ተወካይ የውክልና ስልጣኑን መሠረት በማድረግ ከሶስተኛ ወገን ጋር የሚያደርገው ውል ከወካይ ጋር የጥቅም ግጭት ተፈጠሯል ብሎ ወካይ ካወቀ ይህንን ለመቃወም /ለመስፈረስ/የሚችለው ወካይ ይህንን ሁኔታ መፈጠሩን ካወቀበት እስከ ሁለት ዓመት ጊዜ ድረስ ስለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁ. 2187(1)(2
የሰ/መ/ቁ.98961
መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም
ዳኞች፡- አልማው ወሌ
ረታ ቶሎሣ ሙስጠፋ አህመድ ቀነዓ ቂጣታ
ሌሊሴ ደሣለኝ አመልካቾች፡- 1. አቶ ኡመር መሐመድ ከጠበቃ ገናነው ተሾመ
2. ወ/ሮ ነፍሳ ሲራጅ ጋር ቀረቡ ተጠሪ፡- ሻ/ባሻ ከድር ቬህ አብዱላሂ - አልቀረበም፡፡
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
ይህ ጉዳይ ከውክልና /እንደራሴነት/ ህግ አፈፃፀም ጋር ተያይዞ የቀረበን ክርክር የሚመከለት ሆኖ ክርክሩም የጀመረው የአሁኑ ተጠሪ በባሌ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በአመልካቾች ላይ በመሰረተው ክስ መነሻነት ነው፡፡ ተጠሪ ግንቦት 10 ቀን 2003 ዓ.ም በተጻፈ ለስር ፍ/ቤት ያቀረበው የክሱ ይዘት ባጭሩ፡- ተጠሪ በጊኒር ከተማ 02 ቀበሌ ውስጥ በስማቸው የተመዘገበ ቤት ያላቸው መሆኑን፣ ይህንኑ ቤትና ቦታ 1ኛ አመልካች በአደራ እንዲጠብቁና እንዲያስተዳድሩ የሚል በ4/9/1985 ዓ.ም በውልና ማስረጃ ጽ/ቤት የተመዘገበ የውክልና ስልጣን ተሰጥቷቸው የነበረ መሆኑን፣ ሆኖም ግን አንደኛ አመልካች ከተሰጠው ውክልና ስልጣን ውጭ በመውጣት ባለቤታቸው ለሆኑት ለሁለተኛ አመልካች በዝቅተኛ ዋጋ በብር 2500 የሸጡ መሆኑን፣ በዚሁ መነሻነት ለ1ኛ አመልካች ተሰጥቶ የነበረው የውክልና ስልጣን በተጠሪ መሻሩን፣ ይህንኑን ተከትሎም አንደኛ አመልካች ቤቱን ለማስረከብ ፍላጎት ስላልነበረው በዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ-05861 በሆነው ላይ ክስ ቀርቦ እንደነበረና ፍ/ቤቱም በበኩሉ አንደኛ አመልካች በቤቱ ላይ የፈፀመው የሽያጭ ውል የተጠሪን መብት የሚጋፋ ከሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁ-2187 መሠረት ውሉ እንዲፈርስ የመጠየቅ መብቱን ጠብቆ ወስኖ የነበረ መሆኑን ጠቅሰው ይህ በአመልካቾች መካከል የተፈፀመው የሽያጭ ውል አንደኛ
አመልካች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከራሱ ጋር እንደፈፀመ የሚቆጠር በመሆኑና ይህም በፍ/ብ/ሕ/ቁ-2187 መሠረት የጥቅም ግጭት መፈጠሩን የሚያሳይ ስለሆነ በዚሁ የህግ ድንጋጌ መሠረት ውሉ ፈርሶ አመልካቾች ቤቱን እንዲያስረክቡና እንዲሁም ከ5/3/1998 ዓ.ም ጀምሮ ቤቱን ያለአግባብ ለተጠቀሙበት የቤቱ ኪራይ ገቢ በወር ብር 500 ታስቦ በድምሩ ብር 33,000 አመልካቾች በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍሉ ጭምር ይወሰንባቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ሲሆን አንደኛ አመልካችም በበኩሉ ቀርቦ ለክሱ በሰጠው የመከላከያ መልስ፡- ይህንኑ ቤት በተመለከተ ከዚህ በፊት ክስ ቀርቦ ውድቀ የተደረገ ስለሆነ ክሱ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ-5 መሠረት በድጋሚ ሊቀርብ የማይገባ መሆኑንና ክሱም በ2 ዓመት ይርጋ የሚታገድ መሆኑን በመቃወም የተከራከረ ሲሆን በፍሬ ነገር ረገድም የውክልና ስልጣኑ ቤቱን እንዲያስተዳድር ብቻ የሚል ሳይሆን ቤቱን የመሸጥና የመለወጥ ስልጣን ጭምር ያካተተ ስለሆነ ይህንኑ መሠረት በማድረግ በ19/5/1986 ዓ.ም የተደረገው የአነድ ክፍል አሮጌ ቤት ሽያጭ ውል ከወቅቱ የቤቱ ዋጋ ጋርም ተገናዝቦ ሲታይ ህጋዊና የተጠሪን መብት የነካ ባለመሆኑ ክሱ ውድቅ ይደረግልኝ በማለት ተከራክሯል፡፡ 2ኛ አመልካችም በበኩሏ ከ1ኛ አመልካች ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው መቃወሚያ አቅርበው የተከራከሩ መሆኑን ከስር ፍ/ቤቱ ውሳኔ ግልባጭ መገንዘብ የሚቻል ሲሆን ፍሬ ጉዳዩን በተመለከተም የቤቱ ሽያጭ ውል ህጋዊ በመሆኑ ሊሰረዝ የማይገባ መሆኑንና እንዲሁም ሽያጭ ውሉን ተከትሎ የቤቱ ስመ ሀብት ወደ ስማቸው እንዲዞር ከተደረገ በኋላ በ1987 ዓ.ም ቤቱን አፍርሰው በአዲስ መልክ ትልቅ ቤት ገንብተው እየተገለገሉበት ያለ የግል ንብረታቸው መሆኑን ጠቅሰው ክሱ ተቀባይነት የለውም ተብሎ ይወሰንላቸው ዘንድ ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የዞኑ ከ/ፍ/ቤት በበኩሉ የግራ ቀኙን የቃል ክርክር ሰምቶ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ፡- 1. ጉዳዩ ከዚህ በፊት በፍ/ቤቱ መ.ቁ 05861 ውሳኔ አግኝቷል? ወይስ አላገኘም? 2. አመልካችስ ቤቱን ለመሸጥና ለመለወጥ የሚያስችለው የውክልና ስልጣን ነበረው? ወይስ አልነበረውም? 3. ነበረው ከተባለስ ተጠሪ ሽያጭ ውሉን መቃወም ይችላል? ወይስ አይችልም? 4. ይችላል ከተባለስ ይሄንን ጥያቄ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ማቅረብ አለበት? የሚሉትን ነጥቦች በጭብጥነት ይዞ 1ኛ አመልካች ከተጠሪ በተሰጠው የውክልና ስልጣን መሰረት ቤቱን ስለመሸጡና የውክልና ሰነዱም ይሄንን ለማድረግ ለ1ኛ አመልካች ስልጣን የሚሰጠው ስለመሆኑ በመ.ቁ.05861 ውሳኔ ያረፈበት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሶ በዚህ ነጥብ ላይ በድጋሚ ውሳኔ መስጠቱ አላስፈላጊ ነው በማለት አልፏል፡፡ በሌላ በኩል ተጠሪ በክሱ እንደገለፀው 1ኛ አመልካች በእንደራሴነት ስልጣኑ ቤቱን ባለቤታቸው ለሆኑት ሁለተኛ አመልካች መሸጡን የውክልና ስልጣኑን በ1/3/1998 ዓ.ም በሚያነሳበት ጊዜ ያውቅ የነበረ መሆኑን ስለገለፀና ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ክሱ እስከቀረበበት ጊዜ ያለው ጊዜ ደግሞ ሲቆጠር 5 ዓመት ከ6 ወር በላይ መሆኑን በማስፈር ክሱ በፍ/ብ/ሕ/ቁ-2187/2/ መሠረት በ2 ዓመት ይርጋ ይታገዳል ሲል ወስኗል፡፡ ተጠሪም በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት የይግባኝ ቅሬታውን ለክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቢቀርቡም
ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ሆኖም ግን በተጠሪ አመልካችነት ጉዳዩን የተመለከተው የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ግራ ቀኙን አስቀርቦ ካከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪና አንደኛ አመልካች በዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ-05861 ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ክርክር ላይ የቆዩ መሆናቸውን ጠቅሶ እና ይህም በፍ/ብ/ሕ/ቁ-1851 መሠረት የይርጋውን ጊዜ አቆጣጠር የሚያቋርጥ ሆኖ ሳለ የበታች ፍ/ቤቶች ክሱ በ2 ዓመት ይርጋ ይታገዳል ሲሉ መወሰናቸው ህጋዊ አይደለም በማለት ሽሮ የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በፍሬ ነገሩ ላይ ግራ ቀኙን አከራክሮ ተገቢውን ይወሰን ዘንድ ክርክሩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁ-341/1/ መሠረት መልሶ ልኮለታል፡፡ አመልካቾችም ይህንኑ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም የሰበር አቤቱታቸውን ያቀረቡ ሲሆን አቤቱታውም ተመርምሮ በሰበር ሰሚ ችሎቱ እንዲታይ በመታዘዙ ተጠሪም ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡
የጉዳዩ ይዘት ከላይ የተመለከተውን የሚመስል ሲሆን እኛም በበኩላችን የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ክሱ በይርጋ አይታገድም ሲል የሰጠው ውሳኔ ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ነጥብ በጭብጥነት ይዘን ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል፡፡
መዝገቡን እንደመረመርነውም ተጠሪ ክሱን በስር ፍ/ቤት ሲያቀርብ አንደኛ አመልካች ቤቱን ለማስተዳደር እንጅ ለመሸጥና ለመለወጥ የውክልና ስልጣን አልተሰጠውም በማለት ቢከራከሩም ለአንደኛ አመልካች ተሰጥቶ የነበረው የውክልና ስልጣን ቤቱን ለመሸጥና ለመለወጥ የሚያስችላቸው ስልጣንም ጭምር የሚያካትት ስለመሆኑ ከዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔ ይዘት መገንዘብ ተችሏል፡፡ እንዲሁም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎትም ቢሆን የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በዚህ ረገድ የደረሰበትን መደምደሚያ ሃሳብ በውሳኔው ጠቅሶ አልለወጠውም፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ይህ ክርክር የቀረበበት የውክልና ስልጣን አድማሱ ቤቱንም የመሸጥና የመለወጥ ተግባርንም ያካትታል ተብሎ በስር ፍ/ቤቶች ድምዳሜ የተያዘበት ጉዳይ እኛም ልንቀበለው የሚገባው ነው፡፡
በሌላ በኩል የሰበር አመልካቾች ባልና ሚስት መሆናቸው አልተካደም፡፡ እንዲሁም 1ኛ አመልካችም የውክልና ስልጣኑን መሠረት በማድረግ ቤቱን በ19/5/1986 ዓ.ም በተደረገው ሸያጭ ውል ስምምነት መሠረት የሸጡት ሚስታቸው ለሆኑት ሁለተኛ አመልካች ስለመሆኑ አከራካሪ ጉዳይ ካለመሆኑም በላይ በማስረጃም የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ውክልና ስልጣኑን መሰረት ተደርጐ ከተፈጸመው ሽያጭ ውል ጋር በተያያዘ በፍ/ብ/ሕ/ቁ-2187/1/ ስር እንደተመለከተው የጥቅም ግጭት ስለመኖሩ የሚያከራክር ጉዳይ ባለመሆኑ ተጠሪ የሽያጭ ውሉን በዚሁ በተጠቃሹ ድንጋጌ መሠረት ለማስፈረስ ለመጠየቅ መብት አላቸው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ቤቱ ለ2ኛ አመልካች መሸጡን ተጠሪ የውክልና ስልጣኑን በሻሩበት ጊዜ
/በ1/3/1998 ዓ.ም/ ያውቅ የነበረ ስለመሆኑና ይህንኑም በክሱ አቤቱታ ጭምር እራሱ ገልጾ የነበረ
ስለመሆኑ የስር ፍ/ቤቱ ውሳኔ ግልባጭ ያስገነዝባል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሽያጭ ውሉ ይፍረስልኝ የሚለው ጥያቄ ደግሞ በፍ/ብ/ሕ/ቁ-2187/2/ መሠረት በ 2ዓመት ጊዜ ውስጥ ካልቀረበ ክሱ በይርጋ የሚታገድ መሆኑ ከተጠቀሰው የህጉ ድንጋጌ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ለዚህ ሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነው ክስ ቀርቶ ተጠሪ በቀድሞው የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት መ.ቁ-05861 በሆነው እራሱ ክሱን ያአቀረበው በ22/9/2000 ዓ.ም ስለመሆኑ ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለ ሲሆን ይህም ከ1/3/1998 ዓ.ም ጀምሮ ጊዜው ሲቆጠር ከ2 ዓመት በኋላ የቀረበ ሆኖ ሳለ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት መ.ቁ-05861 የቀረበው ጉዳይ ለክርክሩ አግባብነት ያለውንና በፍ/ብ/ህ/ቁ-2187/2/ ስር የተመለከተውን የ2 ዓመት የይርጋ ጊዜ ስለሚያቋርጥ ክሱ በይርጋ አይታገድም የሚል የመደምደሚያ ሀሳብ ላይ ደርሶ የሰጠው ውሳኔ የፍ/ብ/ሕ/ቁ-1851 እና 2187 ድንጋጌዎች ይዘት፣ መንፈስና ዓላማ ያገናዘበ ባለመሆኑ ውሳኔው የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ወስነናል፡፡
ው ሳ ኔ
1. የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.158348 በ21/4/2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ-348/1/ መሰረት ተሽሯል፡፡
2. የባሌ ዞን ከ/ፍ/ቤት በመ.ቁ-11926 በ19/11/2004 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በማጽናት የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ.ቁ-144852 በ9/4/05 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ-348/1/ መሰረት ጸንቷል፡፡
3. የተጠሪ ክስ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ-2187/2/ መሰረት በሁለት ዓመት ይርጋ ይታገዳል ብለናል፤ በዞኑ ከ/ፍ/ቤት መ.ቁ.05861 በተጠሪ ቀርቦ የነበረው ክስም ተጠሪ ሽያጭ ውሉ መደረጉን ካወቁበት ጊዜ አንስቶ ከ2 ዓመት ጊዜ በኋላ የቀረበ በመሆኑ የይርጋውን ጊዜ አቆጣጠር የሚያቋርጥ አይደለም ብለናል፡፡
4. ግራ ቀኙ የሰበር ወጪና ክሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡
ማ/አ