103049 law of succession/ partition of estate/ valuation

የወራሾች ድርሻ በክፍያ ጊዜ ሊገመትበት ስለሚችልበት አግባብ የፍ/ብ/ህ/ቁ. 1083

የሰ/መ/ቁ. 103049

ቀን 28/01/2008 ዓ/ም

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

 

ብርሃኑ አመነው

 

. ተፈሪ ገብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

አመልካች፡- ወ/ሮ ሊዕማ ሓዲሽ ተጠሪ፡- አቶ አንዋር ሓዲሽ

መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳዩ የውርስ ንብረትን በተመለከተ የተሰጠን ውሳኔ አፈጻጸም የሚመለከት ነው፡፡ የአፈጻጸም ከሳሽ የተባሉት የአሁን አመልካች በአፈ/ ተከሳሽ የአሁን  ተጠሪ ላይ በወረዳው ፍ/ቤት ንብረቱን ለመከፋፈል የአፈጻጸም ክስ አቅርበዋል፡፡

 

ጉዳዩ የቀረበለት የመቐለ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት አስቀድሞ ሌላ የአፈጻጸም ክስ ተከፍቶ እንደነበር ፤ በቀደመው መዝገብ ንብረቱ በባለሙያ እንዲገመት ተደርጎ ብር 163,349.50 መገመቱን ፤ በዚህ ላይ ከግራ ቀኙ ወገኖች የቀረበ ተቃወሞ አለመኖሩን ፤ ነገር ግን ከወራሾች መካከል አካለ መጠን ያላደረሱ በመኖራቸው እድሜያቸው ደርሶ ቤቱን በጋራ ተስማምተን እንሽጠው መዝገቡ ተዘግቶ ይቆይ የሚል ሃሳብ በማቅረባቸው መዝገቡ ተዘግቶ እንደነበር ፤ ለአፈጻጸሙ ምክንያት የሆነው በፍ/መ/ቁ.03151 ታህሳስ 22/2005 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔ ለአፈ/ከሳሽዋ “በድርሻዋ ይሰጣት” የሚል በመሆኑና ከውሳኔው ውጭ ወደ ሽያጭ የሚኬድበት ህጋዊ አግባብ ባለመኖሩ እና ለአንድ ልጅ ሲባል በቤቱ የሚኖሩ አራት ልጆችን በማስወጣት ቤቱ ይሸጥ ማለት ፍትሃዊነት የለውም በማለት የባለሙያው ግምት ለአምስቱ ወራሾች ተካፍሎ የከሳሽ ድርሻ የሆነው ብር 32,669.09 እንዲከፈላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ይግባኙ የቀረበለት የከፍተኛ ፍ/ቤት የተሰጠው ትዕዛዝ ጉድለት የለበትም በማለት ይግባኙን ሰርዟል፡፡

 

አመልካች ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሲሆን ፍ/ቤቱ “አመልካች ያላቸውን ድርሻ በገበያ  ዋጋ  ሊያገኙ ይገባል ወይስ ባለሙያ በገመተው” በሚለው ነጥብ    ላይ


አከራክሮ በመጨረሻ ባሳለፈው ውሳኔ አመልካች ንብረቱ በሃራጀ ተሽጦ ወራሾች እንዲከፋፈሉ የሚያቀርቡትን ክርክር በተመለከተ እንዲፈጸም በቀረበው ውሳኔ አመልካች ድርሻቸውን እንዲያገኙ እንጅ ንብረቱ በሃረጅ እንዲሽጥ ስላልተወሰነ ተቀባይነት የለውም ፤ በሰበር ለማጣራት የተያዘውን ጭብጥ በተመለከተም ንብረቱ እንዲሸጥ እስካልታዘዘ ድረስ የገበያ ግምቱ ይህን ያህል ይሆናል ተብሎ መገመት የሚቻል ባለመሆኑ ባለሙያ ከገመተው ውጭ የገበያ ዋጋው የሚረጋገጥበት ዘዴ የለም በማለት የስር ፍ/ቤቶች ያሳለፉትን ትዕዛዝ አጽንቷል፡፡

 

የሰበር አቤቱታው ለዚህ ፍ/ቤት የቀረበ ይህን ውሳኔ በመቃወም ነው፡፡ አመልካች በውርስ የጋራ የሆነው ቤትና ቦታ በአይነት መካፈል እስካልተቻለ ድረስ በሓራጅ ተሽጦ እንጅ በመሃንዲስ መነሻ ግምት ብቻ ድርሻ ይሰጥሽ በሚል የተላለፈው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ እንዲታረም ጠይቀዋል፡፡

 

አቤቱታቸው ተመርምሮ በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠውን ውሳኔ በፍ/ብ/ህጉ የውርስ  ሃብት የመከፋፈለን አሰራር በተመለከተ ከተደነገገው አንጻር ለመመርመር ሲባል ተጠሪ መልስ እንዲሰጡበት ተደርጓል፡፡ በሰጡት መልስ የአሁን አመልካች ከስር ክሳቸው ጀምሮ ጥያቄያቸው የወላጆች ድርሻ ይሰጠኝ የሚል እንጅ ቤቱ በሃራጀ ተሽጦ ድርሻዬ ይሰጠኝ የሚል ክስ ስላልነበር ፍ/ቤቱ ይህን ታሳቢ በማድረግ ድርሻዋ እንዲሰጣት የወሰነ በመሆኑ ፤ ጉዳዩ በአፈጻጸም ደረጃ ከደረስ በኃላ በሃራጅ ተሽጦ ሊከፈለኝ ይገባል የሚሉት ክርክርም ከውሳኔው ውጭ የቀረበ በመሆኑና የህግ መሰረት ስለሌለው አቤቱታቸው ውድቅ ተደርጎ በቀረበው ግምት መሰረት ሊወስዱ ይገባል ብለዋል፡፡ አመልካቹም ክርክራቸውን በማጠናከር የመ/መልስ ሰጥተዋል፡፡

 

ከላይ ባጭሩ ለመግለጽ የሞከረነው የጉዳዩን አመጣጥ ሲሆን ፍርዱን ለማስፈጸም በተሰጠው ትዕዛዝ እና ውሳኔ የተፈጸመ የህግ ስህተት ቢኖር መርምረናል፡፡

 

ከላይ ለመግልጽ እንደተሞከረው አከራካሪው ጉዳይ የውርስ ንብረት ክፍፍልን የተመለከተ ቢሆንም የተመራው በፍርድ አፈጻጸም ስርዓት ነው፡፡ የፍርድ አፈጻጸም በፍርድ የተገኘ መብት ውጤት እንዲሰጥ እና በፍርድ ባለመብት የተባለው ወገን ፍርዱን እንዲያጣጥም የሚደረግብት ስርዓት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በፍርድ አስፈጻሚው ፍ/ቤት የሚፈጸመው እንደ ፍርዱ ነው፡፡ ነገር ግን ፍርድ አስፈጻሚው ፍ/ቤት በሚያስፈጽምበት ጊዜ ፍርዱ ውጤት እንዲያገኝ አመች የሚሆነውን በህጉ የተፈቀደ ስርዓት ሊከተል ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በአፈጻጸም ወቅት ከፍርዱ ውጭ እንዲየስፈጽም የሚደረግበት የህግ አግባብ የለም፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ አመልካቹ ከፍርዱ ውጭ እንዲፈጸም የሚያቀርቡት ክርክር ተቀባይነት የሌለው ቢሆንም የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ንብረቱ እንዲሸጥ እስካልታዘዘ ድረስ የገበያ ግምቱ


ይህን ያህል ይሆናል ተብሎ መገመት የሚቻልበት ሰርዓት የለም በመሆኑም ባለሙያ ለገመተው ዋጋ አመልካች የድርሻቸውን እንዲወስዱ የደረስበት መደምደሚያ በህጉ የተደነገገውን መሰረት ያደረገ ሆኖ አላገኘነውም፡፡

 

በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1083 በግልጽ እንደተደነገገው የወራሾች ድርሻ በክፍያ ጊዜ እንደሚገመት ፤ የንብረቱን ግምት የሚያደርጉት ራሳቸው ወራሾች መሆናቸው ፤ እንዲሁም ወራሾቹ በግምቱ የማይስማሙ ከሆነ ግምቱ እነሱ በመረጧቸው የሽምግልና ዳኞች ፣ በመምረጥ ባይሰማሙ ዳኞች በመረጧቸው የሽምግልና ዳኞች ግምቱ እንዲሚደረግ ተመልክቷል፡፡ አመልካች “የድርሻቸው እንዲሰጣቸው” የተላለፈው የስር ፍርድ በዚህ የህግ ስርዓት መሰረት መፈጸሙ ህጉን መሰረት ያደረገ ከመሆኑም በላይ ፍርዱ ውጤት እንዲያገኝ የሚያደርግ ነው፡፡

 

ስለሆነም ይህን የህግ ስርዓት መከተል ሲቻል ንብረቱን እንዲሸጥ እስካልታዘዘ ድረስ የገበያ ግምቱን ማወቅ አይቻልም ባለሙያ ከገመተው ውጭ ዋጋው የሚረጋገጥበት ዘዴ የለም ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ ህጉን መሰረት ያላደረገ እና ፍርዱ በህጉ  አግባብ  ውጤት እንዲያገኝ የሚያደርግ ባለመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ብለናል፡፡  ተከታዩም ተወስኗል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1ኛ. የመቐለ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት የዓደር ምድብ ችሎት በመ/ቁ.04388 ግንቦት 6/2006 ዓ/ም ያሳለፈው ትዕዛዝ ፤ የመቐለ ከተማ ማእከላይ (ከፍተኛ) ፍ/ቤት በመ/ቁ.15262 ግንቦት 18/2006 ዓ/ም የሰጠው ትዕዛዝ እንዲሁም የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ/ቁ. 66999 ሰኔ 20/2006 ዓ/ም ያሳለፈው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

 

2ኛ. የወረዳው ፍ/ቤት የአፈጻጸም መዝገቡን በማንቀሳቀስ ንብረቱን ራሳቸው ወራሾች እንዲገምቱ በማድረግ ፣ ወራሾቹ በግምቱ የማይስማሙ ከሆነ ግምቱ እነሱ በመረጧቸው የሽምግልና ዳኞች ፣ በመምረጥ ካልተስማሙ ፍ/ቤቱ በሚመረጣቸው የሽምግልና ዳኞች እንዲገመት በማድረግ ተገቢውን እንዲወሰን ብለናል፡፡

 

3ኛ. የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይተላላፍ፡፡

 

4ኛ. የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪ በየራሳቸው ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ.ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት