99667 contract/ part of contract

የተዋዋዮች የውል ግንኙነት መሰረት ያደረገው ፕርፎርማን ሳይሆን ፕሮፎርማን ተከትሎ በፅሑፍ የተደረገን ውል በሆነ ጊዜ በፕሮፎርማው ላይ ተጠቅሶ ነገር ግን ተዋዋዮቹ የውላቸው አካል አድርገው ያልተሰማሙበት ጉዳይ በፕሮፎርማ ላይ የተጠቀሰ በመሆኑ ብቻ እንደውሉ አካል ተቆጥሮ በተዋዋዮቹ (ከተዋዋዮቹ) በአንዱ ላይ አስገዳጅነት እንዳለው አድርጎ መውሰድ ተገቢ ስላለመሆኑ የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2287-2300 ተፈፃሚነት የሚኖራቸው በተሸጠው እቃ ላይ የተገኘው ጉድለት መኖሩ በገዥው የታወቀው ከርክክቡ በኋላ በሆነ ጊዜ ስለመሆኑ

የሰ/መ/ቁ. 99667

 

መስከረም 27 ቀን 2008 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡-አልማው ወሌ

 

ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ ቀነዓ ቂጣታ

ለሊሴ ደሳለኝ

 

አመልካች፡- ቻኩ ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር -- የቀረበ የለም

 

ተጠሪ፡- ናሽናል ሞተርስ ኮርፖሬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር  -ጠበቃ ነስቡ ሜኮ ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የሽያጭ ውል አፈጻጸምን የሚመለከት ክርክር ሲሆን የተጀመረውም ከሳሽ የነበረው የአሁኑ ተጠሪ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሽ በነበረው የአሁኑ አመልካች ላይ ባቀረበው ክስ ነው፡፡ ከሳሽ በ26/07/2004 ዓ.ም. አዘጋጅቶ ያቀረበው ክስ ይዘትም ባጭሩ፡- ከሳሽ እና ተከሳሽ በ06/04/1998 ዓ.ም. ባደረጉት የሽያጭ ውል ከሳሽ ብዛታቸው 13 የሆነ ሬኖ ክራክስ ተሽርካሪዎችን/ሻሲዎችን/ የተጨማሪ እሴት እና የስም ማዛወሪያ ወጪዎችን ጨምሮ እያንዳንዳቸውን በብር 1,051,346 በጠቅላላው ደግሞ በብር 13,667,498 ለመሸጥ በመስማማት ተሽከርካሪዎቹን ከ29/02/2000 ዓ.ም. በፊት ለተከሳሽ ያስረከበ መሆኑን፣ተከሳሽ ከሽያጩ ገንዘብ ውስጥ ብር 9,434,248.80 በባንክ በኩል የከፈለ መሆኑን፣ከቀሪው ብር 4,233,249.80 ውስጥ ከሳሽ ብር 2,183,125 በውሉ አንቀጽ 4.2 መሰረት መክፈል የነበረበት ተሽርካሪዎቹን ከመረከቡ በፊት ቢሆንም ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ብር 545,781.27 ያልከፈለ መሆኑን፣የመጨረሻውን ክፍያ ብር 2,050,124.70 በውሉ አንቀጽ 4.3 መሰረት ተከሳሽ ተሽርካሪዎቹን ከተረከበ የአንድ ወር የችሮታ ጊዜ ካለፈ በኃላ ባለው 12 ወር ጊዜ ውስጥ ከ9.5% ወለድ ጋር ከፍሎ ለማጠናቀቅ የተስማማ ቢሆንም ክፍያውን ያልፈጸመ መሆኑን፣የሚፈለግበትን ገንዘብ እንዲከፍል ከሳሽ በ23/07/2003 ዓ.ም. ለተከሳሽ ማስጠንቀቂያ የሰጠ ቢሆንም ለመክፈል ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን የሚገልጽ  ሆኖ  ተከሳሽ  የሚፈለግበትን  ገንዘብ  ብር  2,595,905.97  መክፈል    ከነበረበት


ከ20/05/2000 ዓ.ም. ጀምሮ ተከፍሎ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በውሉ አንቀጽ 5 መሰረት በዚሁ ገንዘብ ላይ ከሚታሰበው 9.5% ወለድ ጋር እንዲከፍል ከሳሽ በክሱ ምክንያት ያወጣውን ወጪ እንዲተካ ይወሰንለት ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው፡፡

 

ተከሳሽ በ18/10/2004 ዓ.ም. በፍሬ ጉዳዩ ረገድ በሰጠው መልስ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1803 መሰረት የገንዘብ ዕዳ ያለበት ሰው ወለድ ለመክፈል የሚገደደው ማስጠንቀቂያ ከተሰጠው ጊዜ ጀምሮ በመሆኑ ከሳሽ ማስጠንቀቂያ ከሰጠበት ከ10/08/2003 ዓ.ም. በፊት ወለዱ እንዲታሰብ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን፣ይህ የሚታለፍ ከሆነ ከሳሽ ተሽከርካሪዎቹን አስረክቤለሁ ካለበት ከ29/02/2000 ዓ.ም. ጀምሮ የአንድ ወር የችሮታ ጊዜውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ወለዱ መታሰብ መጀመር የሚገባው ተከሳሽ ገንዘቡን አልከፈለም ሊባል ከሚችልበት ከ29/03/2001 ዓ.ም. ጀምሮ በመሆኑ ከሳሽ ከዚህ ቀን በፊት ወለዱ መታሰብ እንዲጀምር ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን፣ከሳሽ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1757 ድንጋጌን እና በመዝገብ ቁጥር 38568 የተሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በሚቃረን ሁኔታ የበኩሉን ግዴታ ሳይወጣ ክስ ማቅረቡ ተገቢነት የሌለው መሆኑን በመግለጽ ተከሳሽ የመቻቻል ጥያቄ ያቀረበ በመሆኑ ገንዘቡን በማቻቻል ከሳሽ ተራፊውን ገንዘብ ለተከሳሽ እንዲከፍል እንዲወሰን በመጠየቅ ተከራክሮአል፡፡

 

ተከሳሽ በ18/10/2004 ዓ.ም. ባቀረበው የመቻቻል ጥያቄ ከሳሽ ለተከሳሽ በሰጠው ፕሮፎርማ ተሽከርካሪዎቹን ለማስረከብ የተስማማው በስምንት ወራት ውስጥ ሆኖ እያለ ያስረከበው ግን ለ15 ወራት አዘግይቶ በመሆኑ እና ለመኪናው የአካል ግንባታ የሚያስፈልገው ሶስት ወር ሲቀነስ ተከሳሽ በ12 ወራት ከተሽከርካሪዎቹ ስምሪት ማግኘት ይችል የነበረውን ገንዘብ ብር 6,240,000 ያጣ በመሆኑ ከዚሁ ገንዘብ እና በዚሁ ገንዘብ ከሚታሰበው ወለድ ላይ ከሳሽ የሚፈልገው ገንዘብ ተቀናሽ ተደርጎ ቀሪውን ገንዘብ ከሳሽ ከነወለዱ ለተከሳሽ እንዲከፍል እንዲወሰንለት የጠየቀ ሲሆን ከከሳሽ በመቻቻል ጥያቄው ላይ በ12/11/2004 ዓ.ም. በሰጠው መልስ በውሉ አንቀጽ 4.2 መሰረት ተከሳሽ ከርክከቡ በፊት መክፈል ከሚገባው ገንዘብ ብር 2,183,125 ውስጥ ብር 545,781.27 ያልከፈለ እና የውል ግዴታውን ያልተወጣ በመሆኑ ምክንያት በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1757፣2278 (1) እና በመዝገብ ቁጥር 39568 በተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መሰረት የበኩሉን የውል ግዴታ ሳይወጣ የኪሳራ ጥያቄ ሊያነሳ የማይችል መሆኑን፣ተከሳሽ የርክክቡን የጊዜ ስምምነት ያስረዳልኛል በማለት በማስረጃነት ያቀረበው ፕሮፎርማ የተሰጠው ለተከሳሽ ሳይሆን ለ3ኛ ወገን በመሆኑ እና ለተከሳሽ ነው ቢባል እንኳ የውሉ አካል ያልተደረገ በመሆኑ ለጉዳዩ አግባብነት የሌለው መሆኑን፣ውሉ የተደረገው በተሽከርካሪዎቹ ሞዴል እና የመጫን አቅም እንጂ በሻንሲ ርዝመት ላይ አለመሆኑን፣ይሁን እንጂ ተከሳሽ እና ሌሎች ገዥዎች በጠየቁት መሰረት ከሳሽ የውል ግዴታ ባይኖርበትም ለመልካም ስሙ በማሰብ እና በቅን    ልቦና


በርካታ ወጪ በማውጣት እና አስፈላጊ ዕቃዎችን የተሽከርካሪዎቹ የስሪት  አገር ከሆነው ከፈረንሳይ አገር አስመጥቶ በመስፍን ኢንጂነሪንግ አማካይነት የማስተካከያ ስራ እንዲከናወን በማድረግ ርክክቡን የፈጸመ በመሆኑ ተከሳሽ በአስረጂነት የጠቀሰው እና የገዙትን ዕቃ ከነጉድለቱ የተረከቡትን ገዥዎች የሚመለከተው የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2299 (2) ለጉዳዩ አግባብነት የሌለው መሆኑን፣ከሳሽ ተሽከርካሪዎቹን ማስረከብ የነበረበት በዘጠኝ ወር ጊዜ ውስጥ ነው ቢባል እንኳ ተከሳሽ ተገቢነት የሌለውን የካሳ ጥያቄ በማንሳት ማስተካከያ የሚደረግባቸው ከሆነ የሚረከባቸው መሆኑን ወይም አለመሆኑን በወቅቱ ባለመግለጹ እና በኃላ ላይ ግን በከሳሽ በተሰጠው ማስጠንቀቂያ መሰረት የሚረከባቸው መሆኑን የገለጸ ቢሆንም ማስተካከያ ተደርጎባቸው እንዲረከብ በተገለጸለት ጊዜም ባለመረከቡ በአጠቃላይ ርክክቡ ሰባት ወር ከአስራ አምስት ቀን የዘገየው በተከሳሹ ጥፋት መሆኑን፣ተቋረጠብኝ የሚለው ጥቅምም ተከሳሽ የገለጸውን ያህል አለመሆኑን በመግለጽ የመቻቻል ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ተከራክሮአል፡፡

 

ፍርድ ቤቱም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ነጥቦችን በ09/04/2005 ዓ.ም. በብይን በማለፍ በ22/06/2005 ዓ.ም. ክሱን ከሰማ በኃላ የግራ ቀኙን አጠቃላይ ክርክር እና ማስረጃ መርምሮ ከሳሽ ክስ ባቀረበበት የገንዘብ መጠን ላይ ተከሳሽ ያቀረበው የማስተባበያ ክርክር ባለመኖሩ እንደታመነ የሚቆጠር መሆኑን፣ተከሳሽ ወለዱ መቆጠር መጀመር ያለበት ማስጠንቀቂያ ከተሰጠበት ወይም ከርክክቡ ቀን ጀምሮ የአንድ ወር የችሮታ ጊዜን ሳይጨምር ገንዘቡ ተከፍሎ መጠናቀቅ ከሚገባው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው በማለት የተከራከረ ቢሆንም ማስጠንቀቂያ መስጠት አስፈላጊ አለመሆኑ በውሉ አንቀጽ 5.2 የተመለከተ በመሆኑ እና ተከሳሽ የጠቀሰው የፍተሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1803 ድንጋጌም ለጉዳዩ አግባብነት የሌለው በመሆኑ ወለዱ መታሰብ የሚገባው ከርክክቡ ቀን ጀምሮ የአንድ ወር የችሮታ ጊዜ ካበቃበት ቀን ጀምሮ መሆኑን፣የመቻቻል ጥያቄውን በተመለከተ ፕሮፎርማው በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1685 መሰረት የውሉ አካል ነው በማለት ተከሳሽ የተከራከረ ቢሆንም የተጠቀሰው ድንጋጌ ተፈጻሚነት የሚኖረው አስቀድሞ የውል ግንኙነት ባላቸው ተዋዋዮች መካከል በመሆኑ ምክንያት ለጉዳዩ ተፈጻሚነት የሌለው መሆኑን፣በቁጥር 1687 ድንጋጌ መሰረት ፕሮፎርማ የሀሳብ መግለጫ እንጂ ውል ባለመሆኑ የውሉ አካል አለመሆኑን፣በመሆኑም በውሉ መሰረት የርክክቡ አፈጻጸም መሰረት ያደረገው ጊዜን ሳይሆን የክፍያ ሁኔታን መሆኑን፣ከሳሽ ተሽከርካሪዎቹን ማስረከብ ያለበትን ጊዜ ውሉ የማይገልጽ በመሆኑ ምክንያት ሻጭ ማስረከብ የሚገባው በቁጥር 2276 እና 1756 (3) መሰረት ገዥው ሲጠይቀው መሆኑን፣ነገር ግን ተከሳሽ ከርክክቡ በፊት መክፈል ከነበረበት ገንዘብ ውስጥ ብር 545,781.27 ያልከፈለ በመሆኑ እና በባንኩ በኩል የተከፈለው ክፍያም የተከፈለው ከርክክቡ በኃላ ዘግይቶ መሆኑን፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1757፣2278 (1) እና በመዝገብ ቁጥር 39568 በተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መሰረት ተከሳሽ የበኩሉን የውል ግዴታ ሳይወጣ ርክክብ


እንዲፈጸምለት ከሳሽን የመጠየቅ መብት የማይኖረው በመሆኑ ርክክቡ የዘገየው በከሳሽ ምክንያት ነው ለማለት የማይቻል መሆኑን፣ተከሳሽ በአስረጂነት የጠቀሰው ቁጥር 2299 (2) ደንጋጌ ተፈጸሚነት የሚኖረው የዕቃው ርክክብ የተፈጸመው ጉድለት እንዳለበት ሳይታወቅ በሆነ  ጊዜ እንጂ ዕቃው አለበት የተባለው ጉደለት እየታወቀ ተገቢው ማስተካከያ ተደርጎበት ርክክብ በተፈጸመበት ጊዜ ጭምር አለመሆኑን፣ተከሳሽ እንደሚለው ሻሲዎቹ ችግር አለባቸው ቢባል እንኳ ተከሳሽ ውሉን ማፍረስ ወይም የበኩሉን ግዴታ በመፈጸም ርክክብ በመጠየቅ ከተረከበ በኃላ ለደረሰበት ጉዳት ካሳ መጠየቅ የሚችል ሆኖ ሳለ ግዴታውን ሳይወጣ ርክክቡ በመዘግየቱ ምክንያት ለደረሰብኝ ጉዳት ከሳሽ ካሳ ሊከፈለኝ ይገባል በማለት ያቀረበው ጥያቄ የውልም ሆነ የሕግ አግባብ የሌለው መሆኑን ገልጾ የመቻቻል ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ተከሳሽ የሚፈለግበትን ቀሪ ክፍያ ብር 2,595,905.97  (ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ዘጠና  አምስት ሺህ ዘጠኝ መቶ አምስት ከዘጠና ሰባት) ከ26/04/2000 ዓ.ም. ጀምሮ ተከፍሎ እስከሚያልቅ ድረስ ከሚታሰብ 9.5% ወለድ ለከሳሽ እንዲከፍል የወጪን ኪሳራ መብት በመጠበቅ ጭምር ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ተከሳሽ ባቀረበው ይግባኝ ሳቢያ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ወለዱ መታሰብ የሚጀምርበትን ጊዜ በተመለከተ ብቻ ውሳኔውን በማሻሻል ወለዱ መታሰብ የሚገባው ከሳሽ በክሱ ከጠየቀበት ከ20/05/2000 ዓ.ም. ጀምሮ ነው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው ይዘቱ  ከላይ የተመለከተው የሁለቱ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ አመልካች በስር ፍርድ ቤት ያቀረበው የመቻቻል ጥያቄ ከፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2299 ድንጋጌ አንጻር መታለፉ አላግባብ ነው የሚለውን እና ርክክብ የተፈጸመው በ29/02/2000 ዓ.ም. በመሆኑ ክፍያው መጠናቀቅ ያለበት ከ29/03/2000 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 29/03/2001 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑ በውሉ የተመለከተ በመሆኑ አመልካች ገንዘቡን ከፍሎ አላጠናቀቀም ተብሎ በዕዳው ላይ ወለድ መታሰብ መጀመር የሚገባው ክፍያው ከሚጠናቀቅበት የመጨረሻ ቀን ማለትም ከ29/03/2001 ዓ.ም. ጀምሮ እንጂ መከፈል ከሚጀምርበት ከ20/05/2000 ዓ.ም. ጀምሮ መሆን የለበትም የሚለውን የአመልካች የአቤቱታ ነጥቦች ተጠሪው ባለበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡ የከፍተኛ ፍርድ ቤት መዝገብም በ09/03/2007 ዓ.ም. በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ቀርቦ ተያይዞአል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለጉዳዩ ከተያዙት ነጥቦች አንጻር መርምረናል፡፡


በዚህም መሰረት ከፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2299 ድንጋጌ አንጻር የአመልካች የመቻቻል ጥያቄ የታለፈው በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም? በሚል የተያዘውን የክርክር ነጥብ በተመለከለተ አመልካች በከፍተኛ ፍርድ ቤት የመቻቻል ጥያቄ ያቀረበው በፍትበሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1685 ድንጋጌ አነጋገር መሰረት ፕሮፎርማው የውሉ አካል መሆኑን በመጥቀስ እና በፕሮፎርማው ላይ የተመለከተውን የርክክብ ጊዜ መሰረት በማድረግ ሲሆን ተጠሪ በበኩሉ በፕሮፎርማው ላይ የርክክብ ጊዜ የተመለከተ መሆኑን ሳይክድ ነገር ግን ፕሮፎርማው የውሉ አካል ባለመሆኑ የርክክብ ጊዜውን ለመወሰን መሰረት ሊሆን አይችልም በማለት መከራከሩን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ በአመልካች የቀረበውን የክርክር ነጥብ ሳይቀበል የቀረው የፍትበሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1685 ድንጋጌ ተፈጸሚነት የሚኖረው ተዋዋዮቹ አስቀድሞ የተቋቋመ የውል ግንኙነት ሲኖራቸው በመሆኑ እና አስቀድሞ የውል ግንኙነት ያላቸው ስለመሆኑ ደግሞ አመልካች ያላስረዳ በመሆኑ ክርክሩ ተቀባይነት የለውም በማለት ነው፡፡በመሰረቱ የግራ ቀኙ የውል ግንኙነት የተመሰረተው ፕሮፎርማውን ብቻ በቂ አድርጎ በመቀበል ሳይሆን ፕሮፎርማው ከተሰጠ በኃላ ስለ ሽያጩ ዝርዝር አፈጻጸም ራሱን ችሎ በጽሁፍ በተደረገ የሽያጭ ውል ላይ ነው፡፡በፕሮፎርማው ላይ የተጠቀሱት የእያንዳንዱ ተሽከርካሪ የሽያጭ ዋጋ፣የክፍያ ሁኔታ እና የተሽከርካሪው ሞዴል በቀጣይ በጽሁፍ  በተደረገው  ውል ውስጥ የተካተቱ ቢሆንም የእያንዳንዱ ተሽከርካሪ የሽያጭ ዋጋ እና የክፍያ ሁኔታ በሽያጭ ውሉ የተካተተው በፕሮፎርማው ከተገለጸው በተለየ መጠን እና ሁኔታ ነው፡፡ በፕሮፎርማው ላይ የተመለከተውን የርክክብ ጊዜ ግን ግራ ቀኙ የውሉ አካል አላደረጉትም፡፡በውሉ ውስጥ የተመለከቱት ዝርዝር የውል አፈጻጸም ሁኔታዎችም በፕሮፎርማው አልተጠቀሱም፡፡ፕሮፎርማ በባህርይው የዚህ ዓይነት ዝርዝር የውል አፈጻጸም ሁኔታዎችን እንዲያካትትም አይጠበቅም፡፡የተዋዋዮች የውል ግንኙነት መሰረት ያደረገው ፕሮፎርማን ሳይሆን ፕሮፎርማውን ተከትሎ በጽሁፍ የተደረገን ውል በሆነ ጊዜ ደግሞ በፕሮፎርማው ላይ ተጠቅሶ ነገር ግን ተዋዋዮቹ የውላቸው አካል አድርገው ያልተስማሙበት ጉዳይ በፕሮፎርማው ላይ የተጠቀሰ በመሆኑ ብቻ እንደ ውሉ አካል ተቆጥሮ በተዋዋዮቹ ወይም ከተዋዋዮቹ በአንዱ ላይ አስገዳጅነት እንዳለው አድርጎ መውሰዱ የሕግ ጥበቃ ካለው ፈቅዶ የመዋዋል ነጻነት እና መብት አንጻር ሕጋዊ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚገባው አይደለም፡፡ በመሆኑም በፕሮፎርማው ላይ የተመለከተውን የርክክብ ጊዜ በአስረጂነት ጠቅሶ ተጠሪው ርክክቡን ለ12 ወራት ያዘገየው በመሆኑ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከተሽከርካሪዎቹ ስምሪት ማግኘት እችል የነበረውን ገቢ ተጠሪው ሊተካልኝ ይገባል በማለት አመልካች ያቀረበው ክርክር ውድቅ መደረጉ የሚነቀፍበትን ሕግዊ ምክንያት አላገኘንም፡፡አመልካች ከርክክቡ በፊት ማጠናቀቅ ከነበረበት ክፍያ ውስጥ የተወሰነውን ያህል እንዳልከፈለ ያልተካደ ከመሆኑም በላይ ሻሲዎቹ ጉድለት ያሉባቸው ናቸው በሚል መነሻ የዋጋ ቅናሽ  ካልተደረገለት  በስተቀር  ለመረከብ  ፈቃደኛ  አለመሆኑን  ለተጠሪው  አስታውቆ የነበረ


መሆኑን፣ተጠሪውም ለዚሁ ማስታወቂያ በሰጠው ምላሽ በውሉ ምክንያት የተቀበለውን ቅድመ ክፍያ ከሕጋዊ ወለድ ጋር መልሶ ውሉን ለማስቀረት ፈቃደኛ መሆኑን  ለአመልካች የገለጸ መሆኑን እና አመልካች ሀሳቡን በመቀየር ተሽከርካሪዎቹን እንደሚረከብ ሀሳቡን የገለጸው ከዚህ በኃላ መሆኑን ቀርቦ ከተያያዘው የከፍተኛ ፍርድ ቤት መዝገብ ተገነዝበናል፡፡ይህም ተጠሪው ርክክቡን አዘግይቶአል በማለት አመልካች የሚያቀርበው ክርክር ተገቢነት የሌለው መሆኑን ለውሉ አፈጻጸም መዘግየት አመልካቹ ጭምር አስተዋጽኦ እንደነበረው መገንዘብ የሚያስችል ነው፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕግ ከቁጥር 2287 እስከ 2300 የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት የሚኖራቸው ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደገለጸው በዕቃው ላይ ተገኘ የተባለው ጉድለት መኖሩ በገዥው የታወቀው ከርክክብ በኃላ በሆነ ጊዜ እንጂ ጉድለቱ ከርክክቡ በፊት ታውቆ በሻጩ እንዲስተካከል ከተደረገ በኃላ ርክክብ በሚደረግበት ጊዜ ጭምር እንዳልሆነ ከድንጋጌዎቹ አነጋገር እና ይዘት በግልጽ መገንዘብ የሚቻል በመሆኑ ቁጥር 2299 ድንጋጌን ጠቅሶ አመልካች ያቀረበው ክርክር ውድቅ መደረጉም ቢሆን የሚነቀፍ ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

ለተጠሪው በተወሰነው ገንዘብ ላይ ወለድ መታሰብ የሚጀምርበትን ቀን በተመለከተ ርክክብ መፈጸሙን ተከትሎ የአንድ ወር የችሮታ ጊዜ ካበቃ በኃላ አመልካች ከራሱ የሚከፈለውን የመጨረሻ ክፍያ ብር 2,050,124.70 በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ ከፍሎ እንዲያጠናቅቅ ግራ ቀኙ የተስማሙት ዋናውን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከ9.5% ወለድ ጋር ስለመሆኑ በውላቸው አንቀጽ 4.3 ላይ በግልጽ ተመልክቷል፡፡በዚህ የውል ቃል አነጋገር ትርጉም ረገድ ወይም በውል ቃሉ ሕጋዊነት ረገድ አመልካች ያቀረበው ክርክር የለም፡፡ አመልካች እንደሚከራከረው ወለዱ የ12 ወራት ጊዜ ካበቃ በኃላ መታሰብ መጀመር ይችል የነበረው በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ እንዲጠናቀቅ ግራ ቀኙ የተስማሙት ወለድ ሳይታሰብበት ዋናው ገንዘብ ብር 2,050,124.70 ብቻ ቢሆን ኖሮ ነው፡፡በተያዘው ጉዳይ ግን ገንዘቡ በ12 ወራት ተከፍሎ እንዲጠናቀቅ ግራ ቀኙ የተስማሙት ከነወለዱ ነው፡፡ይህም በገንዘቡ ላይ ወለዱ መታሰብ የሚጀምረው የአንድ ወር የእፎይታ ጊዜ ካበቃበት ቀን ጀምሮ መሆኑን መገንዘብ የሚያስችል ነው፡፡እንዲህ ከሆነ ደግሞ አመልካች ገንዘቡን በየወሩ እየከፈለ በ12 ወራት ቢያጠናቅቅም ሆነ በ12ኛው ወር መጨረሻ ላይ ገንዘቡን አጠቃሎ በአንድ ጊዜ ቢከፍል በዋናው ገንዘብ ብር 2,050,124.70 ላይ በግራ ቀኙ ስምምነት መሰረት 9.5% ወለድ የእፎይታ ጊዜው ከተጠናቀቀበት ቀን ጀምሮ መታሰቡ የሚቀጥል በመሆኑ ገንዘቡ በየወሩ መከፈሉ ወይም በዓመቱ መጨረሻ በአንድ ጊዜ ተጠቃሎ መከፈሉ በአመልካቹ የግዴታ አፈጻጸም ረገድ የሚያስከትለው ልዩነት የለም፡፡ ውሳኔ ካረፈበት ገንዘብ ውስጥ ብር 545,781.27 መከፈል የነበረበት ከርክክቡ በፊት በመሆኑ በዚህኛው ገንዘብ ላይ ወለዱ ከ20/05/2000 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲታሰብ መደረጉ አመልካችን ተጎጂ ሳይሆን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡


ሲጠቃለል አቤቱታ የቀረበበት የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ ስላልተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 117102 በ11/10/2005 ዓ.ም. ተሰጥቶ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 92783 በ30/05/2006 ዓ.ም. የተሻሻለው ውሳኔ በፍትሐ ብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348 (1)  መሰረት ፀንቷል፡፡

2.  እንዲያውቁት የውሳኔው ቅጂ ለስር ፍርድ ቤቶች ይላክ፡፡ የስር ፍ/ቤት መዝገብ ይመለስ፡፡

3.  የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

4.  ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡


 

 

ሩ/ለ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡