110040 law of succession/ representation

ተተኪ ወራሽ ለመሆን ሊሟሉ ስለሚገባቸው ሁኔታዎች የፍ/ሕ/ቁ. 842(3)

የሰ/መ/ቁ/ 110040

 

የካቲት 3 ቀን 2008 ዓ/ም

 

 

 

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

አመልካች፡- 1. ወ/ሮ እሴተማርያም አክሎግ

 

2. ወ/ሪት ወይንሸት አክሎግ         የቀረበ የለም

 

3. አቶ መክብብ አክሎግ ተጠሪ፡- የለም

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ይህ ጉዳይ ውርስ ጥያቄ የመመልከት ነው፡፡ አመልካቾች ለአ.አ.ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ባቀረቡት የአያታቸው ወ/ሮ ደብረወርቅ ሀ/ሚካኤል ወራሽነት ይረጋገጥልን  በማለት አቅርበዋ፡፡ የአባታቸው ሻለቃ አክሎግ አድማሱ ወራሽነት ያረጋገጡ ሲሆን የወላጅ አባታቸው እናት ወራሽነት ለማረጋጥ የቀረበ አቤቱታ ነው፡፡ወላጅ አባታቸው በ1981 ዓ/ም ከዚህ አለም በሞት የተለዩ ሲሆን አያታቸው ወ/ሮ ደብረወርቅ ሀብተ ሚካኤል የሞቱት ደግሞ በ1978 ዓ/ም ነው፡፡ በመጀመሪያ የተመለከተው ፍርድ ቤቱም አያታቹህ ከአባታቹሁ ቀድመው የሞቱ ስለሆነ ተተኪ ወራሽ ልትሆኑ አትችልም በማለት ብይን ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ብይን ባለመስማማት አቤቱታቸውን ለአ.አ.ከተማ ይግባኝ ሰሚና ለሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርብም ተቀባይነት ሳያገኝ በትእዛዝ ሰርዞውታል፡፡ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ የበታች ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካቾች ተወካይ የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ/ም በፃፉት  የሰበር


አቤቱታ በበታች ፍ/ቤቶች ብይን ተእዛዝ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶችን ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ ወላጅ አባታችን እናቱ ከሞቱ ጀምሮ እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ በህመም ላይ እንደነበረ ለስር ፍርድ ቤቶች አስረድተን እያለን የአያታችን ወራሽነት አታረጋግጡም መባሉ ከፍተኛ የህግ ስህተት ያለበት ነው፡፡ ወላጅ አባታችን ለ3 አመት የአልጋ ቁራኛ ሆኖ የእናቱ ወራሽነት ሳያረጋግጥ ቢቀርም አመልካቾች ተተኪ ወራሾች የአያታችን ወራሽነት የሚከለክለን አንዳችም ህግ የሌለ በመሆኑ የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ብይንና ትእዛዝ በመሻር የአያታችን ወራሽነት እንዲረጋገጥላቸው አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡

 

የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ ተተኪ ወራሾች ሊሆኑ አይችሉም በማለት የተሰጠ ብይን ከፍ/ብ/ህ/ቁ/ 830፣831/3/844 እና 839 አንፃር ለመመርመር በሰበር ችሎቱ ሊታይ ይገባዋል በመባሉ ሊቀርብ የቻለው፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ እንደተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የሰበር አቤቱታ ካቀረበበት ብይን እና አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

 

የአመልካቾ ጥያቄ ወላጅ አባታቸው ተከተው የአያታቸው ወራሽነት እንዲረጋጥላቸው ነው፡፡ የስር ፍርድ ቤቶች ደግሞ ተተኪ ወራሾች ልትሆኑ አትችሉም በማለት ብይን ተሰጥተዋል፡፡ የፍ/ብ/ህ/ቁ/ 842/3/ ስር እንደተመለከተው የሟች የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾች ሲሆኑ ልጆች ቀድመው ከሞቱና ወደታች የሚቆጠር ተወላጅ ትተው ከሆነ ተወላጆቹ ወላጃቻውን ተተክተው ሟችን እንደሚወርሱ ያመላክታል፡፡ የተተኪ ወራሽነት የተፈፃሚነት ወሰን ወደ ታች የሚቆጥሩ ተወላጆች እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ወላጅ አባታቸው የእናታቸው የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ ናቸው፡፡ አመልካቾችም የወላጅ አባታቸው የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾች እንደሆኑ ህጉ ከመገንዘብ ይቻላል፡፡ ተተኪ ወራሽ ለመሆን ከፍ/ብ/ህ/ቁ/ 842/3/ አንፃር ሲታይ የአመልካቾ ጥያቄ የሚያሟላ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ወላጅ አባታቸው የእናታቸው የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ በመሆን የወረሱ ስለሆነ የምትክ ጉዳይ ሊነሳ አይችልም፡፡ በሌላ አነጋገር አመልካቾች አባታቸው ተክተው አያታቸውን መውረስ የሚችሉት አባታቸው ከአያታቸው በፊት የሞቱ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ስሆነም የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ብይንና ትእዛዝ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አልተገኘም፡፡ በሌላ በኩል አመልካቾች የሟች አባታቸውን ወራሽነት ስለማረጋገጣቸው ከክርክሩ ስለተረዳን አባታቸው የወረሱትን ንብረት ለመጠየቅ ይህ ውሳኔ አያግዳቸውም ብለናል፡፡ በዚሁ መሰረትም የሚከተለው ውሳኔ ሰጥተናል፡፡


 ው ሳ ኔ

 

1. የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪየ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ/ 1118/07 ጥር 6 ቀን 2007 ዓ/ም የሰጠው ብይን፤ የአ/አ፤ የአ/አ ከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት  በመ/ቁ/23073 ጥር 21 ቀን 2007 ዓ/ም እና የአ/አ ከተማ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/ 23140 የካቲት 2 ቀን 2007 ዓ/ም የሰጡት ትእዛዝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ/ 348/1/መሰረት በአብላጫ ድምጽ ጸንቷል፡፡

2. በዚህ ፍ/ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡ መዝገብ ተዘግተዋል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት

 

 

 የል ዩ ነት ሀ ሳብ

 

የአመልካቾቹ መሰረታዊ የአቤቱታ ነጥብ ወላጅ አባታችን ሻለቃ አክሎግ አድማሱ ከወላጅ እናታቸው ከወ/ሮ ደብረወርቅ ሀብተ ሚካኤል በኃላ የሞቱ በመሆኑ አባታችን የነበራቸው እናታቸውን የመውረስ መብት ለእኛ ለሻለቃ አክሎግ አድማሱ ልጆች እና ወራሾች የሚተላለፍ መሆኑ ተረጋግጦ ማስረጃ ይሰጠን የሚል መሆኑን ከስር ጀምሮ ከሚያቀርቡት ክርክር መገንዘብ ይቻላል፡፡ በመሰረቱ ለአንድ ውርስ ወራሽ የሆነ አንድ ሰው ውርሱ ከተከፈተ በኃላ የሞተ እንደሆነ የወራሽነቱ መብቶች ለርሱ ወራሾች የሚተላለፉ ስለመሆኑ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 833 ተመልክቶአል፡፡ ከአውራሹ አስቀድሞ የሞተን ወራሽ ተክቶ መውረስ (ቁጥር 844 (2) እና ከአውራሹ በኃላ የሞተን ወራሽ ተክቶ መውረስ (ቁጥር 833) የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በመሆም ለአቤቱታው አግባብነት ያለው የፍትሐብሔር ሕጉ ድንጋጌ ቁጥር 844 (2) ሳይሆን 833 ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ በቁጥር 833 ድንጋጌ መሰረት ከአውራሹ በኃላ የሞተ ወራሽ ተተኪ ወራሾች መሆናቸው ተረጋግጦ ማስረጃ እንዲሰጣቸው አመልካቾቹ ያቀረቡት የዳኝነት ጥያቄ ተቀባይነት የሚያጣበት ሕጋዊ ምክንያት አይኖርም፡፡በመሆኑም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ  ተሽሮ በአመልካቾቹ አቤቱታ መሰረት ሊወሰን ይገባው ነበር በማለት ስሜ በተራ ቁጥር ሁለት የተመለከተው ዳኛ የልዩነት ሀሳቤን አስፍሬአለሁ፡፡

 

 

መ/ተ                                የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ አለበት