8/ 2005ዓ/ም እና የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ.6054 በቀን 19/10/05ዓ/ም በመ/ቁ. 343/96 በሆነው መዝገብ ላይ የተሰጠ የንብረት ክፍፍል እንዳይነካ ሲል ተወስነዋል፡፡ ስለዚህ የወፍጮ ቤት የነበረው አሁን የእንጨት መሰንጠቂያ የሆነው እና የዘይት መጭመቂያ ቤት ስም ይዛወርልኝ ፒፒሻ ሽጉጥ ታስረክበኝ ወይም ግምቱ 26,000 ብር እንዲከፈለኝ ሲሉ አፈፃፀም መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካችም በሰጡት መልስ በ1996 ዓ/ም ባልና ሚስት መሆናችን የማይካድ እውነት ነው፡፡ ትዳር ሲፈርስ ለኔ የተሰጠኝ የያዝኩት እንጂ የተጠሪ አይደለም፡፡ ያልተወሰነበት የሚፈፅምበት ነገር የለም፡፡ በእጄ የሌለውን ነገር ለመፈፀም አልገደድም፡፡ ጋብቻ ከፈረሰ የሰራሁት በስሜ ካርታ አውጥቼ የሚሰራበት ነው በማለት መልሳቸውን አቅርበዋል፡፡


የስር ፍርድ ቤትም የግራቀኙን ማስረጃ በመመዘን በውላቸው መሰረት መፈፀም አለበት በማለት የዘይት መጨመቂያና የወፍጮ ቤት የነበረ ወደ እንጨት መሰንጠቂያ የተቀየረው ወደ ተጠሪ ስም እንዲዛወር እና ሽጉጥ እንዲያስረክቡ ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡

 

በዚሁ ትእዛዝ ላይ ከአሁኑ አመልካች ይግባኝ የቀረበለት የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በሽጉጥ የተሰጠው ትእዛዝ በማሻሻል በሌሎቹ ንብረቶች ላይ የስር ፍርድ ቤት በማፅናት ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡ በመቀጠል ለኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቅሬታ በአመልካች በመቅረቡ የግራ ቀኙ ክርክር ከሰማ በኃላ የዘይት መጭመቂያ በተመለከተ የተሰጠው ትእዛዝ በማፅናት፤ ወፍጮ ቤት የነበረው ወደ እንጨት መሰንጠቂያ ቤቱ የተጠሪ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ እንጨት ድርጅት ሲቀየር ማሽኖቹና መሳሪያዎቹ የተገዙት እንደ ባልና ሚስት በአንድ ቤት  በሚኖርበት ጊዜ ስለሆነ ማሽኖቹና ዕቃዎቹ በባለሙያ ተገምቶ ግምቱ ወይም በጨረታ በመሸጥ እኩል እንዲካፈሉ በማለት በመሻሻል ውሳኔ ሰጥተዋል፡፡ የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የተፈፀመ መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የለበትም ሲል አቤቱታው ሳይቀበለው በትእዛዝ ዘግቶታል፡፡

 

የሰበር አቤቱታ የቀረበውም የስር ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ የሰጡት ዳኝነት መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበት ስለሆነ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡ አቤቱታው  በሰበር ችሎት እንዲታይ የተያዘው ጭብጥ የእንጨት ድርጅት የተቋቋመው ወፍጮ ቤት የነበረው በ1996ዓ/ም በስምምነት ከተካፈሉ በኃላ እንደገና እንደባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ መሆኑ ባልተካደበት በተደረገው የንብረት ከፍፍል ስምምነት መሰረት ቤቱ የተጠሪ ነው ተብሏል በሚል መነሻ አመልካች በአፈፃፀም መዝገብ ላይ ለተጠሪ እንድትለቅ የተሰጠው ትእዛዝ ህጋዊ የክርክር አካሄድና አመራርን የተከተለ መሆን አለመሆኑን ለመመርመር ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮ ለሰበር ችሎቱ ሊታይ የሚገባ ነው ተብሎ በመታዘዙ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡ አመልካችም የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ እንደተገለፀው ሲሆን በዚህ መሰረትም በጭብጥነት በተያዘው ነጥብ ከግራ ቀኝ ወገኖች ክርክር፤ አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና ከሕጉ ጋር አገናዝበን መርምረናል፡፡ ጉዳዩ የአፈፃፀም ከስ ስለሆነ በዋናው ጉዳይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረት እንዲፈፀም መደረግ አለበት፡፡ በግራ ቀኙ የተማመኑበት ጉዳይ በመሐከላቸው የነበረው ጋብቻ በፍቺ ሲፈርስ የንብረት ክፍፍል በስምምነት በማድረግ በፍርድ ቤት ተቀባይነት አግኝቶ የፀደቀ ነው፡፡ ከፍቺ በኃላም እንደባልና ሚስት አብረው እየኖሩ እንደነበር በስር ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት ፍሬ ነገር ነው፡፡ በ2005ዓ/ም የአሁኑ ተጠሪ የፍቺ ክስ ለፍርድ ቤት አቅርበው ነገር ግን ጋብቻ የለም ግንኙታቸው


እንደ ባልና ሚስት አብረው እንደሚኖሩ ሰዎች የሚባል ነው፡፡ በዚህ ጊዜ አብረው ያፈሩት ንብረት የጋራ እንዲሆንና በ1996 ዓ/ም የተደረገው ክፍፍል የተጠበቀ መሆኑን ውሳኔ ተሰጥተዋል፡፡

 

ውሳኔው ይህ ከሆነ አፈፃፀሙን የዘይት መጭመቂያና የወፍጮ ቤት ለተጠሪ የደረሰው መሆኑን አመልካችም የራስዋ ድርሻ እንደያዘች ከስር መዝገብ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከፍቺ በኃላ አብረው መኖር ከጀመሩ ያፈሩት ንብረት መኖር አለመኖሩን ለማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ባለቸው የስር ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት ወፍጮ ቤት የነበረው ወደ የእንጨት ድርጅት ሲቀየር የተለያዩ ማሽኖችና ዕቃዎች አብረው ያፈሯቸው እንደሆነ ነው፡፡ በዚህ መሰረትም አብረው ያፈሩት ማሽኖችና እቃዎች እኩል አንዲካፈሉ፤ ቤቱ ደግሞ ለተጠሪ እንዲሆን በማለት የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስሕተት ያለበት ሆኖ አልተገኘም፡፡ በዚሁ መሰረትም የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የኦሮሚያ ጠ/ ፍ/ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ.181913 በቀን 12/10/2006 ዓ/ም የስር

 

ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በማሻሻል ሰጠው ውሳኔ እና የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ.185727 በቀን 22/11/2006ዓ/ም የሰጠው ትእዛዝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ.348/1/ መሰረት አጽንተናል፡፡

 

2. በዚህ ችሎት ተሰጥቶ የነበረው የእግድ ትእዛዝ ተነሰተዋል ለሚመለከተው አካል ይተላለፍ፡፡

 

3. በዚህ ችሎት ለተደረገው ወጭና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡ መዝገብ ተዘግተዋል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

መ/ይ