100931 law of person/ incapacity/ sale of immovable property

እብደቱ በግልጽ ያልታወቀ ሰው ወራሾች ወይም ባለገንዘቦች ይህ ሰው የፈጸመው ውል ጉድለት የሌለበት ፈቃድ አልሰጠበትምና ውሉ ሊፈርስ ይገባል ሲሉ እብደቱን ምክንያት በማድረግ የውሉን መፍረስ መጠየቅ የማይችሉ ስለመሆኑ፡- የማይንቀሳቅስ ንብረት ሽያጭ ውልን ዋጋ ተጎዳሁ በሚል ምክንያት ሊፈርስ የማይችል ስለመሆኑ፡- የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ ሕ/ቁ. 348፣347/1//2/፣349፣350፣341፣342 የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2887

 

የሰ/መ/ቁ. 100931 ታህሳስ 18 ቀን 2008ዓ.ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመስል እንደሻው አዳነ ቀንዓ ቂጣታ

አመልካች፡- አቶ ጥላሁን ዓለሙ ጠበቃ አቶ ተስፋሁን ጸጋዬ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ደረጀ ማሞ ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

1. ጉዳዩ የቀረበው አመልካች ወላጅ እናቴ ሟች ወ/ሮ ዘውዴ በየነ የአእምሮ በሽተኛ በነበሩበት ጊዜ የፈጸሙት የቤት ሽያጭ ውል ፈራሽ ይደረግልኝ በማለት ያቀረቡትን ጥያቄ የበታች ፍ/ቤቶች ውድቅ ያደረጉት በህግ አግባብ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ነው፡፡ በስር ፍ/ቤት አመልካች በከሳሽነት ቀርቦ ሟች እናቴ ወ/ሮ ዘውዴ በየነ በአእምሮ ህመም ምክንያት በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲታከሙ ቆይተው፣ ጤናማ አእምሮ ሙሉ ፈቃዳቸውን ለመስጠት በማይችሉበት ሁኔታ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 02 ቁጥሩ 1020 የሆነውንና በስማቸው ተመዝግቦ የሚገኘውን ቤት ሰኔ 18 ቀን 2001 ዓ.ም በብር 200,000 /ሁለት መቶ ሺ ብር/ ለተከሳሽ ሸጠውላቸዋል፡፡ ሟች እናቴ በአእምሮ ህመም ሲሰቃዩ ቆይተው ከዚህ ዓለም በ2003 ዓ.ም በሞት ተለይተዋል፡፡ ስለዚህ እናቴ የአእምሮ ህመምተኛ በሆኑበትና ፈቃዳቸውን ለመስጠት በማይችሉበት ሁኔታ በእርካሽ ዋጋ ቤታቸውን ለተከሳሽ (ተጠሪ) ለመሸጥ የተዋዋሉት ውል እንዲፈርስ ውሳኔ ይሰጥልኝ በማለት ክስ አቅርበዋል፡፡


2. ተጠሪ በስር ፍ/ቤት በተከሳሽነት ቀርቦ የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያና የመከላከያ መልስ አቅርቧል፡፡ ተከሳሽ የከሳሽ እናት የአእምሮ ህመም በግልጽ የታወቀ የአእምሮ ህመም አይደለም፡፡ ተከሳሽ ቤቱን ከከሳሽ እናት የገዛሁት እናቱ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ቀርበው ጤናማ አእምሮ እንዳላቸውና ቤታቸውን ለመሸጥ ፈቃደኛ መሆናቸው ተረጋግጦ ነው፡፡ የከሳሽ እናት የሽያጭ ውሉን ከተከሳሽ ጋር በተዋዋሉበት ጥር 18 ቀን 2001 ዓ.ም ድብርት ውስጥ አልነበሩም፡፡ ተከሳሽ ቤቱን የገዛሁበት ትክክለኛ ዋጋ   ብር

1,350,000 /አንድ ሚሊዮን ሶስት መቶ ሃምሳ ሺ ብር/ ሲሆን የከሳሽ እናት ይህንን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ተቀብለዋል፡፡ ተከሳሽ ቤቱን ከገዛሁ በኋላ ከፍተኛ ወጭ በማውጣት የተለያዩ የእድሳት ስራዎችን የሰራሁ በመሆኑ ውሉ ፈርሶ ተዋዋዮች ወደ ነበርንበት ለመመለስ የማይቻል በመሆኑ ውሉ የሚፈርስበት ምክንያት የለም የሚል መከራከሪያ አቅርቧል፡፡

3.  የስር ፍ/ቤት የከሳሽ /የአመልካች/ እናት ወ/ሮ ዘውዴ በየነ የቤት ሽያጭ ውል   ከተጠሪ

/ከተከሳሽ/ ጋር ሲዋዋሉ የታወቁ የአእምሮ ህመምተኛ ነበሩ? ወይስ አልነበሩም? የቤት ሽያጭ ውሉ ሊፈርስ ይገባል ወይስ አይገባም? ውሉ ሊፈርስ ይገባል ከተባለ ተዋዋዮች ወደነበሩበት መመለስ አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚሉትን ጭብጦች መስርቶ፣ የከሳሽ እናት በድብርት ምክንያት በአማኑኤል ሆስፒታል በየቀጠሮ እየተመላለሱ የህክምና አገልግሎት ሲያገኙ የነበሩ መሆናቸው የህክምና ማስረጃው ያሳያል፡፡ የከሳሽ እናት ተመላላሽ ታካሚ በመሆናቸው በግልጽ የታወቀ የአእምሮ ህመም የነበረባቸው ሴት ነበሩ ብሎ ለመደምደም በህጉ የተቀመጠውን መስፈርት አያሟሉም፤ ተከሳሽ የከሳሽ እናት የአእምሮ ህመም /ችግር/ ያለባቸው መሆኑን እያወቀ ውሉን የተዋዋለ ስለመሆኑ አልተረጋገጠም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የከሳሽ እናት በመጨረሻ ጊዜ  በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኝተው የሕክምና አገልግሎት ያገኙት ጥር 21 ቀን 2001 መሆኑን የቀረበው የሕክምና ማስረጃ ያሳያል፡፡ ይህም ውሉ በተደረገበት ሰኔ 18 ቀን 2001 ህክምናቸውን ጨርሰው በጤናማ የአእምሮ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተከሳሽ የከሳሽ እናት በጤናም አእምሮ የቤት ሽያጭ ውል የተዋዋሉ ስለመሆኑ የመከላከያ ማስረጃ በማቅረብ አስረድቷል፡፡ ስለዚህ የቤት ሽያጭ ውሉ የሚፈርስበት ህጋዊ ምክንያት የለም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

4. አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርቧል፡፡ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ተጠሪ መስቀለኛ ይግባኝ ማመልከቻ አቅርበዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የስር ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡  ተጠሪ የስር ፍ/ቤት ክሱ በይርጋ ይታገዳል፤ አመልካች የመክሰስ  መብት


የለውም   በማለት   ያቀረብኩትን    የመጀመሪያ   የክስ  መቃወሚያ   አላግባብ   ውድቅ አድርጎብኛል በማለት ያቀረበውን መስቀለኛ ይግባኝ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

5. አመልካች ግንቦት 12 ቀን 2008 ዓ.ም በተጻፈ ማመልከቻ፤ ሟች ወላጅ እናቴ 1996 የአእምሮ ህመም ምክንያት ወደ አማኑኤል ሆስፒታል በመሄድ ስትታከም የቆየች መሆኑንና ህመሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረ መሆኑ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 256 መሰረት ለማቅረብ ጠይቀው የነበረው ሆስፒታሉ ጥር 3 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው ማስረጃ ያሳያል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወላጅ እናቴን በሰኔ ወር 2001 ዓ.ም ከሌላ ገዥ ጋር አገናኝቷት የነበረ ደላላ እናቴ እራሷን መቆጣጠር የማትችል እንደነበረች መስክሯል፡፡ እናቴ ቤት ተዘግቶባት የምትኖር ነበረች፡፡ ቤቱንም የሸጠችው በእርካሽ ዋጋ ነው፡፡ እንደዚሁም ውሉ የሟች ጣት አሻራ የሌለው መሆኑ ዋናውን ቅጅ ለማረጋገጥ ፈልጎ ሊያገኘው እንዳልቻለ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ገልጾ እያለ፤ ውሉ የሚፈርስበት ምክንያት የለም ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል፡፡

6. ተጠሪ መስከረም 26 ቀን 2007 ዓ.ም በተጻፈ ማመልከቻ የአመልካች እናት እብደታቸው በግልጽ የተወቀ ወይም የተዘጋባቸው እብድ አልነበሩም፡፡ የአመልካች እናት እብደታቸው በግልጽ ያልታወቁ ናቸው፡፡ ይህ ከሆነ አመልካች ወላጅ እናቱ የተዋዋሉትን ውል ፈራሽ ይሁንልኝ በማለት ክስ ለማቅረብ የሚያስችለው መብት በህግ አልተሰጠውም፡፡ ተጠሪ ቤቱን የገዛሁት የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት በአዋጅ ቁ. 334/95 በተሰጠው ስልጣን መሰረት የሚያጣራቸውን ነገሮች አጣርቶና አረጋግጦ፤ የአመልካች እናትም ውል ለመዋዋል ችሎታ ያላቸው መሆኑንና በነጻ ፈቃዳቸው ውሉን የተፈራረሙ መሆኑ ተረጋግጦ ነው፡፡ አመልካች ውል መዋዋል አይችሉም ነበር በማለት አንድ ሃኪም የሰጠው ማስረጃ የግል አስተያየቱና ከሙያ ስነ ምግባሩ በወጣ ሁኔታ የተሰጠ ነው፡፡ በሆስፒታሉ ህክምና ቦርድ በኩል ተረጋግጦ የቀረበ ማስረጃ አይደለም፡፡ አመልካች እናታቸው የአእምሮ ህመምተኛ መሆናቸውን ካወቁ በህግ በተደነገገው  መሰረት እናታቸው ውል እንዳይዋዋሉ በፍርድ ማስከልከል ሲገባቸው ይህንን ሳያደርጉ ውሉ ይፍረስ በማለት ያቀረቡት ክርክር የህግ መሰረት የለውም፡፡ የአመልካች እናት፤ ሰኔ 18 ቀን 2001 ዓ.ም በተደረገው ውል ከተገለጸው በላይ የሆነ ገንዘብ ከተጠሪ መቀበላቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ቀርቧል፡፡ በአጠቃላይ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ውድቅ ተደርጎ እንዲሰናበት በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ አመልካች ጥቅምት 19 ቀን 2007ዓ.ም የተጻፈ የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡

7. ከስር የክርክሩ አመጣጥና በዚህ ሰበር ችሎት ግራ ቀኙ ያቀረቡት ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም የበታች ፍ/ቤቶች አመልካች ተጠሪ ከሟች ወ/ሮ ዘውዴ    በየነ


ጋር አድርጎት የነበረው የቤት ሽያጭ ውል ፈራሽ ይሁንልኝ በማለት ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ያደረጉት በህግ አግባብ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

8.  መዝገቡን እንደመረመርነው የአመልካች እናት ወ/ሮ ዘውዴ በየነ የፍተሐ ብሔር ህግ ቁ.

341 እና የፍተሐ ብሔር ህግ ቁ. 342 በሚደነግገው መሰረት የነበረባቸው የአአምሮ ጉድለት፤ በግልጽ የሚታወቅ የአእምሮ ጉድለት ስለመሆኑ አመልካች የማስረዳት ግዴታውን /Burdon or proof/ ያልተወጣ መሆኑን ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ባላቸው የበታች ፍ/ቤቶች ተረጋግጧል፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ አመልካች በወላጅ እናቱ ላይ ነበረ የሚለው የአእምሮ ጉድለት በፍተሐ ብሔር ህጉ በግልጽ ያልታወቀ የአእምሮ ጉድለት በሚል መንገድ የሚገልጸው የአእምሮ ጉድለት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

9. የእብደቱ ሁኔታ በግልጽ ያልታወቀ ሰው የፈጸማቸው የህግ  ስራዎች  በዚሁ ሰው የአእምሮ ጉድለት ምክንያት ሊሻሩ የማይችሉ ስለመሆኑ በመርህ ደረጃ የፍተሐ ብሔር ህግ ቁ. 347 ንዑስ አንቀጽ 1 ደንግጓል፡፡ ከዚህ ጠቅላላ መርህ በልዩ ሁኔታ የተፈቀደው በፍትሐብሔር ሕግ ቁ. 347 ንዑስ አንቀጽ 2 እብደቱ በግልጽ ያልታወቀ ሰው ውሉ እንዲፈርስለት የሚጠይቅበት ሁኔታና በፍተሐብሔር ህግ ቁ. 349 እና በፍተሐብሔር ህግ ቁ. 350 የተደነገጉት ልዩ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ ሟች ወ/ሮ ዘውዴ በየነ ቤታቸውን ለተጠሪ የሸጡት በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት በተደረገ ውል ሲሆን፤ አመልካች የሚከራከረው የቤቱ ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑ ሟች እናቴ የአእምሮ ህመም ምክንያት ንብረቱን በበቂ ዋጋ ያልሸጠች እና የአእምሮ ህመም ምክንያት ውል የተዋዋለች መሆኑን ያሳያል በማለት ነው፡፡

10. ተጠሪ አከራካሪውን ቤት በምን ያህል ገንዘብ ነው የገዛው የሚለው ነጥብ፤ በመጀመሪያ ሟች ወ/ሮ ዘውዴ በየነ ከተጠሪ ጋር በውሉና በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት ያደረጉት ውል ፈራሽ ሊሆን ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ጭብጥ ምላሽ ካገኘ በኋላ የሚታይ በመሆኑ አመልካችና ተጠሪ ስለቤቱ ዋጋ ያደረጉትን ክርክርና ክርክሩን ለማስረዳት ለበታች ፍ/ቤቶች ያቀረቧቸውን የተለያዩ ማስረጃዎች ይዘት መመልከቱ አስፈላጊ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በዚህ ደረጃ አመልካች የቤቱ ዋጋ ማነሱን  ለውል ማፍረሻነት ምክንያት አድርገው ያቀረቡት ክርክር የህግ ድጋፍ አለው ወይስ የለውም የሚለውን ነጥብ መመልከቱ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ይህ አመልካች ያነሳው መከራከሪያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል ለማፍረስ በቂ ምክንያትና  መከራከሪያ ሆኖ ሊቀርብ የማይችል መሆኑ በፍተሐብሔር ህግ ቁ. 2887 የተደነገገ በመሆኑ፤ አመልካች ቤቱ በዝቅተኛ ዋጋ የተሸጠ መሆኑ፤ ሻጭ የአእምሮ ጉድለት ያለባቸው


መሆኑን ስለሚያሳይ ውሉ ይፍረስልኝ በማለት ያቀረበው ክርክር የህግ መሰረት ያለው ባለመሆኑ አልተቀበልነውም፡፡

11. በአጠቃላይ ሲታይ የፍተሐ ብሔር ህጉ እብደቱ በግልጽ ያልተወቀ ሰው ወራሾች ወይም ባለገንዘቦች ይህ ሰው የፈጸመው ውል ጉድለት የሌለበት ፈቃድ አልሰጠበትምና ውሉ ሊፈርስ ይገባል ሲሉ እብደቱን ምክንያት በማድረግ የውሉን መፍረስ መጠየቅ እንደማይችሉ በፍተሐብሔር ህግ ቁ. 348 ተደንግጓል፡፡ ህጉ ይህንን የደነገገው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ባለቤቱ በግልጽ ያልታወቀ የአእምሮ ህመም ምክንያት የእለት በእለት እንቅስቃሴው በራሱ መብትና ጥቅም ላይ ጉዳት የሚያደርስ የህግ ተግባር ሊፈጽም የሚችል መሆኑን በቅርበት የሚያውቁት ይህ እብደቱ በግልጽ ያልታወቀው ሰው ወራሾች፣ ወይም አበዳሪዎች፣ እብደቱ በግልጽ ያልታወቀ ሰው /ሴት/ ህጋዊ ተግባራትን የመፈጸም ችሎታው በፍርድ ክልከላ እንዲደረግበት ስልጣን ላለው ፍ/ቤት በማመልከትና በፍርድ በማስከልከል መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚችሉበት እድል በትጋት በመጠቀም፣ እብደቱ በግልጽ ያልታወቀውን ሰው፣ የራሳቸው እና በሶስተኛ ወገኖች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሚከላከል ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡ አመልካች የሟች እናቱ የአእምሮ ህመም በስር ፍ/ቤትና ለዚህ ሰበር ችሎት ባቀረበው ደረጃ የሚያውቅበት ጊዜ፣ የእናቱ ችሎታ በፍርድ ክልከላ እንዲደረግበት መጠየቅና ማስወሰን ሲገባው ይህንን ግዴታውን በአግባቡ አልተወጣም፡፡

12. ተጠሪ ከወ/ሮ ዘውዴ በየነ ጋር ቤት ገዥ ውል ሲዋዋል፣ ወ/ሮ ዘውዴ በየነ የአእምሮ ህመም ያለባቸው መሆኑን የማያውቅና በቅን ልቦና የሽያጭ ውሉን የተዋዋለ መሆኑን የበታች ፍ/ቤት አረጋግጠዋል፡፡ ይህ ከሆነ አመልካች የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስለት ያቀረበው ጥያቄ ከላይ በዝርዝር የገለጽናቸውን የህግ ድንጋጌዎች መሰረት ያላደረገና የህግ ድጋፍ የሌለው በመሆኑ፣ የበታች ፍ/ቤቶች አመልካች ያቀረበውን የውል ይፍረስልኝ ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸው፣ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት፣ ወስነናል፡፡

 ው ሳ ኔ

1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 75175 ህዳር 2 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔና የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁ. 142657 ሚያዚያ 9 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ ፀንቷል፡፡

2. በዚህ ፍ/ቤት ነሐሴ 5 ቀን 2006ዓ.ም የተሰጠው የእግድ ትእዛዝ ተነስቷል፡፡ የእግድ ትእዛዙ የተነሳ መሆኑ ለሚመለከተው ክፍል ይጻፍ፡፡

3.  በዚህ ፍ/ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡ የማይበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡


 የ ል ዩነ ት ሐሳብ

 

ስሜ በተራ ቁ. ሶስት የተመዘገብኩት ዳኛ የስራ ባልደረቦቼ በአብላጫ ድምጽ በሰጡት ውሳኔ ላይ ባለመስማማት የልዩነት ሐሳቤ እንደሚከተለው አስፍሬለሁ፡፡

 

በዚህ መዝገብ አከራካሪው ጉዳይ የአመልካች አውራሽ ወ/ሮ ዘውዴ በየነ ከተጠሪ ጋር አደረጉት የተባለው የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ በሕግ ፊት የሚጸና መሆን ያለመሆን ነው፡፡ አመልካች ከስር ፍ/ቤት ጀምሮ አጥብቀው የሚከራከሩት ወላጅ እናታቸው በከፍተኛ የአእምሮ ህመም እየተሰቃዩ በነበሩበት ጊዜ ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤት በርካሽ ዋጋ ለተጠሪ መሸጣቸውን ነው፡፡ ተጠሪ በበኩላቸው ከአመልካች አውራሽ ጋር ያደረጉት የቤት ሽያጭ  ውል በውልና ማስረጃ የተደረገ መሆኑን በመጥቀስ ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩን የመረመረው የስር ፍ/ቤትም የአመልካች አውራሽ በግልጽ ያልታወቀ የአእምሮ ጉድለት የነበራቸው ስለመሆኑ በመግለጽ የቤት ሽያጭ ውሉ ፈራሽ የሚሆንበት ምክንያት የለም በማለት የአመልካች ክስ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤትም ውሳኔውን አፅንቷል፡፡

 

በመሰረቱ አንድ ውል በተዋዋይ ወገኖች በሕጉ አግባብ ተደረገ የሚባለው በፍ/ሕ/ቁ. 1678 የተመለከቱት መሰረታዊ መስፈርቶች ሲሟሉ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ እንደመሰረታዊነት ከተመለከቱት ነጥቦች አንዱ ፈቃድ /consent/ የሚሰጥበት አግባብ ነው፡፡ አንድ ተዋዋይ ጉድለት የሌለበት ፈቃድ ሰጥቷል ለማለትም ያከናወነው ሕጋዊ ተግባር /juridical act/ በምክንያታዊ ሰው አእምሮ ተቀባይነት ያለው ድርጊት ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በተያዘው  ጉዳይ  አከራካሪ የሆነው መሰረታዊ ጭብጥ አመልካች አውራሽ በህመም ላይ እንደነበሩ ቤቱም የተሸጠው ከገበያ ዋጋ በታች ስለመሆኑ ክርክር መቅረቡን መዝገቡን ያሳያል፡፡ የአመልካች አውራሽ ሃኪም ቤት እየተመላለሱ የድብርት ህመም ህክምና እንደተደረገላቸው የተካደ ጉዳይ አይደለም፡፡ በስር ፍ/ቤት መዝገቡ እንደተገለጸው ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤት ለሌላ ሰው ለመሸጥ በተደረገ ጥረት የአእምሮ ችግር የነበራቸው በመሆኑ ቤቱ ሊሸጥ አለመቻሉን በአመልካች የቀረቡ ምስክር አስረድተዋል፡፡

 

የስር ፍርድ የአመልካች አውራሽ የሕመም ሁኔታ ያልታወቀ የአእምሮ ጉድለት ነው ለማለት እንደመነሻ የወሰደው ሆስፒታል ውስጥ አልጋ ይዘው እየታከሙ አለመሆኑን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በእርግጥ የታወቀ የአእምሮ ጉደለት ታማሚው የተዘጋበት መሆን እንደመነሻ የተወሰደ ስራ መሆኑ በፍ/ሕ/ቁ. 341 ተመልክቷል፡፡ ይሁንና ይህ ድንጋጌ መተርጎም ያለበት አገሪቷ አሁን ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ እና የሆስፒታሎች የማስተናገድ አቅም ተገናዝቦ ነው፡፡ የአእምሮ ህመም ያላቸው ታካሚዎች ለማስተናገድ የሚያስችል በቂ የጤና ተቋም  በሌለበት ሁኔታ ሆስፒታል ወይም ለዚህ ዓላማ በተዘጋጀው መኖሪያ ያልተዘጋበት ግለሰብ እንደ የታወቀ የአእምሮ


ጉድለት ያለበት ሰው አይወሰድም የሚለው ክርክር ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው፡፡ በአመልካች በኩል የቀረበ የሃኪም ማስረጃ ሟች እናታቸው በከፍተኛ የአእምሮ ሕመም ይሰቃዩ እንደነበር ከአማኑኤል ሆስፒታል የቀረበ ማስረጃ ስለመኖሩ በተጠሪ ሳይካድ ሙያዊ አስተያየቱ ዋጋ የሌለው ነው የሚል ክርክር አቅርበዋል፡፡ አመልካች ሌላ ያቀረቡት ክርክር ተደረገ የተባለው ውል የጣት አሻራ የለውም፤ ውሉ ከውልና ማስረጃ ቀርቦ ይጣራ በማለት ያቀረቡት ጥያቄ በተመለከተም ተጠሪ ውሉ በውልና ማስረጃ የተደረገ ነው ከማለት ውጭ በእርግጥም በስር ፍ/ቤት የቀረበው የተጨማሪ ማስረጃ ጥያቄ በሕጉ አግባብ ስለመስተናገዱ የቀረበ ክርክር የለም፡፡

 

የአመልካች አውራሽ ሽያጩ ሲፈጸሙ ሰኔ 18 ቀን 2001 ዓ.ም የአእምሮ ጤናቸው ምን  ደረጃ ላይ ነበር የሚለው ሳይንሳዊ በሆነ አግባብ ማጣራት የተደረገበት አይደለም፡፡ በአመልካች በኩል የቀረበው የሰውና የሰነድ ማስረጃ ሟች ወ/ሮ ዘውዴ በየነ የጤና ሁኔታቸው በጥሩ ሁኔታ እንዳልነበረ ለማጣራት መነሻ የሆነውን የፍሬ ነገር ክርክር አቅርበዋል፡፡ ከአማኑኤል ሆስፒታል የተገኘ ማስረጃ ይሁን በአመልካች የቀረበው የሰው ምስክር የሟች የጤና ሁኔታ ሕጋዊ ተግባር ለማከናወን በሚችሉበት ሁኔታ እንዳልነበሩ መነሻ ክርክር ከቀረበ ፍ/ቤቱ እውነት የማፈላለግ (truth finding) ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ግራቀኙ የሚያቀርቡት  ማስረጃ አግባብነትና ተቀባይነት በሕጉ አግባብ ተጣርቶ የሟች የጤና ሁኔታ ሳይንሳዊ በሆነ አግባብ በዚህ ጉዳይ ሙያ ያላቸው (expert opinion) ሳይከትሪስት ትንታኔ ሊሰጥበት ይገባ ነበር፡፡  የስር ፍ/ቤት የአመልካች አውራሽ የአእምሮ ሁኔታ በግልጽ ያልታወቀ እብደት ነው ከሚል ድምዳሜ ለመድረስ መሰረት ያደረገው አልተዘጋጀባቸውም በሚል ምክንያት እንጂ የአእምሮ ጉድለቱ ያልታወቀ እብደት ስለመሆኑ ሳይንሳዊ ትንታኔ የተሰጠበት ጉዳይ አይደለም፡፡ የህመሙ ደረጃ በግልጽ አልተለየም፡፡

 

በአመልካች አውራሽ እና የተጠሪ የተደረገው ሽያጭ ጉድለት የሌለበት ስለመሆኑ ለመለየት ግራቀኙ ያደረጉት የውል ማቅረብ (offer) እና መቀበል (acceptance)፤ እንዴት እንደተገናኙ፤ ቤቱ በምን ያህል ገንዘብ እንደተሸጠ፤ የሽያጭ ገንዘቡ የተከፈለበት አግባብ በዝርዝር መጣራት የነበረበት ጉዳይ ነው፡፡ የሽያጭ ውሉ በውልና ማስረጃ የተደረገ ነው ከተባለም የሟች ወ/ሮ ዘውዴ በየነ የጤና ሁኔታ አከራካሪ እስከሆነ ድረስ ሂደቱን ሊመረመር ይገባ ነበር፡፡ ሕጉ ጥበቃ የሚያደርገው የቅን ልቦና ገዥ ነኝ ለሚል ሰው ብቻ ሳይሆን የአእምሮ ጉድለት ያለባቸው ግለሰቦችም ሕጋዊ መብታቸው እንዳይጣስ የወራሾችም መብትና ጥቅም ጭምር ለማስከበር በፍ/ሕ/ቁ. 339 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ተመልክቷል፡፡

 

በመሆኑም የአመልካች አውራሽ የሽያጭ ውል አደረጉ በተባሉበት ጊዜ የነበራቸው የአእምሮ ሁኔታ እብደቱ በግልጽ የሚታወቅ ነው ወይስ የማይታወቅ ? የሚለው መሰረታዊ ጭብት


በባለሙያ በተደገፈ ሳይንሳዊ ትንታኔ ተደርጎበት በአግባቡ አለመጣራቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት ሊሆን ይገባው ነበር፡፡ የአመልካች አውራሽ እና ተጠሪ የቤት ሽያጭ ግንኙነት እንዴት እንደተመሰረተ? ተከፈለ የተባለው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ እና ገንዘቡ ማን እንደተቀበለው? በመንደር ውል የተጻፈው የገንዘብ መጠን እና በውልና ማስረጃ ተከፈለ የተባለው ገንዘብ ልዩነት ካለው ለምን ሊሆን እንደቻለ በዝርዝር ቢጣራ በእርግጥም የአመልካች አውራሽ የጤንነት ሁኔታ የሚጠቁም እውነት ላይ ለመድረስ የሚያችል ነገር ይገኝ ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡

 

በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የስር ፍ/ቤቶች የአመልካች አውራሽ እና ተጠሪ አደረጉት የተባለው የቤት ሽያጭ ውል ከጉድለት የጸዳ ስለመሆኑ ከላይ በተገለጹ ዝርዝር ምክንያቶች  ሳይጣሩ የሽያጭ ውሉ በሕግ ፊት የጸና ነው በማለት የአመልካች አቤቱታ ውድቅ ማድረጋቸው በአግባቡ አይደለም፡፡ ጉዳዩ በሕጉ አግባብ ተመርምሮ በእርግጥም በሕግ ፊት የሚጸና የቤት ሽያጭ ውል ነበረ ወይስ አልነበረም? የሚለው አከራካሪ ነጥብ በስር ፍ/ቤት በድጋሚ ከተጣራ በኋላ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባ ነበር፡፡ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎትም በስር ፍ/ቤት የተፈጸሙ ግድፎቶች ሳይጣሩ ውሳኔውን ማጽናቱ ተገቢ አይደለም በማለት በሐሳብ ተለይቻሎህ፡፡

 

 

 

የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 

መ/ይ