116977 law of person/ name/ change of name

አንድ ሰው በወላጅ አባቴ ስም መጠራቴ ቀርቶ በአሳዳጊዬ ስም እንድጠራ ብሎ የሚያቀርበው የዳኝነት ጥያቄ በሕጉ ስለስም ለውጥ የተጠቀሱትን ድንጋጌዎች የማያሟላ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ስለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁ.32(1)፣36(1)

 

የሰ/መ/ቁ 116977

 

የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ/ም

 

ዳኞች፡-  አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች ፡- ወ/ሪት ሃና ታምራት ጠበቃ አሰፋ ካሳ ቀረቡ ተጠሪ፡- የለም

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ አመልካች ያቀረቡትን አቤቱታ ጉዳዩ በመጀመሪያ ደረጃ የቀረበለት የአዲስ አበባ ከተማ የመ/ደ/ፍርድ ቤት ውድቅ በማድረጉና በየደረጃው ያሉ የከተማው አስተዳደር የበላይ ፍርድ ቤቶችም የመ/ደ/ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በማጽናታቸው ነው፡፡

 

አመልካች ሐምሌ 08 ቀን 2007 ዓ/ም ያቀረቡት አቤቱታ ፍሬ ቃሉ፡- ቀድም ሲል ጸሐይ ብርሃኔ እና ሀና ታምራት እየተባልኩ በሁለት ስም ስለምጠራ ጸሐይ ብርሃኔ መባሌ ቀርቶ ሃና ታምራት ብቻ እየተባልኩ እንድጠራ ውሳኔ ይሰጠኝ በማለት ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ሲሆን የስር ፍርድ ቤትም አመልካች የአቶ ታምራት አመዴ ልጅ ለመሆናቸው ከሚመለከተው ፍርድ ቤት የልጅነት ውሳኔ ይዘው ሲቀርቡ መዝገቡ ይቅረብ በማለት መዝገቡን የዘጋው ሲሆን በዚህ ትዕዛዝ አመልካች ይግባኛቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ የሰበር አቤቱታቸው ለከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡

 

የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ የአመልካቸ  የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ሁለት ስም የነበረኝ በመሆኑ የግል ስሜና የወላጅ አባቴ ስም ተቀይሮ በአንዱ የግል ስም እና በአሳዳጊዬ የቤተዘመድ ስም እንድጠራ ያቀረብኩት አቤቱታ ውድቅ መደረጉ ከሕግ ውጪ ነው የሚል ነው፡፡


የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን አመልካች በወላጅ አባቴ ስም እንዲጠራ ይወሰንልኝ ሲሉ ያቀረቡትን አቤቱታ የሥር ፍርድ ቤቶች ውድቅ ያደረጉት በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል፡፡

 

በመርህ ደረጃ አንድ ሰው የቤተዘመድ ስም( family name)፣አንድ ወይም ከዚያ በላይ የግል ስሞች( first names) እና የአባት ስም( patronymic ) እንደሚኖረው በፍ/ህ/ቁ/32(1) የተደነገገ ሲሆን ለልጁ የአባት ስም የሚሆነው ደግሞ የአባቱ የግል ስም እንደሆነ በቁጥር 36 ተመልክቷል፡፡

በመሰረቱ እያንዳንዱ ሰው አንድ የቤተዘመድ ስምና አንድ ወይም ብዙ የግል ስሞች እና የአባት ስም እንደሚኖረው፣እንዲሁም ለልጁ የአባት ስም የሚሆነው የአባቱ የግል ስም እንደሆነ በፍ.ሕ.ቁ.32(1) እና 36(1) ድንጋጌዎች ተመልክቶአል፡፡አንድ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች በአባቱ ብቻ ሳይሆን በአሳዳጊው ስም ጭምር ሊጠራ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ ሰው ተገቢ ሆኖ ባገኘው ጊዜ በአሳዳጊው ስም ጭምር መጠራቱ ቀሪ ሆኖ ከላይ በተጠቀሰው የፍትሐብሔር ሕጉ ድንጋጌ መሰረት በአባቱ ስም ብቻ እንዲጠራ የመወሰን መብት ያለው በመሆኑ ይህንኑ መብቱን በፍርድ ለማረጋገጥ የሚያቀርበው የዳኝነት ጥያቄ የክስ ምክንያት የለውም የሚባልበት ሕጋዊ ምክንያት አይኖርም፡፡ አመልካች ክሱን ያቀረቡት ከሚጠሩበት ሁለት የግልና የቤተዘመድ ስሞች መካከል ባንዱ እንዲጠሩ ሲጠሩበት ከነበረው የቤተዘበመድ ስሞች መካከል ደግሞ አሁን ለመጠራት የፈለጉት ወላጅ አባቴ በሚሉት ሰው ስም ሳይሆን የአሳዳጊያቸው ስም በመምረጥ መሆኑን ከዳኝነት ጥያቄአቸው ይዘት ለመንገዘብ ችለናል፡፡ ይሁን እንጂ አመልካች በአሳዳጊያቸው ስም እንዲጠሩ በፍርድ ቤት ዳኝነት የሚያገኙበት የሕግ መሰረት የለም፡፡ ከግል ሰሞቻቸው መካከል ደግሞ ሃና ተብዬ ልጠራ፣ ፀሐይ መባሌ ይቅርልኝ ብለው በአማራጭ የጠየቁት የሰበር የዳኝነት ጥያቄ የሌለ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ በመሆኑም አመልካች ወላጅ አባቴ ናቸው በማይሏቸው ሰው የቤተዘመድ ስም ልጠራ ይገባል በማለት ያቀረቡት ጥያቄ በሕጉ ስለስም ለውጥ ጥያቄ ማቅረብ ስለሚቻልባቸውና የዳኝነት አካሉም ለመቀበል መሟላት ከሚገባቸው ሕጋዊ መስፈርቶች ይዘትና ሕጋዊ ውጤት  ጋር አብሮ የማይሄድ በመሆኑ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችልበትን አግባብ አላገኘንም፡፡ በሰ/መ/ቁጥር 87420 የተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የቤተዘመድ ስሙ አሳዳጊ በሆኑ ሰው ሲጠሩ የነበሩት አመልካች በትክክለኛ ስጋ ወላጆቻቸው ስም ለመጠራት ባቀረቡት ጥያቄ የተሰጠ ሲሆን በሰ/መ/ቁጥር 95995 የቀረበው ጉዳይም አመልካች ክሱን ያቀረቡት በሚጠሩበት የአሳዳጊያቸው ስም የተሰጡ ሰነዶችን ወደሚጠሩበት አባታቸው ስም በሕግ አግባብ ለማስቀየር እና እነዚሁ ሰነዶች በሚሰጡት መብት ለመገልገል ጭምር ስለመሆኑ ታይቶ ዳኝነት የተሰጠበት በመሆኑ ከአሁኑ ጉዳይ  ጋር በመሰረታዊ  የፍሬ ነገርና የሕግ  ጥያቄዎች ጋር ተመሳሳይነተ    የሌለው


በመሆኑ ይህ ችሎት በእነዚህ መዛግብት የተሠጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(1) መሰረት ለዚህ ጉዳይ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚችልበት አግባብ የለም፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ አመልካች ያቀረቡት ክርክርና የሰበር አጣሪ ችሎት የያዘው ጭብጥ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ አልፈነዋል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

1. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመ/ደ/ፍርድ ቤት በመ/ቁ/ 117/08 በቀን 13/11/2007 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ፣ የከተማው ይግባኘ ሰሚ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/23938 በቀን 17/11/2007 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ  እና የከተማው አስተዳደር ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/24066 በቀን 6/12/2007 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት ጸንቷል፡፡

2. አመልካች ወላጅ አባታቸው ባልሁኑት አቶ ታምራት አመዴ ስም እንዲጠሩ የጠየቁት የዳኝነት ጥያቄ ስለልጅነታቸው ከሚመለከተው አካል ማስረጃ ሲያቀርቡ የሚታይ ነው ተብሎ ውድቅ በመደረጉ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል፡፡ መዝገቡን ዘግተን ወደ መዝገብ ቤት መልሰናል፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

ወ/ከ